ገና ከጠዋቱ በለጋነት ዕድሜው በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ባልጠና የልጅነት አቅሙ ከእናትና አባቱ ቤት ጀምሮ በሥራ ተጠምዷል። በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ካሉት አጎቱ ቤት በኖረበት ጊዜ ሁሉ የተለያዩ የሥራ ጫናዎችን መቋቋም መቻሉ ለዛሬ ብርታቱ ስንቅ ሆኖታል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሥራና በሥራ ብቻ ያደገው ወጣት ዛሬ ላይ ለመድረሱ የትናንት ትጋቶቹ ህያው ምስክሮች ናቸው። በአጎቱ ቤት ሲኖር የከብቶች አዛባን ከመጥረግ አንስቶ ከከብቶች ጋር ያለውን ሂደት በሙሉ በትጋት ማለፍ ችሏል።
ከዚህ ባለፈም በአጎቱ ጋራጅ ቤት ውስጥ ሲያገለግል የተመለከቱት ደንበኞች መካኒክ አልያም ባት ላሜራ ይሆናል ብለው ነበር። ከአጎቱ ቤት ወጥቶ ቤት ተከራይቶ በኖረበት ጊዜ የህይወትን ሌላኛውን አስከፊ ገጽታ ተመልክቷል። ከጋራጅ የሚያገኘው ደመወዝ ለቤት ኪራይ፣ ለምግብና ለትምህርት ቤት ክፍያ ሳይዳረስለት ሲቀር ጾሙን ያደረበትና ደረቅ ዳቦ በስኳር የተመገበበት ጊዜም ነበር። ይሁንና ችግሮችን ተቋቁሞ ለመኪና ቅርብ ሆኖ መሥራት መቻሉ ለዛሬው ስኬት እርሾ ጥሎለት አልፏል።
ከልጅነት እስከ ወጣትነት ዕድሜው እነዚህንና መሰል ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ ዛሬ ላይ ውጤታማ በመሆን ከራስ አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው አቶ ዘላለም መርአዊ የዘላለም አስጎብኚና የጉዞ ወኪል እንዲሁም የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማንፋክቸሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ነው።
በአምቦ ከተማ ተወልዶ፤ ታሪካዊና የቱሪስት መስህቦች የሆኑ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን በያዘችው አዲስ ዓለም ያደገው አቶ ዘላለም፤ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው አምቦ ከተማ መወለዱ እንዲሁም አዲስ ዓለም ከተማ ማደጉ አካባቢዎቹ የቱሪስት መዳረሻ ስለመሆናቸው በመረዳት ዘርፉን እንዲቀላቀል አስችሎታል። ከዚህ ባለፈም በልጅነት ዕድሜው የሽቦ መኪና የመስራት ዝንባሌው እንዲሁም አዲስ አበባ በአጎቱ ጋራጅ ውስጥ መስራቱም አግዞታል።
አቶ ዘላለም እነዚህን ዕድሎች በማቀናጀት እራሱን የመቻልና ቤተሰቦቹን የማገዝ ጥልቅ መሻት ሊፈጽም የስኬት ጉዞውን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ። በ18 ዓመቱ መንጃ ፈቃድ ያገኘው አቶ ዘላለም፤ ሹፍርናን ጋራጅ ውስጥ በነበረው ቆይታ በሚገባ ተለማምዷል፡ በወቅቱ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀ ቢሆንም እራሱን ለማሻሻልና ቤተሰቡን ለማገዝ ካለው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ትምህርቱን አቋርጦ የአጎቱን መኪና በመያዝ በመንገድ ሥራ ድርጅት ውስጥ ገብቶ ለመስራት ሱማሌ ክልል አቅንቷል። ለአራት ዓመታት ያህልም በሱማሌ ክልል በሚገኙ እጅግ ገጠራማና በረሃማ በሆኑ ቦታዎች ተዘዋውሮ በአሽከርካሪነት አገልግሏል።
በዚህ ወቅት ታድያ የወር ደመወዙን 300 ብር ሲሆን አበል የሚከፈለውን 50 ብር በድምሩ የሚያገኘውን 350 ብር በአግባቡ ተጠቅሞ ጥሪት ማጠራቀም ችሏል። አቶ ዘላለም፤ በወጣትነት ዕድሜው ለምንም አይነት ሱስ ተገዢ ሳይሆን ለአራት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በመንገድ ሥራና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ አሻራውን ማኖር ችሏል።
በዚህ ጊዜ ውስጥም 70 ሺ ብር መቆጠብ በመቻሉ የሩቅ ህልሙን ዕውን ማድረጊያ ጊዜው ሆነና ይሰራበት የነበረውን የአጎቱን መኪና የዋጋውን ግማሽ ክፍያ ከፍሎ መግዛት ቻለ። የጀመረውን የኪራይ ሥራ አጠናክሮ በመስራትም በአንድ ዓመት ውስጥ የመኪናውን ዕዳ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ መኪናውን የራሱ አደረገ። የቱሪዝም ዕውቀትና ፍላጎትን ይዞ ያደገው አቶ ዘላለም፤ ቱሪዝም ውስጥ የመግባት ፍላጎቱን ዕውን ማድረግ እንዲያስችለው መኪናውን ለሾፌር ሰጥቶ በአስጎብኚ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ታድያ በማታ የትምህርት ክፍለ ጊዜ የቱር ኤንድ ኦፕሬሽን ሱፐርቪዥን ትምህርቱን ተከታትሎ በማጠናቀቁ ቱሪዝም ምንድነው የሚለውን መረዳት ቻለ።
ከዚህ በኋላ ዘላለም አስጎብኚና የጉዞ ወኪል በሚል የራሱን ድርጅት ከፈተ። የመኪና ኪራይና አስጎብኚነቱን እየሰራ ደንበኞቹን እያበራከተ በመምጣት የመኪኖቹን ቁጥር ከአንድ ሁለት ከሁለት ሶስት እያለ 11 በማድረስ የሥራ ዕድሉንም በዛው ልክ እያሰፋ ሄዶ 18 ለሚደርሱ ሰራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር በዘርፉ ለ14 ዓመታት ቆይቷል። በ14 ዓመታት ቆይታውም ዘርፉን ይበልጥ የማወቅና የመረዳት አጋጣሚውን በማግኘቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ የሚል የቱሪስት ጋይድ መጽሐፍ እና መጽሔት እኤአ በ2014 አሳትሞ በመላው ዓለም እንዲሰራጭ አድርጓል።
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅና ቱሪስቱን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ካለው ተነሳሽነት በመነጨ ፍላጎት ነው። በመሆኑም በዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽኦና ለነበረው ጥሩ አገልግሎት ከሀገር ውስጥ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ከተበረከተለት ሽልማት በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችም ሽልማት ማግኘት የቻለ ሲሆን ለአብነትም ከሲውዘርላንድ ጄኔቫ ያገኘው የወርቅ ሽልማት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።
አቶ ዘላለም፤ የሥራ ዕድል ከፈጠረላቸው ሰራተኞች መካከል በድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አምስት ሰራተኞች ቢሮ በመክፈት እራሳቸውን ችለው የአስጎብኚ ድርጅት እንዲኖራቸው አድርጓል። ለሶስት ሰራተኞችም እንዲሁ ይሰሩበት የነበረውን የድርጅቱን መኪና በረጅም ጊዜ ክፍያ እንዲወስዱት በማድረግ እራሳቸውን እንዲችሉ ደግፏል። በዚህ መልኩ ጠንክሮ የቀጠለው ዘላለም አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ካለፉት አራትና አምስት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ እየታየ የመጣው ግጭት ዘርፉን ክፉኛ በመጉዳቱ አቶ ዘላለምም ከዘርፉ ሊወጡ ተገደዋል።
ቱሪዝም በባህሪው ፍጹም ሰላምንና መረጋጋትን የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑ በተለይም በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በነበሩ የህዝብ አመጽና ግጭቶች ቱሪዝሙ ሙሉ ለሙሉ እንደቆመ ያስታወሱት አቶ ዘላለም፤ በዚህ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ታወጁ በዚህ ምክንያት ቱሪስቶች አይገቡም። ቀጥሎም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም መከሰቱን ተከትሎ ዘርፉ በማይታመን ደረጃ ወደቀ።
በዓለም በተከሰተው ወረርሽኝና በሀገሪቱ በተፈጠረው ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት መሰረት ይዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ ሲዳከም እጁን አጣጥፎ ያልተቀመጠውና የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን ሲያጠና የነበረው አቶ ዘላለም፤ እራሱን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ፊቱን ወደ ቆዳ ኢንዱስትው አዞረ። በመሆኑም ሁለት ሴት ሙያተኞችን እንዲሁም በየቤታቸው ሆነው መስራት ለሚችሉ 10 ዜጎች መስፊያ ማሽን፣ ቆዳና መለዋወጫዎች በማቅረብ ዲዛይን እየሰጠ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት ጀመረ።
የዛሬ አምስት ዓመት በሁለት ሴት ሙያተኞች የተቋቋመው ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ በአሁኑ ወቅት 60 ለሚደርሱ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከእነዚህም መካከል 48 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ስምንት አካል ጉዳተኞችም የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ማለት በጉራጊኛ ቋንቋ መልካም ነገር ሰላም በኢትዮጵያ ይታይ ማለት ነው።
አካል ጉዳተኞች አዕምሯቸው ብሩሀ በመሆኑ ለሀገር ዕድል እንደሆኑ የሚያምነው አቶ ዘላለም፤ የመሥራት ዕድሉ ከተመቻቸላቸው ተአምር በመስራት ሀገርን መለወጥ እንደሚችሉና አቅም ችሎታ እንዳላቸው ያምናል። ይህን በማመኑም ከውጭ ሀገራት ጭምር የተለያዩ በፋሽን ዲዛይን ዕውቀት ያላቸውን አሰልጣኞች ከጣልያን፣ ከአሜሪካና ከቻይና ስፖንሰር በማፈላለግና በራሳቸው ወጪ በማምጣት ስልጠና እንዲያገኙ አድርገዋል። በዚህም ሽመናን ጨምረው በርካታ የእጅ ሥራዎችን እያመረቱ ይገኛሉ።
በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው የተዛባ አመለካከት ዘርፉን ለመቀላቀል ያዳገታቸው ቢሆንም ችግሮቹን ተቋቁሞ የተለያዩ የወንድና የሴት ቦርሳዎች፣ ሻንጣዎች፣ ቀበቶ፣ ጫማና ወንበር ጠረጴዛዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የአመራረት ዘዴዎችን በመከተል እያመረተ ይገኛል። ምርቶቹ የሚሸጡትም በሀገር ውስጥ በሚገኙ ስድስት ሱቆች ሲሆን፤ አምስቱ በአዲስ አበባ ከተማ የውጭ ዜጎች በሚገኙበት አካባቢ ሲሆን አንዱ ኩሪፍቱ ፓርክ ይገኛል።
አንድ ድርጅት ጠንካራ የሚባለው በችግር ጊዜ ያሉትን ሰራተኞች ይዞ በመቆየት አማራጮችን በማምጣት በችግር ውስጥ መፍትሔ መፍጠርና ድርጅቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ሲችል መሆኑን የሚያምነው አቶ ዘላለም፤ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት አንድም ሰራተኛ ሳይቀንስ እንዲያውም ሌሎች የቀነሷቸውንና ጥሩ የማምረት አቅም ያላቸውን ዜጎች በመቅጠር ጭምር በአሁኑ ወቅት እየሰሩ ይገኛል።
ከኮቪድ በኋላ በርካታ የገበያ እድሎች ዓለም ላይ እንዳሉ የሚያምነው አቶ ዘላለም፤ የተለያዩ ፋብሪካዎች በዓለም የተዘጉ በመሆናቸው የምርት እጥረት ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ እድል የሚሰጥ በመሆኑ የተለያዩ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ይቻላል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅትም ያለቀለትና ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ የቆዳ ምርት የሆኑ የተለያዩ ምርቶችን አምርቶ የውጭ ገበያውን እየተጠባበቀ መሆኑን ይናገራል።ኮቪድ 19 ከመከሰቱ አስቀድሞ ምርቶቹን አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት ችሏል።
የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች ወደ ውጭ ሀገር ገበያ ሳይላኩም በሀገር ውስጥ ባሉት ሱቆች የውጭ ምንዛሪ ለሀገሪቷ እያስገባ የሚገኝ ሲሆን፤ ከሁሉም ሱቆች በየወሩ እስከ 20 ሺ ዶላር መሰብሰብ ችሏል። የቆዳ ውጤቶቹ በሙሉ የውጭ ገበያን ታሳቢ በማድረግ የሚመረቱ በመሆናቸው ምርቶቹን በውጭው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራሁ ነው የሚለው አቶ ዘላለም፤ በጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ አፍሪካ ላይ የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ ብራንድን ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ይጠቅሳል ። በቅርቡም አሜሪካን ሀገር የሚከፈተውን ሱቅ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነው። በአሜሪካ የኢትዮጵያ ምርት ብቻ የሚገኝበት ሱቅ የሚከፈተው አሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሆነና የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ ድርሻ ደግሞ 50 በመቶ እንደሆነ አቶ ዘላለም አስረድቷል።
በቀጣይም ጣልያን፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ የሚከፈት ይሆናል። ለዚህም በቂ ምርቶች ተመርተው የሱቆቹን መከፈት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ ከሌሎች የሚለየው በርካታ የቆዳ ውጤቶችን የቢሮና የመኪና መቀመጫዎችን ጨምሮ ሶፋዎችንም ከቆዳና ከእንጨት ኢትዮጵያዊ በሆኑ ግብዓቶች ብቻ ማምረት በመቻሉ ነው። ይህም በኢትዮጵያ የተመረተ የሚለውን ስም ማሳደግና ለውጭው ዓለምም ማስተዋወቅ አለብን የሚል እሳቤን ይዞ እያመረተ ይገኛል።
የምንኖርባት ዓለም የቅንጦት እንደመሆኗ ሰዎች እጅግ ዘመናዊ ነገር ሲያደርጉ የቆዳ ውጤቶችን ተጠቅመው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሰፊ የቆዳ ሀብት ቢኖርም በልኩ መጠቀም አለመቻሉ የሚያስቆጨው አቶ ዘላለም፤ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እሴት እንዲጨመር ማድረግ ይገባል። ዘርፉ ረጅም ሰንሰለት ያለው በመሆኑ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ነው። በተለይም ለአካል ጉዳተኞችና ለሴቶች ትልቅ የሥራ አማራጭ በመሆን ሀገርን መለወጥ ይችላሉ። በቀጣይ የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ ይሄንኑ አጠናክሮ የመቀጠል ሀሳብ አለው።
ኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ በቀጣይ ዓመት ከ200 እስከ 300 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ምርቶቹን በስፋት በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ለዚህም ከመንግሥት ባገኘው ድጋፍ ጭምር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የመሸጫ ቦታ አግኝቷል። በዚህ ቦታ ላይ ከ12 ሚሊዮን የሚልቁ ተጓዦች በመኖራቸውም ትልቅ ገበያ ይፈጠራል። ይህም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው በጎ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
በግል ጥረቱ ዓላማውን ማሳካት የቻለው አቶ ዘላለም፤ ወጣቱ በማያገባውና በማይገባው ቦታ ላይ ከመዋል ተቆጥቦ ሀገሪቷ ያላትን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች በመጠቀም እራሱን መለወጥና ሥራ ፈጣሪ መሆን ይችላል። ኢትዮጵያውያን መስራት እንችላለን፤ አቅም አለንና እንሥራ ሀገራችንን እንለውጥ በማለት ባስተላለፉት መልእክት አበቃን።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013