ሀገሪቱ ካፈራቻቸው ወጣት ፖለቲከኞች አንዱ ነው። ውልደቱ ትግራይ ክልል ህንጣሎ ወረዳ ልዩ ስሙ አዲጉደም በሚባል አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሀሮዕ በተባለ ትምህርት ቤት እስከ 6ኛ ክፍል የተማረ ሲሆን በአካባቢው መለስተኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ ከተማ መሄድ ግድ ይለዋል። ሆኖም ከተማ የሚያውቀው ሰው ባለመኖሩና ለቤት ኪራይና ለቀለቡ ወላጅ እናቱን ማስቸገር ባለመፈለጉ ከተማ የመሄድና የመማር ሃሳቡን ይተወዋል። በምትኩም ታላቅ እህቱ በምትኖርበት ሻሸመኔ ከተማ በመጓዝ እየሰራ የሚማርበትን ሁኔታ ያመቻቻል። እናም ያቋረጠውን ትምህርት ኩየራ እና አድቬንቲስት በተባሉ ትምህርት ቤቶች ቀጠለ። በተለይም አድቬንቲስት ትምህርት ቤት አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የፈጠረውን እድል በመጠቀም እየሰራ መማሩን ቀጠለ። በርትቶ በማጥናት ትምህርቱን በመከታተሉም በጥሩ ውጤት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ማለፍ ቻለ።
በመቀጠልም ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በህዝብ አስተዳደርና ዲቨሎፕመንት ማኔጅመንት በተባለ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። በዩኒቨርሲቲው ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ስለነበርም ገና ትምህርቱን ሳያጠናቀቅ በአቅራቢያው በምትገኝ አንዲት ወረዳ ተወዳድሮ ተቀጠረ። ሰርቶ የመለወጥን ህልም ሰንቆ በተመረቀበት የሙያ ዘርፍ ማገልገል ቢጀምርም ጁንታው ህወሓት ህዝቡ ላይ በፈጠረው የመከፋፋል አስተሳሰብ የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ምክንያት ብቻ በአካባቢው ማህበረሰብና በወረዳው ሠራተኞች ዘንድ እንደሰላይ ይታይ ጀመር። በቅንነት ሰርቶ የመለወጥ አላማ እንጂ የማንም የፖለቲካ ተልዕኮ አስፈፃሚ አለመሆኑ ሊያስረዳ ቢጥርም መገለሉ በረታበት። በመሆኑም ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ አመለካከት ይዞ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው በዚህ አሸባሪ ቡድን ስም መወቀሱ ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሮበት እሱም እንደሌሎቹ ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ለመታገል ቆርጦ ተነሳ። ብዙም ሳይቆይ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ተቀላቀለ። ህወሓት ከሥልጣን ከተነሳ ወዲህም በተለይም የትግራይ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን አፈና እና ጭቆና በገሃድ ሲቃወም ሲታገል የቆየው ይኸው ወጣት የተወለደበት ቀዬ ድረስ በመዝለቅ ህብረተሰቡን በማስተማርና በመርዳት ከጁንታው ብርቱ ክንድ ጋር ተፋለመ። በኋላም ጁንታው በራሱ ጊዜ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያውያን ህብረት ሲወገድ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በመሳተፍ ያፈራውን ህዝብ ሲያገለግል ቆየ። የመከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ እስከሚወጣ ድረስም በክልሉ ደቡብ ምስራቅ ዞን የህንጣሎ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆኖ እያገለገለ ቆይቷል። አቶ ሃጎስ ግደይ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ነው። በክልሉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– ወደ ተቃውሞው ጎራ የገባህበትን አጋጣሚ አጫውተን እና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ሃጎስ፡– የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለን ከተለያዩ ክልሎች የመጣን እንደመሆናችን ሁላችንም በየብሔራችን እንድንደራጅና የፖለቲካ አባል እንድንሆን ከፍተኛ ጫና ያሳድሩብን ነበር። እኔ ግን የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ስለማልፈልግ በተደጋጋሚ የሚቀርብልኝን ጥያቄ ስገፋው ነበር የቆየሁት። በተለይም የህወሓት አባል ላለመሆን ስል ብቻ የመጣሁት ከኦሮምያ ክልል ነው በማለት እና ሰበብ በመፈለግ ከፖለቲካ ነፃ መሆን የምችልበት እድል አገኘሁ። በመሰረቱ እኔ የመጣሁት ለትምህርት ነው፤ እዚህ የደረስኩትም በችግር እንደመሆኑ ጊዜዬን በከንቱ ማሳለፍ የለብኝም በሚል ወስኜ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ላይ ደግሞ የድርጅት አባል የሆኑት ተማሪዎች ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በስብሰባ ነው። እኔ ደግሞ ዋና አላማዬ መማር ስለሆነ በተቻለኝ አቅም እሸሽ ነበር። መጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ ግን አባል ያልሆኑ ተማሪዎች ስራ እንደማያገኙ ስገነዘብ ሳልወድ በግዴ መጨረሻ ላይ ፎርሙን ተቀበልኩኝ። ይሁንና እንደአጋጣሚ ሆኖ አልተጠቀምኩበትም። ምክንያቱም ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለነበረኝ እንዳውም እኔ ገና ከመመረቄ ሁለት ወር ሲቀረኝ ነው ስራ የያዝኩት። በነገራችን ላይ ይህንንም እድል ያገኘሁት ልክ እንደማንኛውም ዜጋ ተወዳድሬ በማለፌ ነው። ከዚያ በኋላ ግን የፖለቲካው አባልነት አይጠቅመኝም በሚል ሙሉ ለሙሉ ትኩረቴን ስራ ላይ አደረኩኝ። እናም በ 2006 ዓ.ም ላይ የለውጥ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲመጣ ራሴን መጠየቅና የሀገሪቱን ነበራዊ ሁኔታ ላይ ብዙ ማሰብ ጀመርኩ። በመሰረቱ ዩኒቨርስቲም ሳለሁ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፓርቲ ለምን ብቻውን አገር ይመራር? የሚል ጥያቄ ነበረኝ። በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እስከ ህልፈተ ሞታቸው ድረስ ብቻቸውን ስልጣን ተቆጣጥረው መቆየታቸው በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጠረ ያለው የአስተሳሰብ ተፅዕኖ እያሳሰበኝ ሄደ።
አዲስ ዘመን፡– ተፅዕኖ ስትል ምን ማለትህ ነው?
አቶ ሃጎስ፡– እኔ ለምሳሌ ከዩኒቨርሲቲ ሳልመረቅ ስራ መቀጠሬ በራሱ ሆን ተብሎ ደብዳቤ ተፅፎልኝ እንደተቀጠርኩኝ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ነበሩ። ይህም የአንድ ብሔር አባላት ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት የፈጠረው ተፅዕኖ መሆኑን ማሰብ ጀመርኩኝ። በተለይም እዛ ወረዳ ላይ ስሰራ ብዙዎቹ ስራ አጥቼ ሳይሆን ለመሰለል እንደተቀጠርኩ ነበር የሚያምኑት። በቻልኩት መጠን እውነታውን ለማስረዳት እሞክራለሁ። ይሁንና ብዙዎቹ በጥርጣሬ ነው የሚያዩኝ የነበረው። እኔ ትግራይ ተወለድኩኝ እንጂ አብዛኛው ህይወቴ የነበረው ኦሮሚያ ላይ ነው። እየዋለ ሲያድር ግን የተለየ ተፅዕኖ በትግራይ ህዝብ ላይ ሊመጣ እንደሚችል እያሰብኩኝ ሄድኩኝ። በተለይም ከ2006 ዓ.ም ወዲህ የለውጥ እንቅስቃሴው እያየለ ሲሄድ እኔ እንደአንድ የትግራይ ተወላጅ ነገሮች እየገፉ ሲሄዱ የማግለል ሁኔታ መጣ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ለምን ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ አይኖረውም የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ። ሌሎች ክልሎች ግን ሁለትና ሦስት ፓርቲዎች እያሉ ትግራይ ውስጥ ለምን አማራጭ አይኖርም የሚል ጥያቄ ማብሰልሰል ያዝኩኝ። በተለይም የሕዝቡን ችግር የሚረዳለት ሌላ ፓርቲ መኖር አለበት እያልኩኝም ማሰብ ጀመርኩኝ።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ነገሮች እየገፉና ተፅዕኖው እየበረታ ሲመጣ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በሰላም የሚኖርበት መንገድ መፈጠር አለበት በሚል ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተነጋገርን። እንደአጋጣሚ ሆኖ የወጣቶች ማህበር መስርተን እየተንቀሳቀስንና እያሳመንን ከመጣን በኋላ እንደሀገር ለውጡ ተሳክቶ ዶክተር አብይ መጡ። ከዚያ በቀጥታ ከነበርኩበት ስፍራ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ነው የመጣሁት። በአጋጣሚ ደግሞ ዶክተር አብይ ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ዶክተር አረጋዊም አንዱ ነበርና በዋልታ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ሲያደርጉለት ተመለከትኩኝ። ከዚያ ዋልታ ድረስ ሄጄ ፈልጌ አገኘሁት። ከዚያ በኋላ ብዙ ሃሳብ ተለዋወጥን። በተለይም ህወሓት የትግራይ ህዝብ እንዲገለል እያደረገ ስላለበት ሁኔታ፤ ስልጣን አልበቃ ብሎ ህዝቡን ወደባሰ ሁኔታ ከመክተቱ በፊት ህይወቱን የምንታደግበት ሁኔታ ብዙ አወጋን። ህወሓት በሰራው ሃጢያት የትግራይ ህዝብ ሊገለል እንደማይገባ ለሌላው ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባን ተማመንን። በወቅቱ የእኔ ዋነኛ ነጥብ የነበረው ትግርኛ ይናገር የነበረው ህብረተሰብ ከህወሓት እንደተወለደ አድርጎ የሚወሰደው እሳቤ መጥፋት አለበት የሚል ነበር። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ትላንት ነበር፤ ዛሬም አለ፤ ነገም ይኖራል። ህወሓት ግን በሆነ ጊዜ ነው የተፈጠረው፤ ሊጠፋ ይችላል። ይህንን እውነታ ህዝቡ መረዳት አለበት የሚል ሃሳብ አነሳሁለት፣ እሱም ወደደው። በዚያ መሰረት እስከአሁን ድረስ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል ሆኜ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የሃገሪቱ ህዝብ ጋር በሰላም የሚኖርበት ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራሁኝ ቆይቻለሁ። ይህች ሀገር የትግራይ ወይም የአማራ ብቻ እንዳልሆነች ይልቁንስ የሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ህዝብ የሚኖርባት ሀገር መሆንዋን በማስረጃ ለማሳመን ሞክረናል። አሁንም እየሄድን ነው ያለነው። ይሁንና ህወሓት ህዝቡን ማታገል የፈለገው ‹‹ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው›› በሚል አስተሳሰብ ስለሆነ ያንን ለመቀየር የራሱ ጊዜ ይወስዳል። በተቻለ መጠን ግን በሰራነው ስራ ህዝቡ ምንም እንኳን በተለያየ ጫና ውስጥ እያለፈ ቢሆንም ሁኔታውን እየተረዳ ነው የመጣው። እኛም ትግላችንን ቀጥለናል። ወደፊትም ህወሓት ወይ ጠፍቶ አለያም ንስሃ ገብቶ ህዝቡን ሰላም እስኪሰጥ ድረስ እንቅስቃሴያችን ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዲኖረው ከሚፈልጉ ወጣቶች አንዱ እንደመሆኑ ቀድመው የተመሰረቱ እንደ አረና የመሳሉ ፓርቲዎች ነበሩ። ለምን እነሱ ጋር መግባት አልፈለግህም?
አቶ ሃጎስ፡– እንደአጋጣሚ ሆኖ እኔ የአረና ሰዎችን ብዙም አላውቃቸውም። እንዳልኩሽ ግን ውስጤ የነበረው ቅንነት ብቻ ነው። እውነቱን ለመናገር ቅንነት ስለነበረኝ ነው የትግራይ ህዝብ አማራጭ ያስፈልገዋል ብዬ ስታገል የቆየሁት። ደግሞም በስራ አጋጣሚ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውሮ የማየት እድሉ ስለነበረኝ በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ የትግራይ ህዝብ በሰላም እንደሚኖር ተመልክቻለሁ። ይሁንና ትግራይ ያለው ህዝብ ህወሓት እያለ ተመችቶት አልኖረም፤ ይልቁንም ተሳቆ በስጋት ነው የኖረው። እውነቱን ለመናገርም እንደሌላው ማህበረሰብ ‹‹መንግሥት ከሆነ ከማህበረሰብ ነው የወጣሁት›› የሚል በራስ መተማመን አልነበረውም። ምንአልባት ግን አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩና ከእነሱ ጋር አብረው ይውሉ የነበሩት ምድሩን ለመሰንጠቅ ሲጥሩ እንደነበር እሙን ነው። ሌላው ከአዲስ አበባ ውጭ የኖረው የትግራይ ህዝብ ግን በስጋት ነው የሚኖረው።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ እኔ ራሴ ከደረሰብኝ ነገር ስነሳ ብዙዎቹ ገንዘብ አጥቼ ሳልሆን ለስለላ እንደመጣሁ ነው ይታሰብ የነበረው። በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖረው የትግራይ ህዝብ በተመሳሳይ መልኩ ግምት ውስጥ የገባበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ ሁሉ የትግራይ ህዝብ ህወሓት ቢቀርበትስ? የሚል ጥያቄ ነበረኝ። ስለዚህ ያንን ለማስቀረት ደግሞ ሌላ ፓርቲ አስፈላጊ ነው ብዬ አመንኩኝ። ይህንን ሳምን ግን ቢያንስ ቢያንስ ንፁህ እና ቅን ልቦና ያለው በመላው ኢትዮጵያ ላይ ሊሰራ የሚችል ፤ ሀገሩን ጠንቀቆ የሚያውቅ ፤ ሁሉንም ማህበረሰብ ባህልና አስተሳሰብ የሚረዳ ፓርቲ ማግኘት ነበረብኝ። አንቺ እንዳልሽው ዓረና ቀድሞም ተመስርቶ ነበር። ግን ከአንድም ሁለት ጊዜ በምርጫ ተወዳድረው ለውጥ አላመጡም። ግን ደግሞ እነሱም ያን ያህል ፈንቅለው አልወጡም ነበር። ደግሞም ህወሓትን እንደፈለጉ ለመቃወም የሚችሉበት እድል አልነበራቸውም። አዲስ አበባ ላይ ሆነው ተወላጅ የሆነውን ማህበረሰብ የማሰባሰብ ስራ አልሰሩም። እንዳውም አንድ ጊዜ አቶ አብርሃ ደስታን አግኝቼ አናግሬው ነበር፡፤ ከትግራይ ውጭ ያለውን ማህበረሰብ ሁኔታ ያውቁት እንደሆነ ጠይቄው አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም። ደግሞም በክልሉ ካለው ህዝብ ያልተናነሰ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ መጠን በየክልሉ የሰፈረ የትግራይ ተወላጅ አለ። እነሱ ይህንን ማህበረሰብ አግኝተውት አያውቁም ነበር።
በመሆኑም እኔ ያሉትን ተግዳሮቶች ጠርምሶ አንድም ተወላጅ ቢሆን ካለበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ስሜቱን መረዳት የሚችል መሆን ይገባዋል ብዬ አምን ነበር። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲን(ትዴፓ)ን አገኘሁ። እውነቱን ለመናገር ደግሞ ከእኔ ጋር የሚታገሉት አባላት በጣም ጠንካሮች ናቸው። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የትግራይ ተወላጆች አሉበት በሚባሉት አካባቢዎች ቄለም ወለጋ ሳይቀር ሄደን ነው የምንጠይቀው። የኢትዮጵያ ህዝብም እኛ ስንሄድ በደረስንበት ሁሉ ተንከባክቦናል፤ ምንም የደረሰብን ችግርም የለም። ባለፈው ከጦርነቱ በፊትም በጣም ብዙ ቁጥር ያለው የትግራይ ተወላጅ ታስሮ እንደነበር ይታወቃል። ለዚህ ደግሞ ህወሓት ነው ዋነኛ ተወቃሽ፤ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ንፁሃን የሆኑ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ስህተት ሰሩ የተባሉ ሰዎችም በይቅርታ ተፈትተዋል። ጋምቤላ ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ ኦሮሚያ ላይ ተዘዋውረን ከአመራሮች ጋር በመነጋገር የታሰሩትን አስፈትተናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ችግር አልደረሰብንም። ይህ ደግሞ ለእኔ ኢትዮጵያዊነቴን የበለጠ እንድወደው አድርጎኛል። ብዙዎቹ ግን ‹‹ትግርኛ ተናጋሪ ሆነህ ለምን ወደ የክልሉ ትሄዳለህ?›› እያሉ እንቅፋት ቢፈጥሩብኝም በጣም ግርግር በነበረበት ወቅት እንኳን ጅማም ሆነ ወለጋ ስሄድ እውነቱን ለመናገር ‹‹ማነህ፣ ወዴት ነህ›› ብሎ የሚጠይቀኝ የለም ። ስለዚህ በመጀመሪያ የልብ ቅንነት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ማን ምን እንደሆነ በደንብ ያውቃል። ያንን ሁሉ ችግር አልፈን ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው።
በአጠቃላይ ከአረና በተጨማሪ ሌሎች ፓርቲዎች ሳይኖሩ ቀርተው ሳይሆን ሊሰሩ የሚችሉ ያስፈልጋሉ ብዬ ስለማምን ነው ሳልገባ የቆየሁት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብዬ ትግራይ ስላለው ህዝብ ብጨነቅ ምንም ጥቅም የለውም። እኔ እንዳውም በጣም የሚያስጨንቀኝ ከትግራይ ውጭ ስላለው ህዝብ ነው። ምክንያቱም ወቅቱ ጥሩ ባለመሆኑ ነው። ትግራይ ያለው ህዝብ ከጦርነቱ በፊት ረሃብ፤ አፈና ነበረበት። ይሁንና ተቋዋሚዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር ሌላው ማህበረሰብ ላይ ግድያ አልነበረም። እርግጥ ነው፤ እነሱ በየአሥር ዓመቱ ከሚፈጥሩት ጦርነት በስተቀር አብዛኛው ህዝብ በሰላም ነው ይኖር የነበረው። በዚህ ረገድ በየክልሉ የሰራነው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ውጤት አምጥቶልናል ብዬ ነው የማምነው። ደግሞም ያ ሁሉ ግርግር በነበረበት ወቅት ወለጋ ላይም ሆነ ቤኒሻንጉል ያ ሁሉ ሰው ሲሞት አንድም የትግራይ ተወላጅ ከትግራይ ውጭ አልሞተም። ያ ሊሆን የቻለው የግንዛቤ ስራ በመሰራቱ ነው። መንግሥትም ደግሞ ብዙ ጥረት አድርጓል። እርግጥ ነው ህወሓቶች የሚፈልጉት ያ እንዲሆን ነበር። እኛ ግን ያሰበው እንዳይሳካለት መንግሥትም እኛም በተቻለ አቅም ጥረት አድርገናል። በዚህ አጋጣሚ ሃሳባችንን የሚቀበልና የሚረዳን ማህበረሰብ ስላለ እኛ በጣም ደስተኞች መሆናችንን መግለፅ እወዳለሁ።
እንደሚታወቀው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ አማራጭ ፓርቲ እንዲኖር አይፈልግም ነበር። ሲነሳም ሲተኛም ህወሓትን እንዲያስብ ነው የሚሻው። ይሄ የስልጣን ፍላጎቱ ፅንፍ የወጣ በመሆኑ ነው። ስልጣንን ላለማጣት ሲል ህዝቡ ታፍኖ እንዲኖር አድርጓል። አሁንም ያለው ነገር የዚያ ውጤት ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሸባሪው ህወሓት ምንም እንኳን ከምስረታው ጀምሮ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ነኝ›› ቢልም የወጣበትን ማህበረሰብ ጭምር በጭቆና ቀምበር ውስጥ እንዲኖር ያደረገውም መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር ህዝቡ ላይ የደረሰው ጫና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ሃጎስ፡– እውነት ነው፤ ህወሓት እንደሚለው ከምስረታው ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ አልነበረም። የህወሓት ዲሞክራሲ ወረቀት ላይ ብቻ ነው። ህወሓት ራሱ ሁለት ችግሮች አሉበት። አንደኛ የትግሉ አላማ ከመጀመሪያውም ከሁለተኛውም የተጣረሰ ነው። ይህንን ያልኩበት ምክንያት እነሱ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያን አንድነት አይፈልጉም ነበር። ማኒፌስቷቸው ላይ የነበረውም ትግራይን ሀገር የማድረግ አላማ ሰንቀው ነበር ሲታገሉ የነበሩት። ያ አስተሳሰባቸው ግን እንደማያዋጣቸው በደንብ አድርገው ያውቁታል። ግን በአንድ የትግል አቅጣጫ ላይ አንድ አሸናፊ ቡድን ካለ ያ ቡድን የሚፈልገውን ነገር ነው ሁልጊዜ የሚያደርገው። ከዚያ በመቀጠል እኔ ህወሓት ሲነሳ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ ቢሆን ኖሮ ለህዝቡ ነበር ምርጫ የሚሰጠው። እኔ እንዳልኩሽ ከትግራይ ውጭ ብማርም ቤተሰቦቼ በክልሉ ስለሚኖሩ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ እሄዳለሁ። ባለፈው 2010 ዓ.ም እና 2011 ዓ.ም እንኳን አራተኛ ዙር የሴፍቲኔት ፕሮግራም በመላው ትግራይ የሰራሁት እኔ ነኝ። ስለዚህ ሁሉንም ወረዳዎች በደንብ አድርጌ አውቃቸዋለሁ። እነዚህ ሰዎች አብረዋቸው የነበሩ በጣም በጎ አሳቢ የነበሩ፤ በጣም ቅን ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሰዎችን እየገደሉ ነው የመጡት። ያኔ ነው ዴሞክራሲያቸው የጠፋው። ያንን እያደረጉ በመጡ ቁጥር ወደ አምባገነንነት እየተቀየሩ ነው የመጡት።
በነገራችን ላይ የእነሱ የክፋታቸው መጠን ሃይማኖት የላቸውም። ሁሉም በ1960ዎቹ የነበሩት የህወሓት መሪዎች ሃይማኖት የላቸውም። ያ ሁኔታ ደግሞ የበለጠ እየከፋ መጣ ። ምክንያቱም ደግሞ አንድ ሰው ሃይማኖት ከሌለው ለሰው ማዘን ምን እንደሆነ አያውቅም። የሰው ችግር አይገባውም። ያ ደግሞ በህዝቡ ላይ በጣም ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ከዚያ በኋላ ትግራይ ውስጥ ዓመቱን ሙሉ የምታከብሪው የህወሓት በዓል ነው። ህዝቡ ሌላ ነገር የሚያስብበት ምንም እድል አልነበረውም። ስለዚህ የቱ ጋር ነው ዴሞክራሲ ያለው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አንድ ለአምስት የሚባልም ነገር አለ። ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ የአንድ ቀበሌ ነዋሪ ሆነሽ ሌላ ቦታ ለመሄድ ፎርም ሞልተሽ ነው የምትሄጂው። አሁን ለምሳሌ አዲስ አበባ የሚመጣ ሰው ቀበሌ ፎርም ሞልቶ ነው የሚመጣው። ‹‹ይህ ለምን ይሆናል?›› ብሎ መጠየቅ አይቻልም። ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት ካለኝ ‹‹የትነው የምትሄደው?›› ተብዬ መጠየቅና ፎርም መሙላት አይገባኝም። በዚያ አደረጃጀት አማካኝነት የህዝቡ አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቁጥጥራቸው ውስጥ አድርገውት ነው የቆዩት። ሌላው ይቅርና የትግራይ ህዝብ ጠበል እንኳን ሲሄድ ለቀበሌ አስፈቅዶ ነው የሚሄደው። በዚያ ደረጃ ከሌላው ህዝብ በባሰ ሁኔታ ተፅዕኖ ነበረበት።
እንደሚታወቀው ደግሞ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በሴፍትኔት ነው የሚኖረው። እኔ እዛ ፕሮግራም ላይ ስሰራ ህዝቡ የሚያውቀው ህወሓት ሴፍትኔቱን እንደሚሰጠው እንጂ የዓለም ባንክ እንደሚረዳው አያውቅም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ እኔ እዛ ፕሮግራም ላይ ስሰራ አክሱም አካባቢ የሚገኝ አንድ ሰመማ የተባለ ወረዳ ላይ የካቲት 11ን መዋጮ እያንዳንዱ ሰው 250 ብር እንዲያዋጣ ተጠይቆ ‹‹አንሰጥም›› ሲሉ ሴፍትኔት ተከለከሉ። እኛ ደግሞ ከዓለም ባንክ ተልከን በአጋጣሚ ስንሄድ ሴፍትኔት የሚወስዱበትን ካርድ የተወሰኑ ሰዎችን ጠርተን ስንጠይቃቸው ለየካቲት 11 በዓል አንከፍልም በማለታቸው እንደተቀሙ ነግረውናል። እናም ይህንን ያህል ነው በዚህ ህዝብ ላይ ተፅዕኖ ያደርሱበት የነበረው። በእርዳታ የምትመጣውን ያቺን ገንዘብ መቀጣጫና ማስፈራሪያ ነበር የሚያደርጉት። ሌላ አይነት ፖለቲካ ውስጥ ሊገባ ቀርቶ የሚፈልገውን ሃሳብ እንኳን መግለፅ የማይችል ማህበረሰብ ነው።
ከዚህ ባለፈ ህዝቡ የእነሱ ባሪያ ሆኖ እንዲኖር በተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎች ነው የሚያሳምኑት።ህወሓት ለማሳመን የሚጠቀመው አንደኛው ፕሮፖጋንዳ ‹‹የሞተው ወንድም አይደለም ወይ?፤ መስዋት ከፍለህ ሳለ አባትህ ተሰውቶበት እንዴት ህወሓትን ትቃወማለህ?›› በማለት ነው። በመሰረቱ የእኔ አባት ግን የተሰዋው ለእኔ ነፃነት እንጂ ዝም ብዬ ዘላለም ህወሓት የሚባለውን ቡድን እያገለገልኩ እላዬ ላይ እየተንከባለለ እንዲኖር አይደለም። ደግሞስ አባቴ መስዋት የከፈለው ለእኔ ነፃነት ከሆነ ለምንድን ነው የማልቃወመው? እነሱ ይህንን አይፈልጉም። በነገራችን ላይ አንድ የትግራይ ተወላጅ በስብሰባ ላይ እንኳን ቢናገር ‹‹የሰማዕታት አጥንት ረገጠ›› ብሎ እዛው ነው በማህበረሰቡ የሚወገዘውና የሚፈረድበት። ይህንን ያህል ነው ህዝቡ አዕምሮ መጥፎ ስዕል ፈጥረው እንዳይናገር ሽባ ያደረጉት። በዚህ ምክንያት እንደፈለገ የሚኖርበትን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጭምር እንዳይኖር ያደረጉት።
ስለዚህ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ትግራይ ውስጥ እንዴት ይታሰባል? ። መቀሌ ላይ እኮ ቡና በረንዳ ላይ የሚሸጡ እናቶች ስድስትና ሰባት ሺ ብር ግብር ክፈሉ ብለዋቸው ተማረው አብዛኞቹ አረብ ሃገር ነው የተሰደዱት። ሆቴል የላቸውም ሰዎች ደብዳቤ እየተፃፈ ለበዓል ማክበሪያ ገንዘብ ሲጠየቁ ‹‹አንሰጥም›› ሲሉ ያልሰሩበትን ግብር እየተጫነባቸው ጥለው ዘግተው ይሄዳሉ። በነገራችን ላይ የህወሓት አንደኛው መርህ ህዝብን አደህይቶ መዝጋት ነው። ደሃ ስትሆኚ እርዳታ እየተቀበልሽ ዘላለም የሱ ባሪያ ሆነሽ እንድትኖሩ ከማለም የመነጨ ነው። ከዚህ በላይ ቅጣት ደግሞ የለም። ድሃ ሆኜ እንድኖር ከፈረድሽብኝ ደግሞ በዓለም ላይ በጥይት ከገደለኝ በላይ ጠላቴ ነሽ። ምክንያቱም ሞት አንዴ ነው፤ ድህነት ግን እስከሞት ድረስ የሚያሰቃይ አደገኛ ነው። ተስፋም ያሳጣል። በመሰረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልነበረው ዴሞክራሲ ትግራይ ውስጥ ሊኖር አይችልም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ ለተፈጠረው ችግር በዋናነት ህወሓት ላለፉት 27 ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ ሲነዛ የኖረው የጥላቻ ፖሮፖጋዳ ውጤት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ሃጎስ፡– እውነት ነው፤ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ በጣም መጥፎ የሆነ የአዕምሮ ስራ ሰርቷል። ያንን ለማስተካከል አሁን ላይ ቀላል አይደለም። የራሱ የሆነ ሰፊ ስራ ይፈልጋል። እንደሚታወቀው የትግራይ ህዝብ ቀበሌ ድረስ የሌለበት ክልል የለም። ዛሬ እንኳን ሞያሌ፣ ቀብሪዳሃር፤ ወይም ደግሞ ቤኒሻንጉል ገጠር ድረስ የትግራይ ተወላጅ የሌለበት አታገኚም። ትራስፖርት የሌለበት አካባቢ ራሱ ሳይቀር የትግራይ ተወላጅ አለ። ዛሬ ሱማሌ ላይ የእጣን ማምረት ስራ የሚሰራው የትግራይ ተወላጅ ነው። እነዚህ ተወላጆች ግን ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በሰላም እንዳይኖሩ ከፍተኛ የሆነ ስራ ሰርቷል። እርግጥ ነው ህዝቡ ወደሃገሩ እንዲገባ ከአሥር ዓመት ጀምሮ ሲቀሰቅስ ነበር። ግን የትግራይ ተወላጆች ትግራይ የምትባለው ክልል ከኢትዮጵያ ውጭ ለብቻዋ እንደማትጠቅማቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ደግሞ በመላው ሃገሪቱ ያለው ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ትግራይ ቢሄድ እንኳን ለመቀመጥ ለመቆምም ቦታ አይገኝም። እኔ ትግራይ ተወልጄበታለሁ፤ አድጌበታለሁ፤ ለእኔ ግን ትግራይ ከሚሰጠኝ ጥቅም ይልቅ ሌላው ክልል የሚሰጠኝ ነው የሚበልጥብኝ። ምክንያቱም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ስለማስብ ነው። ስለዚህ ትግራይም ሆነ ኦሮምያ ለእኔ አንድ ነው። ይልቁንም ትግራይ ልኑር ብል ነፃነት እንደማይኖረኝ አውቃለሁ።
ጁንታው የትግራይ ህዝብ ከሌላው ማህበረሰብ እንደተገለለ አድርጎ እንዲያስብ ቅስቀሳ ከጀመረ ቆይቷል። በዚህም የእኔ የሚላቸው የእሱ ደላላ የነበሩ በሃብት የደረጁ ብዙ ሰዎች ወደ ውጭ ሃገር ልኮ እንዲረዱት አድርጓል። አሁን ላይ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየጮሁ ያሉት የህወሓትን ገንዘብ የበሉ ናቸው። አንድም ዲቪ ደርሶት አሜሪካን የሄደ የትግራይ ተወላጅ አደባባይ ወጥቶ አይጮህም። ምክንያቱም ለምንና እንዴት እንደሄደ ጠንቅቆ ያውቃል። አንድም በባህርና በዓረብ ሃገራት በኩል ተሰቃይቶ አሜሪካ የደረሰ የትግራይ ተወላጅ መሬት ላይ ወጥቶ አይንከባለልም። ለስራ እንደሄደ ያውቃል። የሚጮሁት የእነሱ ተላላኪ የነበሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ ይዘው የሄዱ ነገ ችግር ቢመጣባቸው እንኳን በጩኸት እንዲረዳቸው አስበው የላኳቸው ናቸው።
ለእነሱ ኢትዮጵያ ብትፈርስ ደንታቸው አይደለም። ምክንያቱም ያገኙት ገንዘብ ሰርተው አይደለም። ከዚህ ውጭ ያለው ማህበረሰብ ግን ችግር የለበትም።
እንዲህ እያደረገ ከአሥር ዓመት በፊት የጀመረው ቅስቀሳ አልሄድ ሲለው ሥልጣን ከለቀቀ በኋላ አማራ መጣብህ ማለት ጀመረ። በነገራችን ላይ ሃውዜንን የደበደበው የትግራይ ተወላጅ አይደለም እንዴ? አማራ አይደለም። የአየር ሃይሉ ኃላፊ የነበረው ሊያውም የዓድዋ ተወላጅ ነበር። የደበደበው የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ሳለ ለምንድን ነው አማራ ላይ የሚንጠለጠሉት። ሌሎቹም በርካታ የደርግ ጀነራሎች ነበሩ የትግራይ ተወላጆች። የደርግ አባላት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ናቸው። እነዚህ የደርግ ሰዎች ከህወሓት ጋር ስላልተግባቡ ነው ወደ ጦርነት ውስጥ የገቡት። ያኔም ቢሆን ትግራይ ላይ ለደረሰው ችግር አማራ ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት የለም። ይልቁንም ራሱ የትግራይ ተወላጅ ነው። ስለዚህ እነሱ የትግራይን ህዝብ የያዙበትን ዘዴ ሲፈልጉ አማራ መጣብህ ነው የሚሉት። በታሪክ አማራ የትግራይ ህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ይህንን የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ የለንም። ሁሉም የኢትዮጵያ ነገሥታት የሰሩት መልካምና መጥፎ ነገር አለ። ይሄ ደግሞ ማንም መንግሥት የሆነ ሰው የሚያደርገው ነው። አሁን እንኳን ዶክተር አብይ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያስደስት አይችልም። እንኳን ሰው በሆነ ፍጡር ይቅርና በፈጣሪ እንኳን ሁላችንም እኩል አንደሰትም። ነገ ልናስተካክል የምንችለውን ነገር ዛሬ ላይ ስናጣ ፈጣሪን እናማርራለን። ሰው ደግሞ ከዚያ በላይ ነው። መሪ ስትሆኚ ደግሞ የብዙዎችን ጥቅም ነው እንጂ የምታስጠብቂው የእያንዳንዱን ሰው ልታስጠብቂ አትቺይም። ይሄ በየትኛውም ዓለም ያለ ነው። የነበሩ ነገሥታትም እያደረጉት ይህንን ነው። ሃገራቸውን አስበልጠው የግለሰቦችን መብት ያከበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህንን ደግሞ መጠበቅ አይገባም፤ ሊኖርም አይችልም።
ስለዚህ ‹‹አማራ›› የሚባል መንግሥት እኔ በታሪክ አላየሁም። ይመሩ የነበሩት በጠቅላላው ሃገሪቱን ነው። እንደየአቅማቸው አገራቸው በዓለም ከፍ እንድትል ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ከዚህ ውጭ አማራ ተሹሞ የትግራይ ህዝብ የተባለ የአማራ መንግሥት አላውቅም። እነሱ ይህንን አስተሳሰብ ከየት እንዳመጡት አላውቅም። ለምሳሌ የእኔ እናት ስትነግረኝ በደርግ ጊዜ ለኩራዝ ዘይት እንጂ ጋዝ አይጠቀሙም ነበር። ሃውዜን ራሱ ዱቄት ይሰጣቸው ስለነበረ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያምን ‹‹የፉርኖ ዱቄት አባት ነው የሚሉት። አሁን ላይ ታዲያ የህወሓት ሰዎች ‹‹የአማራ መንግሥት›› የሚለውን ከየት እንዳመጡት እኔ አይገባኝም። ግን ደግሞ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን የጥላቻ አስተሳሰብ ስራዬ ብለው ሰርተው ህዝቡን ማደናገር ችለዋል። በዚህ ምክንያት አሁንም እንደሚታየው ‹‹አማራ ሊገዛ ነው፤ ሊፈጅህ ነው›› እያሉ ህዝቡ ወደ ዘረኝነት እንዲሄድ ከፍተኛ ቅስቀሳ እየሰሩ ነው ያሉት። ትናንትም ሲያደርጉት የነበረው ይሄ ነው። ዛሬም እያደረጉ ያሉት ይሄው ነው። ለእኔ ግን የአማራ ህዝብ የትግራይ ጠላት አይደለም። በነገራችን ላይ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ አይጨነቅም። ህዝቡን የሚጠላ የመጀመሪያ የፖለቲካ ፓርቲ ህወሓት ነው። ‹‹ነፃ አወጣሃለሁ›› ብለሽ ከታገልሽለት የአንቺን ጥቅም አስቀርተሽ ነው ነፃ የምታወጪው። ህወሓት ግን ይህንን አያደርግም። ይልቁንም ስንዝር የምትባል እርምጃ ወንበሩ ላይ እንድትጠጊ አይፈልግም። ዘመኑን ሙሉ ሲያስብ የኖረው ስልጣኑን አስጠብቆ መቆየት ብቻ ነው።
እንደሚታወቀው ደግሞ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሉ ውጪ በኢኮኖሚ የደረጁ፤ የተዋለዱ፤ የተዛመዱ፤ በመላው ኢትዮጵያ ላይ የተበተኑ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ህወሓቶች በመከላከያ ሠራዊት ላይ ያንን ሁሉ ግፍ ሲፈፅሙ ቅንጣት ያክል ለእነዚህ ሰዎች አልተጨነቁም። እዛ ያለው ህዝባችን ምንድን ነው የሚገጥመው? ብለው አላሰቡም። ይህ ቡድን ራስ ወዳድ መሆኑ ይሄ ማስረጃ ነው። ከዚህ በላይ የበለጠ ራስ ወዳድነት የለም። ጎንደር ላይ ‹‹አማራ ነው እንዲህ ያደረገ›› ለማለት የትግራይ ተወላጆች ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ሆን ብሎ ቀስቅሶ ሲያስወጣ ጎንደር ላይ የቀረ በርካታ የትግራይ ተወላጅ አለ። ማንም የነካው የለም። የተወሰኑ ሰዎች በንዴት ጥቃት ላድረስ ብለው ጀምረው ራሱ የጎንደር ህዝብ ልጆቹም ጭምር እዛው እያሳደረ ሲጠብቅ ነበር። ይሄ ነው እኔ የማውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ!። ይህንን ለዘመናት ተቻችሎ የመኖር እሴትን ለማሳታትና አገር ለማፍረስ ሲያሴሩና ሲጥሩ ነው የነበሩት። አሁን በዚህ ፀያፍ ተግባራቸው ቀጥለውበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንደእነሱ ሃይማኖት አልባ አይደለም። ባህልም ያውቃል። እነሱ የፈለጉትን ቢሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አይለያይም። በነገራችን ላይ እንደእነሱ ክፋት የትግራይ ህዝብ የሚጠፋው ከጦርነቱ በፊት ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ቢሆን ህሊና ያለው ማስተዋል የሚችል ማህበረሰብ ነው። በሃይማኖትና በባህል የተጣመረ ህዝብ ስለሆነ የእነሱን ስራ ያውቃል። ስለዚህ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራይ ህዝብ ባለውለታ ነው። እነሱ እንደአሰቡት አልሆነም፤ አይሆንምም። እንደሩዋንዳ የትግራይ ህዝብ እንዲጨፈጨፍ እና የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቅ ዘራችን እንዲህ ሆነ ብለው መጥፎ ታሪክ እንዲፃፍ ነበር የፈለጉት። ግን አልሆነም። ስለዚህ አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ አውቋቸዋል። ከዚህ በኋላም ከትግራይ ህዝብ ጎን ሊቆም ይገባል። የትግራይ ህዝብም የራሱን ድርሻ እንደሚወጣም አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– አሸባሪው ህወሓት አሁንም ሕፃናትና እናቶችን ለጦርነት እየማገደ ነው፤ ከዚህ አኳያ የዚህን ጁንታ ቡድን የትግራይ ህዝብና የዓለም ማህበረሰብ በምን መልኩ ነው ሊያስቆሙ የሚገባው?
አቶ ሃጎስ፡– እንግዲህ ከፋም ለማም ችግሩ ለትግራይ ህዝብ ነው ጣጣው የተረፈው። አስቀድሜ እንዳነሳሁት አለመታደል ሆኖ የትግራይ ህዝብ ጦርነት ለአንተ ነው ተብሎ እንደምርቃት እድል ደርሶት ሁልጊዜ ጦርነት የሚከሰተው ትግራይ ውስጥ ነው። የትግራይ ህዝብ የሚያልቀውም በራሱ ልጆች ነው። ከደርግ ጊዜ የነበረው ልዩነትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ነበሩ፤ መስማማት ይቻል ነበር። ያ ሁሉ ህዝብ መሞት አልነበረበትም። ሌላ ጠላት አይደለም እኮ ከውጭ የመጣብን። መነጋገር ይቻል ነበር። ምክንያቱም ያኔም ቢሆን ጠረጴዛ ነበር። በመሰረቱ ለደርግም የሰጡት ጊዜ አልነበረም። በወቅቱ ነፍስ ባላውቅም አሁን ላይ ታሪክ ሳጠና ለደርግም ነገሮችን በጥሞና የሚያደርግበትና የሚወስንበት ምንም ጊዜ አልሰጡትም። ፋታ አልሰጡትም። ደርግ ስልጣን እንደያዘ ነው ከአዲስ አበባ የወጡት። ከአዲስ አበባ ወጥተው ነው ትግል የጀመሩት። ወታደራዊ መንግሥት ብሎ ገና እንዳወጀ አልታገሱትም። እነሱ ጫካ ወጥተው ትግል ሲጀምሩ እሱም ጦረኛ ሆነ።
በመቀጠልም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም የሆነው የሚታወቅ ነው። በሁለት ግለሰቦች እልህ ብቻ ያ ሁሉ ህዝብ አለቀ። እርስበርሳቸው ‹‹ምን ታመጣለህ!?›› ተባብለው የትግራይ ህዝብ እንደከብት ታረደ። ከዚያም አልፎ ሌላው የሀገሪቱ ህዝብ ላይ ምን ያህል አደጋ እንደደረሰበት የሚታወቅ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ግን እነሱ ሁለቱም ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸውን ውጭ ልከው የተዋለደ ህዝብ ምን እንዳደረጉት ታሪክ በራሱ አስቀምጦታል። ሰው ለሀገር ጥቅም ብሎ ጦርነት ይከፍታል። ለሁለት ሰዎች እልህ ግን አብረው ስለነበሩ ስለተናናቁ ነው ያ ሁሉ ህዝብ ያለቀው። መነጋገር ይቻል ነበር። ዝም ብሎ የጥቅም ጉዳይ ነው የሚባለው ነገር ሁለተኛ ጉዳይ ነው። ደግሞም ለውጊያ የሚዳርግም አይደለም። አሁንም መነጋገር እየተቻለ፤ እነሱ የሚፈልጉትን ዘግናኝ ነገር ሁሉ አደረጉ። ከራሳቸው አልፈው ወዳጆቻቸውን ሳይቀር ውጭ ሀገር ልከው ሲያበቁ ወደዚህ ሁኔታ መግባታቸው በጣም ነው የሚያሳዝነው። የሚገርምሽ የጁንታው ሰዎች ክርስትና ለጠራቸው ሰው ሳይቀር ነው በስጦታ መልክ ቪዛ ይሰጡ ነበር። እነሱን ሰላም ያለ ሰው እኮ ሳይቀር ውጭ ሃገር ሄዷል። እንዲህ እንዳሻቸው የዘለሉባትን ሀገር እኮ ነው ያፈረሱት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ትናንት አደባባይ ላይ ወጥቶ ስራ ስርታችኋል ያላቸውን ህዝብ እኮ ነው ይህንን ብድር የመለሱለት። ትናንት እነሱን ስልጣን ላይ ለማምጣት መስዋት የከፈለ የመከላከያ ሠራዊት እንዲህ አይነት ብድር የተመለሰለት። ግን ማስቀረት ይቻል ነበር። መነጋገር ይቻል ነበር። በነገራችን ላይ እንደእነሱ ዳግመኛ እድል ያገኘ የለም። ዶክተር አብይ መሆኑ በራሱ ለእነሱ ትልቅ እድል ነበር። አልተጠቀሙበትም እንጂ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። የያዙት ገንዘብ በእጃቸው ነው። እንደፈለጉ ነው የሚኖሩት። የኢትዮጵያ ህዝብን ‹‹በድለንህ ከሆነ ይቅርታ›› ብለው ቢኖሩ ማንም አይነካቸውም ነበር። በጣም ቀላል ነበር። ምክንያቱም አብረዋቸው ከእነሱ ጋር ሲሰርቁ የነበሩ ሰዎች እኮ ዛሬ በነፃነት እየኖሩ ነው። እነሱ እኮ እዳውን ሁሉ ተሸክመውት ሄዱ እንጂ ከእነሱ እኩል ሲሰርቁ የነበሩ ሰዎች እኮ ዛሬም በሰላም በሀገራቸው ውስጥ እየኖሩ ነው ያሉት። ይቅርታ ቢጠይቁና ቢኖሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ የይቅርታ ህዝብ ነው። እነሱ ግን ይህንን አልፈለጉም። ከዚህ በፊት እንደሚሉት መቶ ዓመት የመንገሥ እቅድ ይዘው በድንገት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ራሳቸውን ዋሻ ውስጥ አገኙት። ለነገሩ ዱባይ ላይ እንዳሻው ሲንፈላሰስ የነበረ የህወሓት ባለስልጣን በድንገት ከእንቅልፉ ሲነቃ ራሱን ዋሻ ላይ ሲያገኘው ለምን አይደነግጥም?። እንደሰው ያስደነግጣል። ምክንያቱም እንኳን ለእነሱ ለእኔም እንደአንድ ተራ ዜጋ ዝም ብዬ ሳስበው የሆነው ነገር ይገርመኛል። መሳሪያ እጃቸው ላይ ነው፤ ሁሉም ነገር እጃቸው ላይ ነው። ያ ሁሉ ነገር ሲሆን ድንገት ሳይታሰብ በቃችሁ ሲላቸው ፈጣሪ አፋቸውን ለጉመው ራሳቸውን አስረው ጫካ ላይ ተገኙ። ይሄንን ነገር ስታስቢው የእግዚአብሄርም እጅ እንዳለበት ትገነዘቢያለሽ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግፍና መከራም አለበት። ስለዚህ ራሳቸውን በድንገት ዋሻ ላይ ሲያገኙት የሆነው መፈራገጥ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላም ቢፈራገጡም ምንም አያመጡም። እንደተለመደው ንፁሃንን ያስፈጃሉ፤ መስዋት ይከፈላል። ያው የፈረደበት የትግራይ ህዝብ ምን ያህል ችግር እንደደረሰበት ይታወቃል። አሁንም ለእድሜ የደረሰው ወጣት አልቆ ከእድሜ በታች የሆነውን ከኪሎው በላይ የሆነ መሳሪያ እያሸከሙ በጦርነት እየማገዱት ነው። ዞሮ ዞሮ ከማንም በላይ የትግራይ ህዝብ ጠላት ህወሓት ነው። ከዚያ በኋላ የትግራይ ህዝብ ከሌላ ማህበረሰብ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር አይፈልግም። ይህ ወንበዴ ቡድን ሁልጊዜ በሰው ደም ላይ እየተረማመደ ስልጣን ላይ መቀመጥ ነው የሚፈልገው። በደርግም ሆነ በሻቢያ እነሱ አልሞቱም። እኔ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር እነዚህ ሰዎች እስካሁን ድረስ በህይወት መኖራቸው ነው።
በደርግ ጊዜ 17 ዓመት ሲታገሉ ከእነሱ ውስጥ አንድም ሰው አልሞተም። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም ጊዜም የጦር መሪ የሆነ የእነሱ ሰው አልሞተም። ዛሬም አልሞተም። ራስ ወዳድነታቸውን እኮ የምታየው ስብሃት ነጋ ‹‹እንዳትገድሉኝ›› ብሎ እጁን ሲሰጥ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ራስ ወዳድነት አለ?። ለህዝብ ነፃነት የምትታገዪ ከሆነ ራስሽ እየሞትሽ ነው። በመሰረቱ ፈጣሪ በሃይል ካመጣባቸው በስተቀር ሌላውን ያስገድላል እንጂ እነሱ መሞት አይፈልጉም። ህዝብ የሚባል ነገር ለእሱ ደንታቸው አይደለም። ለህዝብ ቢራብ፤ ቢጠማም ግዳጃቸው አይደለም። ስብሃትም ተናግሮታል። የትግራይን ህዝብ ደንቆሮ ነው እያለ የሚጠራው። እውነቱን ነው ደንቆሮ ነው!። ምክንያቱም እነሱ የሚሉትን ‹‹አሜን›› እያለ ተቀብሎ ኖሯል። ግን ህዝቡ ዝም ያለው ሁልጊዜ ከስህተታቸው ይማራሉ በሚል ነው። ግን እነሱ እንደተለመደው በሰው ደም ላይ እየተረማመዱ መቆየትን ነው ምርጫቸው ያደረጉት።
አብዛኞቹ የህወሓት ሰዎች ከ60 ዓመት በላይ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እኮ የድፍረታቸው ብዛት በደርግ ጊዜ 17 ዓመት ውጊያ ተደርጎ እንኳን አሁን ላይ ትምህርት የጨረሰ ወጣት ከአጠገባቸው እንዲቀመጥ አይፈልጉም። ተምረሽም ቢሆን በእነሱ ዘንድ ትናቂያለሽ። ምክንያቱም እውቀትና ገንዘብ ያለው ሰው አይፈልጉም። እነሱ የትግራይ ህዝብን ሁልጊዜ አደህይተው ነው መግዛት የሚፈልጉት። ያ ስለሆነ ዛሬም እንደምታዪው ከችግር ከድህነት እንዳይወጣ ልጆቹን እየነጠቁ ‹‹ለህዘብ ነፃነት መሰዋት አለብህ፤ አማራ መልሶ ሊገዛ ነው፤ አማራ መጣብህ ፤ አላማጣ ደረሰ፤ ወልቃይት ደረሰ›› እያሉ ህፃናትን እያሰለፉ ነው ያሉት። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ህፃናት የት እንደሚሄዱ አለማወቃቸው ነው። እኛ ያገኘናቸው የእነሱ የልዩ ሃይል አባላት እኮ ‹‹ ባዶ እጃቸውን የአማራ ህዝብ ነው የምትከላከሉት ብለው ነው የወሰዱን›› ብለው ነው የነገሩን። ሆኖም እንደተባለው ባለመሆኑ ስለራባቸው ጥለው መምጣታቸውን አጫውተውናል። እናም የህወሓት ግፍ እዚህ ደረጃ ደርሷል። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሄር ልብ ቢሰጣቸው እመኛለሁ። የሚያሳዝነኝ ግን የትግራይ ህፃናት ሞት ነው። እርግጥ ነው ቢዘገይም እነዚህ ሰዎች መጥፋታቸው አይቀርም። ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው መጥፊያቸውን ነው ራሳቸው የጫሩት። ጁንታዎቹ አሁን የለኮሱት እሳት መጥፊያቸው ነው የሚሆነው።
በመሰረቱ በዚህ ሰዓት የሚበላውን አጥቶ የትግራይ ህዝብ ስለመሬት የምትጨነቂበት ጊዜ አልነበረም። ደግሞም እዚህ ሀገር ሃይማኖት አለ፤ የሀገር ሽማግሌ አለ። በቀላሉ የሚስተካከል ነገር ስንት ጣጣ እያለ ትግራይ ውስጥ የሚጠጣው ውሃ፤ የሚቀምሰው እህል አጥቶ እያለ እነሱ ‹‹መሬት አለን›› ብለው ዘራፍ አለ እያሉ ነው። ለዚያውም በሃይል የወሰዱት መሬት!። እነሱም በሃይል ነው የወሰዱት፤ እነዚህም በሃይል ነው የመለሱት። ሃቅ፤ ሃቅ ነው!። መደራደር ግን ይቻል ነበር። እዚህ ሀገር የተማረ ሰው አለ፤ የሀገር ሽማግሌም ሆነ ህግም አለ። ህፃናትን ለማጥፋት ምን ያስቸኩላል?። ከሰው ሞት ምንድን ነው የሚገኘው? እኔ ሰለሞትኩኝ ይሄ መሬት ይመጣል? አይመጣም። ተወደደም፤ ተጠላም መጨረሻ ላይም በመነጋገር እንጂ በሃይል አይፈታም። ይህንን አስቀድመው ማሰብ ነበረባቸው። ግን እነሱ አላሰቡም። ህዝቡ ግን አማራ መጣ መሬትህን ሊወስድ ነው ብለውት መሬቴ ለምን ይወሰዳል የሚል ቁጭት ተፈጥሮበት ሳያውቀው ነው ወደ ጦርነት የገባው። ይህ ህዝብ ያልተማረ ገበሬና ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት አያውቅም። እውነታውን የሚያስረዳው የፖለቲካ ሊሂቅ አላገኘም። በዚህ ሁኔታ ህይወቱን ላማዳን ሲል ወደ ጦርነት ቢገባ አይፈረድበትም። የሚያዳምጠው የእነሱን ሚዲያ ብቻ ነው። ሌላው ምንድን ነው ብሎ የሚከታተልበት እድል የለውም። በነገራችን ላይ እኔ መቀሌ በነበርኩበት ጊዜ የሚከፈተው ‹ቲ.ኤም.ኤች የተባለ ሚዲያ ብቻ ነው። አሁን ላይ በጣም በሚያሳዝን መልኩ የትግራይ ህዝብ እንደፈረስ ጋሪ የፊቱን ብቻ እንዲያይ ለጉመውት ወደጎን ማየት አይችልም። ሌላ ጣቢያ የከፈተ ሰው ከተገኘ እንደጠላት ነው የሚታየውና ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚደርስበት። ወዲህ ወዲያ እንዳይል በአንቀልባ እንደታዘለ ህፃን አስረውት ነው የኖረው። ይህንን ያህል የትግራይን ህዝብ አጥብቀው ምንም ነገር ማሰብ እንዳይችል አድርገው ሰርተውታል።
አዲስ ዘመን፡– መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ ባለመቀበል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴስ ወዴት ያመራዋል ብለህ ታምናለህ?
አቶ ሃጎስ፡– የጥሞና ጊዜው የተለመደ ነው። ይህም ማለት በዓለም ላይም አለመግባባት ሲፈጠር ለጥቂት ቀናት ተኩስ አቁም ይደረጋል። ያቺ አንድና ሁለት ቀን ምንአልባትም መድሃኒት ቀን ትሆናለች ተብሎ ይታመናል። በእኔ እምነት መንግሥት ያደረገው ነገር ትክክለኛ ነው። ለምን ቢባል የትግራይ ህዝብ ያለውን ነገር እንዲረዳ ይጠቅመዋል ብዬ አስባለሁ። እንደአጋጣሚ ሆኖ እኛ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር ሳለን ህዝቡ ውስጥ ገብተን ብዙ ስራ ሰርተናል። ህዝቡ ህወሓት እንደሚለው ከአማራም ሆነ ከሌላው ህዝብ ጋር ችግር የለበትም። እንዳውም ልጆቻችን አማራ ሀገር አይደለም ወይ የሚኖሩት? የሚል መልስ ነው የሚሰጡት። አሁንም በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የትግራይ ተወላጆች አሉ። ምንም ነገር አልሆኑም። ስለዚህ ይህንን እውነታ ስለሚያውቅ ህዝቡ ይጠይቃል። ይህም የሚያስረዳሽ ማህበረሰቡ ላይ ችግር አለመኖሩን ነው። ግን አስቀድሜ እንዳልኩሽ አንድ ለአምስት የሚባለው አደረጃጀት አማካኝነት የቀበሌው ካድሬ የህዝቡን አመለካከት እንዲበረዝ አድርጎታል። የቀበሌ ካድሬ ስልጣን ከምትጠብቂው በላይ ነው። አንድ ቀበሌ ላይ ያለ ካድሬ ከፈለገ ሙሉ የቀበሌውን ህዝብ ማሰር ይችላል። ይሄ የህወሓት አሰራር ነው። ሚሊሻዎቹም ቢሆኑ ቋንቋ አለመቻላቸው እንጂ አደገኞች ናቸው። ስለዚህ ብዙ ህዝብ ማደንቆር ይችላሉ። በጣም በሚያሳዝን መልኩ የህዝቡን አዕምሮ አቆሽሸውታል። በነገራችን ላይ አሁንም ዶክተር አብይን ‹‹አማራ›› ብለው ነው የሚጠሩት። እነሱ ይህንን ቢሉም ህዝቡ ግን ‹‹አማራ ድሮም ሆነ አሁንም አለ፤ አሁን ምን ተፈጠረ ታዲያ?›› እያለ ጥያቄ ያነሳል።
ጥቂት የማይባለውም ‹‹በመልካም አስተዳደር የሚመራን እንጂ የሰውየው ብሄር አይደኝም›› ብሎ በድፍረት ይናገራል። ይህንን የምልሽ እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ህዝቡ ጋር ገብተን ማዳበሪያና እህል ስናከፋል እውነታውን በመረዳታችን ጭምር እንጂ!። ህዝቡ ሰላም ናፋቂ ነው። እንዳውም ‹‹እየወለድን ለጦርነት መስጠት ሆነ ነው›› የሚል ምሬት ውስጥ ገብቷል። ሲጀመርም የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ይሄ አልነበረም። እስካዛሬ ዞር ብለው አይተውን የማያውቁ የህወሓት ሰዎች ‹‹ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ለምን አሁን መደበቂያ ያደርጉናል?›› የሚል ቅሬታም አለው። ምክንያቱም ትግራይን አያውቋትም። 1983ዓ.ም አዲስ አበባ መጡ ለየካቲት በዓል ነው የሚሄዱት። መቀሌ ላይ ቤት እንኳን አልነበራቸውም። አዲስ አበባና ዱባይ ላይ ነው ቤት ያላቸው። የትግራይን ህዝብ አያውቁትም። ስለዚህ አሁን ላይ ህዝቡ ይህንን ሁሉ ዓመት ትተውን ቆይተው ለምንድነው ጦርነት ውስጥ የሚያስገቡን የሚል ጥያቄ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– በእነ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አሸባሪ ሃይል የእርዳታ እህልም ህዝቡ እንዳያገኝ የተለያዩ ክልከላዎችን እያደረገ መሆኑ ለህዝቡ የማያስብ ሃይል የመሆኑ ማረጋገጫ አይሆንም?
አቶ ሃጎስ፡– አስቀድሜ እንዳልኩሽ ህወሓት የፕሮፖጋንዳ ችግር የለበትም። እነሱ የሚፈልጉት አንድ ጊዜ ትግራይን ሀገር እንዳርጋለን ይላሉ። ግን ደግሞ ትግራይ ሀገር እንደማትሆን በደንብ ያውቃሉ ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን የማመስ ስትራቴጂ ነው እየተከተሉ ያሉት። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ተርቧል ይላሉ ግን ደግሞ በቀጥታ በረራ ወደ ትግራይ እንዲደረግ የዓለም አቀፍ ህብረተሰብን ያጭበረብራሉ። እንደምታውቂው ይህንን የሚደርጉት መሳሪያ ለማስገባት ነው። በሌላ በኩል ‹‹የፌዴራል መንግሥት ነው እህሉን ያቃጠለው›› እያሉም ነው። ስለዚህ በአውሮፕላን ይግባልን ነው እያሉ ያሉት። ይህንን የሚያደርጉት እንዳልኩሽ ትጥቅ ለማግኘትና ውጭ ሀገር ያሉ ተላላኪዎቻቸው ጋር በመሆን ይህችን ሃገር ለማፍረስ ነው። ይህንን ደግሞ መንግሥትም አይቀበለውም፤ እኔም እንደግለሰብ ፈፅሞ ሊሆን አይገባም ብዬ ነው የማምነው። በኢትዮጵያ ምድር ላይ እርዳታ ከየትኛውም ዓለም ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን በፌዴራል መንግሥት እውቅና አግኝቶ ተፈትሾ ነው። ማንም የማንንም ድንበር አይጥስም። ይህንን ደግሞ እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል። የሚሳዝነው ነገር የትግራይ ህዝብ በረሃብም ሆነ በጥይት መሞቱ የማይገዳቸው መሆኑ ነው። ለነገሩ ይህንን የሚስቡበት ጊዜ የላቸውም። አእምሯቸው ላሽቋል። የብዙ ሰው ደም አለባቸው። ህሊናቸውም ከጥቅም ውጭ ሆኗል። ለእኔ ለነገሩ እነዚህ ሰዎች በእብደት ውስጥ ያሉ እንጂ በትክክል አስበው እየሰሩ አይመስለኝም። አዕምሮቻቸው ስለማይሰሩ አንድ የሚያስቡት ነገር መበጥበጥ ብቻ ነው። በመሆኑም ድሮም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ ያልነበረው ሃዘኔታ ዛሬ ከምን ተነስቶ ሊኖረው ይችላል?። ለእኔ ይህንን መቀበል ይከብደኛል።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ በራሱ ማዕበል ተነስቶ የህወሓትን አገር የማፍረስ ሴራ አሻፈረኝ ሊል ይገባዋል። ደግሞ አማራጭ ካጣ እንኳን ወደ ደጉ የኢትዮጵያ ህዝብ መምጣት ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይን ህዝብ የሚጠላበት ምክንያት የለውም። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ወደ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ በመምጣት ራሱን ማዳን ይገባዋል። ደግሞ በውጊያ ጊዜ ከትግራይ መውጣት ለትግራይ ህዝብ አዲሱ አይደለም። በ1977 ዓ.ም ከደርግ ጋር ህወሓት ሲጣላ የትግራይ ህዝብ ወገንና ሀገር አለኝ ብሎ ነው የመጣው። አሁንም እሱን ነው ማድረግ ነው ያለበት። ከዚያ ክልል ይውጣ። እነሱ ሞት ነው የሚፈልጉት፤ ይሙቱ። ሌላው ህዝብ ግን በፍጥነት ወጥቶ ህይወቱን ማስቀጠል መቻል አለበት። የትግራይ ህዝብ አላማ ለሌለውና ምክንያታዊ ላልሆነ ሞት መዳረግ የለበትም። በተለይ የትግራይ ወጣት ነገ ለሚያልፍና ታሪክ ለሌለው ሞት በፍፁም ራሱን አሳልፎ መስጠት የለበትም። እውነቱን ለመናገር ለእኔ ከማንም የበለጠ ብዙ የሆነችልኝ ህወሓት ሳይሆን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ናቸው። መሬት ላይ ያለው እውነታም ይሄ ነው። የትም ቀበሌ ላይ አለ የትግራይ ተወላጅ። በኢትዮጵያ ውስጥ ተከብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። በመሆኑም በመላው ሃገሪቱ ያለው የክልሉ ተወላጅ እንደትናንት ሰርቶ መኖር ብቻ ነው ያለበት። አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ መግባት እንደሌለበትም ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ታሪካዊ የሆነ ስህተትም እንዳይሰራ ራሱን መግዛት ይጠበቅበታል። እኛ ሃገራችን ኢትዮጵያ ናት፤ ሌላ ሀገር የለንም። ትግራይ በኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምትኖረው። የትግራይ ህዝብ ህልውና የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አይደለም የፍየል ግንባር በምታክል መሬት ላይ ታጥረን ይቅርና ያን የመሰለ መሬት ይዘው ኤርትራውያን ምንም አልተጠቀሙበትም። በዓመት በርካታ ሚሊዮን ዶላር ማስገባት የሚችል ባህር ይዘው በድህነት ነው እየኖሩ ያሉት። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ መገንጠል ለኤርትራ እንዳልበጀ መማር ነው የሚገባው። እኛ ሃብታችን ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ያደግነው፣ የተማርነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ለእኛ ኢትዮጵያ ከማንም በላይ ሆናልናለች። ትናንት እንደኖርነው መኖር አለብን። የትግራይ ተወላጆች እዚህች ሀገር ላይ ከጥንት ጀምሮ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የስልጣን ባለቤት ሆኖ ነው የኖረው። ምንም የጎደለው ነገር የለም።፡ ስለዚህ የቀረን ነገር ስለሌለ ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ መኖር ነው ያለበት። ሁላችንም የትግራይ ተወላጆች ዘራችንን ሊያጠፉ የሚሞክሩትን የህወሓት አደገኛ መርዞች በአደባባይ ልንቃወማቸው ይገባል። በተለይ እዚህ ያለው የትግራይ ተወላጅ የዓለም ማህበረሰብ እውነታውን እንዲያውቀው ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡–ከዚህ ጋር ተያይዞ ውጭ ለሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህና ውይይታችን በዚህ እናብቃ?
አቶ ሃጎስ፡– እውነት ነው፤ አሁን መላው ኢትዮጵያውያን በሰከነ አዕምሮ ሆነን ስለሀገራችን የምናስብበት ወቅት ነው። እንደሚታወቀው ለውጥ ሲመጣ የሚመቸው እንዳለ ሁሉ የማይመቸው አካል አለ። ሀገራትም ሆነ መንግሥታትም ይኖራሉ። ለእኛ ከተመቸን ሌላው ትርፍ ነው። ግን ህወሓት የሰራውን ፕሮፖጋንዳ ያህል እኛ አልሰራንም። ምክንያቱም ሃቅ ይዘሽ ስትንቀሳቀሺ አንድአንድ ጊዜ አሉባልታዎች ተፅዕኖ አያመጡም ብለሽ ልታስቢ ትቺያለሽ። ግን ደግሞ ብዙ ጊዜ ውሸት እየተደጋገመ ሲሄድ እውነት ይመስላል። ስለዚህ የህወሓት ፕሮፖጋንዳ እግር ለእግር እየተከታተልን ማፍረስ ይገባናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዓለም ማህረሰብ እውነታውን ማሳወቅ አለበት። ፖለቲካ ሌላ ነው፤ ሃገር ሌላ ነው። አሁን የህወሓትና የፌዴራል መንግሥት ግጭት የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ራስ ወዳድነት ነው። ፖለቲካ ነው የሚባለው እኩል ቦታ ላይ ሆነው ፖለቲካ ሲያለያያቸው ነው። ህወሓት በፖለቲካ ምክንያት አይደለም ከስልጣን የተነሳው። የኢትዮጵያ ህዝብ ስላልፈለገ ነው ህወሓትን በቃኝ ያለው። እንዲህ ከሆነ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ህወሓት የተጣላው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው። ህዝብ አልፈልግም ካለ ማስገደድ አይቻልም። ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሀገሩ ማሰብ እና የአቅሙን ያህል ድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖር የትግራይ ህዝብ ያለምንም ጥርጥር ህወሓትን ማውገዝ አለበት። ምክንያቱም ዘራችን እየጠፋ ነው። በየጦርነቱ ወጣቱ የሚማገድ ከሆነ ነገ ጠዋት ሽማግሌ ብቻ ይዘን ልንቀር ነው። ስለዚህ ልናወግዝ ይገባል። ሌላው ውጭ ያለው ዲያስፖራም ለዓለም ማህበረሰብ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ማገዝ ይገባዋል። ሚዲያዎችም እውነታውን ማጋለጥና ከሌሎች ሀገራት ላይ ይደርስ የነበረውን ዓለም አቀፍ ጫና ተሞክሮ በመፈተሽ ህዝቡን ማንቃት ይገባዋል። የህወሓት ጋሻ ጃግሬዎች የአሜሪካ መንግሥት በውስጥ ጉዳያችን እንዲገባ ማድረግ የቻሉት ተግተው በሃሰት ዘመቻ በመንቀሳቀሳቸው ነው። ስለዚህ መንግሥት ከእነዚህ ቀድሞ መስራት አለበት። እኛ የተጣላነው አንድ ተራ ህዝብ አልፈልግህም ያለውን ሽብርተኛ ጋር እንጂ እርስ በርስ አይደለም። ይህንን ማሳወቅ አለብን። በተለይ ደግሞ በየትኛው የዓለም ሀገራት ያሉት የተማሩ ኢትዮጵያውያን አቅሙ ስላላቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን ማገዝ አለባቸው። ፖለቲካ ሌላ ጉዳይ ነው። የግል ስሜታቸውን ወደጎን በመተው ከመንግሥት ጎን በመቆም ይህችን ሀገር ካላስፈላጊ ኪሳራና ሞት መታደግ ይገባቸዋል። እኛም ከሀገር የሚበልጥ ነገር ስለሌለ መንግሥት ጥሪ ካቀረበልን እንሄዳለን። በአጠቃላይ አሜሪካ ሊቢያን እና የመንን ያደረጉትን ማየት በቂ በመሆኑ ከዚያ መማር አለብን። እኛ ኢትዮጵያውያን በውስጣችን ንፋስ ማስገባት አይገባም። በተቻለ መጠን ህወሓትም እነሱ ቢያልፉ እንኳን እዚህም ሆነ ውጭ ያሉ ልጆቹ መኖሪያ ሀገር እንዳያሳጣቸው መጠንቀቅ ይገባዋል። በተለይ በውጭ ያሉ ዜጎች ነገ ካሉበት ሀገር ቢባረሩ የሚገቡበት ቤት እንዳያጡ መጠንቀቅ አለባቸው። በመሆኑም ከዚህ በፊት የሰሩት ግፍ ቢበቃቸውና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ነው ጥሪ ማስተላለፍ የምፈልገው።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሃጎስ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013