ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአፍሪካ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሙዚቃ ንጉስ እያሉ ከሚያሞከሿቸው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በሙዚቃ ስኬቱ ላይም ሰፋ ያሉ ዘገባዎች ተሰርተውለታል፡፡ በሙዚቃ ስራዎቹ በተለይ በሰብዓዊነት በአንድነት እና በፍቅር ዙሪያ አተኩሮ በመስራትም ልዩ ከበሬታ ያተረፈ ሲሆን፤ ለሚሰራቸው ዘፈኖች ለሚፅፋቸው ድርሰቶች ከፍተኛ ምርምርና ጥናት እንደሚያደርግ ተወስቶለታል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
በእያንዳንዱ የሙዚቃ አልበሙ ታሪክ ቀመስና ለታላላቅ ሰዎች መታሰቢያ የሆኑ የሙዚቃ ስራዎችን የሰራ ነው፡፡ ለአፄ ምኒልክ፣ ለአፄ ኃይለስላሴ፤ ለጃማይካዊው እውቁ የሬጌ ኮከብ ቦብ ማርሌይ፤ ለታዋቂዎቹ አትሌቶች ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ የሰራቸው ሙዚቃዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ከሙዚቃ መሳሪያዎች ኪቦርድን ከመጫወቱም በላይ የተለያዩ አኩስቲክ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወት በመድረክ ላይ ባንዶቹን አጅቦ የመስራት ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ በአልበሞቹ ደግሞ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ፤ በመላው ዓለም በርካታ ኮንሰርቶች በመስራት፤ በአገር ውስጥ በሚሰራቸው ኮንሰርቶች ከፍተኛ ታዳሚ በማግኘት እንዲሁም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡
አርቲስት ቴዎድሮስ በተለያዩ ጊዜያት በሚወጡ ነጠላ ዜማዎች ስኬቱም ይታወቃል፡፡ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ምርጥ ብቃት እንዳለው ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሌቦ፣ አቦ ጊዳ፣ ጃ ያስተሰርያል፣ ጥቁር ሰውና ኢትዮጵያ የተሰኙ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቷል፡፡
ቴዲ ከአነጋጋሪ አልበሞቹ በተጨማሪ፤ በተለያዩ ጊዜያት የሚለቃቸው ነጠላ ዜማዎቹ በተሰሙበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሲያነጋግሩ ተስተውሏል፡፡ እንደ “ሰባ ደረጃ” እና “ኮርኩማ አፍሪካ” የተሰኙትን የተሳካላቸው ነጠላ ዜማዎቹን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
አቦጊዳ ከሚለው አልበም አቦጊዳ፣ ልጅነት አላት፣ ለማን ልማሽ እና ሞናሊዛ ፤ ጃ ያስተሰርያል ከሚለው አልበም ያስተሰርያል፣ በል ስጠኝ፣ ላምባዲና የሚታወሱ ናቸው፡፡ መንታ ወድጄ፣ ያረጋል፣ ላሜ ቦራ እና ስደት የተባሉት ሌሎች ሥራዎቹ ከፍተኛ ተደማጭነት በማግኘት የተሳካላቸው ሲሆኑ፤ የመጨረሻው አልበሙ ኢትዮጵያ ከመውጣቱ በፊት ደግሞ ሰላም፣ ፊዮሪና፣ ልረሳሽ አልቻልኩም ፣አባይ፤ ውዴ፤ አይደነግጥም ልቤ እና ትዝታ የተሰኙ ሙዚቃዎች በኪነ ጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ አድናቆትን የተቸሩ ናቸው፡፡
ቴዲ፤ እኤአ በ2003 ላይ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀበት ወቅት የመጀመሪያ ኮንሰርቱን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በ2005 እኤአ ላይ የቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኮንሰርት በተዘጋጀበት ወቅት በመሳተፍም የዝግጅቱን መክፈቻ ሙዚቃዎች ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡ ከአገር ውጭ በአፍሪካ፤ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራልያ እና በመካከለኛው ምስራቅ በመዘዋወር በትልልቅ ከተሞች ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ በዚህም በርካታ አድናቂዎችን በማግኘት አንቱታን የተረፈ ሆኗል፡፡
ቴዲ አፍሮ እምቅ የሆነ ችሎታውን ለዓለም ማሳየት የቻለው ሙያው ለሚጠይቃቸው ባህርያትና ክህሎት ጥልቅ ስሜት ያለው መሆኑን ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። በተለይ በዘመነ ኢህአዴግ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ መከታተል መቻሉና ተራክቦውን አንደበተ ርቱዕ በሆነ መንገድ መግልፅ መቻሉ የማህበረሰቡን ቀልብ ለመግዛት አስችሎታል፡፡
ሥርዓቱንም በማይክ ተፋልሞ ለእስር ጭምር መዳረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ማሰብ በማይፈቀድበት ዘመን ከሥርዓቱ ጋር ተጋፍጦ ዋጋ ከፍሎ ዛሬ ላይ መድረሱ ለብዙዎች ተምሳሌት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በዚህም በ2009 እኤአ ላይ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተዘጋጀ ኮንሰርት ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ ከ60ሺ በላይ ታዳሚዎችን ማግኘቱ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በዚህና መሰል የኪነ ጥበብ አበርክቶው ታላቁና አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለታላቁ ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በትናንትናው ዕለት የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ የሙዚቃ ሊቁ ሰርጸ ፍሬ ስብሐት በማህበራዊ ሚዲያው ስለ ቴዲ አፍሮ ባጋረው መልዕክቱ፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን አዲስ ሙዚቃዊ ልምምድ ወይም ዘይቤ ለዘመናችን ያበረከተ፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ እየተሻገረ ባለ ሙዚቃዊ ተፅዕኖ፣ የትውልድ ተምሣሌት መሆን የቻለ፣ ታላላቅ ብሔራዊ ጭብጦችን በሙዚቃዊ ሥራዎቹ ውስጥ በማንሣት፤ የታሪክ እና የፍልስፍና ሙግት መፍጠር የቻለ፣ ስለ ሀገር ብሔራዊ ክብር በሥራዎቹ የተሟገተ፣ በአጠቃላይም፤ ለሙዚቃ ሁለንተናዊ ክብር፥ የፈጠራም፣ የሥነ ምግባርም አርአያ መሆን የቻለ የጥበብ ሰው መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የክብር ዶክትሬት ዲግሪው ይገባዋል። ይኸውም፥ አዲሱን ትውልድ እንደማክበር አዲስ ጅማሬ ይቆጠራልና ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ሊመሰገን ይገባል ብሏል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ትላንትና በተካሄደው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጀግናን ማክበር ታላቅነት ነው በማለት ዩኒቨርሲቲው ለአርቲስቱ የክብር ዶክትሬት በመስጠቱ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደርም በአርቲስቱ ስም ጎዳናዎችን መሰዩሙን ገልጸዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምርቃት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ አርቲስቱ ኢትዮጵያን፣ አባይን ግድቡን በተመለከተ ትልልቅ ሀሳቦችን እያነሳ የሚያቀነቅን እንደመሆኑ ወሳኝ በሆነ ወቅት ቁልፍ መልዕክት ባለው ሙዚቃው ለፈጠረው የአንድነት ስሜትና ወኔ ምስጋና አቅርበውለታል። በቀጣይም ለአገራችን አንድነት የሚበጁ ድንቅ ሥራዎችን በጉጉት እንጠብቃለን ብለዋል።
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ከኪነ ጥበቡ አበርክቶው በተጨማሪ በሰብዓዊና ማህበራዊ ሥራዎቹ የሚታወቅ መሆኑን አስታውቀው፤ “እንዲህ አይነት ክብርና እውቅና ሁሉም ሰው በተሰማራበት በየትኛውም የሥራ መስክ ከልብ በመሥራት ውጤታማ መሆን ራስንም አገርንም የሚያስከብር መሆኑን ዛሬ ለቴዲ የምንሰጠው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ትልቅ ማሳያ ነው” ሲሉ ለአርቲስቱ የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013