‹‹ከእንግዲህ በኋላ ዓባይ የግጭት ምንጭ ሳይሆን የትብብር፣ በጋራ የመልማት፣ በኢኮኖሚ አብሮ የማደጊያ ምንጭ ነው ። ከዚህ በኋላ መንፈሱ ይቀየራል ። የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በግድ ካልፈረማችሁ የሚለው ሀሳብ ሁሉ ይቆማል›› በማለት የተናገሩት በኢትዮጵያ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ ናቸው።
አቶ እንዳለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቁን አስመልክተው እንዳሉት፤ “ዓባይ ከአሁን በኋላ መንፈሱ ይቀየራል። የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በግድ ካልፈረማችሁ የሚለው ሀሳብ ሁሉ ይለወጣል ። አሁን የሚፈረመው ፍትሐዊነትን ፣የጋራ ተጠቃሚነትንና አብሮ ማደግን መሰረት ያደረገው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ነው። በአፍሪካ ህብረት የበላይነት የምንለው አስተሳሰብ ነው ወደፊት የሚመጣው ። ግብጽና ሱዳን የእነሱ አራጋቢዎች ጭምር ነው ሳይወዱ በግድ የእኛን ሀሳብ የሚቀበሉት።
“ የመጀመሪያው ዙር ውሀ ሲሞላ ጸጥ አሉ፤ አሁንም ሲሞላ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ይሄ እንደገና ሉዓላዊነታችንና ነጻነታችን የተወለደ ያህል ነው እንዲሰማን የሚያደርገን ። ይሄ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዋ ኢትዮጵያን የሚመጥናት እንዲሆን በመደረጉ ነው ። ይሄ የፓርቲ ጉዳይ አይደለም ። ፓርቲ ይመጣል ይሄዳል፤ አገር ግን ቋሚ ነው ። ስለዚህ አሁን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ነው፤ ሁሉም ባለመብት ነው ፤ ሁሉም እኩል የሚሰራ ነው ። ህጻን አዋቂው፤ እናቶች ሳይቀሩ ነው ለህዳሴ ግድብ የተባበሩት። እነዚህ ሕዝቦች ናቸው መቀነታቸውን እየፈቱ የሰሩት፤ ጨርሱት ሲሉ የከረሙት።
“እናቶች የተሳተፉበት ጉዳይ በዓለም ላይ ከሽፎ አያውቅም ። ምክንያቱም እናቶች የሚሰለፉት ለጥሩ ነገር ነው ። ለመጥፎ ነገር እናቶች አይሰለፉም ። ለአንድነት፣ ለፍቅር ፣ ለጋራ እድገት ነው የሚሰለፉት ። ይሄ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነው ። በዚህ ልክ ነው የሀገራችን የዲፕሎማሲ ፍልስፍና የተቀየረው ። የዜግነት ዲፕሎማሲ ፍልስፍና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚመጥን፣ የሰለጠነ አስተሳሰብ ነው ። በዲፕሎማሲ ጉዳይ መንግሥት አሁን ይመራል እንጂ ስራውን የሚሰሩት ሁሉም ዜጋና ወዳጆቻችን ናቸው።
“አሁን ሁለት ነገር አለ ። አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አድዋው ጊዜ መንፈሱ ተነቃቅቷል። አድዋን ስናሸንፍ ይወጉን የነበሩ አገሮች ቶሎ መጥተው ኤምባሲውን፣ ፊርማቸውን ነው ያስቀመጡት ። አሁን የምንጠብቀውም ይህንኑ ነው ። እነ ግብጽና ሱዳን የእነሱ አለቆች ጭምር መጥተው ከእናንተ ጋር እንሰራለን፣ እንነግድ… ይላሉ ። ይሄ ጥርጥር የሌለው እየሆነ ያለና የሚሆን ጉዳይ ነው ። ይሄ ለአገራችን ትልቅ በረከት ነው ።
“ሁለተኛው ውስጣዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር ነው ። የአሸናፊነት መንፈሳችን ወደፊት ይሄዳል። ነገር ግን መጠንቀቅ ያለብን ጉዳይ ደግሞ አለ። ጥሩ ነገር በሚሰራ ሰዓት ጠላቶች ተኝተው ያድራሉ ማለት አይደለም ። እነሱም ጥፋታቸውን የዛኑ ያህል ውስጣችንም ገብተውም ሆነ በውጪ ሆነው ያሳድጋሉ ። ስለዚህ የውስጣዊ አንድነታችንን ሪፎርም ይበልጥ ወደፊት ማስኬድ ያስፈልጋል። ወዳጅ ማብዛት ጠላት መቀነስ ይገባል ። በውስጥ ስንሰራ ደግሞ በዲሞክራሲ መንፈስ መስራት ያስፈልጋል ። ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራሲ የሚመጥኑ ናቸው ። የበላይነቱን ከውስጥም ከውጪም ማስከበር ፣መልካም አስተዳደር ማስፈን ፣ሙስናን መቀነስ ፣ዘረኝነትን ይበልጥ መድፈቅ ያስፈልጋል። በነጻነታችን በሉዓላዊነታችን ላይ ምንም የማንደራደር መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን።
“የያዝነውን አንድነት ይበልጥ ማጠናከር ፣ ለ40 ዓመት የተጫነብንን ዘረኝነት ከጫንቃችን አስወልቀን መጣል ነው ። የሰበሰበን ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነው ታላቅነትን ያጎናጸፈን እንጂ በመንደር መሰባሰብ አይደለም ። አሁን ብዙ ነገሮችን ወደፊትአራምደናል ። ነገር ግን ብዙ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑም መዘንጋት የለበትም ። አንዱ አንዱን የሚወቅስበት ጊዜ ላይ ሳንሆን ተባብረን የምንሰራበት ወቅት ነው ። የህዳሴው ግድብ እኮ እውን የሆነው በእኔ ነው፤ በአንተ ነው፤ በአንቺ ነው፤ በእኛ ነው ። ባለቤቱም እኛ ነን ። ኢትዮጵያ የእኔ ነች በአገሬ ጉዳይ አልደራደርም ብሎ ሁሉም ዜጋ አብሮ መስራት አለበት። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአገር አንድነት፣ በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ መደራደር እንደማይቻልና ቀይ መስመር መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ለጥቅም፣ ገንዘብ ማግኛ ሊያደርጉ የሚያስቡ አሉ ። የሀገር ጉዳይ ቀይ መስመር መሆኑን ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል።
“የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት በድል መጠናቀቁ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ትልቅ ደስታ ፈጥሯል ። ይሄ ጉዳይ ቀላል አለመሆኑን አቶ እንዳለ ይናገራሉ ። ብዙ ችግሮች አሳልፈናል ። ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው በርካታ ዓመታት ለዓለም ያበረከተቻቸው ብዙ ነገሮች አሉ ። አንዱ ነጻነት ነው ። ነጻነት ማለት በቅኝ አለመያዝ ማለት ብቻ አይደለም ። ትርጉሙ ከዛ በላይ ነው ። ለሌላውም ሞዴል ሆኖ መታየት ነው ። ይሄን የነጻነትን ዋጋ ለአውሮፓውም ለአረቡም ሀገር አሳይታለች። ከዚህ አንጻር ሁሉም ሰው እኩል መሆኑንም ሌሎች እንዲረዱ አድርጓለች ።
“ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፈተናው በጣም ብዙ ነበር ። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በጣም ትልቅ ፈተናዎች በውስጥም በውጭም ገጥመዋታል ። ላለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነት ፕሮጀክት ለመስራት ሳይሆን እርስ በእርስ በዘር እንድንከፋፈል ነበር የሚፈለገው ። ይሄንን የሚያስፈጽም ቡድን አቋቁመዋል ። ዋናው ስራቸው ኢትዮጵያውያን እንዲከፋፈሉ፤ ትልቅነታቸው እንዳይታይ፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዳይሰሩ ሲደረግ ነው የቆየው ፤ ባለፈው 30 ዓመታትም አሸባሪው ህወሓት ይሄንኑ ሲያስፈጽም ነው የቆየው ። የህዳሴ ግድቡ ያኔ ይጀመር እንጂ እንደማይፈጸም ብዙ ዓለም ያውቅ ነበር ። ከፋፍለናቸዋል ፤አይፈጽሙትም ነበር የሚሉት ። ህወሓትም ምን ያህል ፕሮጀክቱን ገድሎት እንደነበር፣ በሙስና አጨማልቆት እንደነበር ይታወቃል ። ኢትዮጵያውያን ግን የታሰበልንን መከፋፈል እንቢ ብለው ነው ቡድኑን ያስወገዱት ። ከዚህ አንፃር ብቻ ሲታይ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ማሰብ ይቻላል።
“በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የሚመራው ምዕራባውያኑ ጁንታውን ከአገር ውስጥ ፤ ከውጪ ደግሞ ግብጽን ወኪል አድርገው ነው የተንቀሳቀሱት ። በቀይ ባህርና አካባቢው ግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ወኪል ሆና ይሄንን ነው የምታራምደው ። ከዚህ አንጻር ነው እስኪ ህዳሴ ግድብ ብለው ይነኩና እየተባለ የነበረው ። በዚሁ መሰረት በመጀመሪያው የውሀ ሙሌት ወቅት የነበረው ፉከራና ማስፈራረት ቀላል አልነበረም ። አሁንም ለሁለተኛው ሙሌት ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ ሁላችንም እናውቀዋለን ። የእነሱም ደጋፊዎች የውስጡን ጨምሮ አንድ ጠብታ ውሀ ትነኩና ነበር ሲባል የነበረው ። ከሁሉም በላይ ውሸታቸው ጫፍ ደርሶም ነበር ። በቃ አለቀ ሁለት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሊጎዳ ነው፤ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ሊጎዳ ነው የሚል ነበር ዘመቻው ። ኢትዮጵያ ግን እስካሁን ድረስ በሌሎች አገሮች ጉዳይ ጣልቃ ገብታም ሆነ ጎድታ አታውቅም ። ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ አቋሟ የጋራ ተጠቃሚነት የሚል ነው ፤ ይሄ የኢትዮጵያ ሞራላዊ ዲፕሎማሲና ሞራላዊ የመንግሥት አሰራር እንደምትከተል ያሳየንበት ነው ።
“ለውጡ እውነተኛ ለውጥ መሆኑን ያረጋገጥንበት ነው ። ይሄ የአንድነታችን ፣ የሉዓላዊነታችን ትልቅ ምልክት ነው፤ በዚሀ ጉዳይ የሚመጣብንን ሁሉ ለመቀበል ወስነን ነው። የዲፕሎማሲ ሥራችን ግን ትልቅ ውጤት አምጥቷል ። የአድዋ መንፈስ በድጋሚ እንዲንቀሳቀስና በድጋሚ ወደፊት እንዲራዘም የሆነበት ነው ። ለዚህ ትልቅ ድል የበቃነው በዋናነት በአንድነት መጓዝ በመቻላችን ነው። አንድነት ያለን ትልቅ ሕዝቦች ስንሆን ያሰብነውን አሳክተን ዓለም ፊት እንቀርባለን ። ስንከፋፈልምን ያህል እንደምንናቅ አይተነዋል ። እነአሜሪካን እንኳን በቅርቡ ስለ አገር ብቻም ሳይሆን ስለመንደራችን እጃቸውን አስገብተው ሊነግሩንና ሊያምሱን ነበር የፈለጉት ።በምርጫው በሌላውም የሚታዩ ጣልቃ ገብነቶች ነበሩ። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የመረጡት ነጻነትን ነው፤ ሉዓላዊነትን ነው፤ታላቁን ህዳሴ ግድብ እንሞላዋለን የሚለውን ነው ። የመረጡት ግለሰብ አይደለም ። ይሄ አሁንም ወደፊት እንድንጓዝ ሞራል የሚሰጠን ብርታት የሚሆነን ነው ። ለመላው አፍሪካ ለመላው ጥቁር ጭምር እንደገና ኢትዮጵያ ያቀረበችው ትልቅ የድል ብስራትና የአሸናፊነት መንፈስ ነው ።
“ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደዚህ ወደፊት ሊጓዝና እውን ሊሆን የቻለው በዲፕሎማሲው ነው። ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲውን ፍልስፍና ቀይራለች። በተለይ ከለውጡ ወዲህ አስተሳሰቡን ቀይራለች። ከለውጡ በፊት የነበረው ፍልስፍና አገር የምትፈልገውን ሳይሆን የተወሰኑ ዲፕሎማቶችና ኃላፊዎች የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ነበር የሚያደርጉት። አገሪቱ የምትፈልገው ትልልቅ ጉዳዮች አሉ ። ኢትዮጵያን የሚመጥን ዲፕሎማሲ አልነበረም የምታራምደው ። የአንድ ግሩፕ ዲፕሎማሲ ያንን ግሩፕ ሊጠቅም የሚችል ነው ። ዲፕሎማቶቹ ነቅተው የሚሰሩት ያንን ቡድን ወይም ፓርቲ እንዲያገለግል አድርገው ነው ። በሳይንሱ ግን ዲፕሎማሲ ለአገር ነው፤ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ወዳጆች ጭምር ነው። ነገር ግን ይሄ አልሆነም ። አልፎ አልፎ ጥሩ ዲፕሎማቶች እንዳሉት ሁሉ አብዛኞቹ የሚሰሩት እውቀታቸውን የሚመጥን፣ አእምሯቸው ያሰበውና ያሰላሰለውን ፤ ለአገሪቱ የሚያስፈልገውን ሳይሆን በታዘዙት ልክ ብቻ ነው ። ከዛ ማለፍ አይችሉም። ካለፉ በህይወታቸው ፈርደው ነው፤ ቡድኑ ጨካኝ ነው፤ አገሩን የማይወድ ነው ። ሌላው ቀርቶ የመጣበትን ማህበረሰብ የማይወድ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተቀረጸ ነው ። በዚህ የተነሳ ዲፕሎማሲው የተበላሸ ነበር ። ነገር ግን በዲፕሎማሲ የአገር አንድነት የሚጠበቀው ቀንና ሌሊት ያለ እረፍት ተሰርቶ ነው።
“አሁን ግን ይሄ አስተሳሰብ ተቀይራል። ወደ ዜግነት ዲፕሎማሲ ተገብቷል። ይሄ ዓለም በአሁኑ ወቅት የሚያራምደው ምዕራባውያንና ያደጉት አገሮች የሚከተሉት ዲፕሎማሲያቸውን ለዜጎቻቸው መስጠት ነው ፤በውጪም በውስጥም ያለው ዜጋ በአሁኑ ሰዓት አያገባኝም አይልም ። በምርጫም በሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሁሉ ለምንድነው አያገባኝም የማይለው ከተባለ ፍልስፍናውን መቀየር ተችሏል። ስለዚህ ከቡድንተኝነት ዲፕሎማሲ ወደ ዜግነት ዲፕሎማሲ ተቀይሯል። ሁሉም ሰው የአገሩ ጉዳይ ይመለከተዋል ። ለዜግነት ዲፕሎማሲ የሚያስፈልግ መደላድል መንግሥትም እያዘጋጀ ነው ። አሁን ዓለም አንድ የሆነችበት ሰዓት ላይ ነን ። የሚያስፈልገውና ውጤታማ የሚያደርገውም የዜግነት ዲፕሎማሲ ነው ። ስለዚህ ሁሉም ሰው የማይሰራ ከሆነ የምንፈልገው ነገር አይሳካም። አንዳንዴ በዲጅታል ዲፕሎማሲው ልንሸነፍም እንችላለን ። በደንብ ባለመጠቀም ምክንያት።
“ አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የዜግነት ዲፕሎማሲ ፍልስፍናን ነው። ጊዜው ኢትዮጵያ የሚመጥናት ነው ። የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ለማራመድ ኢትዮጵያ የተመቸች አገር ናት ። በቅኝ ግዛት ያልተያዘች፣ የነጻነት ምልክት ነች ። በቂ ሀብት አላት ፣ለአካባቢው ደግሞ ትልቅ እምነት የሚጣልባት ሀገር ናት ። በመልከዓ ምድራዊ አቀማጧም ወደ እዚህ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ታደላለች የምትባል አገር አይደለችም። በኢትዮጵያ የሚነገር ቋንቋ በጎረቤት አገርም ይነገራል። ይሄንን ለዲፕሎማሲው መዋል ይቻላል። ወደጎረቤት አገር የሚሄድ ሀብቷንም ለጥሩ ግንኙነት ማዋል ይቻላል።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013