የታንዛኒያ ፍርድ ቤት በቅጽል ስሟ ‹‹የዝሆን ጥርስ ንግሥት›› በመባል የምትታወቀውን የ65 ዓመቷን ቻይናዊት ህገ ወጥ የዝሆን ጥርስ ነጋዴ ያንግ ፈንግ ላይ የ15 ዓመት እስር እንደፈረደባት የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ፡፡
የኪሱቱ ፍርድ ቤት ዳኛ ሃሩማ ሻዲ በችሎቱ የተላለፈውን ውሳኔ አስመልክተው እንደገለፁት ቻይናዊቷ የዝሆን ጥርስ አዘዋዋሪና ሁለት የታንዛኒያ ዜግነት ያላቸው ተባባሪዎቿ በተደራጀ መልኩ በፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ይሁንና ሦስቱም ተከሳሾች ጥፋተኝነታቸውን ያልተቀበሉ በመሆኑ የሁለት ዓመት ተጨማሪ እስር እንደሚጠብቃቸው ካልሆነም ከሀገር እያስወጡ ሸጠዋል የተባለውን የዝሆን ጥርስ ዋጋ በእጥፍ እንደሚከፍሉ ውሳኔው ያስረዳል፡፡
ያንግ ፈንግ ኑሮዋን በታንዛንያ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ግምቱ 860 የሚሆን የዝሆን ጥርስ ወደ እስያ አሸጋግራለች በሚል ነበር ከሁለት የታንዛኒያ ዜግነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር እ.አ.አ. ጥቅምት 2015 እጇ የተያዘው፡፡ ያንግ ለዓመታት በተሰማራችበት ህገወጥ የዝሆን ጥርስ ንግድ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ጥቅም እንዳገኘች ፍርድ ቤቱ አትቷል፡፡
ወንጀሉን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ዓቃቤ ህግ በበኩሉ ቻይናዊቷ እንስት ድርጊቱን ስትፈጽም የነበረው ከሰዎች ጋር በመደራጀት፣ ለምትፈጽመው ወንጀል በጀት በመመደብ ፣ በህገ ወጥ መንገድ የዝሆን ጥርስ በማሰባሰብ፣ አንድ ሺ 899 ቶን ክብደት ያለውን የዝሆን ጥርስ ከሀገር በማስወጣትና በመሸጥ የሀገሪቱን ህግ ተላልፋለች ፤ ፍርድ ቤቱም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት አድርሳለች በሚል አስረድቷል፡፡
የታንዛኒያ ዜጎችና አንዳንድ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ፍርድ ቤቱ የወሰደው እርምጃ መንግሥት ህገ ወጥ የዱር እንስሳት አደንን በተመለከተ ትኩረት የሰጠ ስለመሆኑ ጥሩ ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ፈንድ የታንዛኒያ ተወካይ ዳይሬክተር አማኒ ጉሳሩ እንደሚሉት በሀገሪቱ በህገወጥ አዳኞች የጠፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች ሲታሰቡ የተሰጠው ፍርድ በቂ ነው ማለት እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡ ግለሰቧ ከሌሎች ጋር ትስስር በመፍጠር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዝሆኖች መገደል ምክንያት መሆኗ ታውቋል፡፡
ቻይናዊቷ ያንግ ከ1970 ዎቹ ጀምሮ በታንዛኒያ የቻይና እና የአፍሪካ ንግድ አማካሪ ሴክሬተሪ ጀነራል ሆና የሠራች ሲሆን የስዋሂሊኛ ቋንቋን የምትናገር እና በዳሬ ሰላም ታዋቂ የሆነ የቻይና ምግብ ቤት አላት ፡፡ አሁን ግን ኑሮዋን በዳሬ ሰላም ኮንጋ እስር ቤት አድርጋ ከፖሊሶች ጋር ተስማምታ መኖርን ተያይዛለች፡፡
እንደ የዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ፈንድ መሰረት ባለፉት አሥርት ዓመታት አፍሪካ 110 ሺ የሚገመቱ ዝሆኖችን አጥታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው 415 የሚሆኑ ዝሆኖች በአፍሪካ አህጉር እንዳሉ ይገመታል፡፡ በታንዛኒያ እ.አ.አ በ2009 110 ሺ የነበረው የዝሆኖች ቁጥር በ2014 ወደ 43 ሺህ ማሽቆልቆሉን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ አካላት አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በኤዢያ ሀገሮች ህገ ወጥ የዝሆን ጥርስን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በቻይና፣ ቬትናም እና ታይላንድ የሚመረቱት ጌጣጌጦች ግብዓት የሚያገኙት አፍሪካ ውስጥ በሚካሄደው ህገ ወጥ አደን ሲሆን የዝሆን ጥርስ ከሀገር እንዳይወጣ ቁጥጥር መደረግ ከጀመረ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻይና ከዝሆን ጥርስ የሚመረተው የጌጣጌጦች ገበያ እየተቀዛቀዘ ይገኛል፡፡ ቻይ ናዊያን ከዝሆን ጥርስ ጋር በተያያዘ በታንዛኒያ ፍርድ ቤት ተከሰው ለፍርድ ሲቀርቡ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ እ.አ.አ በ2016 ሁለት ቻይናዊያን እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት እስራት ተቀጥተዋል፡፡ በ2015 እ.አ.አ እንዲሁ አራት ቻይናዊያን በተመሳሳይ ወንጀል ተከሰው እያንዳንዳቸው ለ20 ዓመት እስር ተዳርገዋል ሲል ዘገባው ይጠቁማል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ኢያሱ መሰለ