ምዕራባዊያኑ ኢትዮጵያን ማፈራረስ የዘመናት እልማቸው ነበር። ተሳክቶላቸውም ባያውቅም፤ ፍላጎታቸውን በውስጣቸው ደብቀው የህልም ቅዥት እንደሆነባቸው ኖሯል። የተሳካላቸው እየመሰላቸው ቢደክሙ ሌሎች ሀገራት ላይ የፈጸሙትን ሀገር የማፈራረስ ሴራ በኢትዮጵያ ምድር ከቶ ሊሳካላቸው አይቻልም።ሙከራቸው እየከሸፈ ወጥመዳቸው እየተሰባበረ ሴራቸው ተሰነካክሎ ቀርቷል።የሁል ጊዜ ቁጭታቸው የሆነችውን በአፍሪካ ቀንድ ካሉት ሀገራት ቅኝ ሣሳትገዛ ነጻነቷን አውጃ የኖረችውን ሀገር ኢትዮጵያ የቅርጫው አካል ሳያደርጉ መቅረታቸው ሲያንገበግባቸው የኖረ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ጉዳይ እንደማይሆንላቸው ቢረዱ ሙከራ ማድረጋቸውን አላቋረጡም።ኢትዮጵያን በአይነ ቁራኛ እየተከታተሉ በየጊዜው አዳዲስ ስትራቴጂዎችን እየቀረጹ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስልታቸውን እየቀያየሩ መሞከር የሁልጊዜ ተግባር አድርገው ኖረዋል።በደረሱበት ቴክኖሎጂ ጥልቀት ምጥቀትና ስውር መንገድ ረጅም ጉዞ ቢጓዙም ‹‹እኛ እንፈርሳለን፤ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም›› እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሴራቸው በኢትዮጵያውያን የጠነከረ ክንድ መክቶ መና እየሆነባቸው መቸገራቸው እሙን ነው።
ሀገርን የማፍረስ ህዝቦችን የመበታተን የካበተ ልምድ ያላቸውን በምዕራባዊያኑ ለእጅ አዙር አገዛዛቸው የማይመቻቸውን እና ለውስጣዊ ፍላጎታቸው፤ ያልተገዛላቸውን ሀገር ለማፍረስ ያለመ ሴራ መወጠናቸውን አላቆሙም።ወጥነውም አይቀሩም ፍላጎታቸውን ያሳካሉ።ለዚህ ተግባራቸው ደግሞ እንደ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ ያሉ ሀገራት ህያው ምስክሮች ናቸው።
እነዚህ ሀገራት ምስቅልቅላቸው ከወጣ በኋላ እነሱ በኃይላን ዙፋን ላይ እንዳሻቸው እየሆነ ኑራቸውን ቀጥለዋል። ሩቅ ሆነው ረጅሙን እጃቸው ወደ ውስጥ በመስደድ የልባቸውን ከፈፀሙ በኋላ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ራሳቸውን ነጻ አድርገው ለማሳየት በእጅጉ ይጥራሉ። ዓላማ ያደረጉትን ሀገር በጦርነት እንዲታመስ በማድረግ ከጦርነቱ ማግስት መንግስት አልባ ወይም ደካማ መንግሥት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። የፈለጉትን ካሳኩ በኋላ የራሳችሁ ጉዳይ በሚል ለሁከትና ለመፈራረስ ጥለዋቸው ይሄዳሉ።ዱላው ካረፈባቸው ሀገራት አንዷን አፍጋኒስታንን ብንመለከት እንኳን ለ20 ዓመታት የሸብርተኛ አወድማ አድርገዋት ቆይተዋል።እስካሁን ወደነበረችበት መመለስ አቅቷት እንደነሱ ፍላጎት እየኖረች ያለች ሀገር ናት።
የምዕራባዊያን ሀገር የማፈራረስ ውጥን በተለያዩ ሀገራት የተሳካላቸው ይመስላል። በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረው ቀስት ግን ሳይሳካላቸው ቢቆይም በተለያዩ መንገድ ሀገራችን ከድህነት አረንቋ ቀና እንዳትል እንቅፋት ሆነዋል። በተለያዩ መንግሥታት ጊዜ የራሳቸው ጫና ለመፍጠር ደክመዋል።በተለይ አሜሪካ ልክ አሁን እንደምታደርገው በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ሙከራ አድርጋለች።
በ1969 ዓ.ም በነበረው የሶማሊያ ወረራ ወቅት የዚያድ ባሬን መንግሥት በመርዳትና በመደገፍ ኢትዮጵያን የማፍረስ ድብቅ ሤራ ስትፈጽም እንደነበር የታሪክ ድርሣናት ያመለክታሉ።በወቅቱም ለጠላት እጅ ሰጥቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ በአሜሪካ ስትደገፍ የነበረችውን ሶማሊያን ድባቅ መትቶ፤ ድል በማ ድረጉ ጦርነቱ ተደምደሟል።
የአሁኑ ይባስ እንዲሉት ሆኖ ከምንጊዜው በበለጠ ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረገ ስትራቴጂ ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ጂኦፖለቲክስ ፕሬስ የተሰኘው ጽረገጽ ያወጣው መረጃ ያሳያል።‹‹ባዝማን ፕሮጀክት›› “From Basma to Ethiopia” የሚል እጅግ አደገኛ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያለመ ሴራ ይዘው ብቅ ብለዋል።የዚህ ፕሮጀክት ሴራ በምዕራባዊያኑ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራትን ሣይቀር ያካለለና አንዳንድ የኢትዮጵያውያን አክቲቪስት ነኝ ባዮችን የሚጨምር እንደሆነ መረጃው አመላክቷል።
አሁን ደግሞ የዓላማቸው ማሣኪያ አንዱ አካል የሆነውን ‹‹እጄን በእጄ›› እንዲሉት ዓይነት ጨወታ ጀምረዋል።ከትግል ጥንሰሱ ጀምሮ የአሸባሪው ህወሐት ደጋፊ በመሆኑ በእጅ አዙር ወጥመዳቸው እጃቸውን ሰደዋል።የሀሳባቸው በር ከፋች የሆነውን የህወሐት አገዛዝ ባለፉት አሥርት ዓመታት እንዳሻቸውና እንደሚፈልጉት ለማሽከርከር አልከበዳቸውም ነበር።
የህወሐት አገዛዝ ዳግም እንዳታንሰራራ አድርጋ የቀበረች ሀገር በለውጥ ፈላጊው ህዝብ የብርሃን ፍንጣቂ ለማየት ስትበቃና ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግራትን ጉዞ አሃዱ ብላ ስትጀምር ግን ነገሮች ተበላሹባቸው።ዳግሞ የተንኮል ጥንስስ መጠንሰስ በለውጡ የመጣው መንግሥት የእጅ አዙሩ አገዛዝ አጥብቆ በመቃወሙ የምዕራባዊያኑን ቁጣ አበረታው።
በኢትዮጵያ ለመፍጠር የፈለጉት ደካማ መንግሥት ቀርቶ ቀን ከለሊት ለመለወጥ የሚተጋ ብርቱ መሆኑ በእጅጉ አሳሰባቸው።የምስራቅ አፍሪካዋ የጥቁር ህዝቦች ምሳሌ የማትረታዋ ኢትዮጵያ ትንሳኤዋ ሩቅ እንዳልሆነ ቀድሞውኑ ተረድተዋልናል አሸባሪውን ህወሐት መሳሪያ አድርገው መጡ። ይሁን እንጂ ይህንን የማይቀበሉት ደካማ መንግሥት ያላትና የተሽመደመደች ሀገር እንድትኖር የማይፈልገው የለውጡ መንግሥት ፍላጎታቸውን ሸባ አድርጎት እርፍ አሉት።
የረጅም ዘመናት ምኞታቸውን ለማሳካት ‹‹ጠላቴን እኔ እጠብቀዋለሁ፤ ወዳጄን አንተ ጠብቅልኝ›› እንዲሉት ሆኖ ከአሸባሪው ህወሐት ጋር ጋብቻ መስረተው ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ሞክረዋል። አሁን ላይ ይዘውት የተነሱት ዓላማና ፍላጎት ምንድን ነው? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል። የምዕራባዊያኑ ፍላጎት እጅግ ላቅ ያለ ነውና በሀገር ውስጥ ጉዳይ እንኳን ሳይቀር ቀድመው ለመገኘት ሲሞክሩ እያየናቸው ነው።
‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንዲሉ ሆኖ ምዕራባዊያኑና ሚዲያዎቻቸው ለአሸባሪው ህወሐት ዋስ ጠበቃ ሆነው ከጎኑ ቆመዋል። በተለይ የአሸባሪው አድራጊ ፈጣሪ አባቱ የሆነችው አሜሪካ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቷን ተያይዛዋለች።ጫና እና ማዕቀብ ለመጣል ጉጉት እንዳላት በአፈቃላጤዎቿ አሳብቃለች፡፡
ለምዕራባዊያን አሸንጉሊት በመሆኑ በሚነዱት መንገድ እየተነዳ እና የራሱን ክፋት የተላበሰ ባህሪይ በመጠቀም በወገኖቹ ላይ አስቃቂ ጨፍጨፋን አከናውኗል።አሁንም ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትን ከእናታቸው ጉያ ፈልቅቆ በመውስድ የለመደውን የአዋኪነት ተግባሩን አጠናክሯል።
አሁን እንኳን ለጦርነት ያሰለፋቸውን ህጻናት እያዩ እና የዓለም አቀፍ ወንጀል እንደሆነ ከመዘገብ ይልቅ እሰይ አበጀህ ዓይነት ሙገሳ እያቀረቡለት ነው። የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባዮቹ አካሄዳቸውን ማጤን ያስፈልጋል። በሰብዓዊ እርዳታ ምክንያት ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው ጫና ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ያለው ጥረት በእጅጉ ያሳፍራል፡፡
እውን የምዕራባውያኑ ለትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ አስበው ነው ለማለት ይቸግራል።ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሆን በአፋር በኩል ለክልሉ የሚቀርበውን ሰብዓዊ እርዳታ አላስገባ ያለን አሸባሪ ለምን ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ሌላ መስመር በሱዳን በኩል ይከፈት ማለት የጤና እንዳልሆነ ማንም ጤነኛ ሰው የሚረዳው ነው።እውን ዓላማቸው ሰብአዊ ድጋፍ ብቻ ነውን? ሰብዓዊ እርዳታው በፍጥነት ለተጎጂው እንዲደርስ የትኛው ወደብ ይቀርባል? ከፖርት ሱዳን መቀሌ 1 ሺህ 306.8 ኪሎ ሜትር ሲረዝም በተሽከርካሪ በአማካይ 17 ሰዓት ከ36 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን፤ ከጅቡቲ መቀሌ 779 .1 ኪሎ ሜትር ሲረዝም በተሽከርካሪ በአማካይ 12 ሰዓት እንደሚወስድ መረጃዎች ያመላክታሉ።ፍርዱን ለህዝብ ልተወው፡፡
አሁን ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን።የማንቂያው ደውላ ተደውሏልና እኛ የቀደሙቱ መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩልንን ሀገር ለሌላ አሳልፈን አንሰጥም።ትውልዱ ለሀገሩ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን የራሱ ኃላፊነት መወጣት አለበት። አበቃሁ።ሠላም ለሀገራችን ይሁን።
እየሩስ አበራ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 ቀን 2013 ዓ.ም