ያለፉት ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያውያን አስጨናቂ ነበሩ። ብዙዎች ይቺ ሀገር ወዴት እየሄደች ነው ብለው ጠይቀዋል። ብዙዎች ሀገሪቱ በእርግጥ እንደ ሀገር ትቀጥላለች ወይ የሚል ሃሳብ ሲያባዝናቸው ከርሟል። ኢትዮጵያን እናውቃታለን የሚሉ ባዕዳን ሀገሪቱ ከአሁን በኋላ ትፈርሳለች ወይስ አትፈርስም ሳይሆን መቼ ትፈርሳለች በሚለው ላይ ብዙ ትንታኔ ሲሰጡ ከርመዋል። የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ሀገሪቱ ስትፈርስ እንዴት ድርሻቸውን ይዘው እንደሚሸሹ ሲያሰሉ ፤ ሲቀምሩ ፤ ሲጣመሩ እና ሲደራጁ ከርመዋል። እለት ከእለት ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እየተወሳሰበ ሲመጣም ብዙዎች ይህን ጊዜ በጥበቡ እንዲያሻግራቸው ወደ ፈጣሪያቸው ጸልየዋል።
ለብዙ ኢትዮጵያውያን ያለፉት 36 ወራት እንዲሁ አለመሞትን ብቻ ግብ አድርገው የኖሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ብዙዎች ትልልቅ እቅዶቻቸውን ለመተግበር ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አስፈርቷቸው ሃሳባቸውን በይደር አሰንብተው ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ማግባት ፤ ቤት መሥራት ፤ ንብረት ማፍራት ፤ ኢንቨስት ማድረግ ወዘተ…. የማይመከር ሃሳብ እየሆነ ነበር። ለብዙዎች ትልቁ ሃሳብ የነበረው እየሆነ ያለው ሳይሆን ወደፊት ሊሆን የሚችለው ነበር። ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ሲያስቡ ምርጫን ያስባሉ ፤ የህዳሴ ግድብን ያስባሉ፤ የህወሓት እና የፌዴራል መንግሥቱን ግንኙነት መወጠር ያስባሉ ፤ የኦነግ ሽኔን አይን ያወጣ ውንብድና ያስባሉ… እነዚህን ሁሉ ሲያስቡ ደግሞ ይፈራሉ። ምርጫው እንደ ልማዱ ደም ሳያስገብር እንዲሁ በቀላሉ እንደማያልፍ ፤ ህወሓትም ሀገር ሳታፈርስ እንዲሁ በባዶ እጅ እንደማትሰጥ ፤ ግብፅም የሆነ ነገር ማድረጓ እንደማይቀር ፤ኦነግም መበጥበጡን እንደማያቆም እና እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደግሞ የሚያስከትሉት ሁከት ዳፋው እንደሚደርሳቸው ያመኑት ኢትዮጵያውያን ብሩህ ነገር ከፊታቸው አልታይ ብሏቸው ነበር።
ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያውያን ትልልቆቹን ፍርሀቶቻ ቸውን ተጋፍጠው እንደ ተራራ ገዝፈው ይታዩ የነበሩት ችግሮች እንደፊኛ ሲተነፍሱ እየተመለከቱ ነው። 1997ን የሚያስንቅ ደም የመፋሰስ ትርዒት ይታይበታል ተብሎ የተጠበቀው ምርጫ ከተጠበቀው በተቃራኒ ፍጹም ሰላማዊ እና በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሆኖ አለፈ። ብዙዎች ይህ ምርጫ እስከአሁን ሲብላላ የከረመው የፖለቲካ ጥንስስ ገንፍሎ የሚወጣበት እንደሆነተንብየው ነበር። ድህረ ምርጫ ሁከት የተለመደ በሆነባት አፍሪካ እንደሚሆነው ሁሉ በምርጫው ማግስት ለሚፈጠረው ትርምስ የአቅማቸውን ነዳጅ ለማርከፍከፍ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው የጨረሱ “አጋሮቻችን”ም ብዙ ነበሩ። እሳቱ መቀጣጠሉ እንደማይቀር የሰጉ ኢትዮጵያውያንም “ቆይ እስኪ ይሄ ምርጫ ይለፍ” እያሉ በስጋት ታስረው ተቀምጠው ነበር። አሁን አንዱ ተራራ ተንዷል። ምርጫው አሁን ለኢትዮጵያውያን የስጋት ሳይሆን የኩራት ምንጭ ሆኗል። ታሪካዊው ምርጫ በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ የመጣ መከራ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የመጣ ራስን መግለጫ ታሪካዊ ዕድል ሆኖ አልፏል።
ሌላኛው ለኢትዮጵያውያን የስጋት ምንጭ የነበረው የህዳሴ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድቡን ይወዱታል። ብዙ ተስፋም ጥለውበታል። ነገር ግን ትልልቅ ጠላቶች እንደሚያፈሩበትም ያውቃሉ ፤ አፍርተውበታልም። በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከዚያ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ቁጣ እና ፉከራ ከዚያኛው ወገን መምጣቱ ወደ ጦርነት ልንገባ ነው እንዴ የሚል ስጋት ፈጥሮ ከርሟል። የግብፅ እና አጋሮቿ ፉከራ እንዲሁ በንቀት ለማለፍ የሚቻል አልነበረም። ከአባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ከተነካች ጉድ ይፈላል የሚሉት የግብፅ ፕሬዚዳንት እና ሹማምንት በተለይም ሁለተኛው ሙሊት ከተጀመረ ጦርነት አብሮ እንደሚጀመርም በዘወርዋራው አስጠንቅቀው ነበር። በመናጆነት ከያዟቸው አንዳንድ የሱዳን የጦር መሪዎች ጋር በመሆንም የጦር ልምምድ እና ትርዒትም አድርገው ነበር። በዲፕሎማሲውም ረገድ የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማሳጣት ጥረው ነበር። እነዚሁ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ኢትዮጵያውያን ምርጫውን ቢያልፉ እንኳ ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሊት ግን ቀላል እንደማይሆን ገምተው ነበር። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጸጥታው ምክር ቤት በነበረው ስብሰባ ላይ የታየው ነገር ይሔኛውም ፈተና መታለፍ መጀመሩን ነው። ከቁጣ እና ውሸት በቀር ባላንጣዎቻችን እውነት እንደሌላቸው ባሳዩበት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ከግድቡም በላይ ለአፍሪካ እና አፍሪካውያን ሉአላዊነት በመሟገት አፍሪካውያንን አኩርታለች። አሁን ባለው ሁኔታም ግድቡን ከመሙላት የሚያስቆመው ምንም ዓይነት ጥበብ የለም። በእንግሊዙ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆነው እና ላለፉት 10 ዓመታት የግድቡን ግንባታ በጥንቃቄ ሲከታተል የኖረው መሀመድ ባሽር ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት “ከምህንድስና እና ከፊዚክስ አንጻር ካየነው የግድቡን ውሃ መሙላት ማስቆም የሚቻልበት መንገድ የለም” ብሏል። ግድቡን ውሃ ከመሙላት ማቆም አይቻልም ማለት ደግሞ ኢትዮጵያን አሁን ማስቆም አይቻልም ማለት ነው።
ሌላኛው ለኢትዮጵያውያን ራስ ምታት ሆኖ የነበረው የህወሓት ጉዳይ ነው። አሁን የሽብር ቡድንነቱ በይፋ በአደባባይ የተነገረለት ህወሓት ከማእከላዊ መንግሥቱ ጋር ይዞ የነበረው እሰጥ አገባ መጨረሻው እንደማያምር ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱን አንድነት አደጋ እንደሚፈጥርም ነበር። በተለይም ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በዘረፋም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይዞት የነበረው ከፍተኛ ሀብት እና ከክልሉ እንዳይወጣ አግቶት የነበረው ሰራዊት መጠን ህወሓትን በኢትዮጵያ ላይ የተጠመደ ቦንብ አድርጎት ነበር። ይህ ሀገር ላይ የተጠመደ ቦንድ የፈነዳ ቀን ብዙዎችን ይዞ ወደገደል እንደሚገባ ፤ ሀገሪቱንም ወደለየለት የእርስበርስ ጦርነት እንደሚከትም ታምኖ ነበር። ነገር ግን ያ ቦንብ ራሱ አጥማጁ ላይ ፈነዳ። ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ህወሓት የሰሜን እዝን ሲያጠቃ ቀለበቷን ራሱ እና የትግራይ ህዝብ ላይ ሳበው። አሁን ቦንቡ ከጁንታው መሪዎች ግማሹን አስፈንጥሮ ወደ ቃሊቲ ሲልክ የተቀሩትን ወደ መቃብር ሸኝቷል። ዛሬ ላይ ከጁንታው የቀረው ኃይል ራሱ ባፈነዳው የክፋት ቦንብ የራሱን ጭንቅላት፤ እጅ እና እግር ቆርጦ የሚንፈራገጥ ነው። አሁን ላይ ከሰሜን በኩል ለኢትዮጵያ ደህንነት ስጋት የሚሆን ኃይል የለም። ሦስተኛውም የስጋት ተራራ ተንዷል።
ዛሬ ላይ የተወሰነ አባጣ ጎርባጣ ቢኖረውም የኢትዮጵያ ህልውና በስጋት ተራራ የተጋረደ አይደለም። ይልቁንም ወለል ብሎ የሚታይ አዲስ ቀን አለ። ሜዳ እየሆነ ከመጣው ተራራ ወዲያ ደግሞ የሚታይ ለምለም መስክ አለ። እዚያ መስክ ላይ ኢትዮጵያውያን ከስጋት ተላቅቀው ችግኝ እየተከሉ ነው። ዛሬ ትፈርሳለች ነገ እየተባለ ሲሟረትባት የነበረች ሀገር አሁን ከ70 እና 80 ዓመት በኋላ ዛፍ ሆነው ኢትዮጵያን ያለመልማሉ ተብለው የሚታሰቡ ችግኞች እየተተከሉባት ነው። አሁን ላይ ከእለት ተእለት ሃሳብ ከፍ ተብሎ የረዥም ጊዜ እቅዶች ማቀድ ተጀምሯል። የ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ለዚህ ምስክር ነው። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ አፈር ልሳ ተነስታለች። አነሳሷ ደግሞ ወዳጅን የሚያስደስት ጠላትን የሚያሰጋ ሆኗል። የኢትዮጵያ ጊዜ እነሆ ደርሷል!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013