
አዲስ አበባ ፦ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ሰብዓዊ ችግር ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው ሽብርተኛው የህወሓት አመራር ብቻ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ አስታወቁ።
ዶክተር አረጋዊ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ ጁንታው ቡድን እንኳን አሁን ህዝቡ በዚህን ያህል ስቃይ ውስጥ ገብቶ ይቅርና ለውጡን አልቀበልም ብሎ ከኮበለለበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰቱ ለነበሩ ቀውሶችም ሆነ አሁን እየተፈጠረ ላለው እልቂት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው እርሱ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ሽብርተኛው የጁንታው ቡድን የህዝቡ መቸገር መራብ ምንም ጉዳዩ ባለመሆኑ እርዳታ የጫኑ 169 ከባድ መኪኖች አፋር ክልል ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ጥቃት ከፍቷል ፤ይህ ተግባሩ የሚያሳየው ቡድኑ ለህዝቡም ለአገርም ጠንቅ መሆኑንና የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ ነው ብለዋል።
ህዝቡ በጦርነትም ይሁን በረሃብ እየተሰቃየ ባለበት በዚህን ጊዜ የእርዳታ መግቢያ መስመርን መዝጋት ወይም ጥቃት ለመፈጸም መነሳት ከፍተኛ የሆነ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ከመሆኑም በላይ አካባቢውን ሁሉ በሱ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ እንዲታመስ ሆን ብሎ ያቀደውና የፈለገው ነገር ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ ይህ ደግሞ ህዝቡም ሊገነዘበው ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ሁሉ ሊያዩትና መፍትሔ ሊሰጡት የሚገባ እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት ወደ ተቸገረው የትግራይ ህዝብ እርዳታ ለመላክ እንዲሁም በቀጣይ የግብርና ስራውን ሰርቶ ከተረጂነት እንዲወጣ ለማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከተለያዩ ለጋሽ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች ወደ ክልሉ እንዲጓዙ በማድረግ ላይ ነበር፤ ነገር ግን ህዝቤ ለሚለው አካል እንኳን ምንም ግድ የሌለው የጁንታው ቡድን እርዳታው በታሰበው መንገድ ወደ ክልሉ እንዳይደርስ ማድረጉ ምንም ኃላፊነት የማይሰማው ጨካኝ መሆኑንም የሚያሳይ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
ሽብርተኛው ቡድን ህልሙ በኢትዮጵያ 27 ዓመት እንዲሁም ትግራይ ላይ 30 ዓመት በስልጣን የቆየበትን ጊዜ መልሶ ለማምጣት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ የህዝብ መራብም መጠማትም ማለቅ ለእሱ ጉዳዩ አይደለም ዓላማው እንዲሳካ ነው ጥረት እያደረገ ያለው ብለዋል።
ሽብርተኛው ህወሓት እጅግ በጣም መሰሪ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ለህዝብ አሳቢ በመምሰል ህዝቡ ተጎዳ ፣ሞተ ፣ተራበ እያለ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ወሬዎችን ያወራል ያሉት ዶክተር አረጋዊ ፣ ይህን የሚያደርገው ለህዝቡ አስቦ ሳይሆን በህዝቡ ስም የራሱን ጥቅም ለማመቻቸት መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አለም አቀፍ አጋር አካላት የሚባሉቱ ከፍተኛ የሆነ አድሏዊነት ያለባቸው በመሆኑ ነገሮችን እንዳላወቁ እያለፉ ከመሆኑም ባሻገር ባለፉት ጊዜያትም ከዚህ ሽብርተኛ ቡድን ጋር እጅና ጓንት ሆነው በጥቅም ተሳስረው ሲሰሩ ነበር ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ በቀጣይም ይህ ሁኔታ እንዲደገምላቸው ስለሚፈልጉ አሸባሪውን ቡድን ከመደገፍ የዘለለ ተግባር እያከናወኑ አይደለም፤ ወደፊትም የሚያደርጉ አይመስለኝም ብለዋል።
ከአሁን በኋላ ማንኛውም አጋር አካል የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቅሬታ የሚያቀርብበት ምንም መሰረት የለም፤ ምክንያቱም በእያንዳንዱ ነገር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት እንደሚያደርጉት ሁሉ ጁንታው ቡድን በሚሰራቸው ስራዎች ላይም ግፊት ማድረግ ነበረባቸው ፤ ግን ይህንን እያደረጉ አይደለም፤ በመሆኑም እነዚህ አካላት ስለ ጉዳዩ ያገባናል ካሉ መንግሥት ላይ ሳይሆን ጫና ማሳደር ያለባቸው ጁንታው ቡድን ላይ ብቻ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የውጭ ኃይሎቹ የሚፈልጉትን አይነት ተላላኪ መንግሥት ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ማየት እንደማይችሉ ሊገባቸው ይገባል፤ በመሆኑም የትግራይን ህዝብ ማዳን አለብን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ለእውነትና ስለ እውነት ብለው አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብም እነዚህን የጥፋትና የመገንጠል አላማ ያነገቡ ጁንታ ቡድኖችን በመታገል ከወንድም እህቶቹ የትግራይ ህዝቦች ጎን መቆም እንዳለበትም አመልክተዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013