መንግስት በትግራይ ክልል ላይ ሲያደርግ የነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናቆ ወደሌላ ምዕራፍ ተገብቷል። መንግስት የእርሻ ወቅትን ታሳቢ በማድረግ እና የተባባሰ ጥፋትና ውድመት እንዳይከሰት በማለት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ሰራዊቱ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ወስኗል። ይህ ሁኔታ ከወታደራዊ ስትራቴጂ አንፃር እንዴት ይታያል የሚሉና ሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችን የሚዳስሱ ጥያቄዎችን በመያዝ የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ለሆኑት ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ጥያቄዎችን አቅርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ያሳየውን የግዳጅ አፈጻጸም እንዴት ገመገሙት?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ የጦርነትን አስከፊነት ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ያለፉትን በርካታ ዓመታት በጦርነት ውስጥ ነው ያሳለፍነው። በዚህም የደም የአካል እንዲሁም የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ተከፍሏልና የኢትዮጵያ ህዝብ ጦርነት በጣም አስከፊ መሆኑን ይረዳል፡፡ አሁን ያለው መንግስትም ይህንን ጠንቅቆ ስለሚረዳ ወደጦርነት ላለመግባት ብዙ ጥረቶችን አድርጓል። በተለይም ለበጥባጩ የህወሓት ቡድን ሽማግሌ ሰብስቧል። ታዋቂ ሰዎችን ልኳል። የሀይማኖት አባቶችም የበኩላቸውን ተወጥተዋል፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ጥረት ፍሬ ባለማፍራቱ ወደጦርነት ተገብቷል።
ጦርነት ንብረት ያወድማል፣ የሰው ህይወት ይነጥቃል፣ ልማትን ያቆረቁዛል፤ በመሆኑም ለልማት ይውል የነበረን ገንዘብ በሙሉ ለጦርነት ይበላዋል። ትላንት እንግዳ ይቀበል የነበረ ህዝብ ዛሬ ተመጽዋች ለማኝ ይሆናል። በመሆኑም ጦርነትን የሚያውቅ መንግስት ካልተገደደ በቀር ወደ ጦርነት አይገባም።
መንግስትም ጦርነቱ እንዳይቀሰቀስ ብዙ ጥረት አድርጎ አልሳካ ከማለቱም በላይ መጨረሻ ላይ ደግሞ በሰራዊቱ ላይ እንደዛ ያለ ጥቃት ተፈጸመ። ይህ ሰራዊት የአንድ ብሔር ሳይሆን ከሁሉም ብሔር የተውጣጣ ነው፤ የትግራይም ወጣቶች የሰራዊቱ አባላት ናቸው። መጨረሻ ላይ ግን ጁንታው ያደረገው ነገር ከባድ ከህሊናም የማይፋቅ ነው። ይህ ሁኔታ አስገድዶት ነው ማዕከላዊ መንግስት ወደ ጦርነት የገባው፤ ጦርነቱ ተደረገ የጁንታው ቡድን አባላትም የተደመሰሱት ተደመሰሱ፣ የሞቱትም ሞቱ፣ ጥቂቶችም ጫካ ገቡ፤ ከዚህ አንጻር ስናየው ሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸሙ እጅግ የተዋጣለት ብሎም ንጹሀን እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄን ያደረገና ውጤታማ ነበር።
በሌላ በኩልም ጦርነቱ የትግራይን ህዝብ ነጻነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ ከጦርነቱ ድል ማግስት መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቶ ክልሉን እንደገና ወደማልማትና መልሶ ወደመገንባት ገባ። ይህ ስራውን በድል ያጠናቀቀ ሰራዊት አሁን ደግሞ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ አገራዊ ፕሮጀክቶችን የመጠበቅ ግዳጅ ስላለበት ወደዛ ፊቱን እንዲያዞር ተደርጓል ብዬ ነው የማስበው።
ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት የተወጣ ነው ለእኔ፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ሰራዊቱ በወታደራዊ ስነ ስርዓት የታነጸ መሆኑ። በወታደራዊ ሳይንስ በኩል ጥሩ ስልጠናን መውሰዱ እንዲሁም በአካል ብቃት በኩልም ጥሩ የተገነባ መሆኑ ላሳየው ውጤታማ ግዳጅ አፈጻጸም አግዞታል። በሌላ በኩል ደግሞ ብቃት ባላቸው አመራሮች መመራቱ በግልም በቡድንም ላስመዘገቡት ውጤት እንደ ምክንያት መነሳት ይችላል ።
አዲስ ዘመን ፦ መንግስት የወሰደው የተናጠል የተኩስ ማቆም አካሄድ ከወታደራዊ ስትራቴጂ አንጻር እንዴት ይገለጻል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ አንድ ነገር አለ፤ በወታ ደራዊ ሳይንስ ምን ጊዜም ቢሆን ስልት ቀኖናዊ ወይም ግትር አይደለም፤ ከሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጥ ነው። ለምሳሌ የአየር ጸባይ ሊለወጥ ይችላል፤ የጠላት ፍላጎት ወይም ስልት ይለወጣል እነዚህ ነገሮች በሙሉ ታሳቢ በማድረግ ስልትንም አብሮ መለወጥ የግድ ነው። በመሆኑም አንድ ጦር የነበረበት ቦታ ለማጥቃት የማይመች የወገንን አካሄድ ደግሞ ለችግር የሚያጋልጠው ከሆነ ቦታውን ለቆ ሌላ ቦታ ላይ ጦርን ማዘዋወር ወታደራዊ ስልት ነው። አዲስ ነገርም አይደለም።አሁን መንግስት የወሰደው እርምጃም ከወታደራዊ ስልት አንዱና ትክክለኛው ነው።
አዲስ ዘመን፦ የትግራይ ህዝብ ለሰራዊቱ ደጀን መሆን ያቃተው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ ይህ ጦርነት እኮ መጀመሪያውንም አላማው ከትግራይ ህዝብ ጋር ለመዋጋት አይደለም። የትግራይን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው። የትግራይ ህዝብ የፈለገውን አመራር በቦታው ላይ መተካት ነበር። እነዚህ አምባገነኖች ያው በጦርነቱ የደረሰባቸው ኪሳራ እነሱም ዓለምም አይቶታል።
የትግራይ ህዝብ ይህንን እያወቀ ለሰራዊቱ ደጀን መሆን ያልቻለበት ምክንያት ሁሉንም ግራ ያጋባ ነው፤ ይህ ሰራዊት ለህዝቡ ቆስሏል። ደምቷል። ህይወቱንም ገብሯል፤ ከሁሉም በላይ የክልሉን አስቸጋሪ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ጸባይ ተቋቁሞ ለህዝቡ ብዙ ነገር ሆኗል። ነገር ግን ይህ ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት እንደ ውለታ አልተቆጠረም።
ይህንን መሰሉ ስህተት ሲፈጸም የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ የመጀመሪያው ለ20 ዓመት ቀንና ሌሊት የክልሉንና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ዘብ የቆመን ሰራዊት በተኛበት ማረድ፤ አሁን ደግሞ ይህ ሰራዊት በተደረገበት ነገር ቂም ሳይዝ አሁንም ይህ ህዝብ ሰላም መሆን አለበት ብሎ አጥፊዎችን ለመደምሰስ እራሱን ሲሰዋ ከኋላ መውጋት፤ ይህ ከሀዲነት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም።
አዲስ ዘመን፦ መከላከያ ሀይሉ ከውጪም ከውስጥም ሊደርስ የሚችልን ትንኮሳዎች ለመ ቋቋም ያለው አሁናዊ ቁመና እንዴት ይገልጹታል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ አሁን ያለው ሰራዊት አንደኛ ነገር ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ያቀፈ ነው፤ ሌላው ወቅቱ በሚጠይቀው ወታደራዊ ሳይንስ የተቀረጸም ነው፤ የአካል ብቃቱም ቢሆን በተለያዩ መንገዶች የተገነባ ሲሆን፤ ከታችኛው የአመራርነት እርከን ጀምሮ እስከ ላይኛው አመራር ድረስ የስራ ድርሻውን የሚያውቅና አመራር መስጠትንም የሚችል ነው። እነዚህ ሁኔታዎች መቀናጀታቸው ደግሞ በግልም ሆነ በቡድን ግዳጁን መወጣት የሚችል አድርጎታል።
ይህ ብቻ አይደለም የታጠቀው መሳሪያም ከወቅቱ ጋር የሚሄድ በቴክኖሎጂ የተራቀቀ ከመሆኑም በላይ ይህንን መሳሪያ በአግባቡ ተረድቶ በመጠቀም በኩልም ትልቅ ችሎታ ያለው ነው።
እናም ከዚህ የተነሳ ጠላት ከውጪም ይምጣ ከውስጥ ድባቅ መትቶና አሳፍሮ ለመሸኘት የሚሳነው አይደለም። በመሆኑም አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በትግራይ ጉዳይም ይሁን በአባይ ግድብ ምክንያት የጠላትም የወዳጅም አይን አገራችን ላይ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከትም ሆነ የአገርን ሉአላዊ አንድነት ጠብቆ ለማሻገር በቂ አቅም ያለው ነው።
አዲስ ዘመን፦ የመከላከያ ሀይል አካል ሆኖ ግዳጅ የሚወጣ የአየር ወለድ ሀይል በክፍለ ጦር ደረጃ ለማዋቀር እየተሰራ መሆኑ ይነገራል፤ ይህ አጠቃላይ ለሰራዊቱ የሚያጎናጽፈው አቅም እንዴት ይገለጻል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ በክፍለ ጦር ደረጃ ሊቋቋም መታሰቡን ባልሰማም አየር ወለድ እንደ አገር መኖሩ ግን ትልቅ አቅም የሚፈጥር፣ ጠላቶቻችን እንዲፈሩንና እንዲያከብሩን በየትኛውም ጉዳያችን ላይ ጣልቃ እየገቡ እንዳይረብሹን የሚያስችል ብዙ ስራንም ሊያግዝ የሚችል የመከላከያ ሀይሉን አቅም የሚጨምር ነው።
በነገራችን ላይ አየር ወለድ ከሌሎቹ የመከላከያ ሰራዊት ግዳጆች ሁሉ ለየት ያለ ብዙ ጀብዱዎች የሚፈጸሙበት ወገንን በጠባብና በረቀቀ መንገድ ከጠላት እጅ ፈልቅቆ የሚያወጣ ነው። ለምሳሌ አንድ የወገን ጦር በግዳጅ ላይ ሆኖ በጠላት ጦር የተከበበ እንደሆነ ይህንን ጦር ከከበባው ለማውጣት ፈጥኖ ደራሽ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ የወገን ጦርና ጠላት በተፋጠጡበት ጊዜ የጠላትን ሀይል ለማጠናከር ከኋላ የሚመጣን ሌላ ሀይል መካከል ገብቶ በመቁረጥ ደጀን የሚያሳጣ በዚህ መካከልም የጠላትን አቅም በማዳከም ድል ለወገን እንዲሆን የሚያደርግ በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ፈጣንና ስልታዊ እርምጃዎችን የሚወስድ ሀይል ነው።
እንደ ነገርኩሽ አየር ወለድ በጣም ፈጣንና በተፈለገበት ቦታ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርሶ ሁኔታዎችን መቀየር ያለበት ይህንን ሀላፊነት ተሸክሞ የሚሄድ ነው። ለምሳሌ ከዚህ ትግራይ በመኪና ለማጓጓዝ ቢፈለግ ምናልባት ሁለትና ሶስት ቀናትን በመንገድ ላይ ማሳለፍ ሊጠይቅ ይችላል፤ ነገር ግን በአየር ወለድ ከሆነ የአንድ ሰዓት ጉዳይ ነው። በሌላ በኩልም በተፈለገበት አቅጣጫ በፍጥነትና በአነስተኛ ቁጥር ከፍተኛ ውጤትን የሚያስመዘግብ ክፍል ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገር ይህንን ክፍል በብርጌድ አልያም በክፍለ ጦር ደረጃ ብታቋቁም ከፍተኛ ጥቅም እንጂ ምንም ጉዳት የለውም፤ በእርግጥ ከፍተኛ የሆነ ሀብትን የሚጠይቅ ነው። ትጥቁ መሳሪያው ስልጠናው በጠቅላላው ሁሉም ከፍተኛ የሆነ ወጪን ይፈልጋል። ነገር ግን ይህንን እንደ ምንም ተቋቁመን አቅማችን በሚፈቅድ ደረጃ አቋቁመን ብንጠቀምበት በበኩሌ ጥቅሙን ስለማውቀው ደስተኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፦ የውጭ ሚዲያዎች የሰራዊቱን ህዝባዊነትና ወታደራዊ ስነ ምግባር አስመልክተው የሚያሰራጩትን የተዛባ መረጃ እንዴት ያዩታል? ሰራዊቱስ በዚህ ያህል ደረጃ የሚታማ ነው?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ ይህ እኮ ከእነሱ እሳቤ የመነጨ ስም ማጥፋት ነው፤ በነገራችን ላይ ጠላት ከዚህ ውጭ ሊያወራ ይችላል እንዴ? በምንም ተዓምር የፈለገውን ያህል ጥሩ ስራ ብትሰሪ ልቦናው ያንን ጥሩ ነገር ቢያውቀውም ጠላት ጠላት ነውና ስም ከማጉደፍ ከማጠልሸት ያለፈ ነገርን ሊያደርግ አይችልም። በመሆኑም ጁንታው ቡድንን አጋሮቹ የመከላከያ ሰራዊታችንን ስም በዚህን ያህል ደረጃ ቢያጠለሹት ምንም የሚገርም አይሆንም።
ይህ የጠላት ስም ማጥፋት እየተፈታተነው ያለው ሰራዊት ግን በማንም እይታ ቢሆን ህዝባዊና ለህዝብ የቆመ ሰራዊት ነው። እንኳን አሁን የጁንታው ቡድን ስሙን እንደሚያጠፉት አይደለም በሚያልፍበት መንገድ ላይ እንኳን ያገኘውን የገበሬ ቅጠል ያለፍቃድ የማይበጥስ ሰራዊት እንዳለን አፌን ሞልቼ እናገራለሁ። ምናልባት እንኳን በስህተት ሳያስፈቅድ ቢነካ (ቢበጥስ) ዝም ብሎ አይሄድም፤ ገበሬውን ይቅርታ ይጠይቃል፤ ከይቅርታውም በላይ ላጠፋሁት ወይም ለበጠስኩት ቅጠል ግምቱ ምን ያህል ነው? ልክፈል፤ ብሎም ጠይቆ ነው የሚያልፈው። በመሆኑም ይህ መከላከያ ሰራዊት አስገድዶ ወይም በግዴለሽነት በህዝብ ላይ የሚያደርሰው አንዳችም ነገር የለም። በዲሲፕሊን መታነጽ ማለት እኮ አንዱም ይህ ነው።
አሁን እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ህዝብን ለመርዳት ለመደገፍ ለህዝብ ዘብ ለመቆም ነው ውስጡ ያለው ግን ደግሞ ዘብ የቆመለት ህዝብ ላይ አሁን እነሱ እንደሚሉት አይነት ወንጀል ይፈጽማል ተብሎ እንዴት ይገመታል። ሊታሰብም የሚገባ አይደለም። እንግዲህ እኔ እንዳየሁት ነው የምነግርሽ፤ ሰራዊቱ በጣም ጨዋ በወታደራዊ ስነ ሰርዓት የታነጸ እና ለህዝብ የቆመ ነው።
በነገራችን ላይ ይህ ሰራዊት እኮ ለህዝብ የቆመ ወይም ህዝባዊ ባይሆን ኖሮ ለምን ብሎ ነው ከገበሬ ጋር እርሻ የሚውለው፤ የሚያርሰው፤ የሚጎለጉለው፤ የሚያጭደው፤ የሚሸከመው፤ ለህዝብ ፍቅር ስላለው አይደል ? የመከላከያ ሰራዊት ትግራይ ላይ ብቻ እኮ አይደለም የዘመተው፤ የሰላም አስከባሪ ሆኖ የተለያዩ አገራት ላይ ሄዷል። በዚህም እጅግ ስመ መልካም
ነው። ለምሳሌ ብሩንዲ የእኛን ሰራዊት ጨምሮ ከዓለም የተውጣጡ ሰላም አስከባሪዎች ተሰማርተው ነበር። በዚህ ወቅት ምንድን ነው የሆነው? የኢትዮጵያ ሰራዊት ብቻ ከህዝብ ጋር ተቀላቅሎ ህዝቡን መስሎ ሰላማቸው ሲያስከብርላቸው ነበር፤ በዚህም ከሁሉም በተለየ ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርገው እስከ አሁን ያነሱታል። በመሆኑም በዚህ ጨዋነቱና ህዝባዊነቱ በተሰማራበት ሁሉ ተወዶና ተመስግኖ ተደንቆ ነው የሚመለሰው ተወቅሶም አሁን እንደሚሉትም ተከሶ አያውቅም።
አዲስ ዘመን፦ እንደዚህ የምንኮራበትና የአገርን ሉአላዊነት የሚያስከብር ሰራዊት ቢኖረንም አሁን ላይ ወጣቱ ይህንን ሰራዊት ለመቀላቀል የሚያመነታበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፤ እንደው እንደ ዜጋ መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል የእኔም ግዴታ ነው ብሎ ወጣቱ እንዲያስብ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ ይህ እኮ ልመናም የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፤ ለአገር ዘብ መቆም ክብር ነው፤ አገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚል ሁሉ ጤንነቱ እድሜው ከፈቀደለት ለምን አይቀላቀለም፤ ቀስቃሽም መፈለግ አይገባም። እንደውም እድሉን ስላገኘ መደሰት ነው ያለበት። እኔ ድሮ አውቃለሁ ወጣቶች ወታደር ለመሆን ፈልገው ከተመለመሉ በኋላ የጤና ሁኔታቸው ሳይፈቅድ ቀርቶ አትቀላቀሉም ሲባሉ በጣም ነበር የሚያለቅሱት፤ እስከቻልን ድረስ እናገልግል ብለው ይማጸኑም ነበር። ይህ ምንም ሳይሆን የአገር ፍቅር፣ ለአገር መሞትም ክብር መሆኑን በመረዳት ነው። ወጣቱ አገሬን እወዳለሁ ካለ ቁጭ ብሎ በማህበራዊ ሚዲያ የሰራዊቱን ጀግንነት ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ተተኪ ለመሆን ለእናት አገሩ ብሎ ውትድርናን ወዶና ፈቅዶ መቀላቀል አለበት። ይህ ካልሆነማ የጠላት መፈንጪያ መሆን ይመጣል፤ ያን ጊዜ የሚኮራበት አገር አይደለም መኖሪያም ይጠፋል። በመሆኑም ወጣቱ ይህንን አያውቅም ብዬ አላስብም፤ ግን ደግሞ ያለማንም ቀስቃሽና ውትወታ ወዶና ፈቅዶ እናት አገሩን ለማገልገል መነሳት እንዳለበት ይሰማኛል።
አዲስ ዘመን፦ ምናልባት ወጣቱን ከውት ድርና ሙያ ያራቀው ህወሓት ባለፉት 27 እና ከዛ በላይ ዓመታት የሰራው ስራና ያጠፋው አገራዊ ስሜት ይሆን ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ የአገር ፍቅር ስሜት እኮ በደም ውስጥ ያለ ነው። ማንም ምንም ቢል በቀላሉ የሚሸረሸር ነው ብዬ አላስብም።አገር ማለት ሁሉም ነገር ነው፤ አገር የሌለው ሰው እኮ ምንድን ነው፤ እኔንጃ ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም። ወጣቶች የሚማሩት ገንዘብ የሚያፈሩት ቤተሰብ መስርተው ራሳቸውን የሚተኩት አያት ቅድመ አያት ሆነው ተደስተው መኖር የሚችሉት አገር ሲኖራቸው ብቻ ነው፤ ይህንን ማወቅ ያስፈልጋል።
በመሆኑም እኛው እራሳችን ወታደር ሆነን ዘብ ካልቆምንላት ማን ሊጠብቃት ነው ወይስ የውጭ ሀይል ቀጥረን ልናስጠብቃት ነው። አገሩን የሚያቀና የሚጠብቅ ህዝብ ነው። አገር ሲደላት ብቻ ሳይሆን ሲከፋትም ከጎኗ ቆመን የምትፈልግብንን መስዋዕትነት ልንከፍልላት የግድ ነው።
ሰላም እኮ በልመና የሚመጣ አይደለም፤ መስዋዕትነት ይጠይቃል፤ ያ መስዋዕትነት የሚጠየቀው ደግሞ ከጥቂት ሰዎች ሳይሆን ከሁላችንም ነው፤ እናም በዚህን ያህል ማሰብ በግዳጅ ሳይሆን በፍቅር ውትድርና ተቀጥሮ ለማገልገል እና ክብርን ለመጎናጸፍ መነሳት ያስፈልጋል።
ህወሓት አጥፍቶት ይሆን ብለሽ ለጠየቅሽኝ ህወሓት የአገር ፍቅር ስሜትን በምን መልኩ ከውስጣችን ሊያወጣ አይችልም። እንደዛም የማድረግ ሀይል አልነበረውም። እኔ ግን የምጠራጠረው ምናልባት ወጣቱን ወደ ውትድርና ሙያ እንዲመጣ የምንጠራበት መንገድና የምናስረዳበት አግባብ ትክክል መሆን አለመሆኑን ብንፈትሽ ብዬ ነው። ከዛ ውጪ ግን ለአገሩ መስዋዕት ለመሆን የሚሳሳ ህዝብ አለን ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ያለው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ሀይል ለአገር ስጋት የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ብለው ያስባሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ በምንም ዓይነት መንገድ ለአገር ስጋት ይሆናል ብዬ አላስብም፤ ሽምቅ ተዋጊ እኮ በሰለጠኑት አገሮች አለ፤ ይህ ሀይል አዎ ሰላም ይነሳል፤ የልማት አውታሮችን እየተደበቀ ሊያወድም ይችላል፤ ለማጥፋትም ጊዜ ይወስድ ይሆናል፤ ነገር ግን ተደራጅቶ አቅም አግኝቶ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል ግምት በእኔ አእምሮ የለም። ሊሆንም አይችልም። ትላንትና እኮ ወደ ውጊያ የገባው የራሳችንን መድፍ አየር መቃወሚያ ሚሳኤል ይዞ ነው፤ ስጋትም መሆን ቢችሉ ያኔ ነበር፤ ዛሬማ ሁሉንም ነገር ከተቀሙ በኋላ ክላሽ ተሸክመው ነው የአገር ስጋት የሚሆኑት? በፍጹም መቼም የሚሆን አይደለም።
ምናልባት ግምቴ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ አሸባሪው ህወሓት ተደራጅቶ ታጥቆና አቅም አግኝቶ በኢትዮጵያ ህልውና፣ ነጻነትና አንድነት ላይ ስጋት ሊፈጥር አይችልም።
አዲስ ዘመን፦ እንደዚህ አይነት ግጭቶች በወታደራዊ ግዳጆች መፍትሔ አይገኝላቸውም ይባላል፤ አንዳንዶችም የሰሜኑን ጉዳይ በዚህ መልኩ ያዩታል፤ ፖለቲካዊ መፍትሔውስ ምንን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ይጠበቃል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ ህዝቡም ሆነ ይህንን የሚሉ አካላት እንዴት እንዳዩት አላውቅም እንጂ ይህንን አሸባሪ ቡድን ወደሰላም ለማምጣት በፖለቲካዊ ዘርፉ ያልተሞከረ ነገር የለም። እናቶች ጡታቸውን አውጥተው ተንበርክከው እያነቡ ሰላም አውርዱ ብለው ለምነዋል፤ እነሱ እኮ የኢትዮጵያን ህዝብ ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ደሙን መጠዋል፤ ያልሰሩት ወንጀል የለም፤ ይህንን ደግሞ ሁላችንም እናውቃለን፤ ነገር ግን የፌደራል መንግስቱም 27 ዓመት አገርንና ህዝብን የበደላችሁት በደል ሁሉም ይቅር። የዘረፋችሁትንም ገንዘብ አንጠይቅም። በወንጀልም አትጠየቁም፤ ብቻ ሰላም እንፍጠር፤ ብሎ ተደጋጋሚ እድሎችን ሰጥቶ ነበር፤ ከዚህስ በላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ምን አለ? ግን ደግሞ ይህንን ሁሉ እድል ረግጠው መንግስትን ጎትተው ጦርነት ውስጥ አስገብተዋል፤ ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች መፍትሔው ፖለቲካዊ ውይይት ሳይሆን የጦር ግዳጅ ብቻ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜ በራሱ ትምህርት ይሰጣል፤ ህዝቡም ይረዳል የሚል ግምት አለኝ። ምን መሰለሽ ችግር ብዙ ያስተምራል፤ የትግራይ ህዝብም አሁን ህወሓት በፈጠረው ችግር እየተሰቃየ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን 27 ዓመት አእምሯቸው ላይ የተጫወተው ጨዋታ ደግሞ በቶሎ ሊለቃቸው አልቻለምና አሁን መከላከያውን ጠልተው ህወሓትን የወደዱ ቢመስሉም ዋል አደር ሲሉ ችግሩም እየጠና ሲሄድ መማራቸው ወደአእምሯቸው መመለሳቸው የማይቀር ነው።
ህዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ በሆነ ባልሆነ ነገር የቅርቡን እንኳን ብናስታውስ ከሻዕቢያ ጋር በነበረ ጦርነት የመላው አገሪቱ ወጣቶች የተሳተፉ ቢሆንም አብዝተው የተጎዱት ግን ትግራዋያን ወጣቶችና እናቶች ናቸው። አሁን ደግሞ የስልጣን ጥም አልወጣ ባላቸው ሰው በላዎች ምክንያት ወጣቱ እየተማገደ ነው፤ ታዲያ እናቶችስ አባቶችስ እስከ መቼ ድረስ ነው ወልደው ለእሳት እየገበሩ የሚኖሩት? በመሆኑም ይህንን መረዳታቸው ይቀራል ብዬ አላስብም፤ ምናልባት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ግን ሰላም መምጣቱ፣ ሰውም የጥሞና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙም ይቀራል የሚል ግምት የለኝም።
አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻ አገርን በብዙ አውዶች በጀግንነት እንዳስጠራ ወታደር አሁን ካለንበት ጊዜያዊ ችግር መውጫ መንገዱ ምንድን ነው ይላሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ እኔ ለአገሬ ሰላም ነው የምመኝላት፤ ግን ደግሞ አገራችንን ወደፊት ለማስኬድ ከድህነት አውጥተን የበለጸጉት አገራት ተርታ እንድትመደብ ለማድረግ ዋናው የሚያስፈልገን አንድነት ነው። አንድ ከሆንን ሰላማችንን እናመጣለን፤ በእርግጥ ሰላምን ለማምጣት እያንዳንዳችን ለራሳችን መባላታችን ማናቆራችን ምንድን ነው የሚያመጣልን ማለት መቻልም አለብን።
አሁን ያለንበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ የሚመጥናት አይደለም፤ ከማንም በላይ ሀብት አለን ግን ሰርተን ለመበልጸግ ወይም ለመጠቀም ሰላም ያስፈልግናል። ነገር ግን እንደ ህወሓት ያሉ የሚያባሉ አካላት ሀብታችንን በአግባቡ አልምተን እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆነው ነው ያሉት። በመሆኑም ከምንም ጊዜ በላይ በንጹህ ልቦና አንድነታችንን አጠናክረን ከመንግስት ጎን ቆመን አገራችንን ማሻገር ይገባናል። ይህንን በማድረጋችን ደግሞ ማንም ሳይሆን ተጠቃሚዎቹ እኛው ብቻ ነን።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን እኔ እበልጥ እኔ ብለው መፎካከራቸው ጤናማ ቢሆንም ውስጣቸውን ከግጭት ፍላጎት አጽድተው ደጋፊዎቻቸውን አረጋግተው እንደ አንድ አስበው ዛሬ ባይሆን ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት አገርን በሚያሻግር ሀሳብና ስራ ላይ ትኩረታቸውን ቢያደርጉ መልካም ነው።
የትግራይ ህዝብም ባደረገው ነገር ቢጸጸት እርሱ ላይ እየተደረገ ስላላው ንግድም ቢነቃና ኢትዮጵያዊነቱን አጉልቶ ሰላሙን አምጥቶ እርሱ የልማቱ፣ የሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው እንግዲህ ምኞቴን መግለጽ የምፈልገው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013