ጊዜው እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 1977 ዓ.ም ነው። ተፈጥሮ ሚዛኗን ስታ አየሩ እርጥበት ናፍቋል። ሳር ቅጠሉ ደርቋል፤መንጮች ነጥፈዋል። አርሶ አደሩና መሬቱ ተራርቀዋል። በተለይም የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በከፋ ድርቅ ተመትቷል። የሚላስ የሚቀመስ በመጥፋቱ ብዙዎች እንደቅጠል እየረገፉ ነው። ረሃቡ በተለይ በወሎና በትግራይ በመጽናቱ የቻሉት አካባቢያቸውን ለቀው ሲሰደዱ ያልቻሉት በረሃብ ከጎጇቸው ደጃፍ ላይመለሱ አሸልበዋል። ህጻናት የእናቶቻቸው ጡት ነጥፎባቸው በጨቅላነታቸው ተቀጭተዋል።
ይህንን መራር ሁኔታ በወቅቱ የነበረው የደርግ መንግስት ሊደብቀው ቢሞክርም ረሃቡ አፍ አውጥቶ የአለም መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። በርሃብ እንደቅጠል የሚረግፉትን ኢትዮጵያውያን የተመለከተው የአለም ማህበረሰብም እጁን ለእርዳታ ዘርግቷል። በተለይም አለም ላይ አሉ የሚባሉ የኪነጥበብ ፈርጦች ተሰባሰበው ‹‹WE ARE THE WORLD›› የተሰኘውን ድንቅ የሙዚቃ ክሊፕ ከለቀቁ በኋላ አለም በሙሉ ለኢትዮጵያ አነባ። ከፍተኛ መጠን ያለውም ዕርዳታ ወደ ኢትዮጵያ ጎረፈ።
በወቅቱ የደርግ መንግስት በሰሜኑ ክፍል ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ የእርዳታ እህሉን በቀላሉ ለማድረስ የሚቻል አልነበረም። በተለይም በትግራይ የነበረው ሁኔታ ጦርነት ታክሎበት የከፋ በመሆኑ ዕርዳታው ካልደረሰ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንደሚፈጠር የአለም መገናኛ ብዙሃን ጭምር በስፋት ያትቱ ነበር። ይህን አስከፊ ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀምም የወያኔ ቡድን በትግራይ ክልል ስንዴ የማከፋፈሉን ድርሻ ወሰደ። በደርግ መንግስት ፖለቲካዊ ዕሳቤ ቅሬታ የገባቸው ምዕራባውያንና ከነሱ ምጽዋት የሚሰጣቸው የዕርዳታ ድርጅቶችም ለተራቡ ዜጎች እንዲደርስ አለም ማህበረሰብ የሰጠውን ስንዴ የህውሃት ቡድን ያሻውን እንዲያደርግበት መልካም ዕድል ፈጠሩለት ። የሰለለች ንፍሱን ይዞ ሞቱን የሚጠባበቀው የህውሃት ሽፍታ ለረሃብተኞች የመጣውን ስንዴ ሸጦ የጦር መሳርያ ግዢውን አጧጧፈው። እርዳታ ተላከለት የተባለው ምስኪን ህዝብም በየበረሃው ወድቆ ረገፈ::
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የህወሃት የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ እንደሚያስረዱት ‹‹በ1977 በትግራይ የደረሰውን አስከፊ ድርቅ ተከትሎ በለጋሽ አገራት እና ህዝቦች ዘንድ ለነብስ አድንነት ተብሎ የተላከውን እርጥባን የህወሃት አመራር በጥሬ ገንዘብ የመጣውን በቀጥታ ወደግል ካዝናቸው በአይነት የተለገሰውን ደግሞ በሱዳን ገበያ በመቸብቸብ ለትጥቅ መግዣ እና ለግል ሃብት አዋሉት:: እርዳታ ተላከለት የተባለው ምስኪን ህዝብም በየበረሃው ወድቆ ረገፈ:: ለመለመኛ ለታሰበ ድራማ ወደሱዳን እንዲሰደድ በህወሃት የታዘዘው ረሃብተኛም በየመንዱ ቀረ:: የትግራይ ህዝብም ታሪክ ሊረሳው የማይገባው ታላቅ ክህደት ከአብራኩ ወጣሁ በሚሉ ከሃዲዎች ተፈጸመበት:: >>ሲሉ አሳዛኙን ታሪክ እማኝ ሆነው ያስረዳሉ።
ህወሃት ከ1977ዓ.ም ድርቅ በፊት መኖሩ የማይታወቅና የሽፍታነት ባህሪ የነበረው ቡድን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም እንዳስታወሱት ህወሃት ከድርቁ በፊት መኖሩ በአግባቡ የማይታወቅና አንዲትም መሬት ተዋግቶ ያልያዘ ቡድን ነበር። ሆኖም በግብረሰናይ ድረጅት ስም ከሚንቀሳቀሱና በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለመጫን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ስንዴ ሸጦ መሳርያ በመግዛት ኃይሉን ማጠናከር ችሏል። በምዕራባውያንና በረድኤት ድርጅቶቻቸው በመታገዝም የደርግ መንግስትን ገዝግዘው ለመጣል በቅተዋል።
አቶ ገብረ መድህን አርአያ እንደሚናገሩትም ምዕራባውያንና በረድኤት ስም የገቡ የስለላ ድርጅቶቻቸው ባደረጉለት ድጋፍም በ1981 ዓ.ም. ደርግ ትግራይን ለቆ እንደወጣ ህወሃት ካለምንም ችግር በሩ የተከፈተ ቤት በማግኘቱ ሰተት ብሎ መሃል ትግራይ ገባ:: ገብቶም አላረፈም:: በየከተማው ይኖሩ የነበሩ መምህራንን እንዲሁም የመንግስት ተቀጣሪ ዜጎችን ጠላት ብሎ በደርግ ደጋፊነት በመወንጀል ለቅሞ እንደፈጃቸው እማኝ ሆነው ያስረዳሉ።
ብዙዎች እንደሚያምኑት ምዕራባውያንና በረድኤት ስም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የረድኤት ድርጅቶቻቸው ባይኖሩ ህወሃት እንኳን ደርግን አሸንፎ ሀገር ሊመራ ይቅርና በአንድ አውደ ውጊያም ቢሆን የማሸነፍ ብቃት አልነበረውም። ሆኖም ግን በምዕራባውያንና በእርዳታ ድርጅቶቻቸው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በመግባት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በጨካኝ መዳፉ ሲያስተዳድራት ቆይቷል።
ምዕራባውያን በእርዳታ ስም ዘልቆ በመግባት የጠሉትን መንግስት የማውረድ የሚደግፉትን የማንገስ አካሄድ አላቸው። ህዝብ ደገፈም አልደገፈም፤ፈለገም አልፈለገም ምዕራባውያን እስከ ፈለጉ ድረስ በእርዳታ ስም ረጃጅም እጆቻቸውን አስገብተው ያሻቸውን እንደሚሰሩ ከኢኳዶር፤ከፓናማ፤ከኢንዶኔዢያ፤ከቬኒዟላ ታሪክ መረዳት ይቻላል።
ጆን ፔርኪንስ የተባለ አሜሪካዊ ባሰናዳው እና በእርዳታ ስም የሚሰሩ ሸፍጦችን ባጋለጠበት ‹‹confession of an economic hit man›› በተሰኘው መጽሃፉ በግልጽ እንዳሰፈረው በርካታ ሀገራት በእርዳታ ስም ፈርሰዋል፤የከፋ የኢኮኖሚ ድቀት ደርሶባቸዋል ወይም የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል። ከእነዚህ ሀገሮች አንዷ ኢኳዶር ነች።
ጊዜው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር 2003 ነው። የበለጸጉት ሀገራት አይናቸውን ኢኳዶር ላይ ጥለዋል። ሀገሪቱ በነዳጅ ምርት የበለጸገች በመሆኑ የምዕራባውያንን ቀልብ ገዝታለች። ይህንኑ ለመቀራመት ያሰቡ የምእራባውያን መንግስታት እና ተቋማት በድጋፍ ስም በስፋት ወደ ኢኳዶር ፈለሱ። ጥቂት ቆይተውም ለዘመናት በህብር ሲኖሩ የነበሩ ጎሳዎችን በማጋጨት ለዘረፋ እራሳቸውን አመቻቹ። ለዘመናት በሰላሟ የምትታወቀውም ኢኳዶር የግጭት ማዕከል ሆነች። ይህ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው የአሜሪካና የምዕራባውያን ድርጅቶች የኢኳዶርን ነዳጅ በስፋት መዝረፍ ጀመሩ። 1.3 ቢሊዮን ዶላር በመመደብም ሶስት መቶ ማይል ርቀት ያለው የዘይት ማስተላለፍያ ቧንቧ በመዘርጋት ነዳጁ ወደ አሜሪካ በገፍ እንዲሄድ ተደርጓል። ኢኳዶርም ለአሜሪካ ነዳጅ ከሚያቀርቡ አስር ሀገራት አንዷ ሆናለች። ኑሮው ከቀን ወደ ቀን እየጨለመበት የመጣው የኢኳዶር ህዝብ የአሜሪካውያንን ሴራ ባለመረዳት እርስ በእርሱ ሲባላ ቆይቷል። ለአመታት በተካሄደው ግጭትም የሀገሪቱ መለያ የነበሩ ነባር ባህሎች ለመጥፋት ተቃርበዋል።
ይህንን የአሜሪካውያንን ሴራ ቆይተውም ቢሆን የደረሱበት የኢኳዶሩ ፕሬዝደንት ጃሜ ሮልዶስ በእርዳታ ስም የሚሰሩ ሴራዎችንና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቶች እንዲቆሙ ጥረት ቢያደርጉም በመጨረሻ በእነዚሁ ዕኩይ ኃይላት ለመገደል በቅተዋል።
ከኢኳዶር በተጨማሪ በእርዳታ እና ድጋፍ ስም በሚፈጸሙ ሴራዎች ሰለባ ከሆኑ ሀገራት መካከል ፓናማ አንዷ ነች። የስዊዝ ካናልን የሰራው ፈረንሳዊ መሃንዲስ ፊዲናንድ ዲ. ሌሴ በመካከለኛው አሜሪካ ውስጥ የአትላንቲክንና የፓስፊክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኝ ቦይ በባህረ ሰላጤው ላይ ለመገንባት በወሰነበት ጊዜ ፓናማ የኮሎምቢያ አካል ነበረች። ሆኖም ፓናማ ለአሜሪካኖቹ መርከቦች መመላለሻ ሁነኛ ስፍራ መሆኑን የተገነዘቡት ፕሬዝደንት ሩስቬልት ፓናማን ከኮሎምቢያ ለመነጠል አሰቡ። ሲአይኤንና የመሳሰሉ የስለላ ድርጅቶችን በማስረግም ሀገሪቱ የብጥብጥ ማዕከል እንድትሆን አደረጉ። ሁኔታውን የሚቃወሙ ሚሊሻዎችና አስተዳዳሪዎችን በመግደል ፓናማ ከኮሎምቢያ የተገነጠለች ነጻ ሀገር መሆኗን አሜሪካ አወጀች፤፤ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የኮሎምቢያ ህዝብንም ሆነ መንግስት የሚሰማ አልነበረም። ይልቁንም በማን አለብኝነት ፓናማን የመገንጠል ስምምነቱ የተካሄደው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ፊሊፔ ቡኔ በተባለ የፈረንሳይ መሃንዲስ መካከል ነበር።
ሆኖም አዲስ የተመሰረተችው ፓናማ ሀገር ከማለት ይልቅ በረድኤት ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ሃብት መሰብሰቢያ እንጂ ለህዝቡ ጠብ ያለ ነገር ሊገኝ አልቻለም። ትላልቅ ሆቴሎች፤የመዝናኛ ስፍራዎች፤የማዕድን ማውጫዎች ፤ወዘተ የአሜሪካኖች ንብረት ነበር። ይህ ሁኔታ አልዋጥ ያላቸው የፓናማው ፕሬዝደንት ኦማር ቶሬዶስ ሁኔታውን ያወግዙ ጀመር። ይህ ሁኔታ ያስደነገጣቸው አካላትም ፕሬዝዳቱን በማስገደል ሁኔታው እንዲዳፈን አድርገዋል።
የኢኳዶር እና የፓናማ እጣ ከደረሳቸው ሀገራት መካከል አንዷ ቬንዟላ ነች። ቬንዟላ በዘይት ከበለጸጉት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነች። ይህ የተፈጥሮ ሀብቷ ግን ከብልጽግና ይልቅ ሁከትና ብጥብጥ መለያዋ እንዲሆን አድርጓታል። በተለይም እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1998 ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የተመረጡት ሁጎ ቻቬዝ ጠንካራ ሀገራዊ ስሜት የነበራቸው በመሆኑ በአሜሪካና በምዕራባውያን ዘንድ አልተወደዱም። ፕሬዝደንቱ ለአሜሪካና ለምዕራባውያን ፍላጎት ተገዢ ስላልነበሩ ጥርስ ተነከሰባቸው። ወዲያውም በስለላ ድርጅቶች አማካኝነት ሀገሪቱ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ ገባች። በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ መንገድ እስካሁን ውሉ ባልታወቀ ምክንያት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ህይወታቸው ቢያልፍም የሀገሪቱ ችግር ግን በቀላሉ የሚቀረፍ አይመስልም።
በእርዳታ ስም ከሚሸረቡ ሴራዎች ማምለጥ ያልቻለችው ሌላኛዋ ሀገር ደግሞ ኢንዶኔዢያ ናት። ኢንዶኔዢያ በእርዳታ ስም ከሚበዘበዙና ለሃብታም ሀገራት የማይነጥፍ የኢኮኖሚ ምንጭ ከሆኑ ሀገራት በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። የበለጸጉት ሀገራት ኢንዶኔዢያን እንረዳለን በሚል ወደሀገሪቱ በስፋት መግባት የጀመሩት እኤአ በ1970ዎቹ ነው። በዚህ ወቅት ኢንዶኔዢያ የተሻለ መረጋጋት የነበራትና ህዝቡም የነፍስ ወከፍ ገቢ የተሻሉ ከሚባሉ ሀገራት መካከል የሚመደብ ነበር። ሆኖም በእርዳታ ስም የገቡ የስለላ ድርጅቶች ሀገሪቱን ከተቆጣጠሩ በኋላ የሀገሪቱ አጠቃላይ ዕዳ አሻቅቧል፤በሀገሪቱ የደህንነት መጠንም ጣራ ነክቷል።
በአጠቃላይ በእርዳታ እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስም የሚሰሩ ቁማሮች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም። እንዲያውም በእርዳታ ስም የሚቋቋሙ ግብረሰናይ ድርጅቶች ዋነኛ አላማቸው ለተቸገሩ ወገኖች እርዳታ ማቅረብ ሳይሆን የበለጸጉ ሀገራትን ፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸም ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለው ደባም ይህንኑ ሃቅ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የአሸባሪው ህወሀት ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጭቆናና በደል አላንስ ብሎ በመከላከያ ሰራዊት ላይ አሳፋሪ ጥቃት ፈጽሞ እራሱ ከሳሽ ሆኖ ሲገኝ እነዚህ ምእራባውያንና ግብረ አበር የእርዳታ ድርጅቶቻቸው ቁርኝታቸውን ከአሸባሪው ቡድን ጋር ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ቡድኑ የምዕራባውያንን የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈ ጸሚያ መሳርያ በመሆኑ ምክንያት ብቻ ነው።
አሸባሪው ህወሃት ከጥንተ ፍጥረቱ ጀምሮ ለሀገር ደንታ የሌለውና የፖለቲካ ፍላጎቱ እስከተፈጸመለት ድረስም ሀገርን አሳልፎ ከመስጠት እንደማይመለስ በምዕራባውያኑ ዘንድ በሚገባ ስለሚታወቅ ሞቶ ከመቀበሩ በፊት ቡድኑን ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው። በ1977 ዓ.ም በእርዳታ ስም ከመጣ ስንዴ የቡድኑን ነፍስ መዝራት እንደተቻለ ሁሉ ዛሬም ያንኑ ለመድገም የሚደረገው ሩጫ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪ ቡድኑን ማንነት በአግባቡ ከመረዳታችንም በላይ ምእራባውያን በእርዳታ ስም የሚያደርጓቸውን ሴራዎች ለመረዳት የምንቸገር አይደለንም።
አንዳንድ ተዋንያን የሰብዓዊ ዕርዳታን ሽፋን በማድረግ የሽብርተኛ ክፍሉን በድብቅ ለማስታጠቅ እና መሣሪያዎችን ለማስገባት መሞከራቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒ ማስረጃዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮነን ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። እንደትላንትናው ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሙከራ ቢያደርጉም ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሴራቸውን እያከሸፈባቸው ይገኛል።
የረድኤት ድርጅት ነን በሚል የስለላ ስራ የሚያካሂዱና ጁንታውን እንደገና ከመቃብር ለማስነሳት እየተፍጨረጨሩ የሚገኙ አካላት ከባዶ ጩኸት ውጪ ለትግራይ ህዝብ ጠብ ያለ ነገር እንዳላደረጉለት በገሃድ አይተናል ። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት ጁንታውን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ክልሉን የመከላከያ ሰራዊት ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ከወታደራዊ ወጪዎች ውጭ ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ለሰብዓዊ ዕርዳታ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል። ይህም ለክልሉ ከሚመደበው አመታዊ በጀት በ13 እጥፍ የሚልቅ ነው።
መንግስት ይህን ሁሉ ድጋፍ ለክልሉ ህዝብ እያደረገ የሚገኝ ቢሆንም እጁ አመድ አፋሽ ሆኖበት አንድም ዓለም አቀፍ ተቋም መንግስት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ እውቅና የሰጠ የለም። ይልቁንም ችግሮቹን ብቻ እየፈለጉ ሲያናፍሱ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ የኖሩበት የሴራ መንገድ መሆኑን በተለያዩ ሀገራት ላይ ከደረሱ በደሎች መረዳት ይቻላል።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013