ህወሓት ገና ከመጠንሰሱ ጀምሮ ያካሂድ የነበረው የሴራ ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር በነበረባቸው ዓመታት ውስጥ ሰዎች በተፈጥሯቸው የተቸራቸውን መብት እንኳ ነጻ ሆነው እንዳያጣጥሙት ሴራውን ማር በመሰለ ነገር ሸፍኖ መርዝ እንዲውጡ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። ይህን የማድረጉን ተግባር የተያያዘው ገና በረሃ እያለ ሲሆን፣ ጅማሬውንም ያደረገው የእኔ በሚለው የህብረተሰብ ክፍልም ጭምር እንደሆነ ነው በስፋት የሚነገረው። አሁን እንኳ ተንኮታኩቶ ባለበት ጊዜ ብቻውን ከመሞት ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ተረጋግተው ልማታቸውን እንዳያከናውኑ በየቦታው እላቂ መርዙን በመርጨት ላይ ይገኛሉ። እርሱን ይጥቀመው እንጂ ስለማንም ግድ የማይሰጠው አሸባሪው ህወሓት፣ ከሰሞኑን መንግስት ከትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ ደርሶ መውጣቱን ተከትሎ መንግስትን ደግፈዋል በሚል ሰዎችን እየገደለና እያሰቃየ የመጨረሻ መርዙን በማጠንፈፍ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አዲስ ዘመን ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አሰናድቷል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ። አዲስ ዘመን፡– ህወሓት ሰሞኑን ደግሞ የተከዜ ድልድይን ማፍረሱ እየተገለፀ ነው፤ ከዚህ በፊትም የመቀሌ አየር ማረፊያን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ሲያወድም ነበር፤ ለመሆኑ ይህ ምን ፖለቲካዊ አንድምታ አለው?
አቶ ኦባንግ፡– እንዲህ አይነት አካሄዳቸው ሁሉ በእኔ መንገድ ካልሄደ ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። በቀላል ቋንቋ ያለእኔ መንገድ ሌላ መንገድ የለም የሚል ነው። የእነሱ ፍላጎት እኔ እስከተጠቀምኩ ጊዜ ድረስ ስለሌላው አያገባኝም ነው። እንደጠቀስሽውም የመቀሌን አየር ማረፊያም ከዚህ ቀደም ያወደሙት እነሱ ካልተጠቀሙበት ሌላ ሰው እንዳይጠቀም በመፈለግ ነው። በዚህም ምግባራቸው መሰረተ ልማቱ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ቢጠቅም ባይጠቅም ለእነርሱ እስካልሆነ ድረስ ምንም ግድ እንደማይሰጣቸው ያሳያል።
እነርሱ ለትልቋ ኢትዮጵያ ቀርቶ የእኔ ለሚሉት ክልል እንኳ ቅንጣት ያህል አዘኔታ የሌላቸው ናቸው። በየትኛውም መንገድ ይሁን እነሱን ሊጠቅም የሚችል ነገር ካለ ብቻ ነው ደስተኛ የሚሆኑት እንጂ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የቱንም ያህል ፈተና ውስጥ ቢገባ አይጨንቃቸውም።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ የውጭ ሃይሎች የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ መውጣቱን በአወንታዊ መልኩ ሲቀበሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ ትክክል አለመሆኑን ይገልጻሉ፤ ለመሆኑ እነዚህ ሃይሎች የተለያየ አቋም የሚያራምዱበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡– የኢትዮጵያ ጦር ከመቀሌ መውጣት የለበትም ያሉ አካላት እንግዲህ የራሳቸው አቋም ቢኖራቸው ነው። ይውጡ ያሉትም እንዲሁ የራሳቸው አቋም ቢኖራቸው ነው። በእርግጥ ጦርነት እስከተጀመረ ድረስ እስከማጠናቀቂያው መጨረሻው እዛው መቆየት አለባቸው የሚሉ አሉ። በእርግጥ ለዚህ አባባላቸው ጦሩ ከዛ ከወጣ ወያኔ ያይላል ከሚል አስተሳሰብ ይመስለኛል። ምክንያቱም የኢትየጵያ መከላከያ ኃይል በስፍራው የማይኖር ከሆነ ሌሎች ጠላቶች እድሉን ይጠቀሙበታል፤ ከዚህም የተነሳ ችግር ያጋጥማል ከሚልም የተነሳ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ጦሩ ይውጣና እነርሱ ራሳቸውን ያስተዳድሩ ከሚል የመነጨ አስተሳሰብም ይመስለኛል።
እንዲያም ሆኖ ይውጡ አይውጡ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። በጉዳዩ ዙሪያ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጋራ መፍትሄ ሊኖረው ይገባል ባይ ነኝ። አሁን ግን የጋራ መፍትሄ ነው ብዬ አላስብም። ከዚህ በኋላ የሚፈጠረው ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም። ጉዳዩን እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋችነቴ ሳስተውል የሰዎች ህይወት ትናትም ዛሬም እየጠፋ ነውና ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። ተማሪዎችም በዚያው እንደመገኘታቸው ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ጦሩ ከትግራይ መውጣት የለበትም የማለታቸው ምስጢር አንዱ የሲቪሉ ህብረተሰብ ጉዳይ አሳስቦትም ነው ብዬ አስባለሁ። ይውጣም ሲሉ ደግሞ እስከመቼ ድረስ ተጠባብቆ መዝለቅ ይቻላል ከሚልም አተያይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እኔ አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ምንም ይሁን ምን ችግሩን አቅልዬ አላየውም። ኢትዮጵያ ብሄራዊ ፍላጎት ትልቅ ችግር እየሆነ ነው። ለምሳሌ ህገ መንግስት የሰጠው መብት እስከመገንጠል ድረስ የሚል ነው፤ እነሱም ይህን መብት ተከትለው ነገ እንገነጠላለን ካሉ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው መታየት አለበት ባይ ነኝ።
ይህን ስልሽ ጉዳዩን ዳር ሆነው የሚያዩ በርካቶች አሉ፤ በተለይ ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል በብዙ የሚጥሩ መኖራቸው ሊዘነጋ አይገባም። የኢትዮጵያን መበታተን ዳር ቆመው ሲመለከቱ የነበሩ አካላት በሚያገኙት ቀዳዳ ሁሉ በመግባት ለማፈራረስ መቻኮላቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህም ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ስህተት ከተሰራም ስህተቱን በማረም ሁኔታዎችን ማስተካከል የሚቀል ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– ባለፈው እንደተገለፀው የአሸባሪው ህወሓት ቡድኖች ከህዝቡ ውስጥ በመሆን ህዝቡን የጥፋት አካል ለማድረግ የሄዱበት መንገድ እንዴት ይታያል?
አቶ ኦባንግ፡– አካሄዱ ጤነኛ አለመሆኑ የታወቀ ነው። እነሱ እያሰቃዩ ያሉት ተራውን ህዝብ ነው። እነሱ ያሉት በህዝቡ ውስጥ ህዝቡን ተቀላቅለው ነው። ይህን ሁሉ ያደረገው የብሄር ፖለቲካው ነው፤ የብሄር ፖለቲካ ደግሞ መርዝ ነው። የብሄር ፖለቲካ በጣም ኋላቀር የሆነ አካሄድ ነው። የብሄር ፖለቲካ ሌላውን ዓለምም ያልጠቀመ ነው። በብሄር የተደራጀ አገር መጨረሻ ላይ መፍረሱ አይቀርም። በመጨረሻው ሰዓት እርስ በእርሳቸው መባላታቸው አይቀርም።
እነርሱ አሁን እያደረጉ ያሉት ብሄረሰቡን መነገጃ ማድረግ ነው። ለዚህ ማሳያ ደግሞ የእኔ የሚሉትን አካላት ከጎኔ ካልቆማችሁ እጨርሳችኋል የሚል ነው። ይህ የኋላቀርነት የፖለቲካ አካሄድ ነው። ይህ የጽንፈኝነት ፖለቲካ ነው። እንዲህ አይነቱ ፖለቲካ ጠቀሜታ የለውም፤ በመጨረሻም ሰዎች ይጎዳሉ። በተለይ እነሱ የሚጠቀሙበት የፖለቲካ ስልት የማስፈራራት ነው፤ የሚያስፈራሩት ደግሞ እኛ ከሌለን እናንተም የላችሁም በሚል ነው። ይህ አይነቱ ፖለቲካ ደግሞ ከቡድንተኝነት፣ ከሆዳምነትና ከጽንፈኝነት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።
በነገራችን ላይ እንዲህ አይነቱን ስልት የሚከተለው ህወሓት ብቻ አይደለም። ሌሎችም ይህን ስልት የሚከተሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። የብሄር ፖለቲካ የኋላቀርነት ማሳያ እንደሆነ እንኳ በአሁኑ ሰዓት የማያምኑ ሰዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ የህወሓትን መንገድ በመከተል ለመራመድ የሚፈለጉ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳ ብሄርተኝት እንደከረሜላ የሚጣፍጥ ነገር ቢሆንም ከገባ በኋላ ግን መርዝ በመሆን አንዱን ከሌላው ጋር የሚያባላ የሚያናክስ ነው። ይህን ደግሞ ወያኔ ለራሱ ጥቅም ሰርቶታል፤ አሁንም እያስኬደው ያለው ይህንኑ ነው።
ይሁንና ይህ አይነቱ አካሄድ እንኳን ለአገር ቀርቶ ለጥቂቶችም የማይጠቅም ነው። ለህወሓት ግን የራሳቸውን ጥቅም ለማራዘም ይጠቅማቸዋል። የተጠቀሙበት መሳሪያ ደግሞ አንዱ ህዝቡ ነው። ተጠቃሚዎቹ ግን የነበሩት ግለሰቦቹ ናቸው እንጂ ሰፊው ህዝብ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ የውጭ ሃይሎች በእርዳታና በሰብዓዊነት ስም ለነዚህ የሽብር ቡድን አባላት ድጋፍ እንደሚያደርጉ መንግስት በተደጋጋሚ ይከሳል፤ ከዚህ አንጻር ይህንን ለመከላከል ምን ማድረግ ይገባል?
አቶ ኦባንግ፡– እንደእኔ የኢትዮጵያ መንግስት ራሱ ራሱን መመርመር አለበት። አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው፤ ጉዳዩ እንዴት ተከሰተ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ የውጭ አገር ዜጎች እንዴት ነው በስፍራ ሊገኙ የቻሉት ሊል ይገባል። ህወሓት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሬት ላይ በሌለ እውነታ ሰው ሞተ፤ ሰው ተራበ ይላል።
ስለጉዳዩ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር ሊወያይ ይገባል። ለምሳሌ በክልሉ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በተለይ ደግሞ የተናጠል የተኩስ አቆም ውሳኔውንም በተመለከተ መንግስት ለኢትዮጵያውያን ሰፊ መግለጫ አስቀድሞ መስጠት ይጠበቅበት ነበር። ድንገት የሰማነው ከሚዲያ ነው። ያለውን ችግር በጋራ ስንሆን ነው መፍትሄ ማበጀት የምንችለው።
የውጭ አገር ዜጎችም እንዲገቡ በማድረጉ በኩል እኛ ነን በሩን የከፈትነው ባይ ነኝ። እንደ አንድ አካል ሆነን ችግሩን ለመፍታት መወያየት ካልቻልን ችግሩ እየባሰ ነው የሚመጣው። እንደሚመስለኝ የብዙዎቻችንን ምኞት ሰው በሰውነቱ እየተከበረ እንዲመጣ ነው። በመሆኑም ለዚህ ምን ያህል ዝግጁዎችና ቀና አሳቢዎች ነን በሚል ራሳችንን መመርመር አለብን።
አሁን አገራችን እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ አደገኛ ነው። በዚህ ጉዳይ ሁላችንም መወያየት አለብን። አገራችን ወደባሰ አደጋ እንዳትደርስ ልንነጋገር ይገባል። ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ፣ ሶሪያና ሊቢያ እንዳትሆን ምን ማድረግ አለብን በሚል መወያየት አለብን፤ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አለብን።
ስለብሄራዊ መግባባት እንኳ ሲነሳ ስልጣንን የሚቀማ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ይህን የመሰለ ጠንከር ያለ ፈተና ከፊት ተደቅኖ እንኳ ስለአገር ለማሰብ የማይፈልጉ አካላት መኖራቸው የሚያስደንቅ ነው። ስለዚህ በተናጠል ሳይሆን ሁሉም አካላት በመሰባሰብ አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሸማግሌዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም የመንግስት አካላት ስለጉዳዩ መወያየት አለባቸው። ያለን አንድ አገር እንደመሆኑ በተናጠል የሚደረግ ነገር ሳይሆን በአንድነት ነው ስለጉዳዩ ሊያገባን የሚገባው። እኛ ግን እየተነጋገርን ያለነው በዚህ ልክ አይደለም። ያለውን ችግር ወደሌላው ለማላከክ መሞከር የለብንም።
ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በሌሎችም ጫና ይደረግብናል። ይህ ለምን ሆነ ብለን ስንጠይቅ የእኛ መከፋፈልና በአብሮነት አለመንቀሳቀስን ተከትሎ የመጣ ነው የሚል ምላሽ ነው የምናገኘው። በዚህ አካሄዳችን እኛ ስለፈቀድንላቸው ነው ይህ ጫና የሚበረታው። በዚህ ዙሪያ ያለብንን ችግር ካመንንና ችግራችንን ለማስወገድ ቁርጠኞች ከሆንን ጫና አድራጊዎቹ በራሳቸው ጊዜ ያቆማሉ።
አገር ሲኖር ነው ስለፖለቲካም መነጋገር የሚቻለው፤ በመጀመሪያ አገር ሉዓላዊነቷ ሊከበር ይገባል። የውጭ ጣልቃ ገብነት ገዝፎ አንዱን ከሌላው ሊያባላ አይገባም። አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ደግሞ ሁሉም በያገባኛል መንፈስ መንቀሳቀስ አለበት። ለጊዜው ፖለቲካውንም ብሄሩንም ሳይሆን የሁላችን አገር ስለሆነችው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ነው ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን። እኛ እንደዜጋ ያጎደልነው ነገር አለ፤ የመፍትሄው አካል ለመሆን ምን ያህል ተንቀሳቅሰናል ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።
እኛ የውጭ አገር ጫናን ከጫንቃችን ለማውረድ መንቀሳቀስ መቻል አለብን። ህወሓት ከነጮቹ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሰፊ ነው። የውጭ አገር ሚዲያውንም በአንድ ወቅት ተቆጣጥረውት ነበር። በዲፕሎማሲውም ረገድ ህዝባቸውን አይጥቀም እንጂ ለራሳቸው በሚጠቅም መልኩ ሰፊ ስራ ነው የሰሩት። ምክንያቱም ላለፉት 27 ዓመታት ያህል አገሪቱን እንደፈለጉ በማድረግ ሲያስተዳድሩ የነበሩት እነርሱ ናቸው።
እኛ ዝም ብለን ጁንታ ጁንታ እንላለን፤ ጁንታ ማለት እኮ ህወሓት እና ደብረጽዮን ብቻ አይደሉም። የአረብ ጁንታ አለ፤ የጥቁር አሜሪካና የሌላውም ጁንታ አለ። ያለውን ችግር ግን ባለው ልክ እየተነጋገርን አይደለም። ስለዚህም በአግባቡ ስራችንን የማንሰራ ከሆነ ተንኮላቸው እየገዘፈ ይሄድብናል። ምክንያቱም እነሱ የተሻለ ግንኙነት ብሎም ቀደም ሲል ያከማቹት ሀብት አላቸው፤ ከዚህ ቀደም የነበራቸውንም ቀረቤታ እየተጠቀሙ ነውና ለምናደርገው ነገር ሁሉ ጥንቃቄ ያሻል።
እኛ እኮ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሳችንና አሜሪካም ሆነች ምዕራቡ ዓለም አንዴ በህዳሴ ግድባችን አንዴ ደግሞ ሌላ ሰበብ እየፈለጉ ጫና ሊያሳድሩብን መጣራቸው የወያኔ ውጤት ነው። ማንነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው ብለን ነበር የምናምነው። አሁን እየፈተነን ያለው መከራ ከሌላ ከማንም የመጣ ሳይሆን ራሳቸው ያመጡብን ነው። አገራችንን ለማፍረስ የሚዳዳቸው እነርሱ ባመጡብን ህገ መንግስት የተነሳ ነው። ይህንን እንኳ ማመን ነው የተሳነን። እርስ በእርሳችንም የምንባላውና በብሄር ተከፋፍለን ዋጋ እየከፈልን ያለነው እነርሱ ባመጡብን ጣጣ ነው። ይህንን ግን ልናምን አልደፈርንም፤ ችግራችንን ካላወቅን ግን መድኃኒት ማግኘት አንችልም። ዋና ጠላታችን ደግሞ አስተሳሰባችን ነው።
ለዚህ ሁሉ ችግር እየማገደን ያለው ደግሞ ብሄር ተኮሩ ህገ መንግስት፣ የዘረኝነትና የጽንፈኝነት ፖለቲካው፣ የኋላቀርነት ፖለቲካው፣ የብቸኝነት ፖለቲካውና የሆዳምነት ፖለቲካው ነው። ይህን ሁሉ ጠጥተን ሰከርን፤ ነገር ግን እንደሰከርን እንኳን ማመን አቃተን። ቀደም ብዬ እንዳልኩት የእኛ ትልቁ ጠላት የራሳችን አስተሳሰብና ቀና አለመሆናችን ነው። ስለዚህም የተንኮል፣ የቁማር፣ የኋላቀርና የበላይነት ፖለቲካ ከአገራችን ካልወጣ ቀጣይነታችን በራሱ ጥያቄ ውስጥ ነው የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ህዝብ አሁን ካለው ወቅታዊ ቀውስ ለመውጣት ምን ማድረግ አለበት ይላሉ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የሽብር ቡድኑ ሰላማዊ ሰዎችን እንዳይጎዳ ለማድረግ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
አቶ ኦባንግ፡– የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። እስካሁን የኖረውም ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ነው። ህወሓት ከመጣ ግን 27 ዓመቱ ነው። በተለያየ እንቅስቃሴው ከአርባ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። የትግራይ ህዝብ ግን በመቶ ቤት በሚቆጠር ዓመት አይደለም በኢትዮጵያዊነቱ እየኖረ ያለው በሺህ ዓመት እንጂ። ከትግራይ ህዝብ ጋር ተጋብተናል፤ ወልደናል። የትግራይ ህዝብን የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ታገኛለሽ። አንዳንዶች ስለትግራይ ህዝብ ሲነሳ ህዝቡ መቀሌ ብቻ ላይ ይመስለዋል። ህዝቡ ግን በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ እንዳለ መረዳት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ችግር ስለመኖሩ መረዳት የግድ ነው። ሌሎች በፖለቲካው ውስጥ የሌሉ ሰዎች ለዚህ ችግር መፍትሄ ማምጣት የሚችሉበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ለዚህ ችግር ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሊንቀሳቀሱ የሚገባበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው ብዬ አስባለሀ። የአማራ፣ የትግራይ፣ የአሮሞ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ ህዘብ ከሚል አስተሳሰብ መውጣትና ስለኢትዮጵያ መነገጋገር መቻል አለብን። እኛ ከዚህ አይነት አነጋገር በላይ ነን። እኛ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ሳንሆን የሰው ልጆች ነን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ነን።
የሚገርመው አንዳንዶች ከዚያው ከእነሱ መካከል ትግራይ እንድትገነጠል ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። እንበልና ትግራይ ተገንጥላ አገር መሆን ብትችል እንኳ ጎረቤቷ ልትሆን የምትችለው ኢትዮጵያ እንጂ አሜሪካ አይደለችም።
ስለዚህም በስሜትና በኋላ ቀር አስተሳሰብ የሚነዳ ፖለቲካ ለማንም አይጠቅምም፤ እነርሱ አስተሳሰባቸው ኢትዮጵያ ጠላታችን ናት የሚል ነው። ስለዚህም እንገነጠላለን የማለታቸው ምስጢር ስሜታዊ መሆናቸው ነው እንጂ መጨረሻ ላይ አይደርሱም። ለዚህ አስተሳሰባቸው ደግሞ የውጭ ጫና በመኖሩ ነው። አውሮፓውያኑም ሆኑ ሌሎቹ ለእነሱ አስበው ሳይሆን የራሳቸውን ትርፍና ኪሳራ አስልተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። አገራቱ ስለትግራይ ሲነጋገሩ ስለዐብይና ስለደብረጽዮን አይደለም፤ ወይም ስለብልጽግና እና ስለህወሓት አይደለም። ስለትግሬና ስለአማራ አይደለም። ከዛም በላይ ነው። ከዐብይም፣ ከደብረጽዮንም፣ ከብልጽግናም፤ ከህወሓትም ከአማራም፣ ከትግሬም በላይ ነው።
በአሁኑ ሰዓት አንድ ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊነት ብዥታን የሚፈጥርበት ጊዜ መሆኑ ነው። ሁላችንንም እየተሰማ ያለው ነገር ጨለማ ውስጥ እንዳለን አይነት ነው። በመካከላችን ቀናነት በመታጣቱ ስራችን እየከፋ መጥቷል። ለዚህ መፍትሄው መነጋገርና መወያየት ነው። ስለሌላው ከማውራት ይልቅ ስለራሳችን እንነጋገር፤ እንመካከር። ይህን ስል በፖለቲካው ዓለም ስላሉ ሰዎች ሳይሆን ከፖለቲካው ውጪ የሆንን ሰዎችን ነው። የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችንም ነው። አሁንም ጊዜ አለን፤ ብዙ ዜጎቻችን ተሰቃይተዋል፤ የተሰቃዩት ደግሞ በሌላ አገር ዜጋ ሳይሆን እኛው በእኛው ነው። በድንቁርና አመለካከትና በቆሻሻ ፖለቲካ ምክንያት ወገኖቻችን ተሰቃይተዋል። ስለሆነም ለዚህ ሁሉ ችግራችን በእኔ አመለካከት ፍቱን መፍትሄ ብዬ የምለው ብሄራዊ መግባባት ነው።
ቀደም ሲል በነበረው መግባባት አንዱ ወደአንዱ አካባቢ በመሄድ አገራችንን ከጠላቶቻችን እጅ አስጥለናል። አንዱ ዜጋ ወደሌላው አካባቢ በመሄድ ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል ሲሉ ሞተዋል። በወቅቱ ለአገር ፍቅር ካለን የላቀ ፍላጎት አጥንታችንን ከስክሰናል። ፖለቲካችንም እንዲህ የረከሰ አልነበረም። ለአሁኑ ችግራችን መፍትሄው እንደቤተሰብ መነጋገር ነው። ይህ ከሆነ ተሸናፊ አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡– ከልብ አመሰግናለሁ።
አክቲቪስት ኦባንግ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013