ሴቶች ን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከምንጫቸው በማድረቅ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።
በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አማካኝነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ምሁራን ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል።
የምክክር መድረኩም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማስፈን በሚጫወቱት ሚና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
ለአንድ ቀን የሚካሄደው የውይይት መድረክ ዋነኛ አላማ ሴቶች ጥረውና ግረው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡ በሃላ ትምህርታቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ አጠናቀው ለምረቃ እንዳይበቁ በሚያደርጋቸው ተግዳሮቶች ላይ ምክክር በማድረግ የመፍትሄ አማራጮችን በማፈላለግ የድርጊት መርሃ ግብር መዘርጋት ነው።
ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ሴቶችን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከምንጫቸው በማድረቅ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴት ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸው ድርሻ በቅድመ ምረቃ 34 በመቶ፣ በሁለተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር 17 በመቶ እንዲሁም በዶክትሬት ድግሪ ደረጃ 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።