ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ለነፃነቷ፣ ለአንድነቷ እና ለእድገቷ መስዋዕትነትን የከፈሉና አስተዋፅዖ ያበረከቱ አያሌ ባለውለታዎች አሏት:: በእርግጥ ኢትዮጵያ ማንነታቸውና አገራቸው ለሆነችው ሰዎች ለነፃነቷ፣ ለአንድነቷ እና ለእድገቷ መስዋዕትነትን ቢከፍሉና አስተዋፅዖ ቢያበረክቱ ብዙም የሚያስገርም ላይሆን ይችላል:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያላደጉና የዘር ሀረጋቸውም ከኢትዮጵያ የማይመዘዝ ሰዎች ስለኢትዮጵያ ነፃነት ድምፃቸውን ሲያሰሙና በዋጋ የማይተመን አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ መስማት/ማየት አስደናቂ ነው:: እንግሊዛዊቷ ሲልቪያ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ነፃነትና እድገት ያበረከቱት አስተዋፅዖ የዚህ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል::
በሙሉ ስሟ ኤስቴል ሲልቪያ ፓንክረስት በመባል የምትታወቀው እንግሊዛዊቷ የሴቶችና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች፣ የፀረ-ፋሺስት ንቅናቄ መሪና ፀሐፊ የተወለደችው ሚያዚያ 27 ቀን 1874 ዓ.ም ነው:: የትውልድ ስፍራዋ ደግሞ በሀገረ እንግሊዝ፣ ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ነው:: ሚያዚያ 27 ኢትዮጵያ ከፋሺስት ኢጣሊያ የአምስት ዓመታት ወታደራዊ አገዛዝ ነፃ የወጣችበት ቀን ነው:: ሲልቪያ ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አገዛዝ እንድትላቀቅ ትልቅ ተሳትፎ ስለነበራት ቀኑ ለሲልቪያ የልደቷም ድካሟ ፍሬ አፍርቶ ያየችበትም በመሆኑ ሚያዝያ 27 ለሲልቪያ ትልቅ ትርጉም ያለው ቀን ነው:: ግጥምጥሞሹም አስገራሚ
ነው፡፡
አባቷ ሪቻርድ ማርስደን ፓንክረስት (ዶክተር) የሶሻሊዝም አቀንቃኝና የሴቶችን የእኩልነት መብት የሚደግፉ ታዋቂ የሕግ ባለሙያ ነበሩ:: እናቷ ኤመሊን ጎልደን ፓንክረስት ደግሞ ስመጥር የሴቶች መብት ተሟጋችና የማኅበረሰብ አንቂ ሲሆኑ ዝነኛውና አንጋፋው ‹‹ታይም›› (Time) መጽሔት እ.አ.አ. በ1999 ኤመሊን ፓንክረስትን ከመቶ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹እጅግ አስፈላጊና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች›› መካከል አንዷ አድርጎ ሰይሟቸዋል:: ‹‹የሴቶች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኅብረት (Women’s Social and Political Union – WSPU)›› የተባለው እንቅስቃሴ መስራችና የሌሎች ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች ጠንሳሽ የነበሩት ኤመሊን ፓንክረስት፣ እንግሊዛውያን ሴቶች በምርጫ የመሳተፍ መብት እንዲኖራቸው ካደረጉ ግለሰቦች መካከል ዋነኛዋ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል::
ሲልቪያ በማንቸስተር የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት (Manchester School of Art) የስዕል ትምህርት ተምራለች:: በመቀጠልም እ.አ.አ በ1900 ዓ.ም ወደ ለንደን የሮያል የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት (Royal College of Art) በማቅናት ተጨማሪ ትምህርት መማር ችላለች:: እ.ኤ.አ በ1902 ዓ.ም የሞዛይክ ስነ ጥበብ (Mosaic) ለማጥናት ወደ ኢጣሊያ፣ ቬኒስ ከተማ ሔዳ እንደነበርም ታሪኳ ያስረዳል::
እ.አ.አ ከ1906 ጀምሮ እናቷ ኤመሊን ፓንክረስት ያቋቋሙትን ‹‹የሴቶች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኅብረት›› የተባለውን እንቅስቃሴ በመቀላቀል ከእናቷና ከእህቷ ጋር መስራት ጀመረች:: ሲልቪያ የተማረችውን የስዕል ትምህርት በመጠቀም የእንቅስቃሴውን ዓላማዎች በስዕል ለማሳየትና ለማስረዳት ጥረት አድርጋለች:: እ.አ.አ በ1907 በእንግሊዝና በስኮትላንድ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ከተሞችን በጎበኘችበት ወቅት በየከተሞቹ ከነበሩ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጋር መገናኘትና መወያየት ቻለች:: ይህም ከእናቷና ከእህቷ ጋር የጀመረችው እንቅስቃሴ በእንግሊዝና በስኮትላንድ የተለያዩ ከተሞች እንዲታወቅና እንዲስፋፋ አጋጣሚውን ፈጥሯል:: ኤሚ ቡል ከተባለች እንግሊዛዊት የሴቶችና መብት ተሟጋችና መምህርት ጋር በጋራ በመሆን የኅብረቱን የምስራቅ ለንደን ፌዴሬሽን (East London Federation of the WSPU) መሰረቱ:: በወቅቱም ሲልቪያ የኅብረቱ ልሳን በሆነውና ‹‹ቮትስ ፎር ውመን›› (Votes for Women) በተባለው ጋዜጣ ላይ ጽሑፎቿን ታሳትም ነበር::
ሲልቪያ በወቅቱ ለሴቶች እኩልነት ሲታገሉ እንደነበሩት ሌሎች ሴቶች ሁሉ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጋለች:: እ.አ.አ ከየካቲት 1913 እስከ ነሐሴ 1914 ዓ.ም ድረስ ለስምንት ጊዜያት ያህል ለእስራት ተዳርጋለች:: በእስር ቤትም የረሀብ አድማ ታደርግ ነበር::
ሲልቪያ ‹‹የሴቶች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኅብረት›› ጋር ግንኙነት ያለውና ከሴቶች መብቶች ባሻገር ስለሌሎች ጉዳዮችም እንዲታገል መፈለጓና ‹‹ኅብረቱ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ አካሄዶች መታቀብ አለበት›› የሚለው አቋሟ ከሌሎች የኅብረቱ አባላት ጋር ሊያስማማት አልቻለም:: እ.አ.አ በኅዳር 1913 አየርላንድ፣ ደብሊን ውስጥ ከተፈጠረው የሰራተኞችና የቀጣሪዎች አለመግባባት ጋር ተያይዞ ያራመደችው አቋም ከኅብረቱ ጋር ተጨማሪ አለመግባባት እንዲፈጥሩ መንስዔ ሆነ:: በዚህም ምክንያት ሲልቪያ ‹‹የሴቶች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኅብረት›› ከተባለው እንቅስቃሴ ጋር ተለያየች:: እ.አ.አ በ1914 ‹‹የምስራቅ ለንደን የሴቶች መብት ፌዴሬሽን››ን አቋቁማ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረች:: የፌዴሬሽኑን ልሳን (‹‹Women’s Dreadnought››) የመሰረተችውም ራሷ ነበረች:: ይህ ፌዴሬሽን በየጊዜው ስሙንና አደረጃጀቱን እየቀያየረ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል:: ለአብነት ያህልም ‹‹የሴቶች መብት ፌዴሬሽን›› እና ‹‹የሰራተኞች ሶሻሊስታዊ ፌዴሬሽን›› የሚሉ ስያሜዎችን በመቀያየር በሲልቪያ መሪነት ለሴቶችና ለሌሎች ጭቁን የማኅበረሰብ ክፍሎች መብት መከበር ታግሏል::
ፌዴሬሽኑ የሚሊዮኖችን ሕይወት የቀጠፈውንና ግዙፍ የንብረት ኪሳራ ያደረሰውን የአንደኛውን የዓለም ጦርነት በፅኑ አውግዟል:: ባሎቻቸው በጦርነቱ ሲሳተፉ የነበሩ የወታደር ሚስቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለአገሪቱ መንግሥት በተደጋጋሚ አሳውቋል:: ጦርነቱ ሥራ አጥ ያደረጋቸውን ሴቶች ለማገዝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል::
እ.አ.አ በ1915 በዘ ሄግ ለተካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ኮንግረስ (International Women’s Peace Congress) ሲልቪያ ትልቅ ድጋፍ አሳይታለች:: ይሁን እንጂ ይህ አቋሟና እንቅስቃሴዎቿ ከእህቷ ጋር በሃሳብ እንዲቃረኑ ያደረጉ የታሪክ አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል:: ሲልቪያ በየጊዜው ወደ ኮሚኒስት እሳቤ እየተሳበች መጣች:: ለአብነት ያህልም ‹‹የሰራተኞች ኮሚኒስት ፓርቲ›› የተባለ የፖለቲካ ቡድን መስርታ ነበር:: ከዚህ ባሻገርም ‹‹የብሪታኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ›› ከተባለ የፖለቲካ ቡድንም ጋር በጋራ ሰርታለች:: በሩስያ፣ በሆላንድና በሌሎች አገራት በተካሄዱ የኮሚኒስቶች ስብሰባዎች ላይም ተሳትፋለች:: የኮሚኒዝም እሳቤ ትኩረቷን ቢስበውም ከሌበር ፓርቲ (Labour Party) መስራቹ ኬይር ሃርዲ ጋርም የቅርብ ግንኙነት ነበራት::
ሲልቪዮ ኮሪዮ ከተባለ ጣሊያናዊው ጋር ግንኙነት መስርታ እ.አ.አ በ1927 ዓ.ም ሪቻርድ የተባለ ወንድ ልጅ ወለደች:: ይህ ልጅ በኋላ የኢትዮጵያን ታሪክ በማጥናትና በማስተማር ልክ እንደእናቱ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኬይር ፔቲክ ፓንክረስት ነው::
ከተገፉና ከተበደሉ ወገኖች ጎን መቆም መገለጫዋ የሆነው ሲልቪያ፣ እ.እ.አ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ደግሞ የፀረ-ፋሺዝምና ፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎችን መደገፍ ጀመረች:: ወቅቱ ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ የተወረረችበትና ‹‹ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ውጭ አገር ሄደው በውጪ ዓለም ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ትግል ያድርጉ፤ለአርበኞችም እርዳታ እንዲገኝ ያደርጋሉ …›› በሚል ሃሳብ ንጉሰ ነገሥቱ የኢትዮጵያን ስሞታ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations)ና ለኃያላን መንግሥታት ለማሰማት በስደት እንግሊዝ ስለነበሩ የኢትዮጵያን የነፃነትና የሉዓላዊነት ትግል መደገፍ ጀመረች::
የፋሺዝም መሪው ቤኒቶ ሙሶሊኒ ዓላማ፤ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብ፤ ሲልቪያ ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች በመጻፍና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሔድ በጊዜው የነበረው የዓለም መንግሥታት ማህበር በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ወረራ እንዲታደግ ከፍ ያለ ጥረት አድርጋ ነበር። ለእንግሊዝና ለሌሎች መንግሥታት እንዲሁም ለሃይማኖት መሪዎችና ለታላላቅ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የአቤቱታ ደብዳቤዎችን በመጻፍ በኢትዮጵያ ላይ ስለተቃጣው የፋሺስት ወረራ ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ አሳስባ ነበር። የፋሺስት ኢጣልያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ኢትዮጵያም መከላከል እንድትችል የመንግሥታቱ ማኅበር በጋራ ደህንነት ግዴታው መሠረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ከመጠየቋም በላይ፤ ፋሺዝም ለዓለም ጠንቅ የሚያመጣ ስርዓት መሆኑን አስገንዝባ ነበር።
‹‹ኢትዮጵያ የባሪያ ንግድ ስርዓት አራማጅ ናት›› በማለት ፋሺስቶች ያሰራጩት የነበረውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ተቃውማ እንዲጋለጥ አድርጋለች። ፀረ-ፋሺስት አቋም የነበራቸውን አፍሪካ-አሜሪካውያንን እንዲሁም የሙሶሊኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣልያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ ለማድረግ ጥራለች። በጊዜው በለንደን የኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጻሚ ከነበሩት ከዶክተር ወርቅነህ እሸቴ ጋር በመተባበርና ከእቴጌ መነን ጋር ደብዳቤ በመጻጻፍ በኢትዮጵያ በኩልም ስለነበረው ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ታደርግ ነበር። ለኢትዮጵያ ነጻነት የምታደርገውን ትግል እንዲያግዙ ታዋቂ ከነበሩ የእንግሊዝ ምሁራንና የፓርላማ አባላት ጋር በቅርበት ሰርታለች።
በወቅቱ ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ወደ እንግሊዝ አብረው ሄደው ከነበሩት ከዶክተር መላኩ በያንና ሌሎች ግለሰቦች ባገኙት መረጃ በ1928 ዓ.ም ‹‹New Times and Ethiopia News›› የተሰኘ ጋዜጣ አቋቋመች:: በጋዜጣውም ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲኖር ብዙ ተግባራትን አከናውናለች:: የፋሺስት አስተዳደር በአዲስ አበባ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ሕዝብ በመጨፍጨፍ የፈፀመው የጦር ወንጀል በይፋ እንዲታወቅ አድርጋለች:: የዓለም መንግሥታት ማሕበር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በሚወያይበት ወቅት ጄኔቫ ድረስ በመመላለስ መልእክተኞቹን በማነጋገር ኢትዮጵያ ለጊዜው በኢጣልያ ብትወረርም የማኅበሩ አባልነቷ እንደተጠበቀ እንዲቆይና ሌላ ድጋፍም እንድታገኝ ከፍ ያለ ጥረት አድርጋለች:: እነዚህ ሁሉ የሲልቪያ ጥረቶችና የኢትዮጵያውያን አርበኞች እልህ አስጨራሽ ትግል ፍሬ አፍርተው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በ1933 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ::
ሲልቪያ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ትግል በኢጣሊያ መባረር ብቻ አልተገደበም:: የፋሺስት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ከተወገደ በኋላ እንግሊዝ የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ /ሞግዚት ለመሆን የሸረበችውን ሴራ ሲልቪያ ተቃውመዋል:: ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድም ደጋግማ አስገንዝበው ነበር:: ከፀረ-ፋሺስት ትግሉ ባሻገር የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሻሻልና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በአገራቸው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር የሚያሳስብ ደብዳቤ ለቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ
ጽፈዋል፡፡
በ1948 ዓ.ም ሲልቪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግብዣ ቀረበላቸው:: እርሳቸውም ግብዣውን ተቀብለው ከልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መኖር ጀመሩ:: ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ የአገሪቱን አካባቢዎች ተዘዋውረው በመጎብኘትና ‹‹Ethiopia Observer›› የተሰኘ ጋዜጣ በማቋቋም ሌላው ዓለም ስለኢትዮጵያ እንዲያውቅ አድርገዋል:: የልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲቋቋም ገንዘብ በማሰባሰብ ሥራ ተሳትፈዋል:: ሲልቪያ በሕይወት ዘመናቸው ከጻፏቸው ሃያ መጽሐፍት መካከል ስምንቱ በኢትዮጵያ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ሥልጣኔ ቀሪው ዓለም ግንዛቤ እንዲገኝ አድርገዋል። ሲልቪያ ለኢትዮጵያ ነፃነትና እድገት ራሳቸው ካበረከቱት በዋጋ የማይተመን ወደር የለሽ አስተዋፅዖ በተጨማሪ፤ ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪፓርድ ፓንክረስትና የልጅ ልጆቻቸውም ኢትዮጵያን ያለመታከት እንዲያገለግሉ ምክንያት ሆነዋል።
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴም ለሲልቪያ ፓንክረስት በጻፉት ደብዳቤ ለእርሳቸው የነበራቸውን ከፍ ያለ የአድናቆትና የውለታ ስሜት ገልጸውላት ነበር። ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ተጠምቀው ‹‹ወለተ ክርስቶስ›› የሚል ስመ ክርስትና አግኝተዋል:: የኢትዮጵያ ባለውለታዋ ሲልቪያ ፓንክረስት በተወለዱ በ79 ዓመታቸው መስከረም 17 ቀን 1953 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አርፈዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ንጉሳውን ቤተሰቦች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በትልቅ ክብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
ንጉሰ ነገሥቱ በሲልቪያ ስርዓተ ቀብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹…ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ለማገልገል ቆርጠው ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ያደረጉት የሀሳብና የሥራ ተጋድሎ ሰፊ የታሪክ መስመር የያዘ ነው:: ምኞታቸውና እምነታቸው የማይበገር የምሪት ምሽግ ነበር:: የመንፈሳቸው ጽናት በፊታቸው የተጋረደውን እንቅፋት አስወግዶ ለማለፍ የተለየ ሥልጣን ነበረው:: የኢጣሊያ ፋሺስት ጦር በዓለም መንግሥታት የተከለከለ የመርዝ ጢስ እየጣለ ሰላማውያኑን ሕዝብ ሴቱንና ሽማግሌውን ሕጻኑን ለመጨረስ ስለተነሳ ይህን ግፍ ለዓለም ሸንጎ ለማሰማት ወደ ጄኔቭ መሄዳችንን ሲከታተሉ የቆዩት ሚስስ ሲልቪያ፣ ‹በዓለም ላይ ከዚህ የባሰ ምን በደል ይደርሳል?› በማለት ለእውነተኛው ፍርድ በመቆርቆር ተነሱ … ፋሽስቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለ ፍርድ ፈጁት:: ሚስስ ፓንክረስትም የጽሑፍና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እያሰባሰቡ ‹ዓለም ይህን ሰምቶና ዐይቶ ካልፈረደ ለራሱ ወዮለት› እያሉ ጮኹ:: የኢትዮጵያን አርበኞች ተስፋ ለማስቆረጥ ፋሽስቶች በመርዝ ጢስና ቦምብ ያደረጉባቸውን የጭካኔ ውጊያ ሴቱንና ሕጻኑን ያለ ምክንያት እየሰበሰቡ በመትረየስ መፍጀታቸውን ማስረጃ አቀረቡ:: ሚስስ ፓንክረስት በባሕርያቸው እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት ሲታገሉ፣ የዚች ጥንታዊ አገር ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ እንዲሁም የሕዝቦቿ ጀግንነትና ፍቅር እየማረካቸው ሄደ:: ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ ጋር በፍቅር የወደቁት ሲልቪያ ፓንክረስት፣ ለሀገራቸው ነፃነትና አንድነት ክቡር ሕይወታቸውን ከከፈሉት የኢትዮጵያ አርበኞች የሚደመሩ ናቸውና በዚህ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያርፉ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ሆኗል …›› ብለዋል::
በወቅቱ የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አንዳርጋቸው መሳይ በበኩላቸው ‹‹… ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ገና ብዙ ለማገልገል ከፍ ያለ ምኞት ስለነበራቸው በዛሬው ቀን የቀጠሩን እዚህ ሳይሆን ሌላ ስፍራ ነበር:: በእውነት እላችኋለሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ፣ ግፍና ስደት አልቆ ውጤቱ እስኪደርስ ድረስ ሚስስ ሲልቪያ የሠሩት ሥራ በሽማግሌ ጉልበታቸውና ላባቸው ብቻ ሳይሆን ጤናቸውን እስኪያጡ፣ ርስታቸውን ሽጠው እስኪደኸዩ፣ በግል ገንዘባቸው ጭምር ለኢትዮጵያ የሠሩ ሰው ናቸው:: ስለዚህ ታላቋ እንግሊዛዊት ሚስስ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ እውነተኛዋ ኢትዮጵያዊ አርበኛ መባል የሚገባቸው ናቸው…ወዳጃችን ሲልቪያ ፓንክረስት ሆይ 25 ዓመት ሙሉ ያለ ዕረፍት የዕድሜዎን ሸክም ሳያስቡ በእውነትና በታማኝነት የረዱዋቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ሕዝብ አሁን በዙሪያዎ ቆመው ያለቅሱልዎታል:: ወዳጆችዎ አርበኞችና ስደተኞች እዚሁ ባጠገብዎ ቆመዋል:: ያንንም የመከራ ዘመን ያስባሉ:: ታሪክዎ ከታሪካቸው በደም ቀለም ተጽፎ ሕያው ሆኖ ይኖራል:: እርስዎም በዚች በኢትዮጵያ ምድር ላይ በሰላም አርፈው እንዲኖሩ የግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ ስለሆነ እንደኢትዮጵያዊት ዜጋ ቆጥረን በክብር እናሳርፍዎታለን:: እግዚአብሔር በምድር ላይ ሳሉ የሠሩትን በጎ ሥራ ሁሉ ቆጥሮ በሰማይ ቤት የክብር ቦታ እንዲያድልዎ እንመኛለን ›› በማለት ነበር ታላቋን የኢትዮጵያ ባለውለታ በጥልቅ ሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው የተሰናበቷቸው::
የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ የነበሩት እንግሊዛዊቷ የፀረ-ፋሺስት ንቅናቄ መሪ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ጸሐፊ ኤስቴል ሲልቪያ ፓንክረስት፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋእትነት፤ ያሳዩት ፍቅርና ክብር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነው::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም