በአንድ ወቅት በድንቅ ኳስን የማቀበል ብቃቱ የተማረከው የቀያይ ሰይጣኖቹ የምንግዜውም የፊት መስመር ፊታውራሪ እንግሊዛዊው ኮከብ ተጨዋች ዋይኒ ሩኒ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት በነበረበት ወቅት ስኮትላንዳዊውን አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጀርመናዊውን ‹‹ኢንተርናሽናል›› ተጫዋች ኦዚልን፤ ወደክለቡ እንዲያዘዋውሩለት ተማጽኖቸው ነበር። ነገርግን ለተጫዋቾች ዝውውር ረብጣ ዶላሮችን በማውጣት የሚታወቀው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ተጫዋቹ እ.ኤ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ በጀርመን ብሄራዊ ቡድን ድንቅ ብቃቱን ለአለም በማሳየቱ ተጫዋቹን በ2010/11 የውድድር ዘመን ማድሪዶች ለኮከቡ ረብጣ ዶላሮችን በመክፈል ከወርደር ብሬመን ወደ ሳንቲያጎ ቤርናባ አዘዋውረውት ነበር። ተጫዋቹም ሳንቲያጎ ቤርናባ በቆየባቸው ሶስት አመታት ከነ አንሄል ዲማሪያ፤ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፤ ካሪም ቤንዜማ ፤ዣቪ አሎንሶ የመሳሰሉ ከዋክብቶች ጋር በመጣመር ድንቅ ብቃቱን በማሳየት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። በኋላም ክለቡን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ‹‹ዘስፔሻል ዋን›› በማለት እራሳቸውን የሚጠሩት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒዮ ከክለቡ መሰናበትን ተከትሎ፤ በእርሳቸው የተተኩት ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ነበሩ። አሰልጣኙም ከተጫዋቹ ጋር ባለ መግባባታቸው በፔር ሜርተሳከርና ሉካስ ፖዶልስኪ አግባቢነት እ.አ.አ በ2013 በ42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ መድፈኞቹን ሊቀላቀል ችሏል።
ተጫዋቹም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመድፈኞቹን መለዮ አጥልቆ 182 ጨዋታዎችን በማድረግ 36 ጊዜ ኳስና መረብን ማገናኘት የቻለ ሲሆን፤ ሶስት የኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችንም ከክለቡ ጋር ማንሳት ችሏል። መልከ መልካሙ ጀርመናዊው ኢንተርናሽናል ተጫዋች ኦዚል፤ በመድፈኞቹ ቤት ጣጣቸውን ያለቀላቸውን ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በምህታታዊው እግሩ ቀምሮ አቀብሏል፡፡ በንስር አይኖቹ ጓደኞቹ ያሉበትን አቋቋም በማየት ካሶቹ ሳያጥሩና ሳይረዝሙ እግራቸው ላይ አመቻችቶ ሰጥቷል፡፡ ለጎል አመቻችቶ የሰጠውን ኳሶች 500 መቶ ማድረስ የቻለ ሲሆን፤ ተጫዋቹ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከቶትንሀሙ የማህል ሜዳ ፈርጥ ክሪስቲያን ኤሪክሰን ቀጥሎ ለጎል የሚሆን የግብ እድል በመፍጠር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ መድፈኞቹን ለሀያ ሁለት አመታት በማሰልጠን አለም ላይ አሉ ከተባሉ ክለቦች ተርታ ማሰለፍ የቻሉት ፈረንሳዊዉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በክለቡ ውጤት ማስመዝገብና የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ከተሳናቸው 12 ኣመታት በላይን ማስቆጠራቸውን ተከትሎ፤ የክለቡ አመራሮች አሰልጣኙ ክለቡን እንዲለቅ ያደረጉት ባሳለፍነው ዓመት ነበር።
ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ክለቡን መልቀቅ ተከትሎ በሳቸው የተተኩት የቀድሞው የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አሰልጣኝ የነበሩት ኡናይ ኤምሬ ናቸው። አሰልጣኙ ወደ ከለቡ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በክለቡ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአንድ እስከ አራት ይዘው ለማጠናቀቅ፤ ከሊጉ ሀያላን ክለቦች ጋር ተናንቀው ለሚቀጥለው አመት በሻምፒወንስ ሊጉ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ውጤት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። ነገርግን አሰልጣኙ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር አንዴ ጉዳት ሌላ ጊዜ የአካል ብቃቱ ለጨዋታው አይመጥንም በሚሉ ሰበቦች ሜሱት ኦዚልን የመሰለፍ እድል ሲነፍጉት ቆየተዋል። መድፈኞቹ የዛሬ ሳምንት ሀሙስ በዩሮፓ ሊግ 32ኛ ዙር ጨዋታቸውን ወደ ራሺያ አቅንተው ከባቴ ቦሪሶቭ ጋር በመገናኝት የአንድ ለባዶ አሳፋሪ ሽንፈትን ካስተናገዱበት ጨዋታ ቀደም ብሎ፤ ማክሰኞ ዕለት ተጫዋቹ ከቡድኑ ጋር የተሳካ ልምምድ ቢያደርግም አሰልጣኙ ረቡዕ እለት ወደ ቤላሩስ ከተጓዙት ተጫዋች ስም ዝርዝር ውጭ አድርገውታል። ተጫዋቹም ልምምዱን ከክለብ ጓደኞቹ ጋር በብቃት እንዳደረገ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ከጨዋታው በፊት በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ለቆ ነበር። በዚህም ተጫዋቹ ከዩሮፓ ሊጉ ጨዋታ አሰላለፍ ውጭ መሆኑን ተከትሎ ከአሰልጣኙ ጋር
የለየለት ሰጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል። የአሰልጣኙንና የተጫዋቹን ውዝግብ ተከትሎ በክለቡ አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል ሲሉ የተጫዋቹንና የአሰልጣኙን አለመግባባት የስፖርት ቤተሰቡ እየተወያዩበትና አሰተያየት እየሰጡበት ይገኛሉ። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግርኳስ ውጤት ተንባይ የሆነው ፓውል ሜርሶን፤ አርሰናል ሜሱት ኦዚልን ጡረታ እንዲወጣ እየገፋፉት ነው ሲል ለስካይ ስፖርት ተናግሯል። ተንባዩ ሜርሶን አክሎም ተጫዋቹ በመድፈኞቹ ቤት የመሰለፍ እድል እየተሰጠው ባለመሆኑ የክለቡ ምርጡ ተጫዋች በተፈጠረው ነገር ግራ እየተጋባ እንደሆነ ገልጿል። ክለቡ ተጫዋቹን ጡረታ እንዲወጣ እየገፋፋው ቢሆንም፤ ተጫዋቹ ጠንክሮ በመስራት በዋናው ቡድን ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት መታገል አለበት ብሏል። ውጤት ገማቹ ሜርሶን ‹‹መድፈኞቹ ተጫዋቹ ወደ ቤላሩስ ከክለቡ ጋር ባለማቅናቱ ኡናይ ኤምሬ በኤሮፓ ሊጉ ከባቴ ቦሪሶቭ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የአንድ ለባዶ አሳፋሪ ሽንፈትን ተጎንጭተዋል። ይህም ተጫዋቹን ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመለስ በር የሚከፍት ነው። ተጫዋቹም በክለቡ ምርጡ ተጫዋች እንደሆነ እምነት አለኝ፡፡
በክለቡ ተሰልፎ ካልተጫወተ ክለቡ ሽንፈት እንደሚገጥመው ነው የሚሰማኝ፡፡ መድፈኞቹ በሚያደረጉት ጨዋታ ተሰልፎ ካልተጫወተ ክለቡ ወጤት ቢያመጣም ጥሩ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ተጫዋቹ ምንም ጉዳት ሳይኖርበት ለክለቡ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉ ለምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ተጫዋቹ ጡረታ መውጣትን እንዲያስብ አሰልጣኙና ከለቡ ሸፍጥና ደባ እየሰሩባት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ›› ሲል ተናገሯል። ሜርሶን እንደሚለው፤ ኦዚል ክለቡ ባለፈው ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ውስጥ ሶስቱን ብቻ የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆኖ መጫወት የቻለ ሲሆን፤ መድፈኞቹ ከቼልሲና ከማንቸስተር ሲቲ ያደረጉትን ጨዋታዎች ጨምሮ ያደረጓቸውን ስድስት ጨዋታዎች በጉዳት በሚልና በተለያዩ ምክንያቶች ከአሰላለፍ ውጭ በመሆኑ በእነዚህ ጨዋታዎች ሳይሰለፍ ቀርቷል። ኦዚል በእነዚህ ጨዋታዎች ባለመሰለፉ ቡድኑ በአምስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል፡፡ ኦዚል ሜዳውን ሙሉ አካሎ ላይጫወት ይችላል። እንዲሁም ታክል በመውረድ ኳስን ከተጋጣሚ ቡድን ላይ ላያስጥል ይችላል። በመከላከሉ ረገድም ደካማ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለጎል የሚሆኑ ያለቀላቸውን ኳሶች ለክለብ አጋሮቹ አመቻችቶ በማቀበል በየጨዋታው ልዩነት መፍጠር የሚችል በመሆኑ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬቡድኑን በተጫዋቹ ዙሪያ መሰረት አድርጎ ቢሰራ ክለቡ የተሻለ ወጤት ማስመዝገብ ይችላል። ነገርግን አርሰናሎች ተጫዋቹን የሚገባውን ክብር ሰጥተው ባለመያዛቸው ተጫዋቹ ለክለቡ የሚጠበቅበትን ግልጋሎት ለመስጠት አልቻለም፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንና የቀያይ ሰይጣኖቹ አጥቂ የነበረው አንድሪው ኮል በበኩሉ ‹‹ሜሱት ኦዚል ምን ያህል የኳስ ችሎታ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ነገርግን በአሁኑ ወቅት በአርሰናል ቤት በተጫዋቹ ላይ ሆን ተብሎ ድራማ እየተሰራበት ነው። ስለዚህ በአሰልጣኙና በተጫዋቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሊፈታ ይገባል›› ብሏል።
እንደ አንድሪው ኮል ማብራሪያ፤ በመድፈኞቹ ቤት በሳምንት 350ሺ ፓውንድ የሚከፈለው ጀርመናዊ ኮከብ ኦዚል በ141 ጨዋታዎች 50 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል በፕሪሚየር ሊጉ ብዛት ያላቸው ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማቀበል ችሏል። በመሆኑም ኡናይ ኤምሬ ግትረኝነቱን ትቶ ለተጫዋቹ እድል ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም ተጫዋቹ ጠንካራ ሰራተኛ ነው አይደለም የሚለውን ወደጎን ትቶ ተጫዋቹ ተፈጥሮ የቸረችውን ድንቅ ብቃቱን ክለቡ ቢጠቀምበት ለክለቡም ለራሱም ጥቅም ይሰጣል፡፡ ‹‹አርሴን ቬንገር በክለቡ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት በተጫዋቹና በአሰልጣኙ መካከል እንደዚህ አይነት ችግር ተከስቶ አያውቅም ነበር። መልከ መልካሙ ኦዚል ከአርሰናል ተጫዋቾች መካከል ምርጡ ተጫዋች ነው። ይህንንም ለማረጋገጥ ላካዜቲን እና ኦባሜያንግን ኦዚል እንዲጫወት ትፈልጋላቹህ ብለህ በየቀኑ ወይም ቀኑን ሙሉ ብትጠይቃቸው አዎ ነው የሚሉህ። ይህ ሆኖ እያለ አሁን ላይ ግን በጣም እንግዳና ያለተለመደ ነገር ነው በተጫዋቹ ላይ እየሆነ ያለው›› ሲል ኮል ለስካይ ስፖርት አብራርቷል። አንድሪው ኮል ‹‹ባለፉት ጥቂት አመታት የተጫዋቹ አቋም የወረደ ይመስላል። ይህ የግል አስተያየቴ ነው። እንዲሁም አንዱ ሊወደው ሌላኛው ደግሞ ሊጠላው ይችላል።
እንደኔ ግን እርሱ ሲጫወት ሳይ በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡ ፡ ለክለብ አጋሮቹ ኳስ የሚያቀብልበት መንገድም ፈጽሞ ይማርከኛል። በአጠቃላይ በጨዋታ ላይ ደካማ እንቅስቃሴና ዝቅተኛ የመከላከል ችሎታ ያለው በመሆኑ ተጫዋቹ ሊተች ይችላል። ነገርግን በጨዋታ ላይ የእርሱ ሚና በጣም ከፍ ያለ ነው፡ ፡ ምክንያቱም እንደሌሎች ተጫዋቾች ሜዳውን ሙሉ አካሎ ሳይጫወት ነጻ ሆኖ ኳስን በመቀበል ቢያንስ በየጨዋታው ከሶስት ያላነሰ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ለክለብ አጋሮቹ መስጠት ይችላል። ስለዚህ እንዲህ አይነት ተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾች በአለማችን ከጣት ቁጥር የማይበልጡ በመሆናቸው በመድፈኞቹ ቤት ለተጨዋቹ የመሰለፍ እድልና ተገቢው ክብር ሊሰጠው ይገባል›› በማለት የተጨዋቹን ድንቅ አቋምና ሊሰጠው ስለሚገባው ክብር ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል የደይሊ ሚረር የእግር ኳስ ጸሀፊና ደራሲ ጆን ክሮስ በበኩሉ ጀርመናዊው ኢንተርናሽናል ተጫዋች በአሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ የአሰልጣኝነት ፍልስፍና ቦታ እንደሌለው ተናገሯል። አሰልጣኙ በተጫዋቹ ላይ ያላቸው እምነት በጣም የወረደ በመሆኑ በተጫዋቹና በአሰልጣኙ መካከል ያለው እሰጣ ገባ እየከረረ በመምጣቱ በመድፈኞቹ ቤት ነገሩ ዋነኛ የመወያያ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱንም አስታውቋል፡፡ ‹‹በዚህ የውድድር አመት ተጫዋቹ የጀርባ ጉዳት አለበት፤ የአካል ብቃቱ ለጨዋታው አይመጥንም፡፡ የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ተጫዋቹ ውጤታማ በሆነበት ወቅት ጨዋታዎች ሲያልፉት ቆይቷል።
አሰልጣኙም ተጫዋቹን ከአሰላለፍ ውጭ ሲያደርጉት የአሰልጣኙ ሙያዊ ስነምግባር ነው በማለት የስፖርት ቤተሰቡ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ ነበር። ነገርግን የዛሬ ሳምንት ክለቡ ወደ ራሺያ ተጉዞ 32ኛውን የኤሮፓ ሊግ ጨዋታ ባደረገበት ወቅት ተጫዋቹ ከቡድኑ ጋር በሙሉ ጤንነት ሙሉ ልምምዱን እንዳደረገ ሲታወቅ፤ በተጫዋቹና በአሰልጣኙ መካካል አለመግባባት መኖሩና ተጫዋቹ ከአሰልጣኙ የረጅም ዓመት እቅድ ውጭ መሆኑን የሚያሳይ ነው›› ብሏል የደይሊ ሚረር የእግርኳስ ጸሀፊው ክሮስ። ጆን ክሮስ ‹‹ይህን የ30 አመቱን ተጫዋች አሰልጣኙ አለመጠቀማቸው ጥያቄ ቢያስነሳም፤ ጊዜው የአሰልጣኙ በመሆኑ የአሰልጣኙን ውሳኔ ማክበር ግድ ይላል ብሏል። ነገርግን እንደ እነ ማይክል አርቴታና ብሬንዳን ሮጄርስ የመሳሰሉ የወጣት ብስል አሰልጣኞች፤ ተጫዋቾች ብቃታቸው ከፍ እንዲልና ወደ ቀድሞ ከፍተኛ ብቃታቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ሲሰጡ በተጨባጭ እየታየ።
ስለዚህ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ከእነዚህ ወጣት አሰልጣኞች እንዴት ተጫዋቾችን አክብሮ መያዝ እንዳለበት ሊማር ይገባል›› ሲል ተደምጧል። ተጫዋቹ በመድፈኞቹ ቤት መቆየት ቢፈልግም አሁን ላይ የመቆየት ተስፋው የተሟጠጠ ይመስላል። ምክንያቱም ከተለያዩ የክለቦች የስራ አመራሮችና ባለስልጣናቶች ጋር በግሉ ተገናኝቶ በመምከር በከረምቱ የዝውውር መስኳት እንደ ኢንተር ሚላንና ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን የመሳሰሉ ክለቦች ለመዘዋወር በድርድር ላይ ይገኛል። ክለቦቹም ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳደረባቸው እየተነገረ ይገኛል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ሶሎሞን በየነ