የነገረ አሻንጉሊት ማዋዣ ወግ፤
አሻንጉሊቶች ነፍስ ላላወቁ ሕጻናትና ታዳጊ ልጆች የሚፈበረኩ ሰው መሰል መጫዎቻዎች ናቸው። መጫዎቹ “ለልጆች” ብቻ ተብለው የሚመደቡ ሳይሆን በርካታ አዋቂዎችም ቢሆኑ በአሻንጉሊቶች ፍቅር መማረካቸው እውነት ነው። ይህ ጸሐፊም የሀገር ልጅ ስሪት ለሆነው “ስንዝሮ” በመባል ለሚታወቀው ማራኪ አሻንጉሊት ልዩ ፍቅር አለው። አሻንጉሊቶች ከጨርቃ ጨርቅ፣ ከፕላስቲክና ከተለያዩ ቁሳቁሶች መመረታቸውንም አስታውሶ ማለፍ ይቻላል። የዛሬን አያድርገውና ቀደም ባሉት ዓመታት በየቤተሰቡ አባላት እጅ አሻንጉሊቶችን ለሕጻናት ልጆቻችን ሠርቶ መሸለም ለእኛውም ቢሆን እንግዳ አልነበረም።
በእኛ ቋንቋ ሁሉም ዓይነት አሻንጉሊት በአንድ ስም ተጠራ አንጂ በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሻንጉሊቶች የሚለዩት በሦስት ምድቦች ነው። ሰው መሰሎቹን Dolls ብለው ሲጠሯቸው፣ መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላን ወዘተ. የመሳሰሉትን መጫዎቻዎች ደግሞ Toys ይሏቸዋል። ሰው መሰሎቹን፣ እንስሳትንና ልዩ ልዩ ቁሶችን የሚወክሉትንና ለብዙኃን ትርዒት የሚቀርቡትን ደግሞ በጅምላ ስያሜያቸው Puppet በማለት ያስተዋውቋቸዋል።
በአሻንጉሊቶች ምርትና ንግድ አሜሪካና ቻይና ብቻ ይፎካከሩ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ሀገራት ለደረጃ ተፋልመው ጣልቃ ለመግባት የሞከሩበትን ጊዜ ማስታወስ ያዳግታል። ሁለቱ ሀገራት በየዓመቱ በሀገራቸው ገቢ ላይ የሚደምሩት የአሻንጉሊቶች ሽያጭ ገቢ በቢሊዮኖች ዶላር የሚሰላ ነው። የምርት ዓይነት ፉክክሩም እንዲሁ ቀላል የሚባል አይደለም። “የእኔ አሻንጉሊት ከአንተ ምርት ይልቅ ተወዳጅ ነው፤ አይደለም” የሚለው ፉክክርም ሁለቱን ሀገራት ወደ ሕጻንነት ዕድሜ ዝቅ ያደረገ እስኪመስል ድረስ ብሽሽቁ ሁሌም እንደቀጠለ ነው። በፖለቲካና በኢኮኖሚ የበላይነት ብቻ ሳይሆን በአሻንጉሊት ምርትና ንግድ ጭምር የሁለቱ ሀገራት ፉክክር እንደምን የጋለ እንደሆነ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችን በማየት ብቻ በትዝብት ማለፍ ይቻላል።
እ.ኤ.አ በ2018 ሰው መሰል አሻንጉሊቶችን Dolls አምርታ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ አሜሪካ ቀዳሚ የነበረች ሲሆን ቻይና ደግሞ ተከታዩዋ ነበረች። በሽያጩ የተገኘው ረብጣ ዶላርም ከብዙ ታዳጊ ሀገራት ዓመታዊ በጀት ጋር የሚስተካከል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቢሊዮን ዶላራቸውን ሆጨጭ አድርገው የአሻንጉሊቶችን ምርቶች ወደ ሀገራቸው ካስገቡ ሀገራት መካከል በዚያ ዓመት ባርባዶስና ፈረንሳይን የቀደመ አልነበረም።
እ.ኤ.አ በ2019 ምስለ ሰውና ሌሎች የሕጻናት አሻንጉሊቶችን በገፍ በማምረት ተቀናቀኟን አሜሪካን እጅ ያሰጠችው ቻይና ነበረች። በ2020 በተሠራ የአሻንጉሊቶች የሽያጭ ገበያ “የታላቋ አሜሪካ” የችርቻሮ ጣሪያ 25.14 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። ይህን ገንዘብ ወደ እኛ ምስኪን ብር ብንመነዝረው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በማባዣ ማሽናችን ምስክርነት ማረጋገጥ ይቻላል። ሁለቱ ሀገራት በታላላቅ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን እኒህን በማሳሰሉ “ጥቃቅን የልጆች መጫዎቻዎች ሳይቀር” እንደምን ጡንቻ እንደሚፈታተኑ ለመመስከር ጥሩ ማሳያ ይመስላል። እስካሁን እያዋዛ ያጫወተንን የነገረ አሻንጉሊቶች ወግ እዚህ ላይ ገታ አድርገን ወደ ኮምጣጣው “ዓለም አቀፋዊ የአሻንጉሊት መንግሥት” ምንነት እናዘግማለን።
የአሻንጉሊት መንግሥት ፈጣሪዋ “ትጉህ ሀገርi”፤
ከታላቅነት ክብር ላለመነቃነቅ በሁሉም ዘርፍ እንቅልፍ አልባ ሆና አጥብቃ የምትተጋው አሜሪካ፤ የዓለምን ገበያ እያጥለቀለቀች የኖረችው በአርቴፊሻል ምስለ ሰው የልጆች አሻንጉሊቶች በማምረት ብቻም ሳይሆን አሻንጉሊት አድርጋ የምታዘጋጃቸውን “አሻንጉሊት አከል” መንግሥታትን በመፍጠር ጭምር ነው። ይህቺ የምድራችን “ጉዲት ሀገር” አሻንጉሊት መሪዎችን በመፈልፈል ብርታቷ ገናና ተሞክሮ እንዳላት የታሪኳ ምዕራፎች ምስክሮች ናቸው። ያቋቋመቻቸው የየሀገሪቱ የአሻንጉሊት መንግሥታት መሪዎችም ከእርሷ ዘንድ በርቀት በሚቀበሉት መመሪያዎችና ትዕዛዛት በቅርበት እንመራዋለን የሚሉትን ሕዝባቸውን እንደምን ሲያምሱ እንደኖሩና እያመሱ እንዳሉ በቂ ማስረጃዎችን ማጣቀስ አይገድም።
አርቴፊሻል አሻንጉሊቶች ዓይን እያላቸው እንደማያዩ፣ ጆሮ ቢኖራቸውም እንደማይሰሙ፤ አንደበት እያላቸውም እንደማይናገሩ ሁሉ፤ አሜሪካ ይሏት ጀብደኛ ሀገርም እንዲሁ የአሻንጉሊት መንግሥታትን በምታቋቁምባቸው ሀገራት በሥልጣን ላይ የምታስቀምጣቸው “ውላጆቿ” ልክ እንደ መጫዎቻዎቹ ምስለ ሰብ አሻንጉሊቶች አመዛዛኝ ህሊና የጎደላቸው ብጤዎች እንደነበሩ በየዘመናቱ ተስተውሏል። እነዚህን መሰል አሻንጉሊት መንግሥታት ጆሯቸው እውነትን እንዳይሰማ፣ ዓይናቸው የገሃዱን እውነታ ተረድቶ ለሐቅ እንዳይቆም በሴራዋ ተተብትበው ስለሚጠረዙ እንቅስቃሴያቸው በሙሉ “ሲጠሩ አቤት፤ ሲላኩ ወዴት” ይሉት ብጤ ነው። ተልዕኳቸውን የሚመዝኑትም ለጠፊ ዝናና ጥቅም ብቻ ስለሚሆን የሚንቀሳቀሱት ጌታዋ አሜሪካ ጨብጣ በምትዘውረው “ሪሞት ኮንትሮል” አማካይነት ነው።
የአሻንጉሊት መንግሥታት መሠረታዊ ባህርያት፤
የአሻንጉሊት መንግሥታት መሪዎች የፖሊሲና የተግባር ስምሪታቸውን የሚቀበሉት በርቀት ከሚገኙት የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቻቸው ስለሚሆን በዓለም አቀፍ ሕግና ስርዓት ሁሌም እንደተኮነኑ ነው። ሉዓላዊ ከሚሉት ሀገራዊ ክብርና ማንነታችን ከሚሉት አቋምም ጭራሹኑ ስለሚፋቱ በሰብእና ማንነታቸው የሚንቀሳቀሱ በደመነፍስ ስቅቅ ነው።
ጠቅለል ተደርጎ ሲፈተሽ የአሻንጉሊት መንግሥታት ባህርያትን በሦስት መመደብ ይቻላል። የመጀመሪያው ባህርይ “ፈጣሪውን ኃያል መንግሥት” እንደ ዕቃ (ቁስ) ማገልገል ነው። ፈላጭ ቆራጩና አለሁልህ ባዩ ከበስተኋላ የቆመው የአሻንጉሊቱ መንግሥት ወላጅ ሀገር ነው። ሁለተኛው ባህርይው ከማቄልና ከማሞኘት ጋር የተዛመደ ነው። አሻንጉሊት መንግሥቱ የተፈጠረበትን ሀገር ክብር አስከብሮ ለማገልገል ሳይሆን የዓለምን ማኅበረሰብ ለማጃጃልና “ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው” አሰኝቶ ለማሳመን ነው። ሦስተኛው ባህርይው “ፈጣሪው መንግሥት” በተፈጣሪው አሻንጉሊት መንግሥት አማካይነት ያለመውን አጀንዳ ለማስፈጸም ስለሚያግዘው ነው።
ከዓለም የታሪክ ገጾች እንደምናነበው ጥንታዊው የሮም መንግሥት በወረራ በያዛቸው ሀገራት እጅግ በርካታ አሻንጉሊት መንግሥታትን ያቋቁም እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። የቅርብ ዓመታት ታሪኮችን ስንመረምርም እንዲሁ ጃፓን ለሰሜኑ የቻይና ግዛት ለማንቹሪያ የአሻንጉሊት መንግሥት መቋቋሟ፣ ቱርክ በቆጵሮስ ደሴቶች ላይ የመሠረተችው መንግሥት፣ ሩሲያ በዩክሬን፣ በሞልዶቭ፣ በጆርጂያና በመሳሰሉት ራስ ገዝ ሀገራትና በየመን አይዞህ ባይነት የተመሠረተውን ሁቱን መሰል “በአሻንጉሊት” ይታወቁ የነበሩ መንግሥታትን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
“ቀዝቃዛው ጦርነት” እየተባለ ይጠራ በነበረውና “በኮሚኒስትና በኢምፔሪያሊስት ሀገራት” መካከል በነበረው ሽኩቻ ወቅት የተወለዱትን አሻንጉሊት መንግሥታትም ማስታወስ ይቻላል። አሜሪካ ይሏት ሀገር በኩባ (እ.ኤ.አ ከ1959 በፊት)፣ በጓቲማላ (እስከ 1991)፣ በደቡብ ኮሪያ (እስከ 1976)፣ በቬትናም፣ በያኔዎቹ ምዕራብ ጀርመንና ሰሜን የመን ተቋቁመው የነበሩትን “የምስለ መንግሥታት” ታሪኮችም የሚታወሱ ናቸው። ዛሬም በማን አለብኝነት የበረታችው ይህቺው አሜሪካ አላርፍ ብላ በኢራቅ፣ በኢራን፣ በሊቢያ፣ በአፍጋኒስታን ወዘተ. ሀገራት መንግሥታቱን እንደፍላጎቷ “አድቦልቡዬ ካልፈጠርኳቸው” በማለት ጦርነቶችን ስታጋግል እያስተዋልን ነው።
እኛን ጠቀስ የአሻንጉሊት መንግሥት ህልመኞች፤
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አሜሪካና ኢትዮጵያ ጡንቻ በመፈታተን ሳይሆን በዲፕሎማሲ አቅምና ተሰሚነት ረገድ ተመጣጣኝ በሚባል ክብደት ላይ ነበሩ። ዲፕሎማሲው ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚው የሚዘወርበት የብር ኖታችን ሳይቀር የዶላር እኩያ ሆኖ ይፎካከር ነበር። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ታላላቅ መድረኮች ላይ ሲገናኙም ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረው የከበሬታ ወንበር ከፊት ከሚደረደሩት መካከል ተመርጦ እንደነበር እናስታውሳለን።
በዘመነ ደርግ ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ የአሻንጉሊት መንግሥት ለማቋቋም ሴራ ስትጎነጉን የኖረችው በዓይኗ እንቅልፍ ሳይዞር ነበር። ተሳክቶላት ወጥመዷ መያዝ የጀመረው በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተስፋዬ ዲንቃ የሚመራው የልዑካን ቡድን “በአሜሪካ መንግሥት አሸማጋይነት” በሚል ሽፋን ከወያኔና ከሻዕቢያ ጋር ለመደራደር ሎንዶን በተገኘበት አጋጣሚ በሔራማን ኮኸን አማካይነት “ጨዋታው ከፈረሰና ዳቦው ከተቆረሰ በኋላ” ከጎሬው የወጣው ህወሓት/ኢህአዴግ የአራት ኪሎን መንግሥታዊ ስልጣን እንዲቆጣጠር ከተደረገ በኋላ ነበር።
ይህንንው ዕድል አሜሪካ “እንደተመኘኋት አገኘኋት” እያለች በመፈንጠዝ በሁለት ተኩል ዓሠርት ዓመታት ውስጥ በሀገራዊ ምርጫዎችም ሆነ በሉዓላዊነታችንና በራሳችን ዝርዝር ጉዳዮች ጭምር እንደምን ስትፈተፍት እንደኖረች ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው። ህወሓት መራሹ መንግሥት በፌዝ የተለበጠ የአሻንጉሊት ቅርጽ እንዲኖረው ሲውጠነጠኑ የነበሩትን ሴራዎች በዚህ አጭር የጋዜጣ ጽሑፍ ተንትኖ ለመጨረስ የገጹ ውስንነት ይገድበናል። በቅኝ አገዛዝና በአሻንጉሊት መንግሥት መገዛትን በእምቢታ ብቻ ሳይሆን በመጸየፍ ጭምር ራሱን አስከብሮ ለኖረው ሕዝባችን ምሥጋና ይድረሰውና የአሜሪካ አስተዳደር በተመኘውና በቃዠው ልክና መጠን ሙሉ ለሙሉ የአሻንጉሊት መንግሥት ለማቆም እጅግ ተፈትኖ ነበር።
የሰሞኑ ተባራሪ ወሬ ግን “ዓይኔን ሲያመው ጥርሴን አታስቀው” እንዲሉ በዚህው አሜሪካ ጎትጓችነትና አይዟችሁ ባይነት በሕዝብ ሉዓላዊ ድምጽ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስወግዶ የአሻንጉሊት ጥብቆ የደረበ የስደተኞች መንግሥት ለማቋቋም ዱለታ ላይ ናቸው ማለትን ከወሬኞቹ አፍና መንደር በስፋት ማድመጥ ከጀመርን ሰነባብቷል። የሃሳቡን ቅሌት ከፍ የሚያደርገው ደግሞ የአሻንጉሊቱን መንግሥት ለመቋቋም የተስፋ ካባ የተደረበላቸው የስደተኛ ግለሰቦች የማንነት ጉዳይ ነው።
“የምኞታቸውን መንግሥት” መሠረት እንዲጥሉ ከተመረጡት መካከል አንዱ “ስኳር በመቃም ወንጀል” ከርቸሌ ተወርውሮ ሲወጣ የመንፈሳዊነት ቅባት ተለቅልቄያለሁ ብሎ የመሰከረው የዘመነ ኢህአዴጉ ሁለተኛ ሰው የነበረው ምንትስ ነው። ሌላኛው ግለሰብም እንዲሁ በዘረፈው የሕዝብ ሀብት የጭነትና የነዳጅ ቦቴ መኪኖችን ለዘር ማንዘሩ ገዝቶ አከፋፍሏል ተብሎ በአብሮ አደግና በዱር አደር ጓደኞቹ ጥላ ተወግቶ የወህኒ ቤት ደጃፍን ተሳልሞ የወጣው በዘመኑ አይነኬ ከሚባሉት መካከል ግንባር ቀደም የነበረው ሰው ነው። ሦስተኛው ሰው ከአራት ዐሥርት ዓመታት በፊት ገና ከጅምሩ የበረሃ ሽፍትነት አንገሽግሾት ጓደኞቹን ከድቶ የፈረጠጠው የምላስና የብዕር ታጋይ ነኝ ባይ ግለሰብ ነው። አራተኛውና በአሻንጉሊት መንግሥት አዋላጅነት የታጨው የዘመነ ደርጉ ሹመኛና በወቅቱ በአሜሪካኖች ብብት ስር መግባቱ በሹክሹክታና በግብሩ ይታማ የነበረ ማዕረግተኛ ወታደር ነው።
እነዚህ አራት ግለሰቦችና በሥራቸው ያሰባሰቧቸው የሀገር ውስጥ ሠፈርተኞች የሴራው ዋነኛ ተዋናይ ሲሆኑ፤ በእነርሱ የሚደጎሙትና በስደት አደር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋሙት የሚዲያ ተቋማትም በአፈ ጉባዔነትና በፕሮፓጋንዳ ማሽንነት በትጋት እያገለገሏቸው እንደሆኑ እየተከታተልን ነው። ይህንን መሰሉን ወራዳ ምኞት ማሰቡ ምን ያህል ኮምጣጣውን ኢትዮጵያዊ ስሜት ይበልጥ እንደሚያጎመዝዝ ጨዋው ሕዝባችን በሚገባ ይረዳዋል።
ሀገሪቱን ከግራና ከቀኝ የቀሰፏትን ወቅት ወለድ ችግሮችን ሰበብ በማድረግ የሚተበተበው ይህን መሰሉ ሴራ ራሳቸውን ሴረኞቹን ጠልፎ ይጥላቸው ካልሆነ በስተቀር በክብሯና በኩራቷ በማትደራደረው ሀገር ላይ በፍጹም ሊጫን የሚችል ቅዠት አይደለም። ውርደትን እንደ እህል እያላመጡ መኖርን የሕይወታቸው መርህ ላደረጉት ለእነዚህ የቅብዥር ዓለም ቡድኖች መካሪ ዘመድ፣ ተቆጭ ወዳጅ ያስፈልጋቸዋልና “የቅርቤ” የሚሉት ወገን ከውድቅትና ከታሪክ ተወቃሽነት ቢታደጋቸው አይከፋም። ይህቺ ኩሩ ሀገር አንኳንስ ጠላቶቿ እንደሚመኙላት በአሻንጉሊት መንግሥት “ዕቃ ዕቃ ልትጫወት” ቀርቶ ፊት ለፊት የሞከሯት ጠላቶቿ በሙሉ እንደምን በሕዝባዊ ብርቱ ክንዷ ተደባይተው እንደተዋረዱ ታሪኳን ዞር ብለው ቢያስተውሉ እውነቱን ተረድተው በተጸጸቱ ነበር። በሀገራችን ወግና ባህል መሠረት በአሻንጉሊት የሚደለሉት ሕጻናት ብቻ ናቸው። ይህ እውነት አልገባቸው ከሆነ ታሪካችን በግልጭና በሹክሹክታ እውነቱን ይመሰክርላቸዋል። ጆሮ ያለው ይስማ፤ ህሊና ያለው ያስተውል። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013