ከዛሬ ስምንት ወር በፊት ትግራይን ሲያስተዳድር የነበረው መንግስት ባልታሰበና ባልተጠበቀ መንገድ አገርን ወዳልተፈለገ ሁኔታ የሚያስገባ ስህተትን በመፈጸም የሰሜን እዝን በተኛበት ገደለ፣ ማረከ፣ ንብረት ዘረፈ ፣አወደመ። ይህ አገርን የከዳ ተግባር ደግሞ ከፌደራል መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ አድርጎት ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ ችግር ችግርን እየወለደ አገርና መንግስት ብዙ መስዋዕትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ።
በእርግጥ የህግ ማስከበር ዘመቻው በተወሰነ መልኩ የተሳካ ብዙ የጁንታ አመራሮችን የደመሰሰ አይነኬ፣ አይደፈሬ ተብለው የነበሩ አካላትን ለሞትና ለእስር ያበቃ ሆኖ አልፏል። ይህም ቢሆን ግን ከአፈጣጠሩም ጀምሮ ሰላምን የማይወደው ይኸው ቡድን በብጥበጣው ቀጥሎበት አገርን ዳር እስከ ዳር በሚባል ሁኔታ በቅጥረኞቹ አማካይነት ሲያውክ ከረመ። በሌላ በኩልም ጁንታው ቡድን በስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት በተለይም በትግራይ ህዝብ ላይ የተጫወተው የአእምሮ ጨዋታም ቀላል አይደለም፡፡
መንግስት ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገባቸው ወጪዎች እያሉበት የትግራይ ህዝብ በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ በስምንት ወራት ብቻ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጓል።
ይህ ወጪ ሙሉ በሙሉ ህዝቡ እንዳልተጠቀመበትና እንደውም በተረጂዎች አማካኝነት እርዳታው ለጁንታው ይደርስ እንደነበር፤ አምስት የቤተሰብ አባላት ያለው ቤተሰብ ከ 7 እስከ 10 ቤተሰብ እመራለሁ እያለ እርዳታ በመቀበል ግማሹን ለጁንታው ያካፍል እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ሰምተናል።
መንግስት የትግራይን ህዝብ ከችግር ለማውጣት ይህንን ያህል ዋጋ ቢከፍልም ከውስጥም ከውጭም ያሉ አካላት ግን እውቅና መስጠት አልፈለጉም፡፡ መንግስት ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ እየሰራ የነበረ ቢሆንም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከውስጥ የሚደርሱበት ጫናዎች እና በመንግስት ላይ ከውጭ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች የሚከፈለው ዋጋ ለማን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳም አድርጓል።
በዚህ የተነሳ መንግስት እየሞተ ካለ ቡድን ጋር አብሮ ላለመሞት የታክቲክ ለውጥ አድርጓል፡፡ ውሳኔውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሳምንት ሙሉ ውይይት ተደርጎበት የተወሰነ መሆኑም ይታወቃል።
እኛም ወቅታዊ በሆነው የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አካሄድ ዙሪያ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ለዶክተር አረጋዊ በርሄ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት እያሰለፈ ይገኛል፤ ይህንን ጉዳይ ከቀደመ ባህሪው አንጻር እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ በመጀመሪያ ይህ ሽብርተኛ የህወሓት አመራር አገርን ለማሸበር የተሰማራ እንደመሆኑ መጠን ህጻናት። አረጋውያን። ወይም ንጹሀን ዜጎች በጠቅላላ ለጥቅሙ ሲል ሁሉንም ለጦርነት እያሰለፈና በማያውቁት፣ ባላመኑበት እንዲሁም ምንም ዝግጅት በሌላቸው ነገር ላይ ህይወታቸውን እንዲገብሩ እያደረጋቸው ነው።
ይህ ሆኖ ሳለ ግን ለትግራይ ህዝብ አዛኝና ተቆርቋሪ በመምሰል ያወራል፤ ግን ደግሞ እውነታው ለህዝብ ደንታ ቢስ መሆኑ ነው፤ ለዚህ ማሳያውም እነዚህን ምንም የማያውቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ህጻናትን ለጦርነት እሳት መማገዱ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ምንም ከህዝብ ጋር የሚያገናኘው ነገር የሌለ ሆኖ ሳለ ህዝብ ተወረረ ፣ጥቃት ደረሰበት ወዘተ እያለ ያወራል፤ ይህ ሁኔታ ግን አሸባሪው ቡድን የግል ጥቅሙን ብቻ አስቦ የሚያደርገው ነገር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ከዛ ይልቅ ህወሓት ማለት ለህዝብ የማይራራ የማይሳሳ ክፉ አመራር መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል፣ ባለፉት 27 ዓመታትም የነበረው ባህርይ ይኸው ነው፤ አሁንም እንደዛው አይነት ተግባር ላይ ነው ተሰልፎ ያለው።
በመሆኑም ህዝቡና ጁንታው ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውና ለግል ጥቅሙ ብቻ እየተሯሯጠ መሆኑ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚገባው ቋንቋ ሁሉ ሊነገረው ሊገባውና ሊረዳ ይገባል።
ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ ህጻናትን ወደ ጦርነት የማሰለፍ ጉዳይ ግልጽ ነው፤ ዓለም ያወቀው የተቀረጸና በፎቶግራፍ የተደገፈ ማስረጃ ያለው ነው። ምናልባት ህጻናቶቹ ህወሓትን አውቀውት እኩይ አላማውንም ተረድተው ሳይሆን ምንም የሚያደርጉት ነገር ስለሌላቸው የነገ ተስፋቸውንም ስላጨለመባቸው ብሎም በተዛባ ፕሮፖጋንዳና በዘፈን ልባቸውን ስላሸፈተው እንዲሁም ሀሽሽ እየሰጠ ከአእምሯቸው ውጪ ስላደረጋቸው ተቀላቅለውታል፤ ይህ ግን በጣም አስነዋሪ አሳፋሪ ብሎም አለም አቀፍ ወንጀል መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
በመሆኑም ዛሬ አለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም ስለ ህጻናት መብቶች ያገባናል የሚሉ አካላት ዝም ያሉ ቢመስልም ዋል አደር ብሎ ግን ይህ ስራው ከተጠያቂነት የማያድነው ከመሆኑም በላይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ውጤቱን እንደሚያየው ግልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፦ መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ የአሸባሪ ቡድኑ ፉከራና ቀረርቶ እንዲሁም ወደ ግጭት የመግባትን እውነታ እንዴት ገመገሙት?
ዶክተር አረጋዊ፦ መንግስት ይህንን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈበት በርካታ ምክንያቶች አሉት ፤ለምሳሌ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ስራውን እንዲሰራ ብሎም ሌላውም የማህበረሰብ ክፍል የጥሞና ጊዜን አግኝቶ የሚጠቅም የሚጎዳውን በአግባቡ እንዲለይ በማለት ነበር፤ ነገር ግን ይህ አሸባሪ ቡድን ይህንን ሁሉ የመንግስትን ቀና ሀሳብ ወደጎን በማለትና እራሱን እንደ አሸናፊ በመቁጠር ያልተገባ ፉከራና ቀረርቶ ውስጥ ወድቋል፤ ከዛም አልፎ በሌለው አቅም “ኑ ግጠሙኝ” እያለ የጸብ አጫሪነት ስራውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
አሁን እንደምናየው አንዳንዶች የደገፉት ቢመስልም ከአብዛኛው ህዝብ ጋር ግን ሆድና ጀርባ ነው ፤ ምንም አይገናኝም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት 30 ዓመታትም የግል ኑሮውን ከማካበትና በሀብት ላይ ሀብት ከመደረብ ባለፈ ምንም እንዳላደረገላቸውም በሚገባ አውቀዋል። መንግስትም ጦርነት ቆሞ ህዝቡም ተረጋግቶ እንዲያርስ ያለው የወደፊቱ የረሃብ ሁኔታ ታይቶት ነው። ነገር ግን ይህ አሸባሪ ቡድን ማንም ቢራብ፣ ችግር ውስጥ ቢገባ ደንታ ስለሌለው የተናጠል ተኩስ አቁሙን ጥሶ አሁንም ግጭት በመቀስቀስ ላይ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ቅጥ ያጣ ድህነትና ረሃብ እንደሚያስገባን መገመት አያቅትም።
ለህዝብ ደንታ ቢስ በመሆኑም የመንግስትን አሳቢነትና የሰላም ጥሪ አልተቀበለውም። አሁንም በጦርነት አዙሪት ውስጥ ከቶናል፤ መጨረሻው ግን ለራሱ መጥፎ እንደሚሆን ደግሞ አሁን ያለው የህዝቡ መነሳሳት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ምናልባት በሌለ አቅሙ ጦርነት ውስጥ ገብቷልና በኋላም ማጣፊያው እንደሚያጥረው ምንም ጥርጥር የለም።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ አሸባሪ ቡድን በኤርትራም በአማራም ላይ ትንኮሳን በመፈጸም አሁንም ጦርነቱን ለመቀጠል የሚያደርገው ሙከራ በተለይም በትግራይ ህዝብ ላይ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ በነገራችን ላይ ጦርነት ምንጊዜም ቢሆን የሚጎዳው ህዝብን ነው። ምክንያቱም ጸብ አጫሪውም ራሱን ለመከላከል ሳይፈልግ ወደጦር ሜዳ የሚገባውም ሁሉም ቢሆን የየራሳቸው አላማ አላቸው፤ ነገር ግን በመካከል ገና በልቶ ያልጠገበው ሮጦ ሰርቶ ራሱን ለመቀየር ያልቻለው ወጣትና ህዝብ በአራት ወገን እሳት እየነደደበት ለመኖር ይገደዳል። ይህ ህዝብ ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም በነበሩ በርካታ ጦርነቶች መከራውን ያየ ብዙ ልጆቹን የገበረ፣ ነገር ግን እስከ አሁንም በልቶ መጥገብ ያልቻለ ከመሆኑ አንጻር አሁንም ተመልሶ የገባው ከባድ ችግር ውስጥ ነው።
በመሆኑም ይህ ጦርነት ለማንም የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ በተለይም ለትግራይ ህዝብ ምንም ፋይዳ የሌለው ዘላለሙን ልጆቹን እንዲገብር የሚያስገድደው እድገት ልማት የሚባሉ ነገሮች እንዳያገኙት የሚያደርግ በመሆኑ ይህ ጁንታ ሀይል ውስጡ ለተሸጎጠው ህዝብ ሲል ወደ ሰላም መምጣት ብቻ ነው አማራጩ፡፡ ይህንን ቢያደርግ እውነትም ቆሜለታለሁ ለሚለው ህዝብ ያለውን አክብሮት የሚያሳይበት እንደሚሆን እገነዘባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት ይዞት ከመጣው ባህርይ አንጻር ለሰላም እድል ይሰጣል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ በእኔ እምነት ግን ይህ አሸባሪ ቡድን አገርን ለማፍረስ የሚያሴረውን ሴራ የስልጣን ጥማቱን ለማርካት የሚያደርገውን ትግል ትቶ ወደሰላማዊ መንገድ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ወደ ሰላም ከመጣ የሚፈልገውን ጥቅም፣ ስልጣን በዝባዥነት እንደማያገኝ ያውቀዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ስለተፋውና ዞር በል ስላለው የሰላም መንገድ ምን ያደርግልኛል የሚል ሀሳብ ላይ ነው። በነገራችን ላይ ከዛሬ ስምንት ወር ገደማ በፊት እራሱ እኮ ወደጦርነት ላለመግባት መንግስት ሰላም እናውርድ ብሎ በርካታ ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ይህ ቡድን በሰላማዊ መንገድ ፍላጎቴ አይሳካም ያለ በመሆኑ ጥረቱን ሁሉ አልተቀበለውም፡፡ አሁንም በዚሁ አቋሙ እንደጸና ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ አሸባሪ ቡድን ፌደራል መንግስቱ ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ደጋፊዎች ነበራችሁ በማለት ንጹሀንን እየገደለ እንዳለ ይሰማልና ይህ ባህርይውን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ህዝብ ላይ ያልተመሰረተ ሀይል ወይም ድርጅት ሁልጊዜም ቢሆን በጉልበት ነው የሚኖረው። ህወሓት ድሮም ስልጣን የያዘው በጉልበት ነበር፤ ኋላም ስልጣኑ ላይ ለመቆየት ባለፉት 27 ዓመታት በርካቶችን ሲያስር፣ ሲያሳድድ እንዲሁም እየገደለ በጉልበት ነው የቆየው፤ አሁን ደግሞ በጉልበቱ ተጠቅሞ ስለሆነ ስልጣኑን እንደገና ለማግኘት የሚሞክረው በቃ ከድሮም ጀምሮ አካሄዱ ይኸው ነበር።
አሁን እንደሚታየውም እርሱ ፈርጥጦ ጫካ ከገባ በኋላ የተመሰረተውን ጊዜያዊ አስተዳደር ያገዙ አብረው የሰሩትን እየገደለ ነው፤ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የሆኑ 16 የሚሆኑ ሰዎችንም መንገድ ላይ ነው ገድሎ የጣላቸው፤ በጠቅላላው እርሱን የማይደግፉ ከሆኑ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እየገደለና መሬት እየጣለ ለአውሬ እያስበላ ነው። በመሆኑም የሚቃወመውን ሁሉ ቅጣት በማለት እየገደለ መሆኑ አብሮት የኖረ አውሬያዊ ባህርይው ነው። ነገር ግን ይህንን እኩይ ተግባሩን ራሳችን ተባብረን ማስቆም ካልቻልን ህዝቡን እየፈጀ ሊቀጥል ስለሆነ አሁን ላይ በቃህ ሊባል ይገባል።
ይህንን አውሬ የሆነ አሸባሪ ቡድን ደግሞ በቃ፤ ከዚህ በኋላ አትገለንም፣ አታስረንም፣ አታንገላታንም ማለት የሚቻለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖና ተባብሮ መቆም ሲችል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መቀሌ ላይ የሚገደሉት፣ የሚታረዱት፣ የሚንገላቱት የለውጡ ደጋፊዎችም ሆኑ ሌሎች የእኔም ስጋ ናቸው፤ ስለ እነሱ እኔንም ይመለከተኛል ብሎ መነሳትና ማሰብ የግድ ነው።
ይህንን ማድረግ ባልቻልን መጠን ግን ይህ ቡድን ከመስፋፋቱም በላይ የንጹሀንን ደም በአደባባይ ሲያፈስ ሊኖር እንደሚችል ነው ለእኔ የሚገባኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ስምንት ወራት ይህንን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በፌደራል መንግስትና በመከላከያ ሰራዊታችን ድንቅ የሚባል ስራ ተሰርቶ እንደነበር ይታወሳል፤ ነገር ግን አሁን ይህ ቡድን ነፍስ ዘርቶ ለመምጣቱ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ አዎ በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ይህ አጥፊ ቡድን ቅጣቱን አግኝቶ ነበር፤ በዚህም በረሃ የገባውም ወደ በረሃው የሞተውም የታሰረውም ሁሉም የእጃቸውን አግኝተዋል፤ በማግኘት ላይም ነበሩ፤ ነገር ግን አሁን እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ ርዝራዦቹን ለቃቅሞ አገር ወደማሸበር ስራው ለመግባቱ ግንባር ቀደም ተጠያቂው መንግስት የላካቸው ወይም ያቋቋማቸው የጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞች (ሹማምንት) ናቸው።
ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ እነዚህ ሹማምንት ወደ ክልሉ ሲላኩ የተሰጧቸውን ተልዕኮዎች በአግባቡ መወጣት አለመቻላቸው ለዚህ እንዳበቃን ስለምረዳ ነው። ጊዜያዊ እንደመሆናቸው መጠን ቀደም ብለው ቆራጥ ሆነውና አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው የህዝብ የሲቪክ ማህበረሰብ እንዲሁም ሌሎችን አሳትፈው ቢንቀሳቀሱ ኖሮ እነሱም አቅም ያገኙ ነበር፤ ይህ አሸባሪ ቡድንም እንደገና አንሰራርቶ ችግሩ እዚህ አይደርስም ነበር።
በመሆኑም ለእኔ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተጣለበትን ሀላፊነት በወቅቱ መወጣት አለመቻሉ ቆራጥ ሆኖ ውሳኔን አለማሳለፉ እንዲሁም አንዳንድ ፍንጮችን ሲያይ አይቶ እንዳላየ ማለፉ ለችግሩ እዚህ መድረስ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው ህወሓት የትግራይም ሆነ የአማራ አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ስራቸው ተመልሰው ምርት እንዳያመርቱ ግጭት እየፈጠረ ነው፤ ይህ አካሄዱ ሊያስከትል የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ይህ የሽብር ቡድን በተለያዩ ቦታዎች ላይ መረቡን ዘርግቶ አርሶ አደሩ ስራውን እንዳይሰራ ሆን ብሎ እያወከ ይገኛል። ሽብርተኝነት ሁልጊዜ ወደሌላ ሽብርተኝነት ነው የሚያሸጋግረው ፤ ሽብርተኞች ሁሌም ቢሆን አመለካከታቸው በጣም ጠባብ ነው። እነሱ የሚያውቁት ፉከራ በጉልበታቸው ለመጠቀም ማስፈራራት ፖለቲካውንም በማስፈራራት ለማለፍ ነው ጥረት የሚያደርጉት። ነገር ግን አሁን ላይ እንኳን እንደ ህወሓት ያለ ደካማ ሽብርተኛ አይደለም ሌሎች በጣም ትልልቅ አቅም ያላቸው ሽብርተኞች ዋጋቸውን እያገኙ ነው። ነገር ግን ለጊዜው ብዙ ምስቅልቅሎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ዘለቄታዊ ነገር አይኖረውም።
የአማራም ይሁን የትግራይ ህዝብ አንድ ነው፡፡ አሁን እነዚህ ቡድኖች በሚፈጥሩት ችግርም የሚከፋፈል አይመስለኝም። ነገር ግን እነዚህ አሸባሪው ህወሓት አርሶ አደሩ ስራ በሚሰራበት ወቅት እየጠበቀ እሳት የሚለኩሰው ህዝቡ በተደራራቢ ችግር እንዲፈተን ስለሚፈልግ ነው። አሁን በመላው አገሪቱ የግብርና ስራዎች የሚሰሩበት ጊዜ ነው፡፡ ህወሓት ደግሞ የትግራይም ሆነ የአማራ አርሶ አደር አርፎ ስራውን እንዳይሰራ ጦርነት ከፍቶበታል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ አገር በምግብ እህል እንድንቸገር ያለመ መሆኑ የማይገባው አለ ብዬ አላስብም ።
በመሆኑም ሁሌም እንደሚሆነው ህዝቡ ተረጂ ሆኖ ሆዱን ብቻ እያሰበ እንዲኖር እነሱም ምናልባት ወደ ስልጣን የሚመጡባትን እድል ካገኙ የት ናችሁ ተብለው እንዳይታዩ ለማድረግ ያሰቡ ይመስለኛል። ነገር ግን የሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ ላይሆን ይችላል።
በሌላ በኩልም አሸባሪው ህወሓት ነገር ለማስነሳትና ወደ ጦርነት ለማስገባት ይህ መሬት የኔ ነው በማለት የሚከፍተው አጀንዳ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ሁሉም መሬት የኢትዮጵያ መሆኑን ካለመረዳት የመነጨ ስግብግብነት ይመስለኛል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንን ድንበር ለእኛ የጸብ መነሻ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉንም ነገር በውይይትና በፍቅር መፍታት ማሸነፍ ይቻላል። ነገር ግን የማያልቅ ጦርነት ውስጥ መግባት ከባድ ነው። አበው ሲተርቱ “ቅማልም ባቅሙ ሱሪ ያስፈታል” ይላሉ፤ ትንሽ የሚባል ሀይል የለም፡፡ በመሆኑም ትንሽ ተብሎ የተናቀውም ሀይል ቢሆን ጊዜ ጠብቆ ሱሪ የሚያስፈታ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህንን መገንዘብና ራቅ አድርጎ ማሰብ በውይይት ለመፍታትም መጣር ያስፈልጋል።
መንግስትም ባቋቋማቸው እንደ ሰላም ሚኒስቴርና ሌሎችም ተቋማት በጉዳዩ ላይ እንዲገቡ በማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ እንዲመጣ መተባበር ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ግን ብረት አንግቼ ጫካ ገብቼ ችግሬን እፈታለሁ ማለት ዘበት ነው። ምክንያቱም ይህንን ሁሉ አመት እሱኛው መንገድ እንዳላስኬደን ሁላችንም እናውቃለን።
አዲስ ዘመን ፦ ገበሬው በዚህን መሰሉ የጦርነት አውድ ላይ መክረሙ ወደፊት ሊያስከትልብን የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ገበሬውማ ምን ትጠይቂኛለሽ በአራት ማዕዘን በችግር እየተመታ ነው፤ አሁን ላይ እንደውም ተስፋ ያጣም ነው የሚመስለው። ይህ አሸባሪ ቡድን ነገሮችን በዚህ መልኩ ባያስኬዳቸው ኖሮ ገበሬው አሁን ላይ መሬቱን እያለሰለሰ ዘር እየዘራ የዘራውን እየተንከባከበ ምን ያህል ውጤትን አገኝ ይሆን እያለ እህሉ ሲደርስ ልጆቹን ለማብላት ገበያ አውጥቶ ሸጦ በምትኩ ያማረውን የሚያስፈልገውን ነገር ለመግዛት እቅድ የሚያወጣበት ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን ይህ መሰሉ ችግር ገበሬውን በጣም ጎድቶታል፤ ጉዳቱ ደግሞ ዛሬ ላይ ሆነን እንደምናወራው የሚገለጽ አይደለም። ነገ ከነገወዲያ ረሃብን ይዞ ስለሚመጣ ችግሩ በጣም አስከፊ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን መንግስት ጠንከር ሲልበት አለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዱኝ አለ ፤ተገደልኩ። ተዘረፍኩ። ተደፈርኩ ብሎ ይጮሃል ፤ መንግስት ሲተወው ደግሞ ጦርነት የመቀስቀስ ስራውን አጠናክሮ ይሰራል፤ ይህ እንደው ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር አረጋዊ ፦ ይህ እኮ መገለጫ ባህሪያቸው ነው። እነሱ የለመዱት በጉልበታቸው ተጠቅመው ህዝቡን ጭጭ አድርገው የሚፈልጉትን መዝረፍ መግደል፣ ያሻቸውን ማድረግ ነው፤ አሁንም በወደዚህ ጦርነት ሲገቡ የበላይ እንሆናለን ብለው በሙሉ ልባቸው ተማምነው ነበር፤ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሲሆን ድረሱልን እያሉ ጀሌዎቻቸውን ይለምናሉ።
ህዝቡ የእነዚህን መሰሪዎች አስመሳይነትና እኩይ ተግባር ጠንቅቆ በመረዳት ራሱን በማደራጀት ለማንም የትም ሄዳችሁ ብትጮሁ ብትንደባለሉ ጉዳያችን አይደለም ማለት መቻል አለበት።
አለም አቀፉ ህብረተሰብም በነፈሰበት የሚነፍሱ እንዲሁም የራሳቸውን ፍላጎት የሚፈጽምላቸውን ማንኛውንም አካል እንደ ህወሓት አሸባሪውን ሁሉ ከጎኑ ማቆም ልማዳቸው ነው። በመሆኑም እኛ እንደነሱ ሀያላን ስላልሆንን ራሳችንን ችለን ለመቆም ያለብን ድካም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ያሉ ይመስለኛል። በመሆኑም ከእነሱ ነጻ የሆነ አንድነትና ህብረት መስርተን በራሳችን መቆም መቻል አለብን። ህዳሴ ግድባችንም የሚያመላክተው አንድነትን ስለሆነ ተባብረን አንድ ሆነን በእነሱ በኩል የሚመጣውን ችግር መቋቋም ይኖርብናል።
በሌላ በኩልም በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ውስጥም ሆነው የእኛን ምክንያታዊ አካሄዶች የሚደግፉ አሉ፤ እነሱንም ማግኘትና ማስተባበር ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ እንደፈለጋቸው አገር ውስጥ መግባትና መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ሀይላት ቅድመ ሁኔታ ሲቀመጥላቸው አንቀበልም እያሉ ነውና እንደው ይህ ለህዝቡ ከማሰብ የመነጨ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር አረጋዊ፦ ሰብዓዊ ድጋፍ ካለው ችግር አንጻር በጣም አስፈላጊ ነው፤ ይህንንም ለማድረግ በሀቅ የሚንቀሳቀሱ ሀይላት የመኖራቸውን ያህል ሰብዓዊ ድጋፍን ሽፋን አድርገው ደግሞ እኩይ አላማቸውን ለማስፈጸምና ጁንታውን በተለያዩ ነገሮች ለመደገፍ የሚጥሩ አሉ። በመሆኑም እኛ ሰላምና አንድነት ፈላጊ ሀይሎች ተባብረንና ትኩረታችንን ከእነሱ ላይ ሳንነቅል መከታተልና ጥፋትም ሲገኝ አይ አይሆንም እያልን ለህዝቡ ጥቅም የሚሆነውን ደግሞ እየተቀበልን መራመድ የእኛ ሀላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ዶክተር አረጋዊ፦ ህወሓት በህዝብ ስምና ደም ነው የሚሸቅጠው፡፡ በዚህ ጁንታ አመራር ላይ እርምጃ በተወሰደ ቁጥርም በትግራይ ህዝብ ላይ እርምጃ ተወሰደ ብለው የሚሉና ህዝቡንም ለማነሳሳት የሚሞክሩ አሉና ይህ ግን ማጭበርበሪያ መሆኑን የትግራይ ህዝብም ሆነ ሌላው የአገሪቱ ህዝቦች ሊያውቁት ይገባል።
ህዝብን ለማጥፋት የተነሳ ሀይል የለም። ፌደራል መንግስትም ህዝቡ ከእነሱ ተላቆ በራሱ እንዲቆም ሰላሙን እንዲያገኝ ነው ፍላጎቱ፡፡ በመሆኑም ህዝቡንና ጁንታውን የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ እርምጃ የሚወሰደውም የሽብር ቡድኑ ላይ እንጂ ህዝቡ ላይ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013