“ክፈቱልን በሉት በሩን – ኮሪዶሩን!”
ልክ በዛሬው ዕለት “ሀ” ብለን የምንጀምረው ወርሃ ነሐሴ በብዙ የሀገራችን ክፍሎች የሚታወቀው “የልጆች ወር” በመባል ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ በነሐሴ ወር ውስጥ የሚውሉት አብዛኞቹ የብሔረሰቦቻችን ደማቅ ባህላዊ ዐውዳመቶች በሥፋትና በድምቀት ያለ ምንም የእምነትና የዕድሜ ልዩነቶች የሚከበሩት በአብዛኛው ከታዳጊነትና ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ነው፡፡ የታዳጊ ወጣት ወንዶች የቡሄ ጭፈራ፣ የልጃገረዶች ሻደይና አሸንዳ ክብረ በዓለት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ የምንጠቅሳቸው የነሐሴ ወር መልካም ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ለማድረግ የተፈለገው ሁሉንም ባህላዊ ክንውኖች ለመዳሰስ ታስቦ ሣይሆን በዋነኛነት የቡሄ ጨፋሪ ታዳጊ ወጣቶችን አንዳንድ ነባር ግጥሞች በመዋስ ለመጠቀም ታስቦ ነው፡፡ ግጥሞቹ ከወቅታዊው ሀገራዊ ፈተናችን ጋር በደንብ የሚገጣጠሙ ስለመሰለኝ ጥቂቶቹን ብቻ መዝዤ ለማሣያነት እጠቀምባቸዋለሁ፡፡ የቡሄ ግጥሞችና የፖለቲካ ሴራዎችን አሰባስበን ያለቦታቸው ያቀራረብነው ዕድሜ ጠገቡ ባህላችን ከፖለቲካ አይዲዮሎጂ ጋር ቅርበት ስላለው ሣይሆን የወቅቱን ግጥምጥሞሽ ይበልጥ አጉልቶ ለማሣየት ስለተፈለገ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
“እዚያ ማዶ (ሆ!) ጭስ ይጨሣል፣
እዚህ ማዶ (ሆ!) ጭስ ይጨሣል፣
አጋፋሪው ይደግሣል፡፡”
የባህሉ ዋነኛ ባለቤቶች ታዳጊዎቻችን አይቆጡንና እነዚህ ጥቂት የተውሶ ስንኞች የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ የሚገልጹ ይመሥለናል፡፡ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ እናት ሀገር ኢትዮጵያ በክፉዎችና በጨካኞች የሴራ ጭስ የታጠነችበት ወቅት ስለመሆኑ ለማንም ዜጋ የተሰወረ አይደለም፡፡ በሀገር ውስጥ በሽብር ጭስ እያጠናት ያለው ትህነግ ይሉት የክህደት መገለጫ ቡድን ሲሆን፤ እዚያ ማዶ ደግሞ የሰብዓዊነትና የዴሞክራሲ ጭምብል ያጠለቁ ሀገራት፣ ቡድኖች፣ ሚዲያዎችና የዚሁ የሕወሃት “ግፋ በለው!” ባይ ወጥቶ አደር ጀሌዎች የአመጽ ጭሳቸውን እያጋጋሙ ሀገሪቱን ለማቃጠልና ለማዳከም ቀን ከሌት ሲታትሩ እያስተዋልን ነው፡፡
ሀገራዊ ጠላቶቻችን የዘመቱብንና ያዘመቱብን ልክ በመርዝ እንደተለከፈ ውሻ እየተንቀዠቀዡና እየተክለፈለፉ ነው፡፡ በመርዝ የተጠቃ ውሻ ያገኘውን ሁሉ መልከፉ የተለመደ ነው፡፡ የመልከፊያ ስልቱ ደግሞ ንክሻው ብቻ አይደለም፡፡ የሚያዝረበርበው ለሃጭም ከንክሻው ባልተናነሰ ደረጃ ጉዳት የማድረስ አቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ ዳግም በረሃ ገብቶ ሸርጥ ለሸርጥ እየተቅበዘበዘ የሚዋጋው በብረት ብቻ አይደለም፡፡ ጤናማ ሞራል ባልታደሉትና የንጹሕ ህሊና ድኩማን በሆኑ አፈቀላጤዎቹ አማካይነት መርዝ የተለቀላቀለበት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እያዝረበረበ ጭምር ነው፡፡ የዓለም ሕዝብን ለማሳሳት የሚጥረውም በአብሾ ማጋጋያ ሐሺሽ ሰክረው ከውሸት ከፍ ያለ ኩሸት በመፈብረክ ምን ይሉኝ ይሉኝታን ረግጦ በመጣል ነው፡፡
ከደደቢት በረሃ እስከ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት የቆይታ ዕድሜያቸው የንፁሐን ኢትዮጵያዊያን “አቤሎችን” ደም በማፍሰስ የኖሩት እነዚህ የቃየል ውላጆች ዛሬም ደም እየገበሩ ለዳግም የሥልጣን ጉጉት የሚካድሙት ከያዛቸው አጋንንታዊ መንፈስ ጋር እንደተቆራኙ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የሠፈረው የአቤልና የቃየል ታሪክ ከእነዚህ ደም ያሰከራቸው ተቅበዝባዦች ጋር በሚገባ ይገጥም ስለመሰለን ጥቂት ቁጥሮችን ተውሰን እንጠቅሳለን፡፡
“ፈጣሪም ቃየልን አለው፡- ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? ቃየልም መለሰ የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም፡፡ ፈጣሪም መለሰለት፡- የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል፡፡ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን በከፈተች ምድር ላይ እንደ ተንከራተትክና እንደ ተቅበዘበዝክ የተረገምክ ሆነህ ትኖራለህ፡፡…ቃየልም ፈጣሪን አለው፡-ኃጢያቴን ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ነች፡፡ እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሣደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፡፡ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል፡፡” (ዘፍጥረት 4፡9-14) የአማራና የአፋርን ሕዝብ ብቻ ሣይሆን የራሣቸውን ታዳጊ ወጣቶች “አቤሎችን” ሣይቀር ደማቸውን በከንቱ እያፈሰሱ ያሉት የትህነግ ተቅበዝባዥ ቃየሎች ሰብዓዊያን ናቸው ብሎ ለማመን እስከሚያስቸግር ድረስ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ድርጊት ተዝርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ለጦርነት እየማገዷቸው ያሉት ታዳጊ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቢያድላቸው ኖሮ ልክ እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው በሠላማዊ አካባቢያቸው ጅራፍ በማጮኽና በመቦረቅ የነሐሴ ወራትን ባሣለፉ ነበር፡፡ ልጃገረዶችም የአሸንዳ በዓላቸውን እንደለመዱት ደስ እያላቸው ባከበሩ ነበር፡፡ ያለመታደል ሆኖ ግን ታዳጊዎቹን ወጣቶች በዐውደ ግንባር በማዋል ፈፋ ለፈፋ ማንከራተታቸው ሣያንስ ያስታጠቋቸውን ጠብመንጃ ሣይተኩሱ እንዲያልቁ እንደምን እንደፈረዱባቸው ማሰቡ በራሱ መንፈስን ያውካል፡፡ ይህም የጭካኔያቸው ጥግ አንዱ መገለጫ ነው፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን ከዓለም አቀፍ የጥፋት አጋሮቹ ጋር ልብ ለልብ ተቆላልፎ ታዳጊዎቹን ከፊት እያስቀደመ የሚያስጨፍራቸው “በሱዳን በኩል የምንቆጣጠረው ኮሪዶር ይከፈትልን” የሚል አጀንዳ ግቷቸው ነው፡፡ በኃያላኑ እግር ሥር ተደፍተው የሚማፀኑትም ይኼ ምኞታቸው እንዲፈፀምላቸው ነው፡፡ የልመና ሥልታቸውም ቡሄ ጨፋሪ ታዳጊዎች ከሚጠቀሙባቸው ስንኞች ጋር በደንብ ይመሳሰላል፤
“እንደ አሮጌ ጅብ አልጩኽብህ፣
አሮጌ ጅብስ ጮኾ ያባራል፣
እንደኔ ያለው መች ይለቅሃል፡፡”
ርግጥ ነው አሸባሪው ትህነግ አሮጌ ጅብ ብቻ ሣይሆን አዲስ ፍልፍል እባብ መሆኑንም ጭምር በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በተገኙበት የፓርላማ ውሎ እንደገለጹት የትህነግ አሮጌ ጅቦች በ1977 ዓ.ም በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ርሃብ አስታከው የጦር መሣሪያዎችንና በርካታ የጥፋት መገልገያዎችን በገፍ ለማስገባት እንዲያመቻቸው መሆኑን በሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ዓመት የዓለም ማኅበረሰብን ተማፅነው በኢትዮ ሱዳን ድንበር በኩል ኮሪዶር አስከፍተው እንደምን በሁሉም አቅጣጫ ኃይላቸውን እንዳፈረጠሙ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ባረጀ አሮጌ ጅብ ጩኸት ስልቱና ቅኝቱ ሣይለወጥ “አጋር ጌቶቻቸውን” በመማፀን “ክፈት በሉት በሩን!” የሚል ኡኡታ እያሰሙ ነው፡፡
ይህ ያፈጀና ያረጀ ስልት “የኢህዴን ሠራዊት የአሥር ዓመታት ታሪክ (ከ1973 – 1983 ዓ.ም) በሚል ርዕስ በታተመ አንድ መጽሐፍ ላይ የወቅቱን የትህነግ ሴራ የተጋለጠው እንዲህ ተብሎ ነበር፤ “የምዕራቡ (ትግራይ) ግንባር እንደሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም የተትረፈረፈ ኢኮኖሚ ያለው ነበር፡፡ በተለይም በ1977 ዓ.ም ከተከሰተው አስከፊ የድርቅ አደጋ ጋር ተያይዞ ምዕራብ ግንባር (የትህነግ ቀጣና) የነበረው ሠራዊት በተነጻጻሪ በኑሮ የማይጎዳ፣ ድርጅቱ ከውጭ በሱዳን በኩል የተሻለ የምግብ ፍጆታና አቅርቦት ያገኝ ነበር” (በድልና በመስዋዕትነት የደመቀው የኢህዴን ታሪክ፤ አከለ አሳዬ [ብ/ጄኔራል]፤ ህዳር 2003 ዓ.ም፤ ገጽ 164፡፡)ልብ ብለን ይህንን አገላለጽ ስንፈትሽ “እንደ ሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም የተትረፈረፈ ኢኮኖሚ ያለው” የሚለው አገላለጽ አሸባሪው ትህነግ በወቅቱ ባስከፈተው የኢትዮ ሱዳን ኮሪዶር በኩል እንደምን እንደከበረና ረሃቡንም እንደ ተትረፈረፈ መና እንደተጠቀመበት ማረት (ማኅበረ ረድዔት ትግራይ፤ በኋላ ትምእት ተብሎ የተለወጠውን) የዘረፋ ተቋም ታሪክ በማየት ብቻ እውነታውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጥቂት ዐረፍተ ነገሮችን እንጥቀስ “የትግራይ ሕዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት አማካይነት እየተመራ ለ17 ዓመታት ባካሄደው የትጥቅ ትግል ያገኘው ገንዘብና ንብረት ለትጥቅ ትግሉ ማካሄጃ…እና ሌሎች የቁሳቁሶች እጥረቶች ለማስወገድ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡” (የሕወሃት ሕዝባዊ ትግል፤ ከ1967-1992፤ ገጽ 104፡፡) ይኼ ሁሉ የሚፎከርበት ሐብት እንደምን በበረሃ ውስጥ ሊከማች ቻለ? ብሎ መጠየቁ ቀደም ሲል ወደ ጠቀስነው እውነታ ይመራናል፡፡
“የዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች” የሚል ታርጋ የለጠፉና “ታላቅነትን ለራሳቸው የሰጡ” አንዳንድ “ሥልጡን ነን ባይ” ሀገራት “እንደ አሮጌ ጅብ እየጮኹ” ዛሬም እንደ ትናንቱ በሱዳን በኩል “የኮሪዶሩን በር ካልከፈትክ!” እያሉ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመሞገት መሞከራቸው የጥንቱን ተሞክሮ ዛሬም የሚሰራ መስሏቸው ነው፡፡ ረጂዎቹም ሆኑ ተረጂዎቹ “ጉድ እስኪያሰኝ ድረስ” የ44 ዓመታት ታሪክ በመድገም በደም ንግድ ለመክበር የሚቅበዘበዙት በርግጥም በረሃብ ለሚቆላውና ለዓላማ ቢስ ጦርነት ልጆቹን እየገበረ በስቅቅ ውሎ ለሚያድረው የትግራይ ሕዝብ አዝነውና ርህራሄ ተሰምቷቸው አይደለም፡፡ “የከሰረ ዐረብ የዱሮ መዝገቡን ያገላብጣል፤ ስለምን ቢሉ ከዓመታት በፊት የሰጠውን ዱቤ ሊጠይቅ” እንዲል ብሂሉ፤ የአሸባሪው ቡድን ዓላማ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ የሕዝቡን ረሃብ እንደ ትናንቱ ዛሬም የሃብት ማከማቻ አድርጎ እንደገና ለመፋነን፡፡ ይኼው ነው፡፡ ይህ ዓለማ ቢስነታቸው ከሀገራችን ቀዳሚ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል የአንዱን የዜማ ግጥም ያስታውሰናል፤
“ወደ ኋላ ሄደሽ በሐሳብ ከማለም፣
ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡”
ቀድሞውንስ የኢትዮጵያ መንግሥት የርዳታ እህልና መሠረታዊ የኑሮ ማቅለያ ቁሳቁሶች እንዳይገቡ መቼ እምቢ አለ? መንገዱንስ መቼ ዘጋ? ከመቶ ሃምሣ በላይ የእርዳታ እህል የጫኑ ግዙፍ መኪኖች ለሣምንታት ያህል እንዳይንቀሳቀሱ ያገደው ማነው? ራሱ አሸባሪው ቡድን አይደል፡፡ ለሕዝቡ የሚላክን እህል ቅርጥፍ አድርጎ የሚበላውና የሚሸጠውስ ራሱ ለመሞት አንድ ሐሙስ የቀረው ይኼው ድርጅት አይደል?
“ላግባሽ ያለሽ ላያገባሽ፤ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” እንዲል የአበው ብሂል አሸባሪው ቡድን የሩቅ መጽዋቾቹን ተማምኖ በቀቢፀ ተሥፋ ባይንፈራገጥ በበጀው ነበር፡፡ በአማራና በአፋር ወንድም ሕዝብ ላይም እየፈፀመ ባለው ትንኮሣም የሚያርፍበት ዱላ አንበርክኮት ቢፀፀትና እጁን ቢሰጥ በተሻለ ነበር፡፡
“አጫጭሰውና እርጥቡን ከደረቅ
እዚያው ጨሶ ጨሶ እዚያው ነዶ ይለቅ፡፡
አለ ቀረርቶኛው፡፡ “የሱዳን ኮሪዶር ካለተከፈተልኝ!” የሚለው እዮታ “የአሮጌ ጅብ ጩኸት” ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሥያሜ የለውም፡፡ መልሱ አይቻልም ነው፡፡ አሮጌ ጅብ ሌሊቱ ወገግ ሲል ወደ ጎሬው መግባቱ ስለማይቀር ጩኸቱ ታፍኖ የሚቀረው እዚያው በረሃ ውስጥ ነው፡፡ ሠላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013