
ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ተገኝቼ ነበር፤ ወቅቱ ክረምት ነበር። ምክንያቴ ደግሞ የደብረ ታቦር በአልን (የቡሄ በአል) ለማክበር ነው። በቆይታዬ ሁሌም ከአእምሮዬ የማይጠፉ ትዝታዎችን አትርፌያለሁ።
የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህል፣ በዓል አከባበርና ሃይማኖታዊ ስርዓትን መመልከት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። አካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከታዮች ይበዙበታል። ህብረተሰቡ ለሃይማኖቱ ቀናኢና ለደንብና ስርአት የሚገዛም ነው። በከተማው ውብ ተራራ ላይ የሚገኘውን የእየሱስ ቤተክርስቲያንን (ገዳም) ጎብኝቼያለሁ። ከዚህ አጋጣሚ ነው ዛሬ ለማነሳው ጉዳይ መግቢያ የሚጠቅመኝን ሃሳብ የምጠቅሰው።
ስፍራው ልዩ ነው። ረጅም ዘመናት ባስቆጠሩ ሀገር በቀል ዛፎች ተሸፍኗል። በዚያ ግቢ እፅዋት ልዩ ስፍራ አላቸው። ከአእዋፋት ዝማሬ ውጪ ሌላ ምንም ድምጽ አይሰማበትም፤ ጸጥ ረጭ ያለ ነው፤ ሰው ሳይሆን አእዋፋት ቀዳሚ የአካባቢው ባለቤቶች ናቸው። ከዚያ የተረፈውን ነው አባቶችና ምእመናን የአምልኮ ስርዓት ለመፈፀሚያነት የሚያውሉት።
በዚያ ህግ አለ፤ ህጉን የሚያስፈፅሙ አባት ደግሞ ከማንም በላይ ተሰሚነት አላቸው። ቤተክርስቲያኑና በዙሪያው ያሉ ስፍራዎች በሙሉ በአገር በቀል ዛፎችና ሌሎች እጽዋት ተሸፍነዋል። ዛፎቹና እጽዋቱ ለእይታ ማራኪ ከመሆናቸው ባሻገር ለአእምሮ ሰላም ይሰጣሉ። ይህን የሚረዳው በቦታው የተገኘ ብቻ ነው።
ይህን የገዳሙን ውበት እያጣጣምኩ ባለሁበት አጋጣሚ ነው ሌላ ተጨማሪ ጉዳይ የታዘብኩት። ገዳሙ ውስጥ ሆኖ በዙሪያው ያሉ አካባቢዎችን በቀላሉ በቅርበትም በርቀትም ማየት ይቻላል። ጣናን ጭምር ከሩቅ ማየት ስለማስቻሉ ምስክር ነኝ። እዚያ ላይ ተሁኖ ጣና ጭልጭል ሲል ይታያል። ርቀቱን አስቡት፤ ጣናን ያህል ሰፊ የውሃ አካል ጭልጭል ብሎ ሲታይ።
ቁልቁል ስመለከት የደብረታቦር ከተማን አየሁት።’ ወዲያው አንድ አስደንጋጭ ነገር ታየኝ። የቆምኩበት ስፍራ በእጽዋት የተሞላ ሆኖ ከተማዋ ግን ራቁቷን ቀርታለች። በእጽዋት ፈንታ ቤቶችና ግንባታ በስፋት ይታያሉ። ቤተክርስቲያኑና ጥቂት ስፍራዎች ብቻ ተፈጥሯዊ ፀጋቸውን ላለማስነጠቅ እየታገሉ ይመስላል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ተቋም ናት። ከዚያ ባሻገርም የታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ባለቤትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ጠብቆ የማቆየት ተምሳሌትም መሆኗ ይታወቃል፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይም እጅግ የሚያስገርም አስተዋፆኦ አላት። የደብረ ታቦር ጉብኝቴ ይህን በሚገባ አመልክቶኛል።
ይህ ሁኔታ በሌሎች በርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትም ይስተዋላል፤ አዳዲሶቹ ካልሆኑ በስተቀር ሁሉም የተፈጥሮ ሚዛንን በሚጠብቁ እፅዋቶች የተሞሉ ናቸው። ከትውልድ የተላለፉላቸውን ይጠብቃሉ፤ አዳዲስ የሀገር በቀል ዛፍ ችግኞች ይተክላሉ። በዚህ ስራቸው ገደማትና አብያተ ክርስትያናት እውቅና ሊቸራቸው ይገባል። እነሱም ይህን ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል።
ይሄ ግን በከተሞች በሚገኙ ገዳማትና አብያተክርስትያናት በኩል እየተጠበቀ አይመስለኝም። ደብሮች ከእፅዋት ልማት ይልቅ በሚከራዩ ህንፃዎችና ቤቶች ግንባታ ተጠምደው ይታያሉ። ሁኔታው መቀየር ይኖርበታል። የዛፎችን ጥቅም ለዘመናት በተግባር ያሳየችን ቤተ ክርስቲያን በከተሞች ላይ ችግኞች በስፋት እንዲተከሉ ምሳሌ መሆን እንደሚኖርባት ይሰማኛል።
በአጠቃላይ ሲታይ ግን ገዳማትና አብያተክርስትያናት በዛፍ ጥበቃና ልማት ላይ በቂ ተሞክሮ አላቸው፤ ይህ ተሞክሮ ወደ ከተማ ልማትና ሰፋፊ ይዞታ ወደአላቸው ተቋማት ሊሰፋ ይገባል።
እርግጥ ነው ሀገሪቱ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በየአመቱ የዛፍ ችግኝ ተከላ ስራዎችን እያካሄደች ትገኛለች። ለአብነትም ባለፈው አመት በተካሄደ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከ4 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በወቅቱም በአንድ ጀንበር 200ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል። ዘንድሮ ደግሞ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ ነው። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በአንድ ጀንበር 350 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 390 ሚሊየን ችግኞችን መትከል ተችሏል።
ከዚህ ውጪ መንግስት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኞችን በገጠሩም ሆነ በከተማ አካባቢ ለመትከል እያከናወነ ያለው ተግባር በእጅጉ የሚበረታታ ነው። በሀገሪቱ የችግኝ ተከላ ባህል እየተገነባ ነው ማለትም ያስደፍራል።
የችግኝ ተከላው በአዲስ አበባ ከተማም በስፋት ሲካሄድ ቆይቷል፤ እየተካሄደም ነው። በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው የችግኝ ተከላ ጋር ተይያዞ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መኖሩን መጠቆም ግን እፈልጋለሁ።
ክረምቱ፣ ችግኞቹና ትዝብቴ
በአዲስ አበባ ከተማ ክረምቱ በመጣ ቁጥር በዘመቻ ችግኞች እንደሚተከሉ ይታወቃል። በአንዳንድ ስፍራዎች በተለይ በጋራ መኖሪያ መንደሮች፣ በመናፈሻዎች፣ ተቋማት ግቢ በዚህ በኩል ለውጥ መጥቷል። የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ጨምሯል የሚያሰኝ ሁኔታ ይታያል።
በየአመቱ የተተከሉት ችግኞች እና የጸደቁት ችግኞች ሲታሰቡ ግን አነጋጋሪ ሁኔታ እንዳለ ይሰማኛል። በተለይ በመንገድ ዳርቻና አካፋይ ላይ የሚተከሉ ችግኞች ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው ገና ክረምቱ ሳይወጣ ህልውናቸውን ያጣሉ። በበጋው ወቅትም ውሃ የሚያጠጣቸው የሚያገኙት ጥቂቶቹ ናቸው። በአደባባዮችና የመንገድ ማካፈያዎች እና ዳርቻዎች ላይ የተተከሉ ችግኞች ውሃ የሚያጠጣቸው አጥተው ሲደርቁ ተመልክቻለሁ።
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት የመጽደቅ እድሉ ያላቸው በመንግስት ተቋማት ግቢ፣ በመናፈሻዎች፣ ፓርኮች አካባቢ የተተከሉት ናቸው። እዚህ አካባቢ ያሉት ውሃ የሚያጠጣቸው ያላቸው፣ ከሰውና እንስሳት ንክኪም የተጠበቁ በመሆናቸው የመጽደቅ እድላቸው ሰፊ ነው።
ችግኞች ውሃ ቢጠጡ እድገታቸው ይፈጥናል፤ ለተፈለገው አላማ ቶሎ ይደርሳሉ። አብዛኞቹ ችግኞች ውሃ የሚያጠጣቸው ይኖራል ተብሎ ታስቦም አይደለም የሚተከሉት። እንስሳትና ሰዎች እንዳይደርሱባቸው መከለል ግን የግድ ያስፈልጋል። ለችግኞች መጽድቅና ህልውና ወሳኝ የሆነው ይህ ተግባር ሲሰራበት አልተመለከትኩም። በተለይ ሰው በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ይህ ችግር በስፋት ይስተዋላል።
ባለፉት ሶስት አመታት የተተከሉትን ሳስብ አሁን መትከል ያለብን ያኔ ባልተተከላባቸው ስፍራዎች እና ባልጸደቁት ችግኞች ምትክ ነበር። እኛ ግን ሁሌም እንዳዲስ እየተከልን እንገኛለን።
አንዳንድ ጊዜ ችግኞቹን ባረገኝ እላለሁ። ‹‹ላታጸድቁ አትትከሉኝ›› እያልኩ ለመጮህ። አፍ ቢኖራቸው የመጀመሪያው ጩኸታቸው ‹‹ላታጸድቁ አትትከሉኝ፤ ከተከላችሁ ተንከባከቡኝ›› የሚል እንደሚሆን አልጠራጠርም።
አንዳንድ አካባቢ ችግኞቹን በብረት እና በመሳሰሉት/ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች/ የመከለል ሁኔታ ይታያል። አንዳንዶቹ በብረት ፍርግርግ አጥር ይታጠራሉ። ይህ ጥሩ ነው። ሌሎች ግን የብረት ሳጥን በሚመስሉ ነገሮች ነው ተከልለው የሚታዩት፤ ሳጥኖቹ ማስታወቂያ በተለጠፈባቸው ፕላስቲክ የተሸፈኑ ናቸው። ፕላስቲኩ ችግኞቹ በቂ አየር እንዳያገኙ በሙቀት እንዲቃጠሉ የሚያደርግ መሆኑ የታሰበበት አይመስለኝም። በየካ ክፍለ ከተማ ከአበቤ ሱቅ እስከ ኮኮበ ፅባህ አካባቢ በመንገዱ ዳርቻ ላይ ያሉት ችግኞች ያሉበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት እጠቅሳለሁ።
ክረምት በመጣ ቁጥር ለዓመታት ችግኝ የሚተከልበትን አንድ ቦታ አውቃለሁ። የተተከሉት ችግኞች ለምን እንዳልጸደቁ የሚጠይቅ እንዴት ይጠፋል? እውነት እውነት እላችኋለሁ አምስት ዓመት በተመላለስኩበት መንገድ ላይ በየዓመቱ ችግኝ ሲተከል አይቻለሁ። እንክብካቤ ሲደረግ ግን ያየሁበትን ቀን አላስታውስም።
በየአመቱ በተመሳሳይ ቦታ ችግኝ እየተከልን ያለበት ሁኔታ በራሱ የሚያስተላልፈው መልእክት አለው። እንክብካቤ ላይ የሌለን መሆናችንን ያስገነዝበናል። በዚህ አይነት መልኩ በሚቀጥሉት አመታትም መቀጠል የለብንም። ችግኞችን ማጽደቅ፣ ዛፍ ማድረግ ላይ አተኩረን መስራት ይኖርብናል፤ ለእዚህ ደግሞ ችግኞች ባለቤት ወይም ሞግዚት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።
ዘንድሮም ክረምት መግባቱን ተከትሎ እንዳለፉት አመታት ሁሉ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሲካሄድ ሰንብቶ አሁን ወደ ተከላ ተገብቷል። የችግኝ ተከላው ግን ያለፉ ስህተቶቻችንን አርመን ችግኞች ማጽደቅና ዛፍ ማድረግ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል። ችግኞች ባለቤት ወይም ሞግዚት እንዲኖራቸው ይደረግ። ሰላም።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013