አንዳንድ ሰዎች በምድር ላይ ለጥቂት ዓመታት ብቻ ኖረው እጅግ የሚያስገርሙ በርካታ ታላላቅ ተግባራትን ይፈፅማሉ። ከዚህ በላይ የሚስገርመው ደግሞ እነዚህ ጥቂት ዓመታትን ብቻ በሕይወት ኖረው ብዙ ተግባራትን ያከናወኑ ሰዎች ታላላቅ ስራዎቻቸው ምንም ዓይነት እውቅና ሳይሰጣቸው መኖራቸው ነው። ዛሬ በዚህ አምድ የምናስታውሳቸው ኢትዮጵያዊው ዶክተር መላኩ በያን በዚህ ምድብ ከሚመደቡ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
መላኩ በያን በ1892 ዓ.ም ወሎ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ተወለደ። መላኩ በተወለደበት አካባቢ የቆየው ለስድስት ወራት ብቻ ነበር። የመላኩ ወላጆች ለስራ ወደ ሐረር ሲሄዱ ሕፃኑ መላኩም ከወላጆቹ ጋር ወደ ሐረር ተጓዘ። ከወቅቱ የሐረር አስተዳዳሪ ራስ መኮንን ልጅ ተፈሪ መኮንን ጋርም ወዳጅ ሆነ። ተፈሪ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ይሆናሉ ተብለው ይጠበቁ ስለነበር ብዙ እንክብካቤና ክትትል ይደረግላቸው ነበር። መላኩ ከተፈሪ ጋር መገናኘቱ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረለት። ዓለማዊ ትምህርቱንም የመማር እድል አገኘ። የቤተ-ክህነት ትምህርት መማሩም የተለየ የዲስፕሊንና የአትኩሮት እድል እንዲያገኝ ስላስቻለው ወደ ዓለማዊው ትምህርት ሲገባ በፍጥነት ተላምዶና ጉብዝናውን አሳይቶ የተመሰገነ ሆነ። ለቤተ-መንግሥቱ ቅርብ መሆኑ የአገር ፍቅር እንዲኖረውም አድርጓል።
በወቅቱ በርካታ የኢትዮጵያ አጐራባች ሐገሮችና ሌሎችም የአፍሪካ ግዛቶች በአውሮፓውያን ተስፋፊዎችና በቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ስር ነበሩ። ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሀገሮች የቅኝ ተገዢነት ዕጣ ፈንታው እንዳይደርሳት ምጥ ውስጥ ገብታ ነበር። ከዚህ አስከፊ ችግር ይገላግላታል ተብሎ በብዙኃን ባለስልጣናት የታሰበው የተማሩ ልጆች እንዲኖሯት ነበር። በጉብዝናው የተመሰከረለት መላኩ ወደ ውጭ አገር ሄዶ ከፍ ያለ ትምህርት መማር እንዳለበት ተወሰነ። የንግሥት ዘውዲቱንና የልጅነት ጓደኛው የነበሩትን የአልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንን ይሁንታም አገኘ። ከሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን ጋር ወደ ሕንድ ተላከ። አልጋ ወራሹ ለመላኩ ‹‹ዶክተር ሆነህ አገርህን አንድታገለግል›› ብለው ነገሩት።
ይሁን እንጂ መላኩና ጓደኞቹ ለትምህርት የተላኩባትና በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሕንድ ለነልጅ መላኩ የተመቸች አልሆነችም። የሚማሩት ትምህርትም የእንግሊዝን ታላቅነት የሚያወሳ ስለነበር ገና በልጅነቱ የአገር ፍቅር ያደረበት መላኩ፣ ‹‹እንግሊዝ ታላቅ ናት … ፀሐይ በብሪታኒያ ሰማይ ላይ አትጠልቅም … ኢትዮጵያ ወደፊት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ትሆናለች … ›› የሚሉት በሸፍጥና በጉራ የተለወሱ የአስተማሪዎቻቸው ስብከቶች ለነመላኩ ምቾትን የማይሰጡ ብቻ ሳይሆኑ ዝም ተብለው የሚታለፉ ቀላል ነገር አልሆኑም። ከነመላኩ ጋር አብራ ወደ ሕንድ የተጓዘችው ሞግዚታቸውም በዚሁ ብስጭት ሕይወቷ አለፈ። ስለሆነም ለአልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ደብዳቤ በመፃፍ ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ ጠየቋቸው።
በ1916 ዓ.ም በመላኩ በያን በተፃፈ መፅሐፍ ውስጥ ከሕንድ ወደ ስፔን ሲጓዙ ያጋጠማቸውን ትዝታ በሚከተለው መልኩ ሰፍሯል።
‹‹ … በልዑል የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ፈቃድ ለትምህርት ስንሄድ እስፓኝ (ስፔን) አገር ስንደርስ ብዙ ሰዎች በመርከብ ላይ ቆመን ዐይተውን ነበር። እኔን ጠርተውኝ ‹ከወዴት ነው የመጣችሁት?› አሉኝ። ለትምህርት ወደ አሜሪካ እየሄድን ነው አልኳቸው። ‹ሀበሾች ወትሮ የምትወዱት ጦርነት ነበር፤ ዛሬስ ለትምህርት አሰባችሁ› አሉኝ።
እኔም ለባልጀሮቼ ለልጅ በሻህ ወረድና ለልጅ ወርቁ ጐበና ነገርኳቸው። ከዚህ በኋላ አንድ ቀን በመርከቡ ደጅ ብቻዬን ቆሜ ሳለሁ ይህን ሀሳብ ለመፃፍ ተነሳሳሁኝ። ከዚያ በኋላ እርሳስና ወረቀት ከኪሴ አውጥቼ መፃፍ ጀመርኩ። ከፃፍኩትም በኋላ ባነበው ደስ አለኝና ለልጅ በሻህ ውረድና ለልጅ ወርቁ አነበብኩላቸው። ከዚያም ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ በአዲስ አበባ ላሉት ባልንጀሮቻችን እንዲያሳዩዋቸው ብዬ በፖስታ ላክሁላቸው።
የኢትዮጵያ ልጆች ስሙኝ ልንገራችሁ፣
ከትምህርት በስተቀር ሌላም አይበልጧችሁ፣
ዐይን አላነሰ አልጨለመባችሁ … ››
ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ራስ ተፈሪ እነዚህ ወጣቶች አሜሪካ እንደደረሱ እንክብካቤ እንዲደረግላቸውና የሚፈለጉትንም ትምህርት መማር እንዲችሉ የአሜሪካ መንግስትና ሕዝብ እንዲተባበራቸው ደብዳቤ ፃፉላቸው። የመላኩ ቀጣይ መዳረሻም አሜሪካ ሆነች። አሜሪካ እንደደረሰም ወደ ኦሃዮ (Ohio) ግዛት አቅንቶ ማሪየታ ኮሌጅ በመግባት ለኮሌጁ ትምህርት የሚያበቃውን እውቀት የሚሸምትበትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የማጠናከሪያ ትምህርት ተማረ። ይህን ትምህርት እንዳጠናቀቀም ወደ ኮሌጅ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። ይህም በአሜሪካ አገር በዲግሪ የተመረቀ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንዲሆን አስቻለው።
በአሜሪካ ቆይታውም በጥቁር የቆዳ ቀለሙ ምክንያት የሚደርስበትን የዘረኝት ጥቃት ተቋቁሞ በአሜሪካ ዝነኛ ከሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ወደሆነው ወደ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የሕክምና ትምህርቱን መከታተል ጀመረ። በሃዋርድ ቆይታው ዊሊያም ሊዮ ሃንስበሪ ከተባለ ምሁር ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ካውንስል (Ethiopian Research Council) አቋቋመ። አንትሮፖሎጂስቱና የታሪክ ምሁሩ ዊሊያም ሊዮ ሃንስበሪ የአፍሪካ ጥናት መስኮችን (African Studies) ለአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ሰው ነበሩ። ከካውንስሉ ዓላማዎች መካከል አንዱ መዛግብትን እየፈለጉ ስለኢትዮጵያና ስለቀሪው አፍሪካ እውነተኛ ታሪክ መፃፍ ነበር።
መላኩ አሜሪካ በደረሰበት ወቅት ዝነኛው ጃማይካዊ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ማርከስ ጋርቬይ ‹‹Universal Negro Improvement Association and African Communities League (UNIA-ACL)›› የተባለ ድርጅት መስርቶ ለጥቁሮች መብት እየታገለ ነበር። የጋርቬይ ማኅበር ከመቋቋሙ ከበርካታ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ጥቁር ለሆኑ ሰዎች ሁሉ የመንፈስና የጥንካሬ ማሳያ ምድር እንደሆነች ይወሳል። በመሆኑም ጋርቬይ ‹‹ኢትዮጵያ ተነሺ! አፍሪካ ተነሺ! አንዲት ነፃ እና ኃያል አፍሪካን እንመስርት›› የሚል መፈክር ይዞ ተነስቶ ነበር። ይሁን እንጂ ማርክስ ጋርቬይን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካ- አሜሪካዊያን ‹‹የኢትዮጵያ ዜጐች ጥቁሮችም ቢሆኑ እራሳቸውን እንደጥቁር/አፍሪካዊ አያዩም›› የሚል የጥላቻ ዘመቻ ይስፋፋ ነበር ይባላል።
መላኩ በጥቁር አሜሪካዊያኖቹ በወቅቱ የሚባለውን ሁሉ በአንክሮ ያዳምጥ ነበር። ከዚያም እርሱ በአሜሪካ ኮሌጆች ውስጥ ሲማር ይደርስበት የነበረውን የቀለም መድልዎ አስረዳ። ይህ የሆነው ጥቁር በመሆኑ እንደሆነም ተናገረ። ‹‹ … ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን ጥቁር መሆናቸውን ነው። ስለዚህ እኛ ጥቁሮች በኅብረት ሆነን ከጨቋኞች ነፃ ለመውጣት መታገል አለብን …›› ብሎ አስረዳ።
ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማትና ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ በአንድ ወቅት ለመላኩ በያን ‹‹አገርህን ለመታደግ ጥቁር አሜሪካውያንና ምዕራብ ሕንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና እንዲያሳድጓት ብርቱ ጥረት አድርግ›› እንዳሉት በታሪክ ተጽፏል። ከዚህ በኋላ መላኩ በያን በፃፈው ጽሑፍ ኢትዮጵያውያን እንዴት ያለ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል እንደሚያካሂዱ ለጥቁሮች ለማስረዳት እርሱም ወደ ዘመቻ መጓዙን ጠቅሷል። ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዢዎች ያቺን ለዘመናት በነፃነት ፀንታ የኖረች ሀገር ሊቀራመቷት ሲያሰፈስፉ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አሻፈረኝ ብሎ መታገሉ ሌሎች ጥቁሮች ኢትዮጵያ የጥቁር ትግል ተምሳሌት እንደሆነችላቸውም ጽፏል።
በ1928 ዓ.ም መላኩ በያን የሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ተመረቀ። ዶክተር መላኩ በያንም በአሜሪካ በሕክምና ዶክትሬት የተመረቀ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነ። በተመሳሳይ በዚያው ዓመት ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። የአገሩ መወረር ያንገበገበው ዶክተር መላኩ በያን ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በነበረበት ወቅት ዶሮቲ ሀድሲ የምትባል አሜሪካዊት አግብቶ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሆኖ ነበርና ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከባለቤቱና ከልጁ ጋር ነበር። ወደ ኦጋዴን በመሄድም ቁስለኞችን ማከም ጀመረ። በወቅቱ በጅጅጋ፣ በደገሃቡር እና በጐሬ የተዋጣለት የሕክምና አገልግሎት አበርክቷል። በዚህም የአስከፊውን ጦርነት ገፈት ቀመሰ። የኦጋዴን ግንባር ጋራና ሸንተረር የሌለበት ስፍራ በመሆኑ የፋሺስት የጦር አውሮፕላኖች ያለማንም ከልካይ ኢትዮጵያውያንን የጨረሰበት አካባቢ በመሆኑ የዶክተር መላኩ ተልዕኮ እጅግ አስቸጋሪ ነበር።
ንጉሰ ነገሥቱ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሰሜኑ ጦር ግንባር ሲጓዙ ዶክተር መላኩም ከኦጋዴን ተጠርቶ የንጉሰ ነገሥቱ ልዩ ሐኪም በመሆን ለበርካታ ቁስለኞች ሕክምና ሰጥቷል። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ወገን በርካታ ሰዎች በመጐዳታቸው የንጉሱም ጦር ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ትዕዛዝ ተላለፈ። እስከዚያው ድረስ ግን ዶክተር መላኩ የንጉሱ ልዩ ሐኪም፣ አስተርጓሚ፣ ፀሐፊና ቃል አቀባይ ሆኖ ይሰራ ነበር።
በወረራው ወቅት ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ አገር ጥለው ወደውጭ ይሂዱ ወይንስ ከሕዝቡ ጋር ሆነው ይዋጉ?›› የሚለው ክርክር በተነሳ ጊዜ የንጉሰ ነገሥቱን ከአገር መውጣት የሚደግፉት ወገኖች ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይተው በጠላት ከተማረኩ ወይም ከተገደሉ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በጠላት መገዛቷ አይቀርምና ንጉሰ ነገሥቱ ወደ ውጭ አገር ሄደው በውጩ ዓለም ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ትግል ያድርጉ፤ ለአርበኞችም እርዳታ እንዲገኝ ያደርጋሉ …›› የሚል መከራከሪያ አቀረቡ። ብዙ ተቃውሞ ቢያጋጥመውም ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ ወደውጭ ወጥተው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንሞክር›› የሚለው ሃሳብ ቅድሚያ ተሰጠው።
ንጉሰ ነገሥቱ ወደ እንግሊዝ ሲሄዱም በሄዱበት ወቅት ዶክተር መላኩም አብረው ሄዱ። ይሁን እንጂ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያን ስሞታ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ቢያቀርቡም ቀና ምላሽ አላገኙም ነበር። በዚህ ወቅት ቀደም ሲል የንጉሱን ከሀገር መውጣት ይቃወሙ የነበሩት አርበኞች ትክክል እንደነበሩ ዶክተር መላኩ ተቀበሉ። ‹‹የቀረን ተስፋ እዚያው በሀገራችን ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግላችንን ማፋፋም ነው። በዚህም ምክንያት በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች ከጐናችን ይቆማሉ›› ሲሉ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ ለነበሩት ለእንግሊዛዊቷ የፀረ-ፋሺስት ንቅናቄ መሪና የሴቶች መብት ተሟጋች ሲልቪያ ፓንክረስት ስለኢትዮጵያ ብዙ ነገር የነገሯት ዶክተር መላኩ በያን ነበሩ። ሲልቪያ ‹‹New Times and Ethiopian News›› የተሰኘውን ጋዜጣ ማሳተም የጀመሩትም ዶክተር መላኩ ስለኢትዮጵያ በነገሯቸው ነገር ተነሳስተው እንደሆነ ይነገራል።
ባለቤታቸውም አሜሪካዊት ስለነበሩ ወደ አሜሪካ በመጓዝ ከጥቁሩ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆን ስለኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት የነፃነት ታሪክ በመናገርና የኢጣሊያን ወረራ ሕገ-ወጥነት በማስገንዘብ የፀረ-ፋሺስት ትግሉን ቀጠሉ። ‹‹የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኅብረት (Ethiopian World Federation)›› የሚባል ድርጅትም አቋቋሙ። ስለድርጅቱ ሲናገሩ ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላም ቢሆን የኅብረቱ ስራ አይቋረጥም። ለምን ቢባል ኅብረቱና የኢትዮጵያ ድምፅ መላውን የጥቁር ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ቃል ገብተዋል። እኛ የተነሳነው የተባበረ የአፍሪካ መንግሥት (United States of Africa) ለመመስረት ነው›› ብለው ነበር። በሌላ በኩልም ‹‹ … እ.አ.አ ከ1921 ጀምሮ ሁለት ጥንድ ሃሳቦች ነበሩኝ። አገራችን ከአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንደትሆን ሳስብ የሕዝባችን አልበገር ባይነት ከዓለም አቀፉ ንጥረ አፍሪካ ሁሉ ጋር መጣመር የነፃነት ዓላማችንን እንደሚያሳካልን አምን ነበር። የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኅብረት ለዚህ ዓላማ የሚጠቅም ነበር …›› በማለት ጽፈው ነበር። የዶክተር መላኩ በያን ‹‹የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኅብረት›› ከማርከስ ጋርቬይ ‹‹Universal Negro Improvement Association and African Communities League (UNIA-ACL)›› ጋር በትብብር ይሰራ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ትግሉን ለማፋፋም ‹‹The Voice of Ethiopia›› የተባለ ጋዜጣ ማሳተም ጀመሩ። በጋዜጣውና በኅብረቱ በኩልም ስለኢትዮጵያና ሕዝቧ ታሪክ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፅመውን ግፍ፣ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልንና የነፃነትን ክቡርነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት ጥረዋል። በዚህ ጥረታቸውም የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር የሆኑ የሌሎች አገራት ዜጎችም ኢትዮጵያውያን አርበኞችን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ችለዋል። ዶክተር መላኩ አንደበተ ርቱዕና ጎበዝ ተናጋሪ ስለነበሩ በተለያዩ ቦታዎች ንግግር በማድረግ ለአርበኞች ድጋፍ እንዲገኝ አድርገዋል። በርካታ ጥቁር አሜሪካውያንን በየቀኑ እየሰበሰቡ ‹‹እኛ በቅኝ መገዛት የለብንም፣ አርበኞች በዱር በገደል ጠላቶቻችን ከሀገራችን ለቀው እስከሚወጡ ድረስ ይዋጋሉ፤ ጥቁሮች ያሸንፋሉ›› በማለት ንግግር ያደርጉ ነበር።
ዶክተር መላኩ ከባለቤታቸው ዶሮቲ ጋር በመሆን በሚያደርጉት ትግል የአያሌ ጥቁር አሜሪካዊያንን ድጋፍ አግኝተዋል። ‹‹ለነፃነት መፋለሚያው አሁን ነው … ተስፋፊዎችን በኅብረት እንቃወም … ሊግ ኦፍ ኔሽንን እናውግዝ … ጣሊያንን እናውግዝ … ፋሺስቶችን እናውግዝ … ነፃ የጥቁሮች ሀገር ይኑር …›› እያሉ እየተናገሩ በርካታ ተከታዮችን አፍርተዋል።
በፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ከነበሩት ምሁራን መካከል አንዱ የነበሩት ኢትዮጵያዊው ዶክተር መላኩ በያን በትምህርትና በአንድነት በፅኑ ያምኑ ነበር። ‹‹ትምህርት ከተማርን ሀገራችንን ከማንኛውም ጥቃት እንከላከላታለን›› የሚል እምነት ነበራቸው። ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጓት ነገሮች መካከል ዋነኛው ትምህርት/እውቀት እንደነበር በመረዳታቸው፣ ለእውቀት ብለው ከምስራቅ አፍሪካ ደቡብ እስያ፤ ከደቡብ እስያ ወደ አሜሪካ ተንከራትተዋል፤ብዙ መከራዎችንም ተጋፍጠዋል። የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ-አሜሪካውያን ግንኙነት እንዲስፋፋ ብርቱ ትግል አድርገዋል። ኢትዮጵያውያንም ወደ ምዕራቡ ዓለም ሄደው ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ጥረት አድርገዋል።
‹‹ግዙፍ የሆነው የአፍሪካ አህጉር በቅኝ ግዛት ቀንበር ሰር ሊወድቅ የቻለው አንድነቱን ባለመጠበቁ ነው›› ብለው በፅኑ የሚያምኑት ዶክተር መላኩ፣ አፍሪካውያንም ሆኑ ሌሎች ጥቁሮች አንድነታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል። ‹‹እኛ የተነሳነው የተባበረ የአፍሪካ መንግሥት (United States of Africa) ለመመስረት ነው›› ብለው ተናግረውም ነበር። በአፍሪካ ምድር ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካውያን በጋራ ካልተባበሩ የትም መድረስ እንደማይችሉ እነዶክተር መላኩ ተረድተው ነበር። እርሳቸው እንደተመኙት የአፍሪካ አገራት አንድ መንግሥት ባይመሰርቱም እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ‹‹የአፍሪካ ኅብረት›› (የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/OAU) በሚባል ጥላ ስር ተሰባስበዋል።
ሲማሩ፣ የፀረ-ፋሺስት ትግል ሲያደርጉ … እረፍት ያልነበራቸው፣ በአጭር እድሜያቸው ብዙ ነገሮችን የፈፀሙት፣ በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ ታላቅ ሰው ሆኖ መገኘትን ያስተማሩት፣ በለፉላትና በደከሙላት ኢትዮጵያ ለስራቸው ምንም እውቅና ያልተሰጣቸው … ፓን-አፍሪካኒስቱ ኢትዮጵያዊ አርበኛና ሐኪም ዶክተር መላኩ በያን ኢትዮጵያ ከፋሺስት አገዛዝ ነፃ ስትወጣ ሳያዩ፣ የለፉለት ዓላማ ተሳክቶ ሳይመለከቱ … የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ተላቀው በጋራ የተሰባሰቡበትና ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት›› (በኋላ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት››) የተባለው አፍሪካዊ ጥላ ከመመስረቱ ከ23 ዓመታት በፊት ገና በ40 ዓመታቸው በ1932 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013