በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተራዝሞ የቆየው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ምርጫም ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
በዚህ መሰረት ፓርቲው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገሪቱን የመምራት ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ሆኖም የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐብይ አሕመድ በተደጋጋሚ እንደገለጹት በምርጫው ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ በመሆኑም ፓርቲው በዚህ መንፈስ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ከፍ ለማድረግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት አለው፡፡
እኛም በተለይ ፓርቲው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሕዝብ የጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ምን አቅዷል፤ ምንስ ኃላፊነት ይጠበቅበታል በሚሉና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ጋር ቃለምልልስ አድርገን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን፦ በቅድመ ምርጫ 2013 ወቅት የነበረው ድባብ ምን ይመስል ነበር እንደ ብልጽግናስ ምን ተሰርቶበት ታለፈ?
ዶክተር ቢቂላ፦ የቅድመ ምርጫውን ወቅት ከተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ወደኋላ ሄዶ ማገናኘት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ምርጫው በአንድ ጀምበር የመጣ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህልውና የማስቀጠል፣ ከአገርና ከሕዝብ አንድነትና ህልውና ጋር የተያያዘ ታሪካዊ አመጣጥ ያለው ምርጫም መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በጣም ካልተሳካልን ነገሮች አንዱ ዴሞክራሲን በእውነትና ስለ እውነት መሬት ማስያዝና ባህል ማድረግ ነው። በዚህም መንግሥታት እንዲሁ በጉልበትም በሴራም ሲቀያየሩ ነው የኖሩት፤ ይህ ደግሞ ደም መፋሰስን፣ የሰላም የዴሞክራሲ እጦትን፣ ጥርጣሬን እና የዜጎች ሰቆቃን አምጥቶብናል። በመሆኑም ዜጎቻችን እፎይ ብለው የሚኖሩት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እዚህ አገር ላይ መትከል ከቻልን ብቻ ነው በማለት የዛሬ ሶስት አመት በፊት ለውጥ እንዲመጣ ሆነ።
ለውጡም መቋጫው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አድርገን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ስልጣኑን ይዞ የሚመራበትን ሥርዓት በማምጣት አካታች፣ አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓትን እንድንለማመድና ባህል እንድናደርግ ያስፈልጋል ተብሎ ለሕዝብ ቃል በተገባው መሰረት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም በሚገባ ተሳታፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
በተለይም በለውጡ እንቅስቃሴ ወቅት የተገባው ቃል ሲባሉ የነበሩ ነገሮች ለዓለም ሕዝብም በደንብ ይፋ ሲደረጉ የነበሩ ነገሮች እጅግ በጣም ትልቅ ትርጉም ያላቸው ነበሩ፤ በመሆኑም በዚህ ምክንያት ተስፋቸው የለመለመ ብዙ አካላት ነበሩ፤ ለምሳሌ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እናቶች አባቶች በጣም ተስፋቸው ከለመለሙትና አገራችን በቃ አሁን ገና ቀና ልትል ነው ብለው ትልቅ ተስፋ የሰነቁበት ውስጥ ይመደባሉ። እነዚህ ሁሉ ተስፋዎች ደግሞ ምንጫቸው በወቅቱ የነበረው ቃል ሲሆን መቋጫው ደግሞ ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫ ነበር።
ከዚህ አንጻር ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ ብዙ አካላትን ያሳተፈ እንዲሆን በገለልተኛ ተቋማት የሚመራ ለማድረግ ለኢትዮጵያውያንም የሰነቁትን ተስፋ እውን የሚያደርግ እንዲሆን እንዲሁም በውጭ ወዳጆቻችንም ሆነ ጠላቶቻችን ዘንድ መልዕክት የሚያስተላልፍ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርገን መምራት አለብን በሚል እቅድ አውጥተን ነው ወደ ምርጫ ሥራው የገባነው።
በመሆኑም የቅድመ ምርጫው እንቅስቃሴ ወደኋላ ሶስት አመት ሄዶ ግብዓቶች፣ ሀሳቦች የሚወስድ፣ የሕዝብ ቃል ኪዳኖችን የሚወስድና ቃል ኪዳናችንን እንዳንበላ በሚያስችል ደረጃ መታቀድ አለበት ተብሎ የተሰራ ሥራ ነው። በዚህ ምክንያትም እንደ ፓርቲ ሁለት ትልልቅ ግቦችን ይዘን ነው እቅዱን ያወጣነው፤ አንደኛው ግብ ለሕዝብ በአደባባይ ወጥተን ቃል በገባነው መሰረት ነጻ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ እናድርግ፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ጫና ወጥቶ በሰላም ምርጫውን የሚያደርግበትን ነባራዊ ሁኔታ እንፍጠርና ኢትዮጵያ ወደመልካም የዴሞክራሲ ጎዳና እየተጓዘች ነው የሚል ለእኛም ለሌላውም መልዕክት በሚያስተላልፍ ሁኔታ እንስራ ብለን ተነሳን፡፡ በዚህ መሰረትም ቅድመ ምርጫው፣ የምርጫው እለት እንዲሁም ከዛ በኋላ የነበሩ ነገሮች ሁሉ ለሕዝብ እፎይታን የሰጡ ሆነው አልፈዋል።
ሁለተኛው ግብ ደግሞ ፓርቲ እንደመሆናችን እንደ ሌሎቹ ሁሉ የራሳችን ፕሮግራም፣ ሀሳብ፣ ማኒፌስቶ እንዲሁም ለሕዝባችን የምናቀርባቸው መልካም ነገሮች ስላሉን እነሱን ወደ ሕዝብ የማቅረብ ሥራ ሰርተናል። እነዚህን ግቦች አስቀምጠን መንቀሳቀሳችን ደግሞ ጠንካራ የሆነ ቅድመ ምርጫ እቅድ አውጥተን በተለያዩ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲጸድቅ አድርገን ከታች በክልል፣ በዞንና በወረዳ ያሉ መዋቅሮቻችን ይህንን ጉዳይ ተረድተው የራሳቸው እንዲያደርጉ እንዲሁም እቅዱን በአደራና በኃላፊነት ስሜት እንዲመሩት አድርገን ወደ ምርጫ ገባን።
ይህም ቢሆን ግን እንደ ፓርቲ ትልቅ ትኩረትና ኃላፊነት ወስደን የሰራነው ለአንደኛው ግባችን ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ላይ እየታየ ያለው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይደበዝዝ ወደኋላ እንዳይመለስ ሰዎች ከጉልበት ይልቅ ድምጼ ዋጋ አለው ብለው እንዲያምኑ ከደም መፋሰስ ይልቅ ሀሳቤን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት ብገልጽ ይሻላል ብለው እንዲያምኑ፤ ከዚህ በኋላ ወደአደባባይ ወጥቶ ደም መፋሰስና ጎማ ማቃጠል ያን ተያይዞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማሽመድመድ ንብረት መጥፋት፣ ህይወት ማጣት ቀርቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያዋጣን ምርጫና ምርጫ ብቻ ነው ብሎ እንዲያምን የሚያስችል ምርጫ ተካሂዷል ብለን ነው የምናምነው፤ በዚህ መንገድም ነበር ስንመራ የነበረው።
የብልጽግና አመራር እንዲሁም ሌሎችም በዚህ መንፈስ እንዲንቀሳቀሱም ስናደርግ ነበር ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ካሸነፈች ፓርቲያችንም ስለሚያሸንፍ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንኳን ሕዝቡ ድምጹን ቢነፍገን ነገ ሊያገኝ ስለሚችል መጀመሪያ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገን እንስራ በማለት ነበር የሰራነው፤ በዛም ተሳክቶልናል።
ያ በአገሪቱ ላይ ይታይ የነበረ ቆፈን፣ የመጠፋፋት ፖለቲካ ከላያችን ላይ መገፈፍና መቅረት አለበት ብለን ነው የመራነው ፡፡ ምርጫው በዚህ መልኩ እንዲሄድ ሰነድ አዘጋጅተን ሥልጠና ሰጥተን የምርጫ ቅስቀሳ ስትራቴጂና ቴክኒክ አዘጋጅተንና ለሁሉም እንዲደርስ አድርገን መራነው። በዚህም በጣም በተሳካ ሁኔታ የቅድመ ምርጫው እንቅስቃሴ ሁለቱን ግቦች ይዞ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንና የፓርቲውን ወዳጆችና ደጋፊዎች አሳትፎ የተከናወነ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን የምርጫው ውጤት የተነገረበት ወቅት ላይ ነንና ውጤቱን እንዴት አዩት፤ እንደዚህስ አይነት ውጤት ጠብቃችሁ ነበር?
ዶክተር ቢቂላ ፦ አንደኛ ነገር የእኛ ትልቁ ትኩረታችን የነበረው አገራችን ከፓርቲም ከእኛም በተለይም ስለ አገሪቱ እናውቃለን ከሚሉም ሰዎች በላይ በመሆኗ ይህ እንዳይንሸራተት ብዙ ጥረት አድርገናል። ይህ ውጤት የተገኘውም ከላይ እንደ ግብ ካስቀመጥናቸው ሁለት ነገሮች፤ በተለይም የመጀመሪያው ላይ ትኩረት አድርገን በመስራታችን ነው። አይታችሁ እንደሆነ በቅድመ ምርጫ ወቅት ስንሰራው የነበረ ስራ በሙሉ ለዚህ ውጤት መምጣት የራሱን አስተዋፅዖ አድርጓል ብለን ነው የምናስበው፤ለምሳሌ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መሳደብ ማንጓጠጥ ሌላውን ዝቅ ማድረግ ጥላሸት መቀባት በእኛ አመራሮችና አባሎች ዘንድ በፍጹም ሊደረግ አይደለም ሊታሰብ እንደማይገባ ተነጋግረን ተማምነን ነው ወደ ስራ የገባነው፤ ምክንያቱም እኛ ስለ ጥሩ ነገር ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ እናውራ፣ ስለ አገራችን፣ ስለ ሕዝባችን መልካም ነገር እናውራ፤ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፤ ብለን ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ሕዝቡ በጣም በጥንቃቄ ያዳምጠው ነበር፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ በሚፈለገው ደረጃ በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመብዛት ይልቅ በጣም ጠንክረው ወጥተው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር አገር ለመምራት የሚያስችል ድምጽ የሚያገኙበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ምኞትና ፍላጎት ነበረን። ይህ ግን ወደፊትም መሰራት ያለበት የቤት ስራችን ነው።
ይህንን ዓይነት ውጤት ይመጣል ብላችሁ አስባችሁ ነበር ወይ ? ለተባለው በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጠው ድምጽ በጣም አስደንግጦናል። አንደኛ ነገር ሕዝቡ እጅግ በጣም በርካታ ነገሮችን እንደሚያይ፣ እንደሚያገናዝብ፣ እንደሚታዘብና አርቆም እንደሚያስተውል አሳይቷል። ምን ያህል ቁጭ ብሎ ለሰላም፣ ለአብሮነት ለአንድነትና ለኢትዮጵያና ለአገር ቀጣይነት ትኩረት እንደሚሰጥ በሚያሳይ መንገድ መልዕክት አስተላልፏል። ይህ ውጤት የመጣው ከዚህ አንጻር ነው ብዬ አስባለሁ፤ አንዳንድ ቦታ ላይ እንደውም እኛ ከሰራነውና ካደረግነው በላይ ወደፊት ልንሰራና ልንፈታ የምንችለውን ችግር አይቶ ድምጽ የሰጠን የሚመስል በጣም በርካታ ነገር አለ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያውን ውጤት ይፋ ባደረገው መሰረት ብልጽግና ፓርቲ ያገኘው ውጤት በጣም ከፍተኛ ነው፤ ይህ ድምጽ ለፓርቲው መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ብቻ ሳይሆን 47 የተፎካካሪ ፓርቲዎች በተሳተፉበት መድረክ ላይ ለፓርቲው የተሰጠው ድምጽ ትልቅ መሆኑንም የሚያሳይ ነው። ይህ ሕዝቡ የሰጠው ድምጽ እውነት አምኖ ደስ ብሎት ከዚህ በፊት በሰራነው ሥራ ረክቶ ነው ወይ የሚል በርካታ ጥያቄም ውስጣችን እንዲፈጠርና ቆም ብለን እንድናሰብ ያደረገን ነው።
ሁለችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው ተስፋ ያደርጋል መንግሥትም የሚያደርጋቸውን ጥረቶችና መፍጨርጨሮች ያያል፤ ከዚህ በፊት የጠፉትን ጥፋቶች ሁሉ አሁን ላይ እንካስበታለን ብሎም ያስባል፤ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር አነጻጽሮ ደግሞ ለሰላም የሚሰራ ኢትዮጵያውያንን በአንድ አምጥቶ ሁሉንም አቅፎና ደግፎ ወደ አንድነትና አብሮነት የሚወስድ ፓርቲ እንደሆነም ተገንዝቧል፤ ከምንም በላይ ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሰሩ ስራዎችን አይቷል፤ የመጡ ውጤቶችንም ተመልክቷል፤ በመሆኑም ይህንን ያህል ድምጽ ለመስጠት የቻለው በእነዚህና ተያያዥ ምክንያቶች ይመስለኛል።
በመሆኑም ይህ ከሕዝቡ የተገኘው ድምጽ አደራም ሸክምም ነው። በፓርቲ ደረጃ ቁጭ ብለን ምን ማለት ነው? ብለን ተንትነን አይተነዋል ፤ ሕዝቡ ከፓርቲው ምን ጠብቆ ነው በዚህን ያህል ድምጹን የሰጠው? የሚለው ጥናት ሁሉ ይደረግበት እስከማለት ደርሰናል፤ የምርጫው ዕለት ሕዝቡ ጸሐይ ዝናብ ሳይል ራበኝ ቤቴ ልግባ ሳይል ከሌሊቱ 11 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 7 ሰዓት ድረስ ተሰልፎ ድምጹን መስጠቱ ከፓርቲው የሚጠብቀው ምናልባትም እንደ ፓርቲ ያሰብነው ነገር ሁሉ ሊኖር ይችላል ለማለት ነው የተገደድነው፤ በመሆኑም ቀጣይ ከሕዝቡ ጋር በቅርበት መወያየት፣ ፍላጎቱን ማወቅ፣ ይፈታልኛል ብሎ በፓርቲው ላይ እምነት የጣለባቸውን ነገሮች መፈታታቸውን እያረጋገጡ መሄድና ውስጣችንን መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያመላክትም ድምጽ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ የሕዝቡ ከፍ ያለ ደምጽ እንዳሉትም ትልቅ ሸክም ነውና እንደው ሕዝቡ በሰጠው ደምጽ እንዳይቆጭ ይልቁንም ደስተኛ እንዲሆንና መሰረታዊ የሚላቸው ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ለማድረግ ምን አቀዳችሁ?
ዶክተር ቢቂላ፦ ሕዝቡ በጣም ያስተውላል፣ ያስባል፤ አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ሰላምን፣ ልማትን፣ የተረጋጋ አገርን፣ አብሮነትን ችግሮቹ ተፈተውለት እፎይ ብሎ መኖርን ለልጅ ልጆቹ የሚያስተላልፋት የተረጋጋችና ችግሮቿ የተፈቱላት አገርን ይፈልጋል፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ ምን ያህል ዝግጁ ነው ? ይህንን የሕዝቡን መፈለግና መሻት ሊያሳካ በሚችል ቁመና ላይ ይገኛል ወይ? የሚለውን ቆም ብለን ማሰብ አለብን።
የውጭ ኃይሎች አንደኛ ቅድመ ምርጫው ላይ ብጥበጥ ይነሳል፤ ስለዚህ ምርጫ ማካሄድ አይችሉም፤ በምርጫው እለትም ቢሆን ብጥብጥ ይነሳል እያሉ በነበረበት ከምርጫው ማግስትም እነዚህ ሰዎች ሰላም አይሆኑም፣ ይፈርሳሉ እያሉ በሚጠብቁበት ሁኔታ ሕዝቡ ቅድመ ምርጫውንም በጥንቃቄ ወጥቶ ተመዝግቦ የምርጫው እለትም ሌሊቱን ሙሉ ተሰልፎ ያስተላለፋቸው መልዕክቶች ከብልጽግና ፓርቲ የሚጠብቀው ነገር እጅግ በጣም ትልቅ መሆኑን ያሳየበት ነው።
ስለዚህ እንደ ፓርቲ ለዚህ ሕዝብ ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ውይይት ማድረግ ጀምረናል፤ ከዚህ አንጻር ፓርቲው የሕዝብን አደራ የማይበሉ ይልቁንም ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት የሚችል ሆኖ መውጣት አለበት፤ ለዚህም የአባላትና የአመራሮችን አቅም በሚገባ የመገንባት ሥራ የመስራት በዚህም ሕዝቡን በእውቀት በክህሎት በሥነ ምግባር ማገልገል የሚችሉ ማድረግ፤ በዚህም ፓርቲው ለሕዝብ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ማስቻል፤ የሚሉት ነገሮች በትኩረት የሚሰራባቸው ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን እንመሰርታለን፤ በመሆኑም የተቋማት ግንባታ ትልቁ ሥራችን ይሆናል ማለት ነው። ይህ የተቋማት ግንባታ ሥራ አንደኛ ለሕዝብ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ጠንካራ የሆኑ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መመስረት በጣም አሰፈላጊ ነው። በመሆኑም በመስከረም ወር የሚመሰረተው መንግሥት የሕዝብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በብቃት ሊፈታ የሚችል እንዲሆን ከወዲሁ ሥራ ተጀምሯል።
ሕዝቡ ለዘመናት ያልተፈቱ የሰላም የመሰረተ ልማት የልማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄ አለው ከብልሹ አሰራርና ከሙስና ጋር የተገናኙ በርካታ ችግሮች አሉበት ፡፡ እነዚህን በሙሉ ሊፈታ የሚችል የሕዝብን የልብ ትርታ አዳምጦ ለዛ የሚሆን ወቅታዊና ተጨባጭ መፍትሔ የሚሰጥ አካሄዱን አመራሩን በውጤት የሚለካና ቅቡልነት ያለው መንግሥት መመስረት ላይ ከአሁኑ ከፍተኛ የሆነ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን።
ይህ በጣም ወሳኝ ሆኖ ሳለ እንደ አገር ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያስተላለፉልን መልዕክት አለ ፡፡ ይኸውም ጠንካራ ኢትዮጵያ መገንባት አለባት የሚል ነው፤ እንደ አገር እንዳንቀጥል የሚፈልጉ ከፋፋይና የሚበታትኑ አስተሳሰቦችን በሚገባ አስተካክለን ጠንካራ ብዝኃነትን በሚገባ ያቀፈች የጋራ ማንነት፣ ስሜትና አገራዊ ስነ ልቦና የሚያዳብሩ ነገሮች ላይ በጋራ መስራት አለብን።
ይህ በጣም ትልቅ ስራ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ሰዎች ኢትዮጵያን ሳይሆን ብሔራቸውን ብቻ ከዛም ወረድ ብለው መንደራቸውን ብቻ ከዛም በጣም ዝቅ ብለው ዞናቸውን ከዛም ወረዳቸውን እንደውም በከፋ ሁኔታ ቀበሌያቸውንና ሰፈራቸውን እያሰቡ እንዲኖሩ እንዲሰሩ አልፎም እንዲመሩ ተደርጎ ነው የኖረው። ይህ ደግሞ የጋራ ነገር እንዳይኖረን የአገር ህልውናን የሚፈታተኑ ነገሮች እንኳን ሲያጋጥሙን በጋራ እንዳንቆም አድርጎን ቆይቷል፤ እነዚህን ለቃቅመን ኢትዮጵያውያን የብሔር የሃይማኖት ብዝኃነት ቢኖረንም ያንን ባቀፈ ሁኔታ ግን አገራዊ ማንነታችን ጠንክሮ እንዲወጣ የሚያደርግ ሥራ ይኖራል።
ለዚህ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ፕሮግራሞች ይኖሩናል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም አገራዊ ማንነት በብዝኃነት ውስጥ የደመቀች ተደርጎ ይገነባል ማለት ነው። እንደ ብልጽግና ራዕያችንም በብዝኃነት ውስጥ የደመቀች ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ነው።
ፓርቲው ግን እነዚህን ነገሮች ሲያቅድ ወይንም ደግሞ ጠንካራ ቅቡልነት ያለውና የሕዝቡን ችግር የሚፈታ መንግሥት ማቋቋም ሲባል አገራዊ ማንነትና የአገረ መንግሥት ግንባታ ሲባል ፓርቲው ዝም ብሎ ብቻውን በር ዘግቶ የሚሰራው አለመሆኑም መታወቅ አለበት። ፓርቲ አንድ ተቋም እንደመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በሚገባ ማሳተፍና በጋራ መስራት ያስፈልጋል ፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ ለዚህ ሁኔታ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቃል ገብቷል። በመሆኑም የሕዝብን ችግር ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥብቅ ቁርኝትና በጋራ ስሜት እንሰራለን።
ይህ ደግሞ አሁን በሚመሰረተው መንግሥት ውስጥም ሆነ ከዛ በኋላ በሚሰሩ ሥራዎችና ፕሮግራሞች ላይ ተፎካካሪ ፓርቲው አልያም ሌሎች ሲቪክ ማህበራት እንዲሁም የዚህች አገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ቁጭ ብለው ሥራና ኃላፊነትን ተከፋፍለው በጋራ ስሜት አንድ ላይ የሚሰራ ይሆናል ፡፡ እስከ መስከረም ድረስም ለዚህ የሚሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከነወኑ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፦ ብልጽግና በመጪው መስከረም መንግሥት እስከሚመሰረት ድረስ ደግሞ በአገሪቱ ላይ የሚስተዋሉ የውስጥም የውጪም ችግሮች አሉ፤ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የገጠመን ችግር አለና እነዚህን ነገሮች እንዴት እየሄደባቸው ለመቆየት ነው ያሰበው ?
ዶክተር ቢቂላ፦ ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ እንደምናስተውለው ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሆነ ማንነት ያላት አገር ናት፤ ቀና ብሎ መሄድ የሚችል ሕዝብ ያላት፣ በቅኝ ግዛት ባለመገዛቱ ምክንያት የግል ኑሮውን እራሱ በከፍተኛ የራስ መተማመን ስሜት የሚመራ ሕዝብ ያለባት አገር ብትሆንም አገሪቱ ላይ የሚቃጡ የማሽመድመድ ደካማ እንድትሆን ችግሯን በራሷ መፍታት እንዲያቅታት በውስጥ የቤት ስራዎች ተተብትባ የሕዝቧን ጥያቄ መፍታት የማትችል እንድትሆን የሚደረጉ ሙከራዎች ለዘመናት አብረውን የኖሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ መልካም እድሏ የተፈጠረችው በጣም ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ነው፤ ለጎረቤት አገራትም ሆነ ለቀጠናው ሁሉ ትኩረት ሳቢ ናት፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ የተለያዩ አገሮች ለራሳቸው ፍላጎት ሲሉ የሚመኟት አገርም ናት። ጠንካራ የተረጋጋ በሁለት እግሩ የቆመ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር አይፈለግም። በመሆኑም ጣልቃ ገብነቶቹ በጣም በርካታ ናቸው። እነዚህን ጣልቃ ገብነቶች መፍታት የምንችለው እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም ኃይል ቢሆን በህልውናችን ላይ ከመጣ አንድ ነን ብሎን መቆም ስንችል መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ያምናል። የውጭ ጫና መቼም ላይቆም ይችላል ፤መልሱ ግን ሕዝቡ በዚህኛው ምርጫ ወጥቶ እንዳሳየው አይነት አንድነትን ማሳየት ነው።
የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት ለማላላት የውጭ ኃይሎች የሚጠቀሙት ውስጣችን ያለ ክፍተትን፣ ድክመትን፣ አለመደማመጥንና አለመናበብን እዚህም እዚያም ያለን ቅሬታዎቻችንን ተጠቅመው ነው ሊያፈርሱን የሚፈልጉት፤ በመሆኑም በአሁን ሰዓት ይህንን ያልተገነዘበ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም ፡፡ በመሆኑም በሰሜን እንደሚታየው አይነት የተለያዩ የውስጥ አካላትን ተጠቅሞ በድንበር አካባቢ የአገርን ሉዓላዊነት ለመፈታተን የሚደረግን ሙከራና የውስጥ መስተጋብራችን ተዛብቶ በጋራ ነገሮቻችን ላይ ሳንቆም እንዲሁ ስንባላ እንድንኖር የሚደረገው ሙከራ የውስጥ ኃይሎችንም እንደተላላኪ የመጠቀም አቅጣጫ አለው ማለት ነው።
ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር በአብዛኛው የውስጥ ጥቃቅን ቡድኖችና ኢትዮጵያን ለማፍረስና ፍርስራሿን ተጠቅመው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ቅንጅታዊ አሰራር እንዳለበት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያምናሉ። ይህም ስለገባው ነው ሕዝቡ ቀኑን ሙሉ ለምርጫው ድምፅ ለመስጠት ተሰልፎ የዋለው።
ይህ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ውጫዊ ማሸበርና ማስፈራራት ቢኖርም እኛ የውስጣችን ጉዳይ የራሳችን ነው አንሰማችሁም በማለት ውጤቱን ያሳያቸው፤ ይህንን ደግሞ ከምርጫውም በኋላ ባሉ ሌሎች ሁነቶች ሊደግመው ይገባል።
በሰሜንም ሆነ በሌሎች ቦታዎች እዚህም እዚያም የሚታየውን የውስጥን አንድነት የሚጎዳ ነገር ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆ ብለው ወጥተው ከዚህ ጀርባ ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን አደብ ማስገዛትና አይሳካላችሁም የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ያለባቸው ከመሆኑም በላይ በምርጫ ወደ ሥልጣን ያወጣውን የራሱን መንግሥት ደግሞ እያረመ እየገሰጸ የውስጡን ችግር በራሱ እየፈታ ለውጭ ኃይሎች በር ሳይከፍት በዚሁ አቋሙ መቀጠልም አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ እንዳትቀጥል፣ እንድትፈራርስ እየጣሩ ካሉ ኃይሎች መካከል ህወሓት አንዱ ነው፤ ይህ ቡድን የጀመረውን አገር የማፍረስ ስራ ከአማራ ጋር እንዳለ የድንበር ችግር እያስመሰለ ይገኛልና በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አልዎት?
ዶክተር ቢቂላ ኢትዮጵያን የተፍረከረከች ደካማ እንድትሆን የሚፈልጉ በጣም በርካታ የውጭ አካላት አሉ፤ በጣም የሚያሳዝነው እንደ ህወሓት ያሉ አሸባሪ ቡድኖች ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ታክቲካል የሆነ ቁርኝት አድርገው መልዕክት ተቀብለው የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚ እስከመሆን የደረሰ ሥራን በመስራት ላይ መሆናቸው ነው።
አገሪቱ ላይ ሰላም መረጋጋት እንዳይኖር በሕዝቦች መካከል የወንድምና እህትማማችነት ስሜት እንዳይኖር ሕዝብ እንደ ሕዝብ በአይነ ቁራኛ እንዲተያይ የሚያደርግ እጅግ በጣም ኃላፊነት የጎደለው የስግብግብ ስራ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን ነው ።
ይህ ቡድን አብሮ የኖረን ሕዝብ ጭምር ስትራቴጂካሊ የማጋጨት አካሄድን የሚከተል በጣም መሰሪ ቡድን ነው። ህወሓት አዎ ችግሩን የድንበር ለማስመሰል የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ ነው፤ ነገር ግን ይህ አይደለም ጉዳዩ፤ ጉዳዩ ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ ኃላፊ መሪ ሆኜ እንደፈለኩ ካልበዘበዝኩና ካልፈነጨሁ አገር መፈራረስ አለባት እንጂ አገር ሆና መቀጠል የለባትም ነው መልዕክቱ፤ ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንዲገነዘቡት እንፈልጋለን ።
ህወሓት የሕዝብ ደም መጦ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሕዝብና አገር እንዳንቀጥል አባልቶ በመንደር ከፋፍሎ ሕዝብ የመበታተን አደጋ ላይ ከጣለ በኋላና ሕዝብም እኛ እህትና ወንድማማቾች ነን፣ በዚህ መንገድ መቀጠል አትችልም፤ ብሎ ነቅሎ ካወጣውና ይህንንም ማዕበል ሸሽቶ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ከተደበቀ በኋላ እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ መፍረስና መበተን አለባት እንጂ መቀጠል የለባትም የሚል አጀንዳ ነው የሚያራምደው።
ህወሓት በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ቡድን ወይንም ፓርቲ ሆኖ የማይቀጥልበት ጊዜ ይመጣል፣ ሕዝቡም ይህንን እንደሚያደርገው ምንም ጥያቄ የለውም፤ በመሆኑም የአማራም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ኢትዮጵያን ሊያፈራርስና በፍርስራሿ ላይ የሚፈልገውን ነገር ሊያደርግ የመጣ ኃይል በመሆኑ ቡድኑን ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና ታሪክ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ለአገር ህልውና እጅ ለእጅ ተያይዘን ማጥፋት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ በስሙ የሚነግድበት የትግራይ ሕዝብስ የህወሓትን መሰሪ ስራዎች እንዲረዳ ብሎም ከሌሎች ከእህትና ወንድሞቹ ጋር እንዳይጣላ ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?
ዶክተር ቢቂላ፦ ህወሃት ገና ቡድን ሆኖ ጫካ ሲገባ ጀምሮ በጣም ታሪካዊ የሆነ መሰሪ ተግባር ሰርቷል፤ ይህም ሕዝብን እንደ ሕዝብ ፈርጆ ነው የገባው፤ ይህ ነገሩ ደግሞ 47 ዓመት ሙሉ አብሮት አለ። ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ ይሁን የጦር መሪ ብቻ በአጠቃላይ ሁሉም ፖለቲከኛ ከሕዝብ በታች ነው፤ ፓርቲ ይመሰረታል ይፈርሳል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመጣሉ ፍላጎታቸውን አሳክተው ይሄዳሉ፤ ሕዝብ ግን በቋሚነት ይኖራል ፤ ይህንን የፈጣሪን ፍጡር ስም ጠርቶ ፈርጆ መነሳት ግን እጅግ በጣም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው።
የዛሬ 47 ዓመት በፊት ጠንስሶ የተነሳበትን መሰሪ ተግባር ደግሞ እስከ አሁን ሕዝቦችን ከሕዝቦች ጋር ለማቃረንና ለማጣላት እየተጠቀመበት ይገኛል ፤ይህ በጣም ከባድ ታሪካዊ ክህደት ነው ብዬ አስባለሁ።
የትግራይ ሕዝብ ደግመን ደጋግመን እንደምንለው እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹ ያልተፈቱለትና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖር ነው። እንደውም አንዳንድ ቦታ ላይ ያለበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፈተና ከሌላው ኢትዮጵያዊ ክፍል በባሰና በወረደ ሁኔታ የሚሰቃይ ነው። ይህንን ደግሞ ዓለም ያውቀዋል ፤ነገር ግን ጁንታው ቡድን 47 ዓመት ሙሉ በዚህ ምስኪን ሕዝብ ይነግዳል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን መገንዘብ ያለብን ይህ ቡድን ያመጣብን ሕዝብን ከሕዝብ ፈርጆ የማጋጨትና በቁርሾ እንዲተያይ የማድረግ የ 47 ዓመት ሴራ ዛሬ ላይ እንዲበቃ ማድረግና መንቃት ነው። ከሚነቁት ሕዝቦች መካከል ደግሞ ዋናውና ግንባር ቀደሙ የትግራይ ሕዝብ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት እንግዲህ አሁን ላይ በተለይም ህጻናትን ለጦርነት እያሰለፈ ይገኛልና በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ቢቂላ፦ አሸባሪ ቡድን እኮ ምንም ርህራሄ ሰብዓዊነት የውስጥ ቅንነት አርቆ አስተዋይነት ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ እይታ ለሕዝብ አዘኔታ የለውም። በእነዚህ ምክንያቶች ደግሞ እጅግ በጣም ለሰብዓዊነት የሚከብዱ ተግባራትን ይፈጽማል። ከእነዚህም መካከል በጣም ለማየት በሚዘገንን ሁኔታ እንኳን ስለ ፖለቲካና ስልጣን ቀርቶ ስለሚበሉት ስለሚለብሱት ምንም የማያውቁ፣ ገና ከእናታቸው ጉያ ሥር ያልወጡ፣ ግራ ቀኙን አይተው ማገናዘብ የማይችሉ፣ ሰፈር ውስጥ የሚውሉ ህጻናትን ለጦር ማሰለፍና እነሱን ከፊት ለፊት ማግዶ በእነሱ አስከሬን ላይ ተረማምዶ የሚፈልገውን ለማስፈጸም የሚሞክር እጅግ በጣም ጨካኝ የሆነ ቡድን መሆኑን በአደባባይ አሳይቷል።
እንደዚህ አይነት ቡድኖች ስለ ሰው ልጅ ርህራሄ የሌላቸው ስለ ቤተሰብ ሊያስቡ የሚችሉ ስነ ልቦናቸው የተጎዳ ናቸውና በዚህም ምክንያት ነው እንግዲህ ሲቪሊያን እንዲያልቁና እንዲማገዱ እያደረጉ ያሉት።
በመሆኑም ይህ ጨካኝ ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ በፍጹም አንገቱ ቀና እንዳይል ይደረጋል። ምክንያቱም በጣም መሰሪ አጥፊ ደም አፋሳሽ ነው። ግማሽ ክፍለ ዘመን ሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ደም ሲያፋስስ የኖረ በመሆኑም አሁን ላይ ወደማብቂያው እየደረሰ ያለ ይመስላል።
ለህጻናት የሚያስፈልገው ትምህርት እውቀትና የትውልድ ምግብ እንጂ ክላሽ አልነበረም፤ ነገር ግን ህጻናትን ከአንድም ሁለት የጦር መሳሪያ እንዲሸከሙ በማድረግ በአደባባይ ማሰለፍ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ወንጀልም ጭምር ነው። ይህንን ደግሞ መላው ኢትዮጵያውያን ይገነዘቡታል፡፡ቡድኑ ለሰራው ስራም ቅጣቱን ያገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እዚህም እዚያም የሚሰማውን የሰላም መደፍረስ እንዲሁም ሕዝቡን በጣም እየተፈታተነው ያለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል አንድ ሆነን የምንቀጥልበት ሁኔታ እንዴት ነው ሊፈጠር የሚችለው?
ዶክተር ቢቂላ፦ አዎ እነዚህ እንግዲህ በፓርቲያችን ፕሮግራም ላይ የአጭር የረጅም እንዲሁም የመካከለኛ ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ስራ የገቡ ነገሮች ናቸው። ሕዝባችንን በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ እየፈተኑ ያሉት ነገሮች ይታወቃሉ፣ አንዳንዶቹ እንደውም ጊዜ የሚሰጡም አይደሉም። ለምሳሌ እዚህም እዚያም የሚያጋጥም የጸጥታ መደፍረስ የሕዝቡን የእለት ተዕለት ኑሮ የሚፈታተን ነገር በመሆኑ በፍጥነት መፈታት ያለበት ነው። የኑሮ ውድነቱም በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ የሚንጸባረቅ በመሆኑ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። መንግሥትም እነዚህን ነገሮች ለመፍተት የሚያስችሉና በፍጥነት ወደ ስራ የሚገባባቸውን እቅዶች አዘጋጅቷል። በዚህም መሰረት እየተሰራ ነው።
የጸጥታና የደህንነት ጉዳይን በተመለከተ በተለይም በሕዝባችን መካከል በጣም የቆዩ እሴቶች አሉ። በዚህ መሰረት ስናየው ደግሞ ህብረተሰባችን በሰላም ወጥቶ መግባትን ነው የሚፈልገው፡፡ በእርግጠኝነት ህብረተሰቡ በየቤቱ እህል እንዲሰፈርለት፣ እርዳታ እንዲሰጠው አይደለም የሚፈልገው፤ የሚፈልገው ሰላም አግኝቶ እራሱ ላቡን አንጠፍጥፎ ሰርቶ መኖር ነው። በመሆኑም ይህንን ማመቻቸት ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ቢቂላ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013