በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ለዓመታት ሲታይ የነበረውን የቁልቁለት ጉዞ ከመግታት አልፋ አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች።ሀገሪቷ አዲስ ታሪክ ካስመዘገበችባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች አንዱ ቡና ነው። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 248 ሺህ 311 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ይፋ አድርጓል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በ2009 ዓ.ም ከተገኘው 882 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የ25 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው አስታውቋል። ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ከቡና ምርት ከፍተኛ የተባለውን የውጭ ምንዛሪ ያገኘችበት ነው፡፡
ሀገሪቱ ከቡና ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸው ይገለጻል፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ እንደሚሉት፤ መንግስት በወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎችና በተግባር የተተረጎሙ ስራዎች አማካኝነት የተገኘ ውጤት ነው። ከ2013 በጀት ዓመት የወጭ ንግድ አፈፃፀም ቡና አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ለዚህ ውጤት የበቃውም በመንግስት የተለያዩ ስራዎች በመሰራታቸው ነው። ከነዚህ ስራዎች መካከል የውል ምዝገባና አስተዳደር መመሪያ ስርዓት መዘርጋት፣ በህገ ወጥ ንግዱ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተፈጠሩ ቋሚ መድረኮች በዘርፉ የተሻለ ስኬት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ለምሳሌ የውል ምዝገባና አስተዳደር ስርዓትን ብንመለከት፤ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቋማት እንዲሁም በውጭ ንግድ ግብይት ሰንሰለት ተዋናዮችን በማሳተፍ የወጪ ንግድ ምርቶች የውል ምዝገባና አስተዳደር መመሪያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ከጥቅምት 2012 ዓ.ም አውጥቶ ከመጋቢት 2012 ጀምሮ በቡናና ሻይ ባለስልጣንም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የመመሪያው መተግበር የውል ምዝገባ ስርዓቱ የግብይት መረጃ ቋት እንዲደራጅ በማገዙ ላኪዎች የገቡትን ኮንትራት እንዲፈጽሙ ግልጽ የክትትል እና ቁጥጥር ስርዓትን በመፍጠር ኮንትራት አስመዝግበው የማጓጓዝ፣ ምርት ገዝተው በክምችት የያዙ፣ ምርትን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ በህገ ወጥ መንገድ የገበዩ እና ማንኛውም ከውጪ ንግድ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች በመመዝገብ ላኪዎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍና ክትትል ለማከናወን ማስቻሉን ነው ያብራሩት።
በተጨማሪም የውል አስተዳደር ስርዓቱ የምርቶች የሀገር ውስጥ የገበያ የግዥ ዋጋን ከዓለም አቀፍ ዋጋ ስሌት እና የሎጂስቲክስ ወጪ ጋር ተናባቢ እንዲሆኑ በማድረግ የትክክለኛ ላኪዎችን እና ሀገራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ከመቻሉም ባሻገር የወጪ ንግድ በራሱ አትራፊ የሚሆንበትን ስርዓት በመዘርጋት ህገ ወጥ ላኪዎች ከዘርፉ እንዲወጡ በማድረግና በውጪ ንግድ ዘርፍ ትርፋማ ለመሆን የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት ዘርፉ ራሱን ችሎ እንዲያድግ መንገድ ከፍቷል ፡፡
እንደ ወይዘሮ አበባ ማብራሪያ፤ ሀላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው የውል ምዝገባና አፈጻጸም ስርዓት መዘርጋቱ የሀገሪቱን የውል አተገባበር ገጽታን በአዎንታ በመገንባት የላኪዎችን ብሎም የሀገርን ተዓማኒነት በማጠናከር የሀገሪቱ የቡና ምርት በውጭ ገበያ ያለውን ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡
የውል ምዝገባ ስርዓቱ በቀደሙት ዓመታት የነበረውን ቡና ከገበያ ዋጋ በታች የመሸጥ አካሄዶችን በመቀየር ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ ማስቻሉ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ፡፡
ይህ ስርዓት መዘርጋቱ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች የሚላኩበት ሀገር የት ነው፣ የሚሸጥበት ዋጋ ስንት ነው፣ የተላኩት መቼ ነው፣ የትኛው ላኪ ነው ውድቀት ያጋጠመው፣ የትኛውስ ነው ስኬት እያስመዘገበ ያለው፣ ምን ያህል ምርቶችስ በቀጣይ ወደ ውጭ ሀገር ይላካል የሚሉትን ቀድሞ ለማወቅ ያስቻለ የአሰራር ስርዓት ስለሆነ ለስኬት ተጠቃሽ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
በሌላ በኩል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተፈጠሩት ቋሚ የግንኙነት መድረኮች በተለይም ከክልል መንግስታት ግብይትና ወጪ ንግድ ላይ ከሚሰሩ ቢሮዎች ጋር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከግብይት ተዋንያን ማህበራት ጋር የተፈጠሩ የቅንጅት መድረኮች ቡናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ለተመዘገበው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ወጪ ንግድ ገቢ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ብሎም እንዲያሽቆለቁል ካደረጉት ምክንያች አንዱ ህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት እንደነበር ያነሱት ወይዘሮ አበባ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች በተለይም ህገ ወጥ ንግድ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች በዘርፉ ለተመዘገበው እድገት ሚናው የላቀ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013