
‹‹የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ዳግም የመወለድ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኛል›› ሲሉ የገለፁት የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል እና የታሪክና የባህል ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፤ ከነበሩት ችግሮች አንፃር ሲታሰብ ወደደም ጠላ ስለግድቡ ሙሌት መጠናቀቅ የሰማ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደስታው ሰማይ ጥግ መድረሱ እንደማይቀር ጠቁመዋል።
ከችግር የሚያድነው ነገርን ተስፋ በማድረግ ላይ ያለ ህዝብ፤ እንዲህ ዓይነት የብስራት ዜና ሲሰማ ደስታው ወደር ማጣቱ የተለመደ መሆኑን ገልጸዋል፤ የግድቡ መሞላት ይበቃል ማለት ባይሆንም ትልቅ ተስፋን እንደሚያጭር አብራርተዋል።
በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ፤ የኮሙኒኬሽን ግንኙነት፣ የኢንደስትሪ ምርት፤ ከምግብ ማብሰል እና ከፅዳት ጀምሮ የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮ በአጠቃላይ ከሃይል ጋር የተሳሰረ ነው። ለዚህም የሃይል አቅርቦትን በከፍተኛ መጠን ሊያሻሽል የሚችል የሚጨበጥ ተስፋ የተገኘ መሆኑ እርሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ያስደስታል ።
ከህዳሴው ግድብ ወደ 6ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል ማግኘት ይቻላል። ይህ ሃይል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት ጋር ለመጋራት የታሰበበት ቢሆንም እንደመነሻ ትልቅ መሰረት ሊሆን የሚችል መሆኑን አመልክተዋል። ከህዝቡ ጥቅም በተጨማሪ ሃይልን ለጎረቤት ማጋራት ያለን ዝምድና ከማሳደግ ባሻገር፤ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
እንደረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ገለፃ፤ ግብፅ ብቻዋን እቆጣጠረዋለሁ ብላ ያለአግባብ አምና የተፋሰሱን አገራት በዕርዳታም ሆነ በመግባባት በተለያየ መልክ በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ ስትቆይ ኢትዮጵያ ግድብ የመገንባት ፍላጎት ቢኖራትም ችሎታ ስለሌላት ሳትሞክር ቆይታለች። አሁን ግን ግብፅ እና ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ካካሔዱ ጀምሮ፤ ናይል ኢንሼቲቭ ተጀምሮ የአባይ ተፋሰስ አገራትን የሚያገናኝ መስመር ሲመጣ ነገሩ እየተቀየረ ሔዷል።
ናይል ኢንሼቲቭም አሥር ዓመታትን ፈጅቷል። ዲፕሎማሲው ቀላል አልነበረም። በዛ ብዙዎቹ ተስማምተዋል። ከናይል ኢንሼቲቭ ጀምሮ ዲፕሎማሲው እየረገበ የአባይ ተፋሰስ አገራት ወደ አንድ አቅጣጫ እያመጡ አሥረኛ ዓመት የመስማሚያ ሰነዳቸውን አዘጋጅተው ተፈራርመው ማፀደቅ ብቻ ቀርቷቸዋል። አንዴ ፀድቆ ካለቀ የአባይ ተፋሰስ አገራት ሁሉም
የሚስተናገዱበት ማዕቀፍ የሚኖራቸው በመሆኑ ትግሉ እዛ ድረስ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ግብፆች እስከ አሁን የውሃ ክፍፍል ጥያቄን ሥርዓት ባለው መልክ መጠየቅ አልቻሉም። እነርሱ የሚያስቡት ቀኝ ገዢዎቻቸው ለራሳቸው አዘጋጅተው ለራሳቸው የፈረሙትን ከኢትዮጵያ ጋር ምንም የሚያገናኝ ጉዳይ የሌለውን የ1929ኙን እና የ1959 ኙን ሁለቱን ሰነዶች ነው። በዛ ጊዜ ደግሞ ግብፅ እና ሱዳን በቀኝ ግዛት ውስጥ ነበሩ። በእነርሱ ፋላጎት ላይ እንኳን ያልተመሰረተውን ሰነድ በመጥቀስ፤ እኔ ብቻ ኖሬ ሌላው በድርቅ ይሙት የሚለው የግብፆች ተረት ተረት ከአሁን በኋላ ብዙም እንደማያስኬዳቸው ተናግረዋል።
የዓለምን ህዝብ እያወናበዱ እና እነርሱም እየተወናበዱ የሚሄዱበት መንገድ በጊዜ ብዛት ሁሉም እየነቃ ሲሔድ ‹‹ረፉ›› መባላቸው አይቀርም የሚል ዕምነት እንዳላቸውም የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ የሱዳን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው። የግብፅንም ህዝብ በሥርዓቱ ማቅረብ ከተቻለ ከኢትዮጵያ የሚርቅ እንደማይመስላቸው ጠቁመው፤ ዋነኛዎቹ አይበቃንም በሚል ስሜት በረሃው ላይ ውሃውን ከአቅሙ በላይ እየዘረጉ እያስቸገሩ ያሉት ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎችም ማሰብ የሚጀምሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
አባካኝነት የበዛበት አጠቃቀማቸውን አቁመው፤ የኢትዮጵያውያንን ‹‹አብረን ሰርተን የፈጣሪን ፀጋ አብረን እንቋደስ በሚል የሚተላለፈውን ጥሪ ይቀበላሉ›› የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
‹‹ ወደ 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ቢሆንም፤ የተበላሸው ሲጨመር ደግሞ ከዛ በላይ ያስወጣል። ትናንት የተበላሸውን ለማስተካከል ብዙ መንገድ መሔድ ያስፈልጋል። ያም ቢሆን አሸናፊ መሆናችን አልቀርም። የእስከ አሁኑ ተስፋ የሚስቆርጥ አይደለም። ከዚህም በኋላ ሙሌቱን የሚያስቆመው ነገር የለም። ግድቡን እስከ አሁን ያስኬድነው የማንችለውን ተራራ እየወጣን ነው። ጫናውን አልፈናል። አሸናፊ ሁሌም ተከታይ አለው። ማሸነፋችን አይቀርም።›› ብለዋል።
ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያውያን ውስጥ ያለው ውህደት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት ላይም ብዙ የሚጠቅም ነገር ያለው መሆኑን በማስታወስ፤ ኤሌክትሮ መካኒካል ችግሩ ተፈትቶ ሃይል በማመንጨት አንዴ ማምረት ከተጀመረ የሰው ደስታ ገደብ የሚኖረው እንደማይመስላቸው፤ በዛ ጊዜ የሚኖረው ውህደት የበለጠ እንደሚሆን እና ዲፕሎማቲክ ጫናውም እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
‹‹የህዳሴው ግድብ ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ መሰራቱን ተከትሎ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። ሂደቱ ቀላል አልነበረም።›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ ‹‹ ዓምና ጫና ነበረ። ዘንድሮ ደግሞ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ብንሆንም የዓለም ሃያላን አገራትን ለማስተባበር የተሞከረበት ሁኔታ በተወሰነ መልኩ አገሪቱን ጎድቷል። ነገር ግን በዚህ ውስጥም ማሸነፍ ተችሏል›› ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ አሁንም ጫናውን ለማስተካከል ጊዜ ይፈጃል ጉልበት ይጠይቃል፤ በሞራል ያለውን ፅናት በማቀናጀት ሙሌቱ የተከናወነ እና ዲፕሎማሲው ላይ ለውጥ ለማምጣት የተቻለ ቢሆንም የግብፅ ግብ ግብ እና የቃላት ጨዋታ መጨረሻ እንደሌለው ማወቅ ይገባል ብለዋል። በመሆኑም የዲፕሎማሲ ጫናው የማያበቃ በመሆኑ፤ “ግመሉም ይሔዳል ውሻውም ይጮኻል “እንደሚባለው ጫናው ቢቀጥልም ሥራውን አጠናቆ አሸናፊነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዓለም ደረጃ በ1895 አካባቢ የሃይል ማመንጫ ግድብ ተጀምሯል። በኢትዮጵያም እንዲህ አይነት ግድብ ከታሰበ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የግድቡ ወሬ ቢሰማም፤ በዛ ጊዜ ማድረግ አልተቻለም። አሁን ደግሞ መገንባት ተችሎ የውሃ ሙሌት ደረጃ በደረጃ መከናወኑ ያስደስታል።
ተጠናቆ ለምርት ይደርሳል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ በመጨረሻም በዓሉ በደስታ ቀን ውሏልና ደስታውን ሁሉም ይቋደስ በማለት ኢድን አስመልክቶ እና የግድቡን የሁለተኛ ዙር ሙሌት በሚመለከት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013