የተወለዱት በቀድሞው አጠራር በሸዋ ክፍለሃገር ጨቦና ጉራጌ አውራጃ ከአምቦ 12 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ጉደር ከተማ ውስጥ ነው:: ይሁንና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ በምትገኘው ወንጪ ወረዳ ነው ያደጉት:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ዳርያን በሚባል ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፤ አስከ 6ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ግን በአካባቢው መለስተኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት እዚያው ሆነው መቀጠል አልቻሉም:: በመሆኑም ወሊሶ ከተማ በሚገኘው የሥነ ጥበብ አርበኛው ደጃዝማጅ ገረሱ ዱኪ ትምህርት ቤት 25 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተጓዙ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ለመማር ተገደዱ:: ይሁንና መንገዱ ሩቅና ጫካ የበዘበት በመሆኑ በልጅነት ጉልበታቸው የሚገፋ ሆኖ አላገኙትም:: በተለይም ደግሞ የሰባት ቀናት ሥንቃቸውን ተሸክመው እየተመላለሱ መማሩ አዋጭ ባለመሆኑ እናታቸው ወደሚገኙባት ጉደር ከተማ በመሄድ ማዕረገ ሕይወት በተባለ ትምህርት ቤት 9ኛ ክፍልን ተከታተሉ::
እንግዳችን ወደ 10ኛ ክፍል እንዳለፉ ግን አሁንም ዳግም ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጠረ:: ወቅቱ 1969 ዓ.ም ላይ ነው፤ ኢትዮጵያ በሱማሊያ መወረሯን ተከትሎ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለመላው ሕዝብ የክተት አዋጅ ታወጀ:: እሣቸውም ሀገሬ በጠላት ተወራ እያለ እኔ እንዴት ተረጋግቼ እማራለሁ ብለው ጥሪውን ተቀብለው ገና በለጋ ዕድሜያቸው ዘመቱ:: በአየር ወለድ ሥር የነበረና አዲስ በተቋቋመ ክፍልም ፓራ ኮማንዶ ሆነው ወደ ሥልጠና ገቡ:: ወራሪውን ሃይል ከወገን ጦር አባላት ጋር ድባቅ ከመቱና ወደመጣበት ከመለሱ በኋላም በሠራዊቱ ውስጥ ለ15 ዓመታት ቆዩ::
የዛሬው የዘመን እንግዳችን በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በተለይም የሱማሌን ወራሪ ሃይል ድባቅ በመምታቱ ሂደት ብርቱ ትግል በማድረጋቸው ምክንያት ከኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ጓድ መንግሥቱ እጅ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል:: ይሁንና የደርግ መንግሥት ከሥልጣን መወገዱን ተከትሎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ሕወሃት መራሹ ሃይል የቀድሞውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ በማባረር በራሱ አባላት ተካ:: እንግዳችን ለሀገርና ለሕዝባቸው ሉዓላዊነት ደማቸውን ቢያፈሱም ወረታቸው በግፍ ከሠራዊቱ መባረር ሆነ::
ከዚህም ባሻገር በተሃድሶ ሰበብም ማሠልጠኛ ተልከው ብዙም ሣይቆዩ ‹‹የተሸለምከው እኛን ለመውጋት ነው›› በሚል ሐሰተኛ ትርክት ለረጅም ዓመታት ታስረው ተንገላቱ:: በአዲሱ መንግሥት ቅጠረኞች በተለይም ደግሞ ጨለማ ቤት ብቻቸውን ባዶ ክፍል ውስጥ በማስገባት በደረሠባቸው ድብደባና ሥቃይ ሣቢያ ዛሬም ድረስ የአካልም ሆነ የሕሊና ጠባሳ አትርፈዋል:: ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› እንዲሉ አገራቸውን ከጠላት የታደጉት እኚሁ አርበኛ በወህኒ ቤት ሣሉ በግፈኛው መንግሥት የደረሰባቸውን ሁሉ በመፅሃፍ መልኩ ፅፈው ለሕትመት አበቁ:: ከእሥር ከተፈቱ በኋላም እንደማንኛውም ዜጋ በተለያዩ የግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው አገለገሉ:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ ልክ እንደእርሳቸው በግፍ ከሠራዊቱ ከተባረሩ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን ማህበር አቋቁመዋል:: በማህበሩ ውስጥም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ:: ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከመቶ አለቃ በቀለ በላይ ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አድርገናል:: እንደሚከተለው ይቀርባል::
አዲስ ዘመን፡- ስለቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲነሳ ጎልቶ የሚወሳው ጉዳይ የነበረው የሃገር ፍቅርና ወኔ ነው:: ከዚህ በመነሳት በአሁኑ ወቅት ስላለው የሠራዊቱ የሃገር ፍቅር እና ወኔ በእርሶ እይታ ምን እንደሚመስል ያጫውቱን እና ውይይታችንን እንጀምር?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ ግን አሁንም ቢሆን ያ የሀገር ሥሜት ፍቅር እንዳለ ነው እኔ የሚሰማኝ:: ርግጥ ነው፤ የቀድሞው ሠራዊት በክልል ኮታ የተደራጀ አልነበረም:: የቀድሞ ሠራዊት ‹‹አንዲት ኢትዮጵያ›› በሚል መንፈስ እንጂ ጎሣም ሆነ ሃይማኖት አልነበረውም:: ከምንም በላይ የሚያስቀድሙት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ነው:: በዚህ መካከል ምንም ዓይነት ትርፍም ሆነ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲጥር አታስተውይም ነበር:: በነፃ ነበር ሀገሩን በቀናነት ሲያገለግል የነበረው:: ኢትዮጵያ ስትወረር ያለአንዳች ማንገራገር ጨርቄን ማቄን ሣይል ነበር የሚዘምተው:: ሁላችንም ጦርሜዳ የምንሰለፈው ያለምንም ክፍያ ነው:: የሚገርምሽ በእኛ ጊዜ 300 ሺህ ይጠጋ የነበረው የገበሬ ልጅ ሚሊሻ ደመወዙ 20 ብር ብቻ ነበር:: ለዛሬ ወጣት 20 ብር ምኑ ነው?:: ያን ጊዜ የነበረው ሠራዊት በነፃ ኖረ፤ በነፃ ሞተ:: በሕይወት የቆየውም ቢሆን ወያኔ ሃገሪቱን ከተረከበ በኋላ እንደአገለገለ ዕቃ የትም ተጣለ:: ስለዚህ የቀድሞ ሠራዊት የሃገር ሥሜት መገለጫው ዳር ድንበር የለውም:: የኢትዮጵያ ፍቅር ከልቡ ጋር ወይም ከደም ሥሩ ጋር የታተመ ነው:: አንድነቱ በኢትዮጵያዊ ማንነት የተገመደ ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊነት እንጂ ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም:: እንደአሁኑ ‹‹አማራ ነህ፤ ኦሮሞ ነህ›› የሚባል ነገር የለም:: እንዲህ ዓይነት ነገር መስማት የጀመርነው ወያኔ ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ ነው:: አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያዊነት ሥሜት ያለው የሃገር ጉዳይ የሚያሳስበው ወጣት ወታደር እየተፈጠረ ነው:: ይህንን ሳስብ ጨርሶ ተሥፋ እንዳልቆርጥ የሚያደርገኝ በመሆኑ እኮራለሁኝ::
አዲስ ዘመን፡- እስቲ እንደ አንድ የቀድሞ ወታደር በሕወሃት መራሹ መንግሥት በነፃ ሃገሩንና ሕዝቡን ሲያገለግል የቆየው የቀድሞ ሠራዊት ያለምንም ሁኔታ መበተኑ የፈጠረብዎት ሠሜት ምን እንደነበር አያይዘው ያስረዱኝ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ያ ሁኔታ እንኳንስ ደሙን ላፈሰሰው ሠራዊት ይቅርና ለማንኛውም ሰው ሲታሰብ በጣም ይጎዳል:: ከመጉዳትም በላይ ከመኖር ወደ አለመኖር የፈጠረ ጉዳይ ነው:: በመሠረቱ ይኼ የወያኔ ሴራ ነው:: ያንን ሲያደርግ እኮ ሀገር አፍርሷል:: አሁን ላይ እኮ የፈረሰችን ሃገር ነው እየጠገንን ያለነው:: አንድ ሀገር ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወይም የፖሊስ ሠራዊት ከፈረሰ አገር እንደፈረሰ ነው የሚቆጠረው:: ወያኔ የራሱን ሽፍታ ሠራዊት ለማስገባት ሲል ነው እኛን የበተነን:: ከመበተንም አልፎ ገደለን፤ አሠረን፤ አሠቃየን:: እኔ በወያኔ አገዛዝ ዘመን ብቻ አራት ጊዜ ታሥሬያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የታሰሩበት ምክንያት ምን ነበር?
መቶ አለቃ በቀለ፡- እኔ ወታደራዊ ግዳጄ ከሚጠይቀኝ በላይ በመሥራቴ ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅ የጦር ሜዳ ጀግና ተሸላሚ ሆኜያለሁ:: በጦርነቱ ከጠላት ታንክ ጋር ግብ ግብ ገጥሜ ባመጣሁት ውጤትና የወራሪውን የሱማሊያ ታንክ ማቃጠል በመቻሌ የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችያለሁ:: ወያኔዎች ግን ‹‹እኛን ጨርሶ ነው ሜዳሊያ የተሸለመው›› ብለው ነው የከሰሱኝ:: እኔ በወቅቱ ለሀገሬ ዋጋ በከፍልኩኝ ወሮታዬ መታሰር ሲሆን፤፤ እጄ ላይ መሣሪያ አለመኖሩ እንጂ እነሱን መግደል ባልችልም እንኳን ራሴን መግደል አያቅተኝም ነበር:: በመሠረቱ በዚህ ሽፍታ መንግሥት ከዚያ በላይ ነው በደል የተፈፀመብኝ:: እነሱ ‹‹ዘረባ ግደፍ›› የሚባል ቋንቋ አላቸው፤ ይህም ማለት ነገር አቁም፤ አትናገር ማለት ነው:: ከማሰር በላይ ደግሞ ሐሳቤን እንኳን እንድገልፅ አይፈቀድልኝም ነበር:: እናም በእኔ እና በሌሎች አባላት ላይ የፈፀሙት ግፍ ታሪክ የማይረሣውና ፈጣሪም እንኳን ይቅር የማይለው ነው::
በነገራችን ላይ ያኔም ቢሆን የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በርካታ የደርግ ሠራዊት አባላት ነበሩ:: ሃገራቸውን የሚወዱና ዛሬም ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች ብለው የሚያስቡ በርካታ ሰዎች አሉ:: መንግስሥም ቢሆን ‹‹ወገኖቻችን ናቸው›› የሚለው ወዶ አይደለም:: ጥሩ…ጥሩ የሆኑ አርበኞች አሉ:: እኛ የምንመሠክርላቸው ጀግኖች አሉ:: የሚገርምሽ እኔ ሜዳሊያ የተሸለምኩት ሱማሊያ ላይ ባደረኩት ተሣትፎ እንደሆነ ሳስረዳቸው ‹‹ከሱማሊያ ጋር የተደረገው ጦርነትም ቢሆን አግባብ አልነበረም›› የሚል ምላሽ ነው የሰጡኝ:: ይህ የሚያሣይሽ እነሱ ሀገር ለመውረር የሚመጣ የውጭ ሀይል ጋር ሣይቀር የሚተባበሩ ባንዳዎች ስለመሆናቸው ነው:: በመሠረቱ ግን ለሀገሬ ለከፈልኩት ዋጋ እሥራት አይገባም ነበር:: በዚህ ምክንያት ስበሳጭ ከአካል ጉዳት ባለፈ የሥነ ልቦና ቀውስ አስከትሎብኝ ነበር::
የሚገርምሽ ደግሞ በስመ ተሃድሶ አራት ዓመት ጦላይ ወስደው ነው ያሰሩኝ:: በተለይም እኔና የክፍለ ጦር አዛዦችን ከሠራዊቱ ለይተው ሊፈጁን ነበር:: ከሁሉም ለይተው ጨለማ ቤት ውስጥ ነው እኔን ያስቀመጡኝ:: በነገራችን ላይ የመጀመሪያው ጨለማ ቤት ታሣሪ እኔ ነኝ:: አሁን ላይ አንዳንዴ አይኔ ላይ ብዥታ ነገር ፈጥሮብኝ ጥርት አድርጎ ለማየት እቸገራለሁ:: ሲያስሩኝ ደግሞ ዝም ብሎ አይደለም:: በጣም ሊቀጡኝ ሲያስቡ መሬት ላይ እርቃኔን አስተኝተው ውሃ እያፈሰሱ ይገርፉኛል:: ያ ሁሉ ግፍ እየተፈፀመብኝ ግን እዚያው ሆኜ ‹‹የጀግናው ወሮታ›› የሚል መፅሃፍ ፅፌ ነበር:: ለወሮታዬ እሥራት፤ ለከፈልኩት ዋጋ ድብደባና ግፍ ነው የተፈፀመብኝ::
አዲስ ዘመን፡- ከተሞክሮዎት አንፃር አሸባሪው የሕወሃት ቡድን አሁን ላይ የሚፈፅመው ተግባር ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- እኔ በአጋጣሚ በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ተናግሬያለሁ:: ዛሬ አንቺም ሆነ ሌላው የቆማችሁት በእኔና በጓደኞቼ ደም ላይ ነው:: አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሠንደቁን አንግቦ ቀይ ባህርን አልሰጥም ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው አሰብ በርሃ ላይ የቀረው እነጀነራል ተሾመ ተሠማ ደም ላይ ነው ቁጭ ያልሽው:: በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ላይ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብለው ሽጉጣቸውን የጠጡ ጀግናው ጀነራል ለገሠ አበጀ አጥንት ላይ ነው ዛሬ ሁሉም በነፃነት የሚረማመደው:: እናም ይህች ሃገር የቆመችው በእነዚህ ጀግኖች ብርቱ ትግል ነው:: ሆኖም ወያኔ ከጅምሩም ቢሆን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን መንፈሱ ከውስጡ ታጥቦ የወጣ የኢትዮጵያ ብቸኛ ጠላት ነው:: ውልደቱም በዚህ ሁኔታ ነው የተፈጠረው:: የትግራይ ሕዝብ ዛሬም መከራ የሚበላው ሀገሩን እንዲክድ ነው:: ልጆቹንም ሀገር ጠል በሆነ አስተሰሳብ አንፆና ገንብቶ ነው:: ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ጠላታችሁ ናት፣ አንድንነት ሠይጣናዊ እንደሆነ አድርጎ እያስተማረ ነው ትውልዱን የቀረፀው::
ደደቢት ላይ የተወለደው ይህ ቡድን ከመነሻው ሀገር ለማፍረስ ነው የተመሠረተው:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይረዳው ዘንድ አስቀድሞ የመከላከያ የፖሊስ ሠራዊትን ነው ያፈረሰው:: ከዚህ በሻገር ሥልጣን ላይ እንደወጡ የፈፀሙት ሕዝብን በዘር መከፋፈል ነው:: ባለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመኑ የማያውቀውን መከፋፈል ነው ያስተማሩት:: ሲጀመርም ደግሞ ሠራዊት ውስጥ ዘረኝነት አስፈላጊ አይደለም:: በዘር የሚያምን በሠራዊት ውስጥ ካለ ያንን ሠራዊት ይበክላል:: በሄደበት ቦታ ሁሉ ሠላምና ፀጥታ ከማስከበር ይልቅ ስለመጣበት ጎሣ ነው የሚያስበው:: ከዚያም በዚህ መልኩ እንዳሰበው ከፋፈለን::
ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሊሰጠን አስቦ ለ30 ዓመት እንደፈለገ ሲያደርገን ቆይቷል:: ብዙዎቻችን ‹‹ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ተገዝታ አታውቅም›› ብለን በተለያየ ጊዜ እንናገራለን:: እኛ ግን በታሪካችን በወያኔ ለ30 ዓመታት ተገዝተናል:: በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ምርኮኛ ነበር:: ግን ደግሞ ምርኮኛው ያደረገን በዘር በመከፋል ነው:: እርስ በርስ በዘር አባልቶን ሲያበቃ እሱ መልሶ ገላጋይ መስሎ ጣልቃ እየገባ ግጭታችን ወደተባባሰ ሁኔታ እንዲገባ አድርጓል:: ሆኖም እኛን እያባላ ዕድሜውን ማራዘም ቻለ:: ለመቶ ዓመት በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ግን እነሱ እንዳሰቡት ቀላል አልሆነላቸውም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የቤት ሥራውን ሲሰራ የወያኔ የጥፋት አጀንዳቸው ፉርሽ ሆነ:: እንደምታስታውሽው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ወጣቶች አልቀው ለሁላችንም ለውጥ ማምጣት ቻሉ:: አሁንም ቢሆን የጁንታው ርዝራዦች ኢትዮጵያን ካላፈረሱ አርፈው አይተኙልንም:: ምክንያቱም ለአባቶቻቸው ለሣጥናኤል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቃል ገብተዋልና ነው:: ዲያቢሎስ ፊት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተማማሉትን ቃል ኪዳን ለመፈፀም ሲሉ ብቻ የብዙዎችን ደም ለማፍሰስ ነው ቆርጠው የተነሱት::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያለውን የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ከገባንበት ችግር ውስጥ ለመውጣትስ መፍትሄው ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡– በመሠረቱ እኔ ወታደር እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም:: ነገር ግን እንደማንኛውም ዜጋ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ያሳስበኛል:: ፖለቲካው መንገድ ስቶ ወደማይሆን አቅጣጫ ሲሄድ ለምን? ብለን መጠየቅ መቻል አለብን:: ፖለቲካና ፖለቲከኛ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል:: በእኔ እምነት ግን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ነው:: ለምንም የማይበገር፣ ዳር ድንበሩን በአጥንቱና በደሙ የሚጠብቅ ጠንካራ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ያስፈልገናል:: ከዚህም ባሻገር የሕዝቡ ሠላም ሊጠበቅ ይገባል:: ከዚህ ውጭ በእኛ ሀገር ሁኔታ ፖለቲካና ፖለቲከኛ መኖሩ ብዙም አስፈላጊ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ይህ በራሱ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመፍጠር ምክንያት አይሆንም?
መቶ አለቃ በቀለ፡- እኛ ሀገር እኮ አንዳንድ ፖለቲከኞች እኛ ካልገዛን፤ ሥልጣን ካልያዝን እያሉ ነው ሀገር እያተራመሱ ያሉት:: ይህንን የሚሉት ደግሞ ሀገርና ሕዝብን ለመዝለፍ እንዲሁም እንዲመቻቸው ነው:: ምንም አጀንዳ የሌላቸው ማህተማቸውን እንኳን በኪሣቸው ይዘው የሚዞሩ ሰዎች ናቸው ሀገር እንመራለን ብለው በተቃውሞ ጎራ ለይምሰል የተደራጁት:: እነዚህ ሰዎች ደግሞ ወያኔ ለ30 ዓመታት ለይምሰል ፖለቲካ አሠልጥና የፈታቻቸው ናቸው:: ወያኔ ይህንን ሁሉ ዓመታት ለእነዚህ ፓርቲዎች ፍርፋሬ እየጣለላቸው ሲቀለቡ ነው የኖሩት:: የምርጫ ሰሞን እነሱን ለማጀብ ብቻ የተቋቋሙ ፓርቲዎች በእኔ እይታ አያስፈልጉንም:: ሠላም ባለበት ሀገር ላይ የፖለቲካ ድርጅት መመሥረት ማለት እንደ ነዳጅ ጉድጓድ የገቢ ምንጫቸው ነው:: ለዓመታት ወያኔ በሚጥልላቸው ፍርፋሬ መሬት የገዙ፣ የራሣቸውን ኑሮ ያደራጁና ውጭ ሄደው የሚዝናኑ በርካቶች ናቸው::
እንደሚታወቀው ደግሞ ወያኔ የኢትዮጵያ ገፀምድር ያፈራውን ሐብት ሙሉ በሙሉ ነው የዘረፈው:: ሀገሪቱን በኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ አዳክመው ሲዘርፉ ነው የኖሩት:: እነዚህ ፓርቲዎች ደግሞ ከወያኔ የተረፈውን ሲለቃቅሙ ነው የኖሩት:: ለእኔ እነዚህ ፓርቲዎች ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ከሰው ተርታ የማይሠለፉ ናቸው:: ስለዚህ መኖር አለመኖራቸው ጥቅም አለው ብዬ አላምንም:: ይሁንና የተጨቆነ ሕዝብ ራሱን ነፃ ማውጣቱ አይቀርም:: የኢትዮጵያ አንድነትም ይመለሳል:: አሁን ላይ እያየን ያለነው ይኸው ነው:: ወያኔ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን ካረጋገጥንበትና በጋራ ከተነሣንበት እለት ጀምሮ ስለአንድነታችን እየታገልነው ነው የምንገኘው::
ወያኔዎች ጨለማን ተገን አድርገው ሕዝባቸውን ሲጠብቅ የቆዩትን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሌሊት አረዱ:: ማይካድራ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በዘር ለይተው ሲጨፈጭፉ ልክ ሩዋንዳ ላይ ከተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ አይለይም:: ይህ ሁሉ የመነጨው ከዘረኝነት ነው:: ዘረኛው ጀነራል ኢትዮጵያዊውን ጀነራል አገተ:: በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ይህንን የሀገርና የሕዝብ ጠላት የሆነውን ሃይል ድምጥማጡን እስከምናጠፋ ድረስ ፖለቲካው መረጋጋት አለበት ብዬ አምናለሁ:: አሁን ምርጫችንን በሠላም አካሂደናል:: የጀመርነውና ኢኮኖሚያችን ፈቅ ያደርግልናል ብለን ተሥፋ ያደረግነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ መስመር እየያዘም በመሆኑ በዋናነት ይህንን ሃይል ማጥፋቱ ላይ ነው ትኩረት ልናደርግ የሚገባው:: አሁን ላይ ሀገራችን ውስጥ እየበጠበጠ ያለውን ሠይጣን ማስወገዱ ላይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን አሁን ላይ ሕፃናት በጦርነት እንዲማገዱ ማድረጉ ለማህበረሰብ ሣይቀር የማይበጅ ሃይል ማረጋጋጫ አይሆንም ይላሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ይኼ ምንም አጠያያቂ አይደለም፤ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ጦርነት የገባበት ዋነኛ ዓላማ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የመግዛት ዓላማውን ለማስፈፀም ሲል ነው:: ትልቁና ዋናው ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ጦርነት ላይ ሕፃናትንና ደካሞችን የሚያሣትፈው ከጅምሩ የጦርነትን ሣይንስ የማያውቅ በመሆኑ ነው:: በውትድርና ሣይንስ ሚሊተሪ ማለት ሣይንስ እና ሙያ ነው:: በመጀመሪያ ደረጃ የሠራዊት አባል መሆን ያለብሽ አምነሽና ወደሽ ነው:: ከገባሽ በኋላ ሣይንሱን ማጥናት ይገባሻል:: ደግሞም ሣይንሱ እንደየጊዜው ራስን መቃኘት ያስፈልጋል:: በእኔ እምነት የእነሱ ሠራዊት ከሣይንሱ አንፃር ያልሰለጠነ ነው:: የቡድኑ መሥራቾችም ቢሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ሣይንሱን አያውቁትም:: ለዚህም ነው በጦርነቱ ላይ ሕፃናቱንና ደካሞችን እያሣተፉ ያሉት:: ሽፍታ ሆነው ሽፍታዎችን መለመሉ:: ዓለም አቀፍ የጦር ሕግን ስለማያውቁ ነው ሕፃናትን ከፊት እየማገዱ ራሳቸውን ደብቀው በሽምቅ የሚዋጉት:: እኛ እንደተማርነው በተለይም ሲቪል ያለበት ቦታ ላይ ጦርነት አይካሄድም:: ሲቪሎችን ካስወጣሽ በኋላ ነው ጦርነት የምትገጥሚው:: እኔ እንደማስታውሰው በሱማሌ ጦርነት ላይ እንኳን ደካሞችን ከጦርነት ቀጠና አስወጥተን ነው ስንዋጋ የነበረው:: ያም ሆኖ ግን ወራሪውን ሃይል ወደመጣበት ለመመለስ ሦስት ወር አልፈጀብንም:: በአጠቃላይ የወያኔ ውድቀት የሚጀምረው ሣይንሱን ሣያውቅ ንፁሃንን ማስፈጀት ከጀመረበት እለት ነው ብዬ ነው የማምነው::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የቀድሞ ሠራዊት አባላትም ሆነ መላው የሀገር ተቆርቋሪ ሕዝብ የአሸባሪውን ቡድን ትንኮሣ ለመመከት በአንድ ልብ መነሣታቸው በራሱ ምን የወለደው ነው ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ይህንን ሣስብ በእውነቱ ሐዘንና ደስታ የተቀላቀለበት ሥሜት ነው የሚፈጥርብኝ:: ሐዘን የሚሰማኝ ያ መፍረስ ባልነበረበት እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፈረሰ ሠራዊት በረሃብ፤ በበሽታ፤ አሁንም ወጣ ብትይ በየጥጋጥጉ እና በየቤተክርስቲያን ደጅ ላይ ወድቆ ነው የምታይው:: አልተሰበሰበም:: ዛሬም የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ፍትህ አላገኘም:: አሁንም የለውጡ መንግሥትም ከተለያየ ፓርቲ አባላቶች ጋር ሠላም ፈጥሯል:: እኛም ሆነ እሱ ማለፋችን አይቀርም:: ምንአልባት ወደፊት ግን ‹‹ኢትዮጵያን ለማቆም የማዕዘን ድንጋይ ነበራችሁ፤ እንደሚገባችሁ ክብር አልተሰጣችሁም›› ብሎ ይቅርታ የሚጠይቅ መንግሥት ይመጣ ይሆናል:: የለውጡ መንግሥት ግን በዚህ በሦስት ዓመት ውስጥ እኛን ዞር ብሎ አላየንም:: በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ነው የማዝነው::
በእኛ አጥንትና ደም ነው ይህች ሀገር የተሠራችው:: ይህም ቢሆን ግን አሁንም የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማህበር አቋቁመን ራሣችንን እና ሀገራችን ለመደገፍ በጋራ እየሠራን ነው ያለነው:: አሁን በሀገራችን ላይ ይህ ዓይነቱ መከራ ሲመጣበት አጋርነታችንን ለማሣየት ጊዜ አልወሰድንም:: ጥያቄው ከእነሱ መምጣት ሲገባው እኛ ራሣችን ነን ጠርተን እናግዛችሁ ያልነው::
እንደምታስታውሺው ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ ወጥተን አሁን ላሉት ልጆቻችን ድጋፍ ሠጥተናል:: እናንተ ያስለቀቃችሁት ቦታ ላይ አሮጌ መትረየሶቻችንን ይዘን ሕዝቡን እንጠብቃለን ብለናቸዋል:: የግድ ጦር ሜዳ ሄደን ከጠላት ሠራዊት ጋር መጋጠም ላይኖርብን ይችላል:: ግን ደግሞ የቀደመ እውቀትም፤ ልምድም ስላለን ልናካፍላቸው፤ ልናማክራቸው እንችላለን:: ማሠልጠን፤ ሎጅስቲክስና አስተዳደራዊ ሥራዎችን መሠራት እንችላለን:: ከዚህም ባለፈ የየአካባቢያችንን ሠላምና ፀጥታ ማስጠበቅ እንችላለን:: እገዛ ሲባል ጠመንጃ መተኮስ ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡን ማደራጀት፤ ቀለብ መስጠት፤ ጥይት ማቅረብ፤ የተፈናቀለውን ሕዝብ ቦታ መስጠትና መደገፍ ይቻላል:: ቁስለኛ ማንሣት የሞተውን መመዝገብ የመሣሰሉትን ሥራዎች እንሰራለን:: እኛ በአጠቃላይ እያልን ያለነው ተጠቀሙብን ነው::
አዲስ ዘመን፡-አሸባሪው ቡድን በሐሰት ፕሮጋንዳ ሕዝብን የማሸበር ሴራን በማጋለጥ ረገድ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ድሮም የእኛ አባቶች ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚል አባባል አላቸው:: ይህም የተባለው ወሬ ወይም ፕሮፖጋንዳ ሃገርን ለማሸበር ትልቅ አቅም ስለለው ነው:: አሁንም ጦርነት በማህበራዊ ሚዲያ አየር ላይ ነው እየተከናወነ ያለው:: ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ለተንኮልና ሴራቸው ጥሩ መሣሪያ ሆኖላቸዋል:: በመሠረቱ እኛም ጦር ሜዳ ከወያኔ ጋር በታገልንበት ወቅት ባልነበሩበት ጦር ሜዳ ሣይቀር ያልሰሩትን ገድል እየተናገሩ፤ የሐሰት ወሬ እየነዙ ሀገር ለማተራመስ ጥረት ያደርጉ ነበር:: እኛ አጠገባችን ያለውን ክፍለ ጦር ሣይቀር ‹‹ደምስሺያለሁ›› እያለ ሕዝብን ያስጨንቅ ነበር:: የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ እንኳን በወያኔ ፕሮፖጋንዳ ተማሮ ‹‹እነዚህ ሰዎች ገና ከሚወለደው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር ነው የሚገድሉት ›› የሚል ሐሳብ ነው የተናገረው:: እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝቡ አልቆ ምድሪቷ ሰው አልባ በሆነች ነበር::
ይህ የወያኔ የቀደመም ማንነቱ ውሸታምነቱ ነው:: እነሱ የተካኑት በውሸት ነው:: በነገራችን ላይ በዚህ መጥፎ ሥራቸው የቀጠሉት ውጤትም ስላገኙበት ነው:: ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የሄድሽበት መንገድ ላይመልስሽ ይችላል:: አሁን ባለንበት ዘመን ምንም እንኳን ሕዝቡ የማህበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚ ቢሆንም በተግባር ፈትኖ ማረጋገጥ የሚፈልግ ጠያቂ ትውልድ ስለተፈጠረ ይህ የሐሰት ፕሮፖጋንዳቸው እንኳንስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ከጎናቸው የተሠለፈው የህብረተሰብ ክፍልም ሣይቀር እያደር በራሣቸው ላይ እንደሚነሣ አልጠራጠርም:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም የእነዚህን ባንዳዎች ሴራ ቀድሞም የነበረ ባህሪ መሆኑን ተገንዝቦ ሴራቸውን ማክሸፍ ይገባል:: ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ ገብቶ አንድነታችንን ማጥፋትና ሃገር የመበተን አጀንዳ እንዳይሣካ ነቅተን መጠበቅ ይገባናል:: ይህንን የታሪክ አተላ የሆነውን ጁንታ ቡድን መቃብሩ ውስጥ እስክንከተው ድረስ እንቅልፍ አይኖረንም::
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል የምለው ምንም እንኳን ይህ ከሃዲ ቡድን ከትግራይ እናት ማህፀን የወጣ ቢሆንም ሽፍታውን በማስወገድ ሂደት ንጹሃን እንዳይጎዱ መጠንቀቅ ላይ ነው:: ርግጥ ነው፤ እነሱ ሕዝብን ነው መከታ አድርገው ሕዝብ ውስጥ የተሸሸጉት:: ይሁንና አሁንም ተገድዶ ወደ ጦርነቱ የገባ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን ልንዘነጋ አይገባም:: ይህም ማለት የእንቁላሉን አስኳል ከነጩ ክፍል ለይቶ ለመጥበስና ለመብላት አስቸጋሪ እንደሆነው ሁሉ ሕዝብ ሥር የተደበቀውን ጁንታ ነጥሎ መምታት ከባድ ነው የሚሆነው:: በመሆኑም ህዝቡ ከዚህ አሸባሪ ቡድን ስር መላቀቅና ራሱን ችሎ ሊቃወምና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ሊቆም ይገባል:: የትግራይ ሕዝብ እነዚህን እኩይ ሰዎች ከጉያው ሥር አውጥቶ እስካልሰጠ ድረስ አብሮ ሊጎዳ የሚችልበት ዕድል አለ:: ምንአልባት ልክ እንደእንቁላሉ ሁሉ አልለይ ካለ አብረሽ ለመጥበስ ትገደጃለሽ:: እኔ ለትግራይ ሕዝብ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር አሁን ላይ ሠራዊቱ እየተቸገረ ያለው ጁንታውን ነጥሎ ለመምታት ያለመቻሉ ነው:: በመሆኑም ሕዝቡ ከሠራዊታችን ጎን ሊተባበር ይገባል:: ራሱን ብቻ ሣይሆን ሃገሩንም ከዚህ ባንዳ ቡድን ማዳን አለበት:: በተለይ ያለዕድሜያቸው እየሞቱ ያሉትን ሕዝብ መታደግ የሚችሉት ለዚህ ቡድን ዛቻና ማስፈራሪያ ሣይበገሩ አሻፈረኝ ሲሉ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ይህ አሸባሪ ቡድን ነፃ አወጣሃለሁ የሚለው ማህበረሰብ እርዳታ እንዳያገኝ ክልል እያደረገ ነው:: ከዚህ አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- አንቺም እንዳልሽው ወያኔ በ30 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑም ሆነ ከዚያ በፊት በነበረው የ17 ዓመታት የትግል ሕይወቱ የትግራይን ሕዝብ ነፃ አወጣሃለው እያለ ሲያስጨርሰው ነው የኖረው:: እናቶች እውነት መስሏቸው ከአንድ ቤት ሦስትና አራት ልጅ ለጦርነት እሣት የገበረበት ሁኔታ ነው ያለው:: ይህ የደም ዋጋ የተከፈለበት ድርጅት ግን በሥልጣን ዘመኑ አንድም ቀን ሕዝቡን አልጠቀመም:: ለትግራይ ሕዝብ ቢያስብማ ለእርዳታ የተባበሩት መንግሥታት ሰዎችን እንዳይገቡ ባልተከላከለ ነበር:: በሌላ በኩል ደግሞ የእርዳታ ድርጅቶቹ በዚያ መልኩ ገብተው እርዳታ ቢሰጡም በቀጥታ ለሕዝቡ የማይደርስበት ነባራዊ ሁኔታ ነው ያለው:: ለዚህ ማረጋገጫ እንዳለ ደግሞ በተለያየ መረጃዎች ሠምተናል:: አንዳንዱ ሰው አሥር ቤተሠብ አለኝ ብሎ የአሥር ቤተሠብ ቀለብ ይወስድና ግማሹን ሃገሩን ለመበተን ደፋ ቀና እያለ ላለው ጁንታ ነው እየሰጠ ያለው:: እኛ ‹‹ወገናችን ነው›› እያልነው የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ወገን ነው ስንል እነሱ ግን አሁንም ጁንታውን እየደገፉ ነው ያሉት:: ይህ ሊሆን የቻለው ወያኔ ለዓመታት ሕዝቡ ጭንቅላት ላይ በዘራው ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ምክንያት ነው::
ጥቂት የማይባሉት የወያኔ አጋፋሪዎች በመርዛማ ዘረኝነት አስተሳሰብ በመመረዛቸው ምክንያት ዛሬም ድረስ ከእነሱ በላይ ሰው እንደሌለ ነው የሚያስቡት:: እኛ የቱንም ያህል ብናዝንላቸውም እነሱ ዛሬም ከጀርባችን ነው የሚያሴሩት:: የትግራይ ሕዝብ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄድና እዚያ በዘረኝነቱ ታጥሮ እንዲኖር አድርገውን ነው የሰሩት:: እንደሚታወቀው ደግሞ ትግራይን ሲያስተዳድሩ የአንድ ጎሳ ማለትም የአድዋ ልጆች ናቸው:: ከነሥብሃት ነጋና ከነመለስ ዜናዊ ውጪ ሌላው እኮ ሚስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ምንም ያገኘው ጥቅም የለም:: ስለዚህ አሁን ላይ ይህ ሕዝብ መንቃት ነበረበት:: ግን የትግራይ ሕዝብ አሁንም እየተበደለ ዝምታን ነው የመረጠው::
በሌላ በኩልም ከወያኔ በስተጀርባ የአሜሪካ እጅ እንዳለበት ግልፅ ነው:: ላለፉት 30 ዓመታት ሙሉ ሲላላኩ የነበሩት ለአሜሪካኖች ነው:: አሁንም ሆነ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ውስጥ ከፈጠረው ችግር በስተጀርባ ያሉት አሜሪካኖች እና አውሮፓዎች ናቸው:: አሜሪካ ደግሞ በታሪኩ በየትኛውም ዘመን ኢትዮጵያን ደግፎ አያውቅም:: በ1828 ዓ.ም፣ በ1888 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ከኋላ ሆኖ ለጠላት መሣሪያ ሲሰጥና ሲደግፍ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት ነው:: አሜሪካኖቹ ሶማሊያ ዝመት ሲሉት ይዘምታል:: ይሁንና በሠላም ማስከበር ሰበብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሰጠውን ዶላር በሙሉ ወስደው ለራቸቸው ነው የሚያደርጉት:: ምስኪኑ የኢትዮጵያ ልጅ ግን እዚያ ሄዶ ይሞታል:: በወያኔ ጥግ ድረስ እኮ ነው ግፉ የተሠራብን:: ርዋንዳ ሄደው ምን አገኘህ ብለን ከኛ የሚያንሱት በጓደኝነት ስንጠይቃቸው በሙሉ ዩናይትድ ኔሽን ሊሰጠው ያሰበውን አንድ እጁን አልሰጡትም:: ይኼንን ስትሰሚ በጣም ነው የምታዝኚው:: እዚያ ሄዶ ሞቶ ለቤተሠቡ ጡረታ ያልሰጡት ሰዎች አሉ::
ስለዚህ የውጭ ሃይሎችንም ቢሆን በጠላት ፈርጀን ማየት ነው የሚገባን:: ዘንድሮም ቢከዱንም ድንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ እናውቃለን ነው:: እኛ ከልምዳችን እናውቃለን:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ከኋላቸው ያሉት እነሱ ናቸው:: አሁን ከጊዜ በኋላ እውነቱ በገሀድ ሲወጣ እያመኑ እየመጡ ይመሥለኛል:: ያውቁናልም ደግሞ፤ እኛ የሰው ሀገርን ድንበር ወርሰን አናውቅም፤ የራሣችንንም አሣልፈን ሰጥተን አናውቅም:: የሰው መብት ነክተን አናውቅም:: ኢትዮጵያ የሰውም አትነካም፤ የራሷንም አሣልፋ የማትሰጥ ለዘመናት በነጻነት ታፍራና ተከብራ የኖረች፤ ለጥቁር ሕዝቦች ምሣሌና ተምሣሌት የሆነች ሀገር መሆኗን ያውቃሉ:: በተቃራኒው ደግሞ አሜሪካኖች የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነበሩ:: ስለሆነም አንዲት የአፍሪካ ሀገር ራሷን አስከብራ መቆየቷ ሁልጊዜም ራስ ምታት ሆኖባቸው ነው የቆየው:: አሁን ደግሞ የዚህ ዘመን መሪ ብቻውንም ቢሆን መከራውን የሚበላው ‹‹እኔ ለናንተ አልላላክም፤ አንገቴ ይቀላል እንጂ ሀገሬን ለእናንተ አሣልፌ አልሰጥም›› ብሏቸዋል:: ይህ እንደ አንድ ደሃ ሀገር መሪ የማይጠበቅ ነው:: ይህ ሁኔታ ስለሚያበሳጫቸውም ነው ለወያኔ ድጋፍ እየሰጡ ያሉት::
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ጋር አያይዘን የምናነሣው ነገር ሕወሃት ራሱ እየገደለ የመጮህ ባህሪ አለው:: ይህ ባህሪው አሁን ከሚያሣየው ሁኔታ ጋር ተመሣሣይነቱ እንዴት ይገለጻል?
መቶ አለቃ በቀለ፡– አንድ ተረት አለ፤ አንድ ሰው በመስማት ላይ ሕይወቱ ቆይቶ ዱዳ ቢሆን ምንድነው የሚያወራው ጥያቄ ቢጠይቅሽ ያንኑ ያለፈውን ዘመን ታሪክ እንጂ የዚህን ዘመን ወሬ አይደለም:: ልክ መስማት እንደተሣነው ሰው እነሱ ያኔ ደደቢት ላይ ያሴሩት ተንኮልን ነው ዛሬም ድረስ ይዘው የዘለቁት:: በርግጥ ብዙዎቹ የተንኮሉ ጠንሣሾች አሁን ላይ አልቀዋል:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መለስ ዜናዊ ነው:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እዚያ ጋር የፃፉት ዶክትሪን እንጂ ሌላ አዲስ ነገር የላቸውም:: እሷም ምንድነች ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው:: አሁንም እሱ ያንን ታሪክ ለመድገም ነው:: እነሱ እኮ መንግሥት ከሆኑ በኋላ ራሣቸውን ለማስተማርና እንደጊዜው አሠራራቸውን ለመቃኘት አልሞከሩም:: ከዚያ ይልቅ ግን ሀገር መዝረፍ ላይ ነው የተጠመዱት:: ደጋግመን የምንናገረው ይኼንን ነው:: ግን አሁን እነዚህ ሰዎች ቅድም እንደነገርኩሽ የመጨረሻ ግብዓተ መሬታቸው እየተቃረበ ስለመጣ ነው እየተንቀዠቀዡ ያሉት:: ከመሠሪነታቸው የተነሣ ራሣቸው እየገደሉ ተገደለብን ይላሉ:: ግን እውነት ተደብቆ አይቀርም፤ በሂደት የዓለም ሕዝብ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ:: ደግሞም የኢትዮጵያ ሕዝብም ደም ይጮኻል:: ስለዚህ ራሣቸውም ሆነ ለሕዝባቸው የሚጠቅም ሥራ ሣይሰሩ ነው የሚያልፉት::
አዲስ ዘመን፡- ሕወሃት በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ተግባር እየፈፀመና እየገደለ ነው ያለው:: በሌላ በኩል ደግሞ ውጪ ያሉ የነሱ ፕሮፓጋንዳ አቀንቃኞችን በመጠቀም የዘር ፍጅት እየተካሄደበት እንደሆነ ይገልጻል:: እነዚህ ነገሮች እንዴት አብረው ሊሄዱ ይችላሉ?
መቶ አለቃ በቀለ፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ሕጎች አሉት:: ሀገራት ወደውና ፈቅደው ፈርመው ያፀደቁት ሕጎች አሉት:: ያን ሕግ ወያኔ አያውቅም:: በዚህ ምክንያት ሕጎቹንም ጠንቅቆ አያውቅም፤ ቢያውቅም ተግባራዊ ስለማያደርገው ነው አሁን ላይ በጠላትነት ከተፈረጀው የኤርትራን ወገኖቻችን አምነው በተጠጓቸው እየገደሏቸው ያሉት:: በኤርትራ ስደተኞች ላይ የተፈፀመው የሽፍታ ሕግ ነው:: የሚከተሉትም ሕገ-አራዊት ነው:: እጁን የሰጠ፣ ካምፕ ውስጥ የሚኖር ሰው ጠመንጃ የለውም:: ሌላው ይቅርና የረባ የሽንኩርት ቢለዋ እንኳን የለውም:: ስደተኛ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር የሚፈፅሙት በምንም ዓይነት ሕሊና የሌላቸው ሰዎች መሆናቸውን ነው የሚያስረዳሽ:: ሌላው ይቅርና ምርኮኛ እንኳን ሲያዝ ሕጎች አሉ፤ የምትፈልጊውን ነገር ለማግኘት ያንን ምርኮኛ ከያዝሽ በኋላ ሁሉንም ነገር ነው የምትተይው::
እንኳንና በስደት መጥቶ እቺ ትሻለኛለች ብሎ የተጠለለ እንደዚህ ዓይነት ማድረግ በጣም የሚያሣዝንና የሚያሣፍር ተግባር ነው:: የሚገርመው ትናንትና አብሯቸው የተዋለደ እና የኖረ ሕዝብ ላይ በዚህ ደረጃ ጭካኔን ማሣየት ከሰው ተርታ አያስመድብም:: በአጠቃላይ ስደተኛን የሚገድል፤ ሴት የሚደፍር፤ እርጉዝ ሴትን ለጦር ሜዳ የሚጠቀም ሃይል ከሰውነቱ ይልቅ አውሬ ነው ብንለው ይመረጣል::
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ቡደን ትንኮሣ ሕዝቡ ዳግም ሕብረቱን እንዲመልስ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ብለው የሚያምኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ:: እርስዎ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድነው?
መቶ አለቃ በቀለ፡- ዕድሜ ይስጥሽ፤ ጥሩ ጥያቄ ነው ያመጣሽው፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ መከራና ፈተና የተለያት ቀን የለም:: ይሁንና አንደኛው መከራ አንድ ዘመን አስተምሮ ያልፋል፤ ሌላ መከራ ደግሞ ሌላውን አስተምሮ ያልፋል:: ስለዚህ አሁን የተፈጠረው ነገር ወያኔ ለ30 ዓመት ሙሉ ያፈረሰብንን አንድነት፣ መተሳሰብ፣ መፈቃቀር፣ መተዛዘንና ኢትዮጵያዊነታችንን ዳግም ለማደስ መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ ነው የማምነው:: አሁን ላይ ለዓመታት የተዘራብን ዘረኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቀለልን ነው:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት በማወጃቸው እግዜህር ይስጣቸው ባይ ነኝ:: አምላክ እኔ ኢትዮጵያን እንደምወዳት ሀገሬን ስለሚወዳት ሊያድናት ሲፈልግ ወያኔ በገዛ እጁ ተንኩሶ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲነሳበት አደረገ:: ስለዚህ በቀጣይም ወያኔም ሆነ ሌላ የውጭ ጠላት እንዳይመጣብን ይህንን ሕብረት ይዘን ነው መቀጠል ያለብን ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሠግናለሁ::
መቶ አለቃ በቀለ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሠግናለሁ
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013