የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ በትግራይ ክልል ይገኝ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት በቅርቡ አስወጥቷል። መንግስት ሰራዊቱን ያስወጣው ትህነግ ለሀገሪቱ ስጋት ከመሆን መውጣቱን ፣ ሀገሪቱ ሌላ አጀንዳ ያላት መሆኑን ተከትሎ ነው። የትግራይ ህዝብም ጉዳዩን ቆም ብሎ እንዲመለከተው እድል ለመስጠት ታስቦ ነው።
ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ፋይዳ በተለያዩ መንገዶች ስታስገነዝብ ቆይታለች፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ዲያስፓራ በመንግስት ውሳኔ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ብዥታ ተፈጥሮባቸው የነበረ ቢሆንም እርምጃውን ወዲያውኑ ደግፈው ከህዝብ ጎን ቆመዋል። በርካታ መንግስታትና አለም አቀፉ እና አህጉራዊ ተቋማትም ለተኩስ አቁሙ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የተኩስ አቁሙ ለትግራይ ህዝብ የሰብአዊ አቅርቦት ለሚያደርጉ አካላት እንቅስቃሴ ከእስከ አሁኑም በላይ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይታመናል። መንግስት ለትግራይ ህዝብ ከሚያስፈልገው ሰብአዊ ድጋፍ 70 በመቶውን ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል። የእርዳታ ሰጪዎች አቅርቦት ከ30 በመቶ የማይበልጥ ነበር። ከሆነ ጊዜ በኋላም አብዛኛው ድጋፍ በረድኤት ድርጅቶች በኩል እንዲፈጸም በማድረግ ሙሉ አቅሙን በመልሶ ግንባታ ላይ ለማድረግ ወስኖ እየሰራም ነበር። የመኸር የግብርና ስራው እንዳይስተጓጎል በሚልም በክልል ግብርና ቢሮ ከተጠየቀው በላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ማቅረቡም ይታወቃል። ለእዚህም ስራ የሀገሪቱ አቅም ከሚፈቅደው በላይ ሀብት በመመደብ ነበር ሲሰራ የቆየው።
ይህ ሁሉ እየተደረገ ነው እንግዲህ መንግስት ሲከሰስ የነበረው። ጁንታው በክልሉ ሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር ስለሚፈልግ ብቻ የመንግስትን ሰብአዊ አቅርቦት በማስተጓጎል ላይ ተጠምዶ ቆይቷል። የመንግስት ጥረት እንዳይሳካ በጁንታው ያልተፈጸመ ተንኮል የለም።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን በክልሉ ረሀብ እንዲኖር አጥብቆ የሚሰራ ነው። ረሀብ ወደ ስልጣን ያመጣው መሳሪያ መሆኑን አሁንም በማስታወስ ወደ አጣው ስልጣን ለመመለስ ረሀብን መሳሪያ ማድረግ ፈልጎ እየሰራ ነው። የሰብአዊ አቅርቦት እንዳይዳረስ የሚያደርገውና የግብርና ስራው እንዳይካሄድ እንቅፋት የሚፈጥረው ለእዚሀ ነው።
በክልሉ ሰብአዊ ቀውስ ሲፈጠር ተጠቃሚ እንደሚሆን ስለሚያስብ ለዚህ ይረዳሉ ያላቸውን የጥፋት እርምጃዎች እየወሰደ ነው። ለክልሉ ሰብአዊ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለውን የተከዜን ድልድይ መስበሩም ይህንኑ ነው የሚያመለክተው።
የቡድኑ የክፋት ጥግ አሁንም እየታየ ነው። ቡድኑ ረሀብ ለመስራት ስላሰበ መንግስት በግብርናው ዘርፍ ላይ የያዘው እቅድ እንዲሳካ አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ ማደናቀፉን ተያያዘው። በሰው ልጅ ህይወት እየነገደ ነው፤ ይህን ማድረግ ለእሱ ምኑም አይደለም። ይህን እኩይ ተግባር እየፈጸመ፣ መንግስት ጉዳዩን ጨርሶ እንደተወው በማድረግ ህዝብ ተጎዳ እያለ በውሸት ፕሮፓጋንዳው ከመቃብር አውጥተው ስትንፋስ ለዘሩበት ምእራባውያን መንግስታትና አለም አቀፍ ተቋማት ሲከስ ቆይቷል፤ እነሱም ግራና ቀኙን ሳይመለከቱ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ሳያጤኑ መንግስትን ሲወቅሱ ሲኮንኑ ቆይተዋል።
መግደል ማሰቃየት ማፈናቀል ለስደት መዳረግ ስሪቱ የሆነው ይህ ቡድን ፊት ራሱ እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ መንግስትን ይከስ ነበር፤ ሲያሳብብበት የነበረው የመንግስት የጸጥታ ሀይል አሁን በአካባቢው የለም፤ አሁንስ ማንን ይከስ ይሆን።
አሁን ደግሞ ዜጎችን በጭፍጨፍ ዘመቻ ተጠምዷል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርንና የመከላከያ ደጋፊ ነበራችሁ ያላቸውን መግደሉን ማስቃየቱን ማፈሱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን ግፍ የፈሩ በርካቶች ደግሞ ወደ አማራ ክልል እና ኤርትራ እየተሰደዱ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ስደተኞችን እየገደለ ስለመሆኑም የሚመለከተው አለም አቀፍ ተቋም ጭምር ሪፓርት እያረገ ይገኛል።
ቡድኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመም ነው። ከአማራ ክልል ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለ እያለም ይገኛል፤ ወልቃይትና ራያን አስመልሳለሁ እያለ ነው። አማራ ክልል ላይ ዛቻ ከመሰንዘር አልፎ መተኮስም ጀምሯል። በቅርቡም በኮረም በኩል ተኩስ ከፍቶ የነበረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል። በሱዳን አሉኝ ያላቸውን 30 ሺ ታጣቂዎች በመጠቀም በአማራ ክልል ላይ እርምጃ እወስዳለሁ እያለ ነው። ይህ ሀይል በማይካድራ ጭፍጨፋ አድርጎ ወደ ሱዳን የሸሸ የተባለው የትህነግ ሰራዊት ስለመሆኑ ቀደም ሲልም ይታወቃል። ይህም በአለም አቀፍ ተቋማት ይፋ የተደረገ ነው። ይህ ቡድን በሱዳን ይህን ያህል ጦር አለኝ ማለቱ አንድ ነገር ማመኑን ያመለክታል። ጉዳዩን ጉዳይ ብሎ ለሚከታተል ሰብአዊ አካል የኢትዮጵየ መንግስት በማይካድራ ጭፍጨፋ ያደረገው የትህነግ ታጣቂ ቡድን ሱዳን ስደተኛ ሆኖ ይገኛል ሲል ለነበረው ክስ አንድ ማስረጃ ይሆናል።
አሁን የትግራይ ክልል እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለመሆኑ የትህነግን የሀሰት መረጃ ሲያሰራጩ የቆዩት አለም አቀፍ ድርጅቶችና የአሜሪካ መንግስት የሚያወጧቸው መረጃዎችም ያመለክታሉ። ሰብአዊ ድጋፍ የሚያቀርቡ ድርጅቶችም በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ናቸው። አሜሪካ በትግራይ ክልል ካለው የደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ ዜጎቿን ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ ለማዘዋወርና ለማስወጣት እየሰራች መሆኑን ማስታወቋ ይታወሳል። አንድ የእርዳታ ድርጅትም በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ስራዎቹን ማቆሙን አስታውቋል።
ለቡድኑ ድጋፍ ሲያደርግለት የቆየው አለም አቀፉ ማህበረሰብና የምእራባውያን መንግስታት አሁን እንኳ ወደ አቅላቸው ተመልሰው ይህን የቡድኑን የጥፋት ተግባር አጢነው የትግራይ ክልልን ህዝብ ሊታደጉ አለመነሳታቸው አሁንም ያነጋግራል። አሜሪካ ዜጎቼ ያለቻቸውን ለመታደግ እየሰራች ከመሆኑ ጎን ለጎን የትግራይ ህዝብ ከሰቆቃ እንዲወጣ ቡድኑ ላይ ጫና ማሳደር ሲኖርባት አሁንም የኢትዮጵያ መንግስትን ይህን አርግ፤ ያን አታድርግ ማለት ውስጥ ተጠምዳለች።
አብዛኞቹ የቡድኑ ደጋፊ ሆነው የቆዩ አለም አቀፍ ተቋማትና አንዳንድ ምእራባውያን መንግስታት እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ቡድኑን የፈለገውን ሲያደርግ ቆመው እየተመለከቱ ናቸው። እርግጥ ነው እነዚህ አካላት የቡድኑን የውሸት መረጃ ይዘው ብዙ ሲሰሩ የቆዩ እንደመሆናቸው ከዚህ ማጥ ውስጥ ለመውጣት ጊዜ ሊወስድባቸው ይችል ይሆናል፤ አሁን በትግራይ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ለእነሱም ጭምር አሳሳቢ እንደመሆኑ ራሳቸውን ለማዳን ብለው እንኳ እውነታውን ቢያወጡ ለትግራይ ህዝብም ይጠቅሙ ነበር።
እነሱ ግን ይህን ከማድረግ ይልቅ ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን እንዳለው ይህን ግፍ ትተው አሁንም የኢትዮጵያ መንግስትን የሚኮንኑና የሚከሱ ከሆነ ሰብአዊ ተግባር ማከናወን ሳይሆን ሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚሰሩ መሆናቸውን ከትግራይ ስምሪታቸው መረዳት ይቻላል።
ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ተጨባጭ ድጋፍ ነው፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የትግራይ ክልል ህዝብ ችግር እንዲፈታ አለም አቀፍ ተቋማትና ምእራባውያን መንግስታት መስራት ይኖርባቸዋል ። ቡድኑን በሚገባ ማወቅ በሚያስችላቸው ስፍራ ላይ እንደመሆናቸው አሁን በትግራይ እየተፈጸመ ካለው ሰብአዊ ጥሰትና ጭፍጨፋ በቀላሉ መረዳት ይችላሉ።
ትህነግ በትግራይ ህዝብ ላይ የተጫነ እዳ ነው፤ የትግራይን ህዝብ ሊታደግ ቀርቶ ራሱንም የሚያድን አይደለም፤ ይህ ደግሞ ባለፉት ስምንት ወራት በግልጽ ታይቷል። በመሆኑም ለትግራይ ህዝብም ለኢትዮጵያም የሚበጀው የኢትዮጵያ መንግስት የያዘው አቋም ነው። በዚህ በፍጥነት መዳን ይቻላል። ከዚህ ውጪ ያለው የትግራይን ህዝብ ይበልጥ ወደ ማጥ የሚከት መሆኑ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013