ጌትነት ተስፋማርያም
ከአፍሪካ ሕዝብ 77 ከመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ነው ተብሎ ይገመታል። ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ 70 በመቶው የሚሆነውም በወጣትነት እድሜ ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ወጣቱ በፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውነው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።
የወጣት ማህበራት ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ከማስተባበር አኳያ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ። በርካታ ወጣቶችን በአባልነት ከያዘውን የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበር በተደራጀ አካሄድ ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት አንዱ ነው። እኛም በወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም ከህወሓት የግጭት ተልዕኮ፣ ህጻናት በጦርነት ስለመሳተፋቸው፣ ስለወጣቶች ስለአገራዊ እንቅስቃሴ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች አንስተን ከኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ከድር እንዳልካቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር በስሩ ምን ያክል አባላትን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው?
ከድር እንዳልካቸው፡– የኦሮሚያ ወጣት ማህበር በቅርቡ ሪፎርም አድርጓል። ወጣቱን አንቀሳቅሶ በሙሉ አቅም ወደማህበሩ ያመጣቸው የኦሮሞ ወጣቶችን ቁጥር ወደሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በማሳደግ በአባልነት ይዟል።
በማህበሩ ውስጥ ሴቶችም ሆነ ወንዶች በስፋት ይሳተፋሉ። ቄሮ ወይም ያላገቡ የኦሮሞ ወጣቶች በዋናነት የማህበሩ አባላት ናቸው። በማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴዎች መካከል በክረምት ከሚደረጉ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አሉ።
ከዚህ በተረፈ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም ህወሓትና ሸኔ የሚፈጥሩትን ችግር ለመግታት ወጣቱ ምን ማድረግ አለበት የሚለው ላይ በየደረጃው ውይይት የማካሄድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠና የመስጠት ሥራዎች ይከናወናሉ። ማህበሩ በእያንዳንዱ የኦሮሚያ ቀበሌዎች በተዘረጋው መዋቅሩ አማካኝነት ወጣቶችን በማስተባበር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቷን ወቅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተመለከተ በተለይም ከህወሓት ጋር ተያይዞ መንግሥት የሚያከናውናቸው እርምጃዎች በተመለከተ የማህበራችሁ አቋም ምንድን ነው?
ከድር እንዳልካቸው፡– ከህወሓት ጋር በተያያዘ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት ነው። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ሀገራችን ላይ ምን አይነት ችግር ሲያደርስ ቆይቷል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ለ27 ዓመታት አስፋፍቶ ህዝብን ሲያሰቃይ የኖረ ነው።
በዚህ የተነሳ ከተለያየ የማህበረሰብ አካል ተቃውሞ ገጥሞታል። ከዚህም መካከል የኦሮሞ ወጣቶችን ንቅናቄ ብናይ የህወሓትን አገዛዝ በየመንገዱ ወጥቶ እንደተቃወመው ይታወሳል። ህይወታቸውም ያለፈ አካላቸውም የጎደለ ወጣቶች እንዲሁም በእስርና እንግልት ያሳለፉ በርካታ ወጣቶች አሉ።
የለውጡ አካል ወደስልጣን እንዲመጣ የኦሮሚያ ወጣት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። የለውጡ አካል ከመጣ በኋላ ህወሓት ለውጡን ለማደናቀፍ ብዙ ሲጥር ቆይቷል። መንግሥትም ለሁለት ዓመት ታግሶ ወደሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ብዙ ጥረት አድርጓል። ይሁንና ህወሓት መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጸም ማህበራችን በጽኑ ነበር ያወገዘው።
በኋላም የመንግሥትን የህግ በማስከበር እርምጃ ደግፈን ወጣቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ስናስተባብር ቆይተናል። ለአገር አስቸጋሪ የሆነውን አካል ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ በሚደረጉ ጥረቶችም እንደኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር የምንደግፈው ጉዳይ ነው። ዘላቂ ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን ካስፈለገ ሽብርተኞች እኩይ ተግባራቸውን እንዲያቆሙ ተባብረን መስራት አለብን የሚል አቋም አለን።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት ቡድን አባላት ችግራቸው ከአንድ ክልል በተለይም ከአማራ ክልል ጋር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?
ከድር እንዳልካቸው፡– ህወሓት ችግሩ ከአንድ ክልል ጋር ብቻ አይደለም። ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው ችግሩ። የአሸባሪው ህወሓት ግጭት ከአማራ ክልል ብቻ እንደሚያያዝ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል።
ይሁንና ህወሓት የሚፈጥረው ችግር አማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብንም የሚነካ እና የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። አሸባሪው ህወሓት በሚፈጥረው ግጭት ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገባው ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው።
እንደክልላችን ወጣቶች መናገር የምችለው የህወሓት ቡድን ለሀገራችን ነቀርሳ እንደሆነ ነው። በአማራ ክልል ላይ በግልጽ በከፈተው ጦርነት የአጎራባች ክልልም ብቻ ሳይህን የመንግሥት ጦርን ህይወት ቀጥፏል። የትግራይ ህዝብም በእራሱ ከዚህ ነቀርሳ ነጻ እንዲወጣ በማሰብ ነው የህግ ማስከበር እርምጃ የተወሰደው።
ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተሰልፎ የህግ ማስከበር እርምጃውን የደገፈው እኮ የአማራ ህዝብ ብቻ አይደለም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ነው። አሁንም በተጨባጭ ቢታይ ህወሓት የጥሞና ጊዜውን ባለመጠቀሙ ወደግጭት ሲገባ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ የተገኘው የኦሮሞ ልዩ ኃይል፣ የሲዳማ ልዩ ኃይል፣ የአፋሩም የጋምቤላውም ሆነ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው።
ይህ ደግሞ የሚያሳየው ህወሓት የሚፈጥረው ችግር የኦሮሞውም፣ የሶማሌውም በአጠቃላይም የመላው ኢትዮጵያዊ ችግር መሆኑን ነው። ስለዚህ የህወሓት ሰዎች ከአንድ ክልል ጋር ብቻ ችግራቸው እንደሆነ የሚናገሩት ነገር ፍሬ አልባ ነው። ህወሓት የፈጠረው ችግር ከአማራ ብቻ ሳይሆን ከመላው ብሔር ብሔረሰቦች ጋር መሆኑን በግልጽ መታወቅ አለበት።
ግጭት የመፍጠርና ሀገር ለመበተን የተነሳን ኃይል በጋራ መመከት እንደሚገባ ሁሉ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተዋል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ ሳይል በኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለው ወጣት በሙሉ የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት አጀንዳ እየተቃወመው ይገኛል። ይህ እውነታ ደግሞ የሚያሳየው መላው ህዝብ አሸባሪን እንደማይደግፍ እና እንደማይታገስ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት ሰዎች በግልጽ አላማችን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው ብለዋል፤ እንደ ማህበር በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አይነት አስተያየት አላችሁ?
ከድር እንዳልካቸው፡– የህወሓት ቡድን በዋነኛነት የኢትዮጵያን መልካም የማይፈልጉ አካላት ተላላኪ ነው። በሀገራችን ላይ ብዙ ጫና እየደረሰብን እንደሆነ ይታወቃል። ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሀገራችን ሰላም እንዳትሆን እና ግድቡ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ከውስጥ ሆነ ከውጭ ባሉ አካላት ጫና አለ።
የአሸባሪ ቡድኑ ህወሓት ደግሞ የኢትዮጵያን ልማት ከማይፈልጉ መካከል ነው። ተረጋግተን የልማት ሥራዎችን ፣ የፕሮጀክት ግንባታዎችን እንዳናከናውን ሀገር ለመበጥበጥ ይሞክራሉ። ዋነኛው አላማቸው ኢትዮጵያን ማፈራረስ መሆኑን እና ለዚህ እቅዳቸው እንደሚሰሩ በግልጽ ተናግረውታል።
መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሞ ሀገሩ እንድትፈርስ የሚሰራን ኃይል ሊታገስ አይችልም። ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም፤ እናፈርሳለን ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ናቸው እራሳቸው የሚፈርሱት። እኔ እንደኦሮሚያ ወጣት የማስበው እኛ በዚህች ሀገር ላይ እያለን ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም።
ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ እና ለመበታተን ቢመኝም መላው ህዝብ በአንድነት ስለተቃወመው እቅዱ አይሳካለትም። ለእራሳችንም ህልውና እና ለሀገራችን ልዓላዊነት ስንል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንሰለፋለን። እንደኦሮሚያ ወጣት በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከመከላከያ ጎን እንቆማለን።
ለእራሳችንም ስንል ልዓላዊነታችንን ለማስከበር ወጣቱ በአካል ሄዶ እስከመሰለፍ ደርሷል። ሀገሩ እንድትፈርስ የማይፈልግ ዜጋ ሁሉ ደግሞ ህወሓትን መታገል አለበት። እንደኦሮሚያ ወጣት ማህበርም በየደረጃው ምክክር እያደረግን ነው። ወጣቱን በማወያየት ክልላችንና ሀገራችንን እንዴት መጠበቅ አለብን በሚሉ ጉዳዮች ወጣቱን አሰማርተን እየተነጋገረበት ይገኛል።
ሀገራችንን የሚበታትን ኃይልን ለማስቆም በእራሳችን ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ዝግጅት እያካሄድን ነው። ሀገር ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ወጣቱን ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው እናስተባብራለን።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ለአቅመ ውጊያ ያልደረሱ ህጻናትን ከፊት ማሰለፉ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ታይቷል፣ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
ከድር እንዳልካቸው፡– የጥሞና ጊዜውን ያልተጠቀመው ህወሓት ህጻናትን ለግጭት ማሰለፉን በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት እየተስተዋለ ነው። ህጻናትን በጦርነት ማሰለፉ የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበሩ ያወግዘዋል።
ቡድኑ አካላቸው ያልጠነከሩ ህጻናትን በውጊያ ማሰለፉ እጅግ አሳፋሪ ነው። በተጨማሪ አደንዛዥ እጾችን በመስጠት የህጻናቱን ህይወት እያበላሹ በመሆናቸው አሳዛኝ ተግባር ሆኗል። እድሜያቸው 12 እና 13 የሆኑ ወጣቶችን ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጦር መሳሪያ አስይዞ ማሰለፉ ለጥፋት የማይመለስ አሸባሪው መሆኑን ያሳያል።
ህጻናትን ከፊት በማሰለፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መጣጣርም በዓለም አቀፍ ህግ ጭምር የሚያስጠይቅ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።የዓለም የህጻናት መብት የቆሙ ተቋማት ይህን ኢሰብአዊ ተግባር መቃወም አለባቸው።
ህወሓት በጦር ግንባሮች አካላቸው ያልጠነከሩ ህጻናትና ብቻ ሳይሆን ሽማግሌዎችንም ነው ያሰለፈው። ከዚህም አልፎ መሸሽ የማይችሉ አካል ጉዳተኞችን ጭምር በውጎያ የማሰለፍ አዝማሚያ አለው።
መከላከያም ወጣቶችንና አረጋውያን ከፊት መሰለፋቸውን አይቶ እና የእርሻም ጊዜ ስለሆነ የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋል በሚል ነበር ጊዜ የሰጣቸው። አሸባሪው ቡድን ግን ይህን እድል ባለመጠቀሙ በድጋሚ ህጻናትን አሰልፎ ለግጭት ተነሳስቷል።
ጉዳዩን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን እንዲረዳ ማህበሩም እየሰራ ይገኛል። ኢሰብአዊ ተግባር በክልል እየተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ የበኩላችንን ድምጽ እያሰማን ነው። ወጣቶችም በተለያዩ የኢንተርኔት አማራጮች ይህን ኢሰብአዊ ድርጊት እየተቃወሙት ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ህጻናትን ለግጭት ማሰለፉ በቀጣይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እስከምን ድረስ ነው?
ከድር እንዳልካቸው፡- ህጻናትን በውጊያ ቦታዎች ማሰለፉ ዞሮ ዞሮ ትግራይ ክልልን መጉዳቱ አይቀርምና ህወሓት ድጋሚ ድጋሚ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
በቀጣይ ለሥራ የሚሰማራውን የልማት ኃይል ነው አሁን ላይ ህወሓት በግጭት እየማገደ ያለው። ጦርነቱ እየገፋ በሄደ ቁጥር ደግሞ ጉዳቱንም የከፋ ስለሚያደርገው እንደማህበር የህወሓትን ራስ ወዳድ አካሄድ ያሳስበናል።
ህወሓት የጥሞና ጊዜውን በመጠቀም በክልሉ እርሻ እንዲከናወን እና ህጻናት ወደትምህርት እንዲመለሱ ነበር ማገዝ ያለበት። አሁን ግን ግጭቱን በማስፋፋቱ ስለትምህርት ማሰብ የነበረባቸው ህጻናት ናቸው መሳሪያ የሚሸከሙት፤ ይህ ደግሞ በትውልዱ የትምህርት እና የቀጣይ ህይወት ላይ በቸልተኝነት መፍረድ ነው።
መከላከያም እነዚህን ህጻናትና አረጋውያንን ጭምር ማዳን ስላለበት ነው የህወሓት ሰዎችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራ ያለው። እንደ አጠቃላይ ካየነው ግን ህወሓት እራሱ በጀመረው ግጭት የትግራይ ወጣት ቀጣይ ህይወት ጉዳት ቢደርስበትም የሚጨነቅ ቡድን አይደለም። በዚህ የተነሳ የትግራይን ወጣት የማይገባው ችግሩ ውስጥ ከቶታል።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ በአሸባሪነት የተፈረጁት ሸኔ እና ህወሓት በአሁኑ ወቅት ያላቸው ግንኙነት እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ለማየት ሞክሯል?
ከድር እንዳልካቸው፡- የአሸባሪው ሸኔ ጉዳይ በቀጥታ ከህወሓት ጋር ይያያዛል። እኛ ክልል ውስጥ በህገወጥ መንገድ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ሸኔ ነው። ህወሓትና ሸኔ ደግሞ በተናበበ መንገድ ነው ለጥፋት የሚንቀሳቀሱት።
ሁለቱም ከግብጽና ከሱዳን ተልኮና መሳሪያ ተቀብለው ነው ተልዕኮውን የሚያስፈጽሙት። ተልዕኳቸው እናንተ ግጭት ፍጠሩልን ከዚያም በጋራ መንግሥትን እናንሳው በሚል ላይ የተመሰረተ ነው። በየቦታው ግድያ እና መፈናቀል እንዲኖርም ነው ሁለቱም የሚጥሩት።
በሀገር ሰላም ስታጣ ደግሞ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸምም አቅም አይኖርም ከሚል ምኞት ነው ተቀናጅተው የሚንቀሳቀሱት። ስለዚህ ይሄን ለመከላከል ወጣቱ ተደራጅቶ አካባቢው ላይ የሚያየውን ማንኛውንም ችግር ሊፈጥር የሚችል ንቅስቃሴ ማሳወቅና በእራሱ መከላከል ነው።
ለአብነት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲካሄድ ወጣቱ በየምርጫ ጣቢያው ተደራጅቶ ቀንና ምሽት ሊፈጠር የሚችል የጸጥታ ችግር እንዳይኖር ሲሰራ የቆየው። ከደህንነት አካላት ጋር በመተባበር የውጭ አካላት ያዘጋጀውን ሁከት ለማስቀረት ሰርቷል።
ልክ በዚህ መልኩ በእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ንቁ በየአካባቢው እና በአካባቢው ሀገር ለመበጥበጥ የተዘጋጁ አካላት ሰርገው እንዳይገቡ የሚቻለውን እያደረገ ነው። በህብረተሰቡ ትብብር ደግሞ የህወሓትን እና የሸኔን የጥፋት አላማ ማስቆም ይቻላል። ማህበራችንም የጥፋት ቡድኖቹን አላማ ያደረጉት ወጣት እኩይ ተግባራቸውን እንዲያጋልጥ እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከህወሓት ጋር በተያያዘም ይሁን በሌሎች ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የውጭ ኃይሎች የሚያሳድሩትን ጫና በመከላከል ረገድ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ?
ከድር እንዳልካቸው፡- የህወሓት ጉዳይም ሆነ የህዳሴው ግድብ እንዲሁም ሌሎች የውስጥ ጉዳያችን ላይ የሚያሰማሩት ተላላኪዎች መኖራቸው አይቀርም፤ እራሱ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓትም እና ሸኔም ተላላኪዎች ናቸው።
በክልላችንም ሆነ በትግራይ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ህገወጦች የውጭ አካላትን አላማ ለማስፈጸም የሚሰሩ መሆናቸው ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ወጣቱን በሰፊው ማወያየት እና ቡድኖቹን አላማቸውን እንዳያስፈጽሞ እያንዳንዱ ወጣት እንዴት መከላከል አለበት የሚለው ላይ ውይይት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ እንደማህበር የጀመርናቸው መጠነ ሰፊ ሥራዎች አሉ። የውጭ ተጽእኖው አላማ ሀገርን በማዳከም የእራሳቸውን አላማ ማስፈጸም ነው። ለዚህ ደግሞ ብጥብጥ መፍጠር አመቺ እንደሆነ አስበው ይንቀሳቀሳሉ። የህዳሴው ፕሮጀክት እንዳይጠናቀቅም ሆነ እንዳንጠናከር ለማድረግም ግጭት ያስነሳሉ።
ይህ አላማ ደግሞ የግብጽም ሆነ የሱዳን ፍላጎት ተጨምሮበት የሌሎችም ሀገራት ጫና አለበት። ወጣቱ ደግሞ ይህንን በሀገር ላይ የመጣ ጫና ተገንዝቦ መዘጋጀት ይኖርበታል። መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እራሱ የተገነዘበውን ለማህበረሰቡ ማሳወቅና በጋራ ለመከላከል መነሳት ያስፈልጋል።
አሁን ሀገራችን አንድ ሆነን ለጋራ ጥቅማችን የምንነሳበት ጊዜ ነው። በአንድነት ቆመን ስንነሳ ደግሞ የሚበግረን ኃይል አይኖርም። ህብረተሰቡም ለሀገር አላማ በመቆም አንድነቱን ይበልጥ ማሳየት አለበት። ማህበራችንም አንድነቱን ይበልጥ በሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ላይ የማስተባበር ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በጸጥታ መዋቅር ውስጥ ገብተው ሀገራቸውን ማገልገል የሚችሉ ወጣቶችን ከማስተባበር አኳያ ምን የምታከናውኑት ሥራ አለ?
ከድር እንዳልካቸው፡- እድሜው በጸጥታ መዋቅር ውስጥ ገብቶ እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድለት ወጣት በአቅሙና በችሎታው እንዲሳተፍ እናበረታታለን። በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ገብቶ እንዲሳተፍም ባገኘነው አጋጣሚ ጥረት እያደረግን ይገኛል።
በቅድሚያ ወጣቶችን በብዛት ሰብስበን ስለጉዳዩ አወያይተናል። አሁን ሀገራችን ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አንስተን ችግሩን ለመቅረፍ የወጣቱን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ተነጋግረናል። ከውይይታችን በኋላ መግባባት ላይ ስንደርስ በየአካባቢው ወጣቱ በመከላከያ አባልነት እንዲሳተፍ ምዝገባ እያደረግን ነው።
በዚህም ከወጣቱ ጋ ያለው ምላሽ መልካም ነው። በርካቶች ፍቃደኝነታቸውን ገልጸው በሚመለከተው አካል በኩል ምዝገባቸውን እያከናወኑ ይገኛል። መስፈርቱን ያሟሉ ወጣቶችም በሰራዊቱ የስልጠና ማዕከላት አስፈላጊውን ስልጠና እያገኙ ነው።
ሀገር መጠበቁም ላይ ወጣቱ እንዲሳተፍ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር የበኩላችንን ግንዛቤ ሰጥተናል። ወጣቱም ሀገር ለማፈራረስ የሚያስብን አካል ለመታገል ያሳየው ተነሳሽነት አኩሪ ነው። መላው ህዝብ ለህልውናው ሲል የሚመጣበትን ኃይል ለማስቆም መልካም እንቅስቃሴ እያሳየ ነው።
ህወሓትን ከጥፋት አላማ ለማስቆም ወደሰሜን የሀገራችን ክፍል ካቀኑት የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት በኩልም በርካታ ወጣቶች ተሳትፎ እያደረጉ ነው። ሀገርን በመጠበቅ ረገድ ወጣቱ ግንባር ቀዳሚ እንዲሆን በቀጣይም እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር በህዳሴው ግድብ ተሳትፍ ወጣቱን በማስተባበር ረገድ ምን አይነት ሥራ እያከናወናችሁ ነው?
ከድር እንዳልካቸው፡- በአባይ ጉዳይ ላይ አይናችንም ሆነ ቀልባችን ከህዳሴው ግድብ አይነሳም በሚል እየተንቀሳቀስን ነው። በተጓዳኝ ሌሎች ሥራዎችም ቢኖሩብንም የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ሥራ ግን በዋናነት ከሚከናወኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው።
ከሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ወጣቱ የህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ እንዲያከናውን እያደረግን ነው። ባለፈው ሳምንት ጅማ በደሌ ላይ እንቅስቃሴውን ከፍተናል። በርካታ ወጣቶች ቦንድ ለመግዛት ያላቸው ተነሳሽነት አስደሳች ነው።
ከዚህ ባለፈ ወጣቶች እያቀናጀን ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ ቦታው ወስዶ ለማስጎብኘት ጥረት እያደረግን ይገኛል። በጉልበት፣ በገንዘባችንም ሆነ በምንችለው ሁሉ ለህዳሴው ግድብ እናበረክታለን የሚል እምነት አለን፤ የፕሮጀክቱን ሂደት በትኩረት እየተከታተልን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቱን በማስተባበር ረገድ ምን ሰራችሁ?
ከድር እንዳልካቸው፡- እንደወጣት ማህበር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በስድስት ዋና ዋና ዘርፎች ከፍለን እያከናወን ነው። በነዚህ ስድስት ዘርፎች ስር 22 ዓይነት ሥራዎች አሉን።
ለአብነት የደም ልገሳ፣ የአረጋውያን ቤት መጠገን፣ ችግኝ የመትከል፣ የአካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን መሬት ማረስ፣ የክረምት ማስተማር አገልግሎት እና ሌሎችም አገልግሎቶች ተካተዋል።
የአረጋውያንን ቤት እድሳትን ብናይ ወጣት ማህበሩ እራሱን ችሎ 22 ሺህ 600 ቤቶችን ለማደስ እቅድ ይዟል። ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን አስተባብረን ከሰራን ይህን መፈጸም አያቅተንም በሚል እያከናወነው ይገኛል። እስካሁን 8ሺ 620 ቤቶችን በኦሮሚያ መጠገን ተችሏል።
በአረንጓዴ ልማት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአንድ ቀን ብቻ 24 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወጥተን 25 ሚሊዮን 680 ሺህ ያክሉን ተክለናል። ዘንድሮ በተለየ ወጣቶችን ብቻ አስተባብረን ሙሉ ኦሮሚያ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ችግኝ እንዲተክሉ አድርገናል።
አራት ሚሊዮን ወጣቶች ናቸው በበጎ ፍቃድ ሥራው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት፤ በአጠቃላይ ወጣቱ ብቻ በክልሉ የተከለው ችግኝ 118 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ ሥራ እስከ መስከረም ወር ሲቀጥል ቁጥሩ ከፍ ይላል። እኛም እስከ 350 ሚሊዮን ችግኞች ወጣቱ ብቻውን መትከል አለበት የሚል እቅድ አለን።
ከዚህ ባለፈ የደም ልገሳ በተለያዩ ጤና ተቋማት እና በቀይ መስቀል እየተከናወነ ነው። በክረምት ሴቶችንና ህጻናትን በማሰባሰብ ወጣቶች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ይገኛል። በአጠቃላይ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ሀገርን ሊጠቅም በሚችል መልኩ ተጠናክረው እየተከናወኑ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ ከንትርክና አሉባልታ ወጥቶ በሚጠቅመው ነገር ላይ እንዲያተኩር ከማገዝ አኳያ ምን አይነት ተሳትፎ አላችሁ?
ከድር እንዳልካቸው፡- አንድ በጎ ነገር በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ አንድ ሆነውና ተደራጅተው በመደማመጥ እየሄዱ ያለበት ሁኔታ አለ።
የጊዜው ሀገርን የማፈራረስ ሴራ ያላቸው አካላት በማህበራዊ ሚዲያውም የሚያስተላልፉት ቅስቀሳና አላስፈላጊ ንትርክ ቢኖርም ወጣቱ ስለጉዳዩ ምንነትና አስፈላጊነት ግንዛቤ እንዲያገኝ ነው በቅድሚያ እየሰራን ያለው።
እውነታውን በአግባቡ ሲረዳ እና የንትርኩ ፈጣሪዎችን አላማ ሲረዳ በቀጣይ እራሱ ነው ለምን ብሎ የሚከላከላቸው። በየደረጃው ያለው የኦሮሚያ ክልል ወጣት ይህን ሴራ እና ጨዋታ በአግባቡ እንዲነቃበት ያስፈልጋል። ለግጭት የሚዳርጉ መረጃዎችን ላይክ፣ ሼር ከማድረግ እና ከመለጠፍ ተቆጥበው ሀገር የሚገነባ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ ጥረት እናደርጋለን።
ለዚህ ደግሞ ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋልና ሙያውን በተከተለ መንገድ እያከናወንን ይገኛል። አንድ ሀገር ነው ያለን፣ ተረባርበን አሁን ያለብንን ጫና ካልመከትን ደግሞ የውጭውም ሆነ የውስጥ አካላትን መቋቋም አንችልምና አንድነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን በስፋት እያደረግን ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሩ ጠበቃ ሆኖ የሚቆምበትን መንገድ እናስተምራለን። ከአላስፈላጊ የፖለቲካ ንትርክ ወጥቶም እውቀትን በሚሰጡ እና መልካምነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፍ እናበረታታለን።
አንድም የሃሰት መረጃ ማጋለጥ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ከመከላከል አኳያ ያለውን ጠቀሜታ በማስገንዘብ ላይ ነን። ወጣቱ ማህበራዊ ድረገጾችን ሲጠቀምም ሀገሩን ሊደግፍ በሚችልበት መንገድ በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ጭምር ስልጠና እንሰጣለን።
ለአብነት በህዳሴው ግድብ ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሃሰት መረጃዎች ሲሰራጩ በማጋለጥና እውነታውን ከቦታው ሆኖ በማስረዳት እንዲሳተፍ ክህሎቱን እያሳደግን ነው። ወጣቱ ከግጭት ቀስቃሽ እና ጊዜ ከሚያባክኑ ንትርኮች ወጥቶ ለቀጣይ ህይወቱ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር በባለሙያ የተደገፉ አሰራሮችንና ምክረ ሃሳቦችን በማሰራጨት የበኩላችንን እተወጣን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭት ለመቀስቀስ እና ወጣቱን ወዳልተፈለገ ንትርክ ለመውሰድ የሚጥሩትን ወጣቶችን በምን መልኩ ለመረቅ ሙከራ ታደርጋላችሁ?
ከድር እንዳልካቸው፡- ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚለጥፉትን እና ሆን ብለው ችግር ለመፍጠር የሚሰሩትን ከህብረተሰቡ የሚደበቁ አይደለም። ወጣቶች በየአካባቢያቸው እርስ በርስ ይተዋወቃሉ።
በአንድ በኩል ጥፋት የሚያከናውኑ ወጣቶችን በአካባቢያቸው በሚገኙ ጓደኞቻቸው እና በቅርብ ሰዎቻቸው ምክር እንዲያገኙ እናደርጋለን። ይህ የምትሰራው በፌስቡክም ሆነ በሌሎች የኢንተርኔት አማራጮች የምታስተላልፈው መልዕክት አግባብ አይደለምና ታረም የሚል መልዕክት ከቅርብ ሰዎቻቸው እንዲደርሳቸው ይደረጋል።
ይህም ካልሆነ እና የማይታረሙ ከሆነ ደግሞ መረጃውን ለሚመለከተው በማሳወቅ እንዲስትካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን። በዚህ መልኩ ካየነው በአጭር ጊዜ የተለየ ለውጥ ያመጣል ማለት ባይቻልም እየሄድንበት ያለው መንገድ ግን የተወሰኑ ለውጦችን አስገኝቷል።
አሁን ላይ ወጣቱ በመደማመጥ መንፈስ ንግግሮችን ያከናውናል፤ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ድጋፉን በመስጠት አጥፊዎችን እየተቃወመ ነው። ይህን መነሻ አድርገን ካየነው ጥሩ ለውጦች አሉ ማለት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- እንደአንድ የማህበር ፕሬዚዳንት ወጣቱ ሀገሩን ወዳድ ሆኖ እንዲኖር ምን ያስፈልጋል ይላሉ?
ከድር እንዳልካቸው፡- ወጣቱ ያለፉትን ዘመናት የሀገራችንን ችግሮች በአግባቡ እንዲረዳ እና የእራሱ አስተዋጽኦ ምን መሆን እንዳለበት ጠንቅቆ በቤተሰብም ሆነ በአካባቢ ደረጃ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ወጣቱ ለሰላምና ለልማት ያለው ፍላጎት በእራሱ እያደገ ከመጣ ሀገር መውደዱን በሥራ እየገለጸ ይሄዳል።
ሀገራችን ስትረጋጋ ወጣቱ ሀገር ወዳድነቱን በኢኮኖሚው ተሳትፎ እንዲያረጋግጥ በማድረግ በሰፊው እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ይገባል። የወጣቱ የሥራ አጥነት ችግሮችን ሊቀርፉ የሚችል በርካታ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ያስፈልጋል። ሥራ ሲገኝ እና ሥራ መፍጠር ሲችል የበለጠ ምርታማ መሆን ይችላል፤ ያኔ ሀገር ወዳድነቱንም በይበልጥ አጠናክሮ መሄድ ይችላል።
ወጣቱም ደግሞ ሥራ ከመናቅ አስተሳሰብ እንዲወጣ የተለያዩ የግንዛቤ ሥራዎች ያስፈልጉታል። ትንሽ የሚለውንም ሥራ መስራት ከቻለ ከአልባሌ ጉዳዮች ይርቃል፤ ለቤተሰብ፣ ለወገን ለሀገር ይበልጥ ማሰብ ይጀምራልና ሀገር ወዳድነት በሥራ ሊደገፍ ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ ታሪኩንና ማንነቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ በማድረግ ሀገሩን የበለጠ እንዲረዳ ማድረግ ይገባል። ሀገሩን የበለጠ ሲያውቅ ለመጠበቅ ይነሳሳል በተጨማሪም ሀገር ወዳድነቱም የበለጠ እያጠናከረ ይሄዳል።
በዋናነት ወጣቱ እምቅ ጉልበት እና ኃይል ያለው በመሆኑ ለጥፋት አላማ እንዳይውል ከቤተሰብ ከአካባቢ እና ሀገር አቀፍ ደረጃ የጥንቃቄ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ። በአንጻሩ ወደበጎ ሥራዎች እንዲሳብ እና ሰብአዊነት የሚሰማው ንቁ ዜጋ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ከድር እንዳልካቸው፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም