“ሞቼ እገኛለሁ!”
የግለሰቡ ስም ሌላ ቢሆንም፤ የሰፈር ልጆች የሚጠሩት ግን “ሞቼ እገኛለሁ” ብለው ነው:: “ሞቼ እገኛለሁ በቀን ውስጥ በትንሹ ከአስር ጊዜ በላይ ሞቼ እገኛለሁ ይላል” ብለው የሚወራረዱም አሉ:: ሞቼ እገኛለሁ በእያንዳንዱ ንግግሩ ውስጥ ይህን ቃል መጠቀሙ ምክንያት ምን እንደሆነ ባይታወቅም የልጁን አስተዳደግ የሚያውቁ ግን ስለ አስተዳደጉ የሚናገሩት ከወጣለት ስም ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስረዳናል:: በልጅነቱም ጀምሮ አንድ የጀመረውን ስራ ዳር ማድረስ ካልቻለ ሰላም የማይሰጠው ልጅ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ልጆች ኳስ የሚጫወቱ ከሆነ ሞቼ እገኛለሁ የእነርሱ ቡድን አባል እንዲሆን በጉጉት ይፈልጋሉ:: ምክንያቱም ሞቼ እገኛለሁ ያለበት ቡድን የመሸነፍ እድሉ አነስተኛ ስለሆነ፤ ቢሸነፍ እንኳን በሞቼ እገኛለሁ ጥረትና ንጭንጭ የሆነ ነጥብ ቡድኑ ይዞ ስለሚወጣ::
የዛሬው ሞቼ እገኛለሁ በሱሰኝነት የሚታወቅ፣ በንግግሩ ውስጥ ሞቼ እገኛለሁን የሚጠቀም ቀን ነግቶ ሲመሽ እዚያው ባለበት ላይ የሚረግጥ በተጨባጭ ግን ይህ ነው የሚባል ተጽእኖን መፍጠር የማይችል ሰው ሆኖ የሚታይ፤ ራሱንም እንደዚያ የሚቆጥር ነው:: በልጅነት ዘመኑ የነበረው እልከኝነትና ያቀደውን ለማሳካት የሚሄድበትን እርቀት የሚያስታውሱ ሰዎች በሞቼ እገኛለሁ ወቅታዊ ቁመና ያዝናሉ::
ይህ ሰው በሚሰክርበት ጊዜ ከሚናገራቸው የተለመዱ ንግግሮች መካከል “ብዙ ጀግኖች መቃብር ቦታ ይኖራሉ፤ የቀሩት ደግሞ መጠጥ ቤት” ናቸው የሚለው ይገኛል:: አባባሉን ለማስረዳትም ብዙ ይጥራል:: ነገር ግን አላምንም የሚል ሰው ሲገጥመው “ሞቼ እገኛለሁ ያልኩህ እውነት ነው:: አዎ ወደ መቃብር ስፍራ ሂድ ጀግኖች አሉ፤ እዚህ መጠጥ ቤት ውስጥም ጀግኖች አለን::” ይልና ረጅም ሳቅ ከሳቀ በኋላ በእጁ ደረቱን ይመታል:: በጣም ሞቅ ካለው ደግሞ ለማትሪክ የሚገባውን ሁሉ አድርጎ አለማለፉን ምክንያት ይተነትናል:: ታሪኩ ምንም እንኳን ያለፈና ከሃያ አመታት በላይ የሆነው ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ያወራዋል፤ ይተርከዋል:: ከእርሱ በኋላ ለሃያ አመታት ሌሎች ማትሪክ ወስደው የጨረሱ ቢሆንም እርሱ ከሃያ አመት በፊት ሄዶ ዛሬ የሆነ እስኪመስል ድረስ ጉዳዩን ይተርካል:: በትረካው መሃል የማይጠፋውን ቃል ሞቼ እገኛለሁን ይደጋግማል:: ሞቼ እገኛለሁ፤ ሞቼ እገኛለሁ!
ሁለቱ የስሜት ድባቦች፣
“ቀኑ ደስ ይላል” የሚል ጽሁፍ አዘጋጅተው ቢሯቸው ላይ የሚለጠፉ ሰዎችን እናስተውላለን:: የሞባይላቸው ምስልም አድርገው የሚጠቀሙበት እንዲሁ አሉ:: ጥረቱ የሚያሳየን እኛ ቀኑን በምንስልበት ስእል ሊሆንልን ይችላል ከሚል ልብ የሚነሳ ነው:: በተወሰነ ደረጃ ትክክል ነው፤ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ትክክል አይደለም::
ደስ የሚል ቀንን ለመፍጠር የምንዘራው መልካም ቃል ዋጋ እንዳለው አምናለሁ:: ነገር ግን ከምንዘራው ቃል ባሻገር በተጨባጭ የሚሆነው ነገር የስሜት ድባባችንን የመወሰን አቅም አለው::
ሁለት አይነት የስሜት ድባቦች አሉ አዎንታዊና አሉታዊ:: ሁሉም ሰው አዎንታዊ በሆነው በደስታ፣ በመልካም ስሜት፣ በፈገግታ ውስጥ በሚጨምር ድባብ ውስጥ ራሱን ማግኘት ይፈልጋል:: በተጨባጭ ግን የስሜት ድባባችን በተቃራኒው ሆኖ ልናገኘው እንችላለን:: ለምን? መልሱ አሁን ያለንበት ቦታ ላይ ያለን ትርጉም ነው:: ምን ማለት ነው?
በምሳሌ እንመልከተው
አሁን ያለኸው ሕዝብ በተሰበሰበት ቦታ ላይ ንግግር በማድረግ የመድረኩ አንዱ ጠርዝ ላይ ነው ብለህ አስብ:: አሁን ካለህበት ተነስተህ ወደ ሌላኛው ጠርዝ ለመሄድ ግን ፈልገሃል:: ዝምብለህ አልፈለክም፤ ወደ ሌላኛው ጠርዝ በመሄድ የምታከናውነው ስላለህ እንጂ:: ሰውን ተወውና መንገድ የምታቋርጥ ዶሮ ዝም ብላ መንገዱን አታቋርጥም፤ መንገድ ከማቋረጧ በኋላ እንደምትደርስበት ያሰበችው ነገር አላት:: አንተም አሁን ካለህበት ተነስተህ መድረስ ወደምትፈልግበት አሻግረህ አይተህ እዚያ ላይ ለመድረስ ጉዞ ትጀምራለህ:: አሻግረህ ማየትህ፤ ሄጄ እደርስበታለሁ የምትለው ነገር መኖሩ ውስጣዊ ተነሳሽነት/ቀና አሳቢነትህን ይሰጥሃል:: ይህም በጥሩ ስሜት ወደፊት የመራመድ ፍላጎትህ አዎንታዊ ድባብን ይፈጥርልሃል::
የዶፒን ስርዓት እንዲሁም ሌሎች መድሃኒቶች/እጾች በውስጣችን የሚሰሩት ስራ ስለሆነ ነገር አዎንታዊ ምልከታ ኖሮን ወደ እዚህ መራመድና መድረስ እንደምንችል እንዲሰማን በማድረግ ያሰቡት ጋር እደርሳለሁ በሚል ስሜት ውስጥ እንድንደሰት ማድረግ መቻላቸው ነው:: መልካም ስሜት ውስጥ ሆነህ አሁን ካለህበት ተነስተህ ያሰብክበት ጋር መድረስን ማሰብ ጥሩ ነው፤ ችግሩ እጾቹ እንዲሰማህ የሚያደርጉትን በተጨባጭ ማድረግ የምትችልበት አቅምን ግን አለመስጠታቸው ነው:: ወዳሰብንበት ለመሄድ በመነሳት ውስጥ የሚፈጠረው የአዎንታዊነት ስሜት ውስብስብ ስርዓት ነው፤ በቅጽበታዊ የአእምሯችን ስርዓት ውስጥ ትርጉም የሚያገኝ::
ከውስብስብ ስርዓቱ ውስጥ በሁለት ነገር ደስታን ታገኛለህ:: አንደኛው የምትሄድበትት ቦታ የት መሆኑን ስትለይ ወይንም አጥርተህ ስታይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተጨባጭ መሄድ ስትችል ነው:: ከመድረኩ ጫፍ ተነስተህ ወደ ሌላኛው መድረኩ ጫፍ መድረስን ስታስብ አዎንታዊ/posititve ስሜት ተሰማህ፤ ይህ የመጀመሪያው ደስታ ነው:: ነገርግን ጉዞ ከጀመርክ በኋላ አስቀድሞ ያላየኸው መድረስ የሚገባህ ቦታ እንዳትደርስ መሰናክል የሚሆን ጠረጴዛ ተመለከትክ:: በዚህ ጊዜ አሉታዊ/negative ስሜት ይፈጠራል:: ምክንያቱም ሁለተኛው ደረጃ ደስታ ያለው በመድረስ ወይንም ያሰቡትን በማሳካት ስለሆነ:: ዓለምንም የምናይበት መንገድ እንዲህ ነው:: ነገሮችን ነጣጥለን ተንትነን ትርጉም ሰጥተን ማለፍ ሳይሆን የምናየው መድረስ የምንፈልግበትን ነው::
በተጨባጭ ጉዞ ተጀምሮ የሚገጥመው ነገር የሚጠበቅም የማይጠበቅም ሊሆን ይችላል:: በሂደት የሚፈጠረው የስሜት ውጥረት፣ ንዴት፣ ቁጣ፣ እልህ፣ ወዘተ አሉታዊ ስሜትን ግፋ ሲልም የፍርሃት ድባብን ፈጥሮብን ሊያልፍ ይችላል:: ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተገብቶ ጉዞን ማቆምም ሊያስከትል ይችላል:: የአሉታዊው ስሜት ድባብ ጥጉ ከባድ ነው:: ሞቼ እገኛለሁን አስበነው እንለፍ::
ህልምን አሻግሮ በማለም ውስጥ የተጸነሰው አዎንታዊ ድባብ፤ በመድረስ ውስጥ ከፍታውን ሲይዝ ከእቅድ መጨናገፍ ሲኖር ግን ወደ አሉታዊ ስሜት ይቀየራል:: ተጽእኖው እንደ ሁኔታው ከተወሰነ ክስተት ተሻግሮ አመታትን በሚነካ ደረጃም ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም የሰው ልጅ ለእቅዱ ቦታ ስላለው:: ሰዎች እቅዳቸው እንዲጨናገፍ አይፈልጉም:: እቅድ አንተ አለምን የምታይበት ስሜት-ተኮር ህይወት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው:: በቀላል ምሳሌ እንየው:: ወደ አንድ ክትፎ ቤት ለመሄድ አቅደህ በሆነ አስገዳጅ ሁኔታ መሄድ ሳትችል ቀርተህ ወደ ሌላ ክትፎ ቤት ብትሄድ በውስጥህ ምን እንደሚፈጠር ለማሰብ ሞክር:: ምናልባት ሁለቱም ክትፎ ቤቶች በተቀራራቢ ቁመና ላይ የሚገኙም ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገርግን ያሰብከው ባለመሆኑ አሉታዊ ስሜትህን መጠን ይጨምረዋል፤ ምክንያቱም እቅድህ ተቀይሯል:: ይህም ዓለምን የምታይበትን መንገድ የሚቀይርብህና፤ ስሜትህን የሚረብሸው ነው:: በምን ደረጃ መረበሹ ይሆናል የሚለውን በተለያየ ደረጃ ሊሆን ይችላል:: በሁለቱ የስሜት ድባቦች መካከል ያለው ሰው ከህይወት ጉዞ የተበላሸ አቅጣጫ ለመጠቀም ሊያደርጋቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ዋናውን ቀጥሎ እንይ::
በጥንካሬያችን ላይ መመስረት ማዝገምና ማቆምን ለመግታት
ያሰቡትን ባለማሳካት ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው አሉታዊ ስሜት በህይወታችን ውስጥ ማዝገምን ሊያስከትል ይችላል፤ ግፋ ሲልም ማቆምን:: በፍጥነት ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ባለንበት መርገጥ ወይንም የማዝገም ህይወት ይፈጠራል:: ተስፋ በመቁረጥም ከሩጫ ራስን መቆጠብም እንዲሁ:: አሉታዊ ስሜት አይሎ ወደ ማዝገም ህይወት እንዳያደርሰን ግፋ ሲልም ወደ ማቆም ራስን አውቆ በራስ ጥንካሬ ላይ እርምጃን ስለመወሰን ማሰብ ይገባል:: መፍትሄው ራሱ ግለሰቡ ነው:: የራሱን ጥንካሬ ተመልክቶ አዎንታዊ ድባብን በሚያበዛ መንገድ ህይወቱን መምራት:: ስለ አንድ ጉዳይ ሁላችንም ያለን መረዳት የተለያየ ሊሆን ይችላል:: ነገርግን ሁላችንም በተለየ ሁኔታ ጠንካራ የሆንበት ነገር ግን አለ:: ነገሮችን በመተንተን ይሁን ውሳኔ በመስጠት::
ጠዋት ስትነሳ የህመም ስሜት በውስጥህ ተሰማህ እንበል:: የህመም ስሜቱ ምክንያት ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል:: ምናልባትም ጉንፋን ብጤ የፈጠረው ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ካንሰር የፈጠረው የህምም ስሜትም ሊሆን ይችላል:: ተመሳሳይ ስሜት ለተለያዩ አይነት በሽታዎች:: አንዳንድ ሰዎች የሆነ ነገር ሲያስቡ፤ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ሌላ ነገር ነው ምክንያቱ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ:: አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ትክክል ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል:: አንዳንድ ሰው በትንሹ ነገር ነርቨስ ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ነገር ደግሞ ነገሩ በጠነከረበት ልክ:: ነገርግን ትንሽ ነገር ነው ብሎ የታለፈው ጉዳይ ሆስፒታል ሲደረስ ጊዜው አልፎ የህክምና ሰዎች ምንም ማድረግ በማይችሉት ደረጃ ላይ ደርሶም ሊሆን ይችላል:: እዚህ ላይ የምንረዳው ሁላችንም አንድ አይነት መረዳትና የነገሮች ትንተና አቅም እንደሌለን ነው:: አቅልለን ያየነው ነገር አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍልም ይችላል:: ጠንካራ የሆንበትን ነገር ለይተን በዚያ ላይ ማተኮር አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው::
እኛ ጠንካራ በሆንበት ነገር ችግሮችን በቀላሉ ልንፈታ እንችላለን:: በምን ይሆን እኔ ጠንካራ የሆንኩት የሚለው ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል? ምናልባት ሌሎች ሰዎች ጠንካራ እንደሆንበት የሚነገሩን ነገር ሊሆን ይችላል:: እኔ ከሌሎች ነገሮች የተሻልኩ ነኝ በምትልበት አቅጣጫ ውስጥ ስሜትህ ሲሆን በአዎንታዊ ድባብ ከፍታው ላይ ትደርሳለህ:: ይህም የራስ መተማመንህን ይጨምረዋል:: የነርቭ ስርዓትህም ጤናማ በመሆን አሉታዊ ድባብን ዝቅ በማድረግ አዎንታዊ ከፍ እንዲል ያደርጋል:: ሞቼ እገኛለሁ ከገባበት አሉታዊ ድባብ አውጥቶ ወደ አዎንታዊ ድባብ ለመፍጠር የሚቻልበት ዋናው መንገድ አሁን ባለበት ሁኔታ በእርሱ ውስጥ ያለውን ጠንካራ አቅም ራሱ እንዲያየው ማድረግ ነው:: በመነሻና መድረሻ መካከል ያለው ለአሉታዊ ስሜት መፈጠር ተጋላጭነት ከፍተኛ ስለሆነ ስለመካከሉ ሲታሰብ ስለራስ አቅም ማሰብ ግድ ይላል:: ካልቻለ የሚፈጠረው ግን …
በመነሻና መድረሻ መካከል
በመነሻና መድረሻ መካከል ያሉት ሁለቱ ድባቦችን በአግባቡ ገርቶ ጉዞን ለማድረግ በራስ ጥንካሬ መመስረት አስፈላጊ መሆኑን አይተናል:: ይህን ማድረግ በማይቻልበት ጊዜ ግን አሉታዊው ድባብ ሲያይል፤ ድባቡ ያየለበት ወቅት የሌሎች የወደፊት ቀናትን ቀለም በመወሰን እርምጃን ይበይናል:: በትላንት ውስጥ የመኖር እስረኝነትን!
በትላንት ውስጥ ከመኖር ለመውጣት በትላንት ላይ የሚቻለውን ማስተካከያ በማድረግ ከመዝጋት ባሻገር የነገውን ጉዞ አዎንታዊ ድባብን በመፍጠር እንዲሆን መሰረቱ የራስን ጠንካራ ጎን አውቆ በእርሱ ላይ መስራት ነው::
ትላንትና ውስጥ በሆኑ ነገሮች ውስጥ ቆሞ ዛሬን ለመኖር በመጣር ውስጥ የፍርሃት ድባብ ይፈጠራል:: በትላንት ውስጥ የሆነውን ነገር የአዕምሯችን ስርዓት በሚገባ ይዞ ዛሬም እንደትላንት እንዲንቀሳቀስ ስናደርገው የሚፈጠር ድባብ ነው:: እድሜያችን ጨምሮ ይሆናል፤ ቦታም ቀይረን ይሆናል፤ ከትላንትናው ጉዳይ የራቅንም ይሆናል ነገር ግን ትላንትን ዛሬ ላይ ስንኖር የአዕምሯችን ስርዓት ትላንት ከሆነው ነገር ጋር ተገናኝቶ የሚያሰማው ድምጽ “አይሆንም!”፤ “አይሆንም!” ወዘተ የሚል መልእክት ሊሆን ይችላል:: አዕምሯችን የትላንትና የዛሬ ድንበርን መለያየት ሳይችል ቀርቶ፤ በፍርሃት ውስጥ ወጥተን እንድንገባ የሚያደርግ የትላንት እስርቤተኝነት ህይወት ነው::
ምንድንናቸው ልንረሳቸው ሳንችል ቀርቶ በየጊዜው ወደ አእምሯችን እየመጣ ወደ ትላንት የሚመለስን? ያልረሳነው፤ አሁንም ያልረሳነው፤ በፍጹም ልንረሳው ያልቻልነው?
ሊረሳ ያልተቻለው የትላንት ነገር በአዕምሯችን ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ አካላችን ሁልጊዜ እንደ አዲስ ጉዳዩ እንዲሰማው ያደርጋል፤ ድንገተኛ አደጋ ውስጥ እንዳለም ይሰማዋል::
በትላንት ውስጥ እንድትኖር የሚያደርግህ ጉዳይ የግድ ችግሩ የአንተ/የአንቺ መሆን የለበትም፤ የሌላ ሰው ችግር በፈጠረው ሁኔታ ሊሆን ይችላል በትላንት ውስጥ እንድትኖር የሆንከው:: በትላንት ውስጥ የሚያኖርህ አንተ ብቻ ጥፋተኛ የሆንክበት ነገር ማለት አይደለም:: ሌሎች ያጠፉት ጉዳይ ሆኖ ነገር ግን ዛሬ ላይ ስንኖር በትላንት ሙድ ውስጥ፣ በትላንት ስሜት ውስጥ፣ በትላንት ከባቢ ሁኔታ ውስጥ እንድንኖር የሚያደርግ ነው:: የእሳት አደጋ እንዳይፈጠር የሚያነፈንፍ መሳሪያ እሳት አደጋ እንዲፈጠር ያደረገው አካል ማን እንደሆነ አይደለም የሚመረምረው፤ በቃ እሳት የሚባል ነገር መፈጠር አለመፈጠሩን እንጂ:: እሳት ሲፈጠር ቤቱ ውስጥ እሳት አለ ብሎ ነው የሚገልጸው እንጂ እከሌ ያስነሳው እሳት ብሎ አይደለም::
በትላንት ላይ የሚፈጠር ስጋትም ሆነ ጉጉት/anxiety system በተጨባጭ በሆነው ነገር ላይ ሆኖ ነው የስሜት ሰንሰለቱን የሚሰራው::
መፍትሄው ወደ ኋላ ሄዶ መስተካከል ያለበትን ማስተካከል፤ መጽዳት ያለበትን ማጽዳት ነው:: ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የእኔስ ድርሻ ምንድን ነበር? የአንተ ድርሻ ጥቂት ቢሆንም ምን ነበር የእኔ ድርሻ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: ዋናው ነጥብ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ራስህን ማግኘት የሌለብህ መሆኑ ነው:: ራስህን ለማጠናከር ለቀጣዩ የሚሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲረዳ ነው:: ምናልባት እኮ ትውስታው የሚመጣው ከህጻንነት እድሜህ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ዛሬ ህጻን አይደለህም:: እስከአሁን ተከትሎ የመጣ የስሜት ሰንሰለት ካለ ግን አድምጦ ማስተካከል የሚገባውን ለማስተካከል መስራት ይገባል:: ሂደቱ የአዕምሮህን ስርዓት ከአሁኑ ሁኔታ ጋር የተስማማ/update የሆነ እንዲሆን ያደርገዋል::
አንድ ሰው አለ በልጅነቱ ወቅት በሆነው ትውስታ ውስጥ የሚኖር:: አሁን እድሜው 58 ቢሆንም የአዕምሮ ስርዓቱ ግን ከልጅነት ወቅቱ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ህልም ሲያልም ራሱን የሚያገኘው የ 5 አመት ልጅ ሆኖ ነው:: ይህ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው፤ ቀላል ነገር አይደለም:: ከፍተኛ የሆነ የውስጥ ችግርም አመላካች ነው:: እንዴት ሰው በጎልማሳነት እየኖረ በ5 ዓመት እድሜው ላይ በሆነው ነገር ላይ ቆሞ እንዲቀር ይሆናል?
ስለእዚህ የት እንዳለን ማወቅ አስፈላጊ ነው:: ራስን አዳምጦ የት እንዳሉ ማወቅ በ5ኛ እድሜ ላይ ወይንስ በ58ኛው?
በመነሻችን ላይ ያገኘነው ሞቼ እገኛለሁ የተባለው ግለሰብን በመነሻና መድረሻ ውስጥ ፈልገን እናግኘው:: ወደ መስመር ለማስገባትም የመፍትሄውን መንገድ እናሳየው::
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013