አዲስ አበባ፡- በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር እየተከናወኑ ያሉ የምርምር ስራዎች የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያሳድግ መልኩ መተግበር እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ አስተዳደር ያከናወነው የተቀናጀ የአሳና የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ተመርቋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ሚኒስቴሩ ባለፉት አራት ዓመታት ከ60 በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራዎች ድጋፍ ማድረጉንና ጥቂቶቹም ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ የምርምር ተግባራቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱን የሚያሳኩ በመሆናቸው የኅብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት እንዲለውጡ ታሳቢ ተደርገው ሊከናወኑ ይገባል፡፡ የይምሎ ቀበሌ የተቀናጀ የአሳና የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት በትንሽ ሀብትና በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት የሚችል ሥራ በመሆኑ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት የሚያስችል የአሰራር መመሪያ ስለተዘጋጀ በቀጣይ ጊዜያት ስራው በሌሎች ክልሎች እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ክልልም የፕሮጀክቱን መልካም ተሞክሮዎች ወደሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዲያስፋፋ የአሰራር መመሪያ ርክክብ ተደርጓል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ከሚያከናውናቸው የልማት ምርምር ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ የመንግሥትን የልማት ስራዎች የሚያግዝ በመሆኑ የምርምር ስራውን ወደሌሎች አካባቢዎች በማሸጋገር የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያከናውኗቸው የጥናትና ምርምር ተግባራት ወደተግባር ተቀይረው ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ ስለመሆናቸው ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ፣ መሰል ፕሮጀክቶች ለወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩና ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልጸው፣ ስራውን ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
አንተነህ ቸሬ