ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በጋዜጣችን ለወላጆች መልዕክትን ማስተላለፍ ከጀመሩ ሠነባብተዋል። ወይዘሮ ሣራ የሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ፤ በማህበራዊ መገናኛ ለወላጆች የተለያዩ ሐሳቦችን እያነሱ ያካፍላሉ። እሳቸውን ማግኘት የፈለገ ሰው ቢኖር በዚህ የኢሜል አድራሻ ያግኙኝ ብለዋል። Enatleenat@gmail.com
እኛ ወላጆች ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ በልጆች አስተዳደግ ላይ የያዝናቸው ግንዛቤዎች አሉን። እነዚህ ግንዛቤዎች የልጆቻችንን አስተዳደግ ሁኔታ ይወስናሉ። ሆኖም ግን የእነዚህን ግንዛቤዎች ትክክልነት ወይም ስህተትነት ብዙውን ጊዜ አንመረምርም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ይዘን በእነሱ የተነሳ በልጆቻችን አስተዳደግ ላይ አንዳንድ ችግሮችን እንፈጥራለን።
እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ፣ ወይም ተከስተውም ከሆነ ችግሮቹን ለመቅረፍ፣ ቆም ብለን የያዝናቸውን ግንዛቤዎች መመርመር ያስፈልጋል። እስቲ ከዚህ በታች ሦስት የተለመዱ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን እንመልከት።
አንደኛው የተሳሳተ ግንዛቤ ልጄ እንደምወደው ስለሚያውቅ እወድሀለሁ፣ ወይም እወድሻለሁ ብሎ መንገር አያስፈልግም የሚለው ነው። እኛ ወላጆች ለልጆቻችን ደህንነትና የተሳካ እድገት ብዙ መስዋዕትነት እንከፍላለን፣ ብዙ እንደክማለን። ለልጆቻችን ስንል የማንከፍለው ዋጋ የለም። ይህንንም የምናደርገው ልጆቻችንን ማሳደግ የእኛ ሃላፊነት ከመሆኑ ባሻገር ከሁሉ በላይ ስለምንወዳቸው ነው። ነገር ግን ልጆቻችን ይህንን ለእነርሱ ያለንን ፍቅር በቃላት ሳንገልፅላቸው የሚያውቁት ይመስለናል። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።
ልጆቻችን በተለይ በትንሽነታቸው ዕድሜ ደግመን ደጋግመን እንደምንወዳቸው በየጊዜው በቃላት መንገር አለብን። ልጆቻችን ይህንን ሲሰሙ ነው አባቴ እና እናቴ ይወዱኛል የሚለው ሥሜት በውስጣቸው የሚቀረፀው።
ሁለተኛው የተለመደ የተሳሳተ ግንዛቤ ልጅ ከበላ ከጠጣ፣ ከለበሰ እና ትምህርት ቤት ከተላከ ከዚያ በላይ ምን ይፈልጋል የሚለው ነው። ርግጥ ነው፣ ልጆች ከዚህ በላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ነገሮች የሚያስፈልጋቸው ነው። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የሥነ ልቦና ፍላጎታቸውን አያሟሉም። ለሥነ ልቦናዊ ጤንነት ዋንኛው የመወደድ ሥሜት በውስጣቸው መቀረፁ ነው። ለዚህም ከልጆቻችን ጋር ጊዜ ማጥፋት አለብን። አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ለልጆቻችን ጤናማ ዕድገት ወሣኝ ነው።
ሦስተኛው የተሳሳተ ግንዛቤ ልጅ ሲያለቅስ፣ አይ እሱ ቀብጦ ነው፣ ዝም በሉት፣ ሲበቃው ዝም ይላል በማለት የሚያለቅስን ልጅ ችላ ማለት ነው። ይህም ከላይ በሁለተኛነት ከተጠቀሰው የተሳሳተ ግንዛቤ ጋር የተያያዘ ነው። ልጅ የሚያለቅሰው አንድ ፍላጎቱ ስላልተሟሉለት ነው። በዚህን ጊዜ እንደ ወላጅ በመጀመሪያ ያልተሟላለት ፍላጎት ምን እንደሆነ መረዳት፣ ከዚያም ወይም በተቻለ ማሟላት፣ ካልተቻለም የማይቻልበትን ምክንያት ማስረዳት ያስፈልጋል። ልጆቻችን በምክንያት ስናስረዳቸው ይረዱናል።
ሥሜታቸውም እንዳይጎዳ እንጠብቅላቸዋለን። በልጅ አስተዳደግና አያያዝ ላይ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ጉዳታቸው ጥልቅ ነው። ስለዚህ የያዝናቸውን ግንዛቤዎች እየመረመርን በነቃ እና ጊዜውን በዋጀ መንገድ ልጆቻችንን እናሣድግ።
አስመረት ብስራት