
አጣዬ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአጣዬ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በድምሩ የ400 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።
በወቅቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ፤ ድጋፉ ነዋሪዎችን ለማበረታታት እና አለንላችሁ ለማለት መጥተናል ብለዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍም በተለያየ መንገድ ይቀጥላል። በዚህ የክረምት ወቅት ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን መደገፍ እንደሚያስፈልግ የገለፁት ወይዘሮ ጽዮን፤ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ቤት ለሚሰራላቸው ወገኖች የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሀሰን መሀመድ ፤ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። ወቅቱ የእርሻ ወቅት በመሆኑ ወደ ግብርና ስራቸው ገብተዋል ብለዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ አካባቢው ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ሲሆን፤ የግብርናም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ቀጥሏል።
የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በጥፋት ሃይሎች ከተማዋ ብትወድምም የህዝቦችን ወንድማማችነት ግን ማጥፋት አይችሉም። ወደነበረችበት ለመመለስ እየተሰራ ነው።
እንደ አቶ አገኘሁ ገለጻ፤ “ጥቁሩን በመግፈፍ አረንጓዴ እናልብስ” በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተካሂዷል። ከተማዋን ጥቁር ያደረጋት ከሰል አረንጓዴ ይሆናል ብለዋል።
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013