
ጎንደር፡- የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከ500 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ለ50 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑም ተገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከተማዋን ለጎብኝዎችና ለአልሚ ባለሀብቶች የምትመች ከተማ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ብቻ 500 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።
ለሪል ስቴት 90 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል፤ በቅርቡ ለአምስት ባለኮከብ ሆቴሎች ፈቃድ ተሰጥቷል። በምደባ ከሚተላለፈው የኢንቨስትመንት መሬት በተጨማሪ በጨረታ ለባለሀብቶች የሚተላለፍ መሬት መኖሩን አመልክተዋል።
ለሦስት ሆቴሎች ግንባታ የሚውል መሬት በጨረታ እንዲተላለፍ ተደርጓል፣ በቀጣይ ጊዜያት ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የሚውል ከ26 ሄክታር በላይ መሬት በጨረታ ይተላለፋልም ብለዋል።
ከለውጡ በፊት ለአካባቢው እድገት ትኩረት በመነፈጉና አንዳንዴ ሆን ተብሎም ጭምር የአካባቢው ችግር እንዲወሳሰብ በመደረጉ ከተማዋ ያላትን ሀብትና ታሪክ የሚመጥን እድገት ሳታስመዘግብ ቆይታለች ያሉት አቶ ሞላ ፣ባለፈው ችግር እየቆዘሙ መቀመጥ መፍትሄ ስለማይሆን ችግሩን በመፍታት ልማቱን ለማፋጠን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የከተማዋ እድገት መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞላ፤ እስካሁን አራት የኢንደስትሪ መንደሮችን መገንባታቸውን ገልጸዋል ። አምስተኛውን የኢንደስትሪ መንደር ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።
በዓለም ባንክ ፕሮጀክት 470 ሚሊየን ብር የሚገመት መሠረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው። በተለይ ካሳ ከፍለው መሬት ለሚወስዱ ባለሀብቶች መሠረተ ልማቱን አሟልተን ለማስረከብ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።
ጎንደርን ለ50 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እየተዘረጋ ነው ያሉት አቶ ሞላ ፣ኢንቨስትመንቱ እየተስፋፋ ሲሄድ የመብራት ኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳይኖር ይህንን ሊሸከም የሚችል የመስመር ዝርጋታ፣ ፖል ተከላና የትራንስፎርመር ዝርጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የከተማዋን የጸጥታ ሁኔታ ለማስጠበቅ የአካባቢው አስተዳደር ከክልሉ መንግስትና ከሌሎች አካባቢ አመራሮች ጋር በጋራ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ሞላ ፤ በቀጣይም አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
በ ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም