የተወለዱት አዲስ አበባ ሾላ ከተባለ አካባቢ በ1951 ዓ.ም ነው። ልጅነታቸው እንደማንኛውም የሰፈሩ ልጆች ነበር። ለወላጆቻቸው ሲታዘዙ ለጎረቤት ሲላላኩ አድገዋል፡፤ ወቅቱ የፈቀደውን ለብሰው ትምህርት ቤት ውለዋል።
አቶ መኮንን ገብሬ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደበቃ አንደኛ ክፍልን የጀመሩት በወቅቱ ዘርፈሸዋል ከሚባል ትምህርት ቤት ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ቀጣዩን ክፍል ለመጀመር ኡራዔል ወደተባለው መለስተኛ ትምህርት ቤት መግባት ነበረባቸው። አካባቢው ከቤታቸው ይርቃል። የዚያኔ ወጣ ብለው የሚይዙት፣ በቀላሉ የሚሳፈሩት የትራንስፖርት አማራጭ የለም። ቢኖር እንኳን በየቀኑ ለታክሲና ለአውቶቡስ የሚከፈለው ላይሞላ ይችላል።
አሁን መኮንን ሰባተኛ ክፍል ገብተዋል። ሾላ ካሳንቺዝ፣ ኡራዔል ለመድረስ በእግር መጓዝ ግድ ይላቸዋል። እሳቸውን ጨምሮ እኩያ ጓደኞቻቸው ከሰፈር እስከ ትምህርት ቤት በእግራቸው ይጓዛሉ። ማታም በእግራቸው ወደቤት ይገባሉ። ይህ የዘመኑ ተማሪዎች ተለምዷዊ ውሎ ነበር።
ተማሪው መኮንን ሰባተኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት ጨርሰው ወደ ስምንተኛ ተዛወሩ። ለከርሞ የሚጀምሩት የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ለወደፊቱ ህይወታቸው እንደሚበጅ ያውቃሉ። የዚያኔ 12ኛ ክፍል የደረሰ ጥሩ ስራ ከወፍራም ደመወዝ ያገኛል። እሳቸው ለዚህ ከበቁ ራሳቸውን ጨምሮ ቤተሰባቸውን ይረዳሉ። በቂ ገቢ፣ ጥሩ ቤትና ንብረት ለመያዝ ዕድል ያገኛሉ፡፤
መኮንን ክረምቱን ትምህርት በተዘጋ ጊዜ ብዙ አሰቡ፡፤ የልጅነት አዕምሯቸው ከወዲያ ወዲህ እያለ ማተረ፣ አወጣ፣ አወረደ። አሁን በሚገኙበት የትምህርት ደረጃም ቢሆን መተዳዳሪያ እንደማያጡ ያውቃሉ። ያላቸውን የትምህርት ማስረጃ ለሚመለከታቸው ቢያቀርቡ ለወር መተዳደሪያ አያጡም። ትምህርቱን ቀጥለው እስከ 12 ቢገፉ ግን የሚመኙትን የወር ደመወዝ አያጡም።
መኮንን የክረምት ጊዜውን ከብዙ ሀሳቦች ጋር እየገፉት ነው። መስከረም አስኪጠባ ከአንድ ውሳኔ መድረስ አለባቸው። ትምህርት ካሉ ስምንተኛ ክፍልን ይቀጥላሉ። ገንዘብ ካሻቸው ስራ ይፈልጋሉ።
ምርጫ …
አሁን በሀሳብ ሲወጠር የከረመው አዕምሮ ከአንድ ጥግ አርፏል። ወጣቱ መኮንን ከትምህርት ይልቅ ብር አስፈልጎታል። በየቀኑ ከመማር ወር ሙሉ ሰርቶ ደመወዝተኛ መሆንን መርጧል። መኮንን በአዲሱ ሀሳብ አልተቆጩም፣ ከራሳቸው መክረው የደረሱበት ውሳኔ ካሰቡት እንደሚያደርሳቸው አምነዋል።
አዲሱ ዓመት ገብቷል። ተማሪዎች በአዲስ ልብስና ጫማ ወደትምህርት ቤት እየሄዱ ነው። መምህራን ተማሪዎቻቸውን በልዩ ስሜትና ፍላጎት ተቀብለዋል። የመኮንን ባልንጀሮች ደብተራቸውን ይዘው ትምህርት ቤት ሄደዋል። ትምህርት ከተጀመረ ጥቂት ቀናት ተቆጥረዋል።
መኮንን ያላዩ፣ ከትምህርት ገበታው መራቁን ያስተዋሉ አንዳንዶች የት እንደሄደ ጠየቁ። ምክንያቱን ያላወቁ ባልንጀሮች ‹‹እንጃ›› ብለው መለሱ። ቀናት ተቆጠሩ፤ ሣምንታት አለፉ፡፤ የስምንተኛ ክፍል ተማሪው መኮንን ትምህርት ቤት ዝር አላሉም። ጥቂት ቆይቶ መኮንን ትምህርታቸውን አቋርጠው ውትድርና መግባታቸው ተሰማ።
የእሳቸው ባልንጀሮች ከዕውቀት ገበታ ታድመው ከብሄራዊ ፈተና ተቀመጡ። መኮንን ጠመንጃ ታጥቀው፣ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተገኙ። ቆይታቸው በድሬዳዋ ወታደራዊ ተቋም ነበር።
በማሰልጠኛው ማልዶ መነሳት፣ ጋራ ተራራ መሮጥ፣ ከባድ ኪሎ አሸዋና መሳሪያ መሸከምዋነኛ ግዴታ ነው። በዕውቀት ታንጾ፣ በሥርዓት ተቀርጾ ቆራጥ ወታደር ለመሆን ከባድ ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል። መኮንን የልጅነት አቋምና ውስጣዊ ፍላጎታቸው ለገቡበት ዓላማ ስኬት ሆኗቸው ወታደራዊ ስልጠናውን በብቃት አጠናቀውም በክብር ተመረቁ።
አዲስ ህይወት …
ወቅቱ የደርግ መንግሥት አፍላ የሥልጣን ጊዜ ነበር። የዘመኑ ወጣቶች በህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ገጠር ይዘምታሉ። የፖለቲካ ቡድኖች በራሳቸው ዓላማ ይታገላሉ። ፖለቲከኞች በየቦታው ይሞታሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ። ፖሊሱ መኮንን ይህን ጊዜ ጅማ ሆነው ተቀበሉት። የሚያዘውን እያሰሩ፣ የሚከሰሰውን ከፍርድ እያቀረቡ፣ የሚያመልጠውን እያሳዳዱ ሙያቸውን ተወጡ። ጥቂት ቆይተው የያዙት ሙያ አሥመራ አደረሳቸው። በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ሲሰሩ ቆዩ። ገጠር ከከተማ እየሮጡ ሙያውን ተገበሩ።
ከቀናት በአንዱ ቀን አቶ መኮንን ከባድ ፈተና ገጠማቸው። ከእጃቸው የነበረ እስረኛ ድንገት መጥፋቱን አወቁ። ይኼኔ አለቆቻቸው ተጠያቂ አደረጓቸው፡፤ እሥረኛውን ፈልገው እስኪይዙ በጥፋተኝነት ተፈረጁ፡፤ ይህ አጋጣሚ ከታላቅ ስህተት ቢቆጠር በእስር እንዲቆዩ ተፈረደባቸው።
ይህን የፈተና ጊዜ አልፈው በሙያው ጥቂት ዘለቁ። አራተኛውን ዓመት ሲደፍኑ ግን ውስጣቸው ሌላ ስራን ተመኘ። ፖሊስነትን ለቀው መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወሰኑ። ወቅቱ በብሄራዊ ውትድርና ዘመቻ ወጣቶች የሚፈለጉበት ዘመን ነበር። መኮንን ከፖሊስ ሲወጡ መከላከያን ለመቀላቀል አልተቸገሩም። ያለፉበት ልምድ አግዟቸው የሰራዊቱ አባል መሆን አመቻቸው።
ተመልሰው ከማስልጠኛ የገቡት ወጣት ብቁ ወታደር ለመሆን አልተቸገሩም። ግዴታቸውን በወጉ አጠናቀው ወደስራ ተሰማሩ። አሁን የቀድሞው ፖሊስ የመከላከያ ወታደር ሆነዋል። አገራቸው በምትሻቸው ጊዜ ጥሪዋን ለመመለስ ዝግጁ ናቸው። ከማሰልጠኛ በኋላ ከአንዱ የጦር ክፍለ ጦር ተመደቡ። ጥቂት ቆይተው የመጀመሪያው ግዳጃቸው በትግራይ ተራሮች ሥር ሆነ። ወታደራዊ ግዳጃቸው ቀጠለ። እየደሙ፣ እየቆሰሉ ወታደርነታቸውን አስመሰከሩ። ይህ ጊዜ እንዳበቃ ክፍለ ጦሩን ተከትለው ወደ ባሌ ወታደራዊ ተቋም አመሩ።
1983 ዓ.ም
ይህ ጊዜ የደርግ መንግሥት በእጅጉ የተፈተነበት ወቅት ነበር፡፤ ወታደሩን ጨምሮ በርካቶች በታላቅ ፈተና ውስጥ ናቸው። በየቦታው ወታደሩ የሞት ትግል ተጋድሎዎች፣ ይፈጽማል። ገሚሱ አገር ጥሎ ይሰደዳል። በየስፍራው የሚሰሙ ወሬዎች መልካም አልነበሩም።
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፉት ወታደሩ መኮንን አሁንም ከባሌ ተራሮች ስር ናቸው፡፤ የሚሰሙት አጉል ወሬ እውን እስኪሆን ተስፋ አልቆረጡም። አንድ ቀን በወርሀ ግንቦት አጋማሽ እሳቸውን ጨምሮ የበርካቶች ታሪክ የመቀየሩን ክፉ ዜና ሰሙት። አሁን የሞቱለት፣ የተዋደቁለት ሰራዊት ከእሳቸው ጋር አይደለም። አገሪቱ በሌሎች ሀይሎች ቁጥጥር ስር ሆናለች።
የወታደሩ መኮንን ዕጣ ፈንታ ከሌሎች የሰራዊቱ አባላት የተለየ አልሆነም። የቀድሞው መንግሥት መፍረስ፣ የሰራዊቱ መበተን እንደተሰማ ብዙዎች ተስፋ ቆረጡ። መኮንን አሁን ቆራጥ፣ አገር አስከባሪ፣ ድንበር ጠባቂ ወታደር አይደሉም።
በተስፋ መቁረጥ ውስጥ…
የቀድሞው ጦር መበተን እንደታወቀ መኮንን የነበሩበትን ካምፕ ለቀው ወደከተማ ዘለቁ። ወላጆቻቸው ካሉበት አዲስ አበባ መመለስ አልቻሉም፡፤ ልሂድ ቢሉም መንገዱ አልጋ በአልጋ አልሆነም። ምርጫቸው በሚያውቁት የባሌ ህዝብ መሀል ተመሳስሎ መኖር ብቻ ነው።
ከደርግ መፍረስ በኋላ ከውትድርና የተሰናበቱት መኮንን ራሳቸውን ለማሳደር ያገኙትን ሁሉ ሰሩ። ድንጋይ ተሸከሙ፣ የታዘዙትን ፈፀሙ፣ በቀን ስራ ደከሙ። ጥቂት መቋቋም ሲጀምሩ አንዳንድ ሰዎች የሚሰሩ፣ የሚጠገኑ ቴፕ ሬዲዮና ሰዓቶች ሰጧቸው። እሱን ፈተው እየገጠሙ ጥሩ ባለሙያ ሆኑ።
የሚጠግኑት ዕቃ ውሎ አድሮ የእንጀራ ማግኛ ሆናቸው። ሙያቸውን አይተው እጃቸውን የሚሹ በረከቱ። ይኼኔ የጀመሩት ሙያ ከቀን ስራ አውጥቶ ከተሻለ አቆማቸው። አጋጣሚው ከበርካቶች እያግባባ ገቢያቸውን አሳደገ።
መኮንን ባሌ ጎባንና ነዋሪዎቿን በወጉ ሲያውቁ ዓይናቸው በርካቶችን አማተረ። እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አንድ ቀን ከግራ ጎናቸው አጣምሮ የትዳር አጋር ሰጣቸው። የትናንቱ ወታደርና የቀን ሰራተኛ በድንገት ባለትዳር ሆኑ። ቤቴን፣ ጎጆዬን ማለት ያዙ። ህይወት ተቀየረ። መኮንን ከሰው ቤት ምግብ ተላቀው የቤታቸውን ትኩስ ሽሮ በወፍራም እንጀራ ጎረሱ።
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ባለቤታቸው የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ በስጦታ ‹‹እነሆ›› አለቻቸው፡፤ ሁለት የነበሩት ሦስት ሆነው ጎጇቸውን በልጅ ፍቅር አሞቁት። ጎልማሳው መኮንን ፊታቸው በደስታ ፈካ። ትዳራቸውን አክብረው ቤታቸውን ለመሙላት በትጋት ታተሩ።
ይህ ከሆነ ጊዜት በኋላ የጥንዶቹ ጎጆ በሌላ ህጻን ደመቀ። ሁለተኛዋ ሴት ልጅ ስትመጣ ደስታው አልጎደለም። መኮንን ከቤተሰቡ መበርከት ጋር የቤቱ አቅም እንደሚፈተን አላጡትም። ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሯቸው ሁሉን ለማሳደር እንደማይበቃ አሳምረው ያውቁታል።
አሁን አቶ መኮንን አባወራና የልጆች አባት ሆነዋል። ውሏቸውን ከሚያሰልፉበት ሙያ ጥቂት የዕለት ገቢ አላቸው። የቤተሰቡ ቁጥር ሲጨምር የመኖር አቅም እንዳይፈተን እየሰጉ ነው። በአቅማቸው የሚውሉበት ሙያ የሚያስገኘው ገቢ እምብዛም ነው። ገንዘቡ ሁለት ልጆች የሚያሳድግ፣ እማወራዋን የሚያኮራ፣ አባወራውን የሚያስመካ አይደለም።
እሳቸው ከውትድርና የዘለለ ልምድ የላቸውም። ያሉበት ጊዜና ዕድሜም ለአማራጮች አይጋብዝም። መኮንን ራሳቸውን የሚያስችል ቤተሰቡን የሚደጉም ገንዘብ ማግኘት እንዳለባቸው እያሰቡ ነው። ጊዜ ሲገፋ ኑሮ ሲወደድ ከሌማቱ እንጀራ እንዳይጠፋ አስግቷቸዋል።
ጥሩ ስራ የማግኘቱ ጉዳይ ቢያሳስባቸው ጊዜ ወስደው አሰቡ። ልጆች በወጉ በልተው ማደር አለባቸው። ሚስትም በእሳቸው ማጣት ሊጨነቁ፣ ሊፈተኑ አይገባም። መኮንን እንደለመዱት ከራስ መክረው ከውሳኔ ደረሱ። ቤተሳባቸውን ባሌ ጎባ ትተው አዲስ አበባ ሊገቡ ቆረጡ።
አዲስ አበባ 2005 ዓ.ም
መኮንን ከዓመታት በኋላ ከአዲስ አበባ ተገናኙ። የዚያኔ ትተዋት ሲወጡ እንዳሁኑ አልነበረችም። አሁን ከተማው ተለውጦ፣ ህዝቡ ጨምሯል። ግርግሩ ትርምሱ አይሏል። ከተማዋ ተውባለች፡፤ እሳቸው አርጅተዋል። ጊዜውን መለስ ብለው ቃኙት። ዛሬ ዕድሜያቸው ከ62 እያለፈ ነው። ዕጣ ፈንታቸውን አሰቡት፣ ለአፍታ ግራ ገባቸው። እንዳሰቡት አልሆነም። ጥቂት ቀናት ቆይቶ ከአንድ ድርጅት የጥበቃ ስራ አገኙ።
መኮንን ተደሰቱ። የቀጠራቸው ድርጅት ወታደር እንደነበሩ ሲረዳ መርጦ ተቀበላቸው። ከስራው መዋል ማደር ጀመሩና የወር ደመወዝ ማግኘት ያዙ። አቶ መኮንን ዓመታት ሲጨምሩ ልምድ አዳበሩ። በኤጀንሲዎች ቅጥር በየድርጅቱ መስራት ቀጠሉ። አሁን የቀጠራቸው ኤጀንሲ ከአንድ የግል ባንክ መድቧቸዋል። ስፍራው ከሌሎች በተለየ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ያውቃሉ። በቦታው ሲገኙ ገቢ ወጪውን በአትኩሮት ይቃኛሉ። ለሊት ዕንቅልፍ ይሉትን አያውቁም። ተረኛ በሆኑ ጊዜ ከሌሎች
ጥበቃዎች ጋር መዋል ማደር ግድ ይላቸዋል። መኮንን ጠመንጃ ይዘው፣ ከእነሱ ተቀናጅተው ግዳጃቸውን ይወጣሉ።
መጋቢት 29 ቀን 2011…
ዕለተ ዕሁድ ነው። መኮንን ከባንኩ ደርሰው ከተረኞቹ ጥበቃዎች ስራውን ተቀብለዋል። አብሯቸው የተመደበው ወጣት ከእሳቸው ጋር ውሎ አዳሪ ነው። ማለዳውን በሻይና ፓስቲ የተጀመረው ቀን ረፋዱን ‹‹በጠበል ቅመሱ›› ጥሪ መቀጠሉ ሁለቱንም አሰደስቷል። ጥሪው የመጣው የባንኩን ህንጻ ካከራዩት ወይዘሮ ነው። ጥበቃዎቹ ይህን ሰምተው የሰዓቱን መድረስ ጠበቁ።
አመሻሽ ላይ ሁለቱም ወደጥሪው አመሩ። ከቀረበው ብፌ ከተቀዳው ጠላ ደጋገሙ። ጥበቃዎቹ ወደ ስራ ሲመለሱ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሆኗል። መብራት ጠፍቷል። ዝናብ መጣል ጀምሯል።
መኮንን እንደሁሌው መሳሪያቸውን አቀባብለው ይዘዋል። እንዲህ ሲጨልምና መብራት ሲጠፋ ንቁ መሆን ልምዳቸው ነው። መሳሪያውን ጥበቃዎች ደንበኞች ከሚስተናገዱበት ባንኮኒ ሥር ያኖሩታል። ወጣቱ ጥበቃ አቶ መኮንን መሳሪያውን አንግተው ፊት ለፊት ሲመጡ እያያቸው ነው። እሱ ለመኝታ የሚሆን ፍራሽ ማመቻቸት ጀምሯል።
አሁን አቶ መኮንን ከወጣቱ ጥበቃ ዘንድ ደርሰዋል። በጎኑ አልፈው ወደበሩ ማምራት እንደያዙ ጣቶቻቸው ሲነዝሩ ተሰማቸው። ጥበቃው ክፉኛ ደነገጡ። ድንገት ከእጃቸው ያመለጠው ክላሽንኮፍ ጠመንጃ በፍጥነት ከወለል ከመውደቁ ሀይለኛ የተኩስ ድምጽ አስተጋባ። መኮንን የሆነውን ባለማመን ፊታቸውን ወደወጣቱ አዞሩ። ተረኛው ጥበቃ በጀርባው ወድቆ ጨኸት ያሰማል። ከግራ እግሩ ያለማቋረጥ የሚፈሰው ትኩስ ደም ፍራሹን አርሶ መሬቱን አልብሷል።
ጥበቃው መኮንን በሥራ አጋራቸው ላይ የሆነውን ባዩ ጊዜ ራሳቸውን ይዘው ጮሁ። መላ ሰውነታቸው እየተንቀጠቀጠ ለፖሊስ ስልክ ሊደውሉ ሞከሩ። አልቻሉም በስቃይ ውስጥ ያለው ወጣት ጩኸትና የሚፈሰው ትኩስ ደም ሠላም ነሳቸው።
ጥቂት ቆይቶ ከውጭ በኩል በር ተንኳኳ። ፖሊሶች ናቸው። በሩን እንዲከፍቱ ጠየቋችው። መኮንን ሪፖርት ሳላደርግ መክፈት አልችልም ሲሉ ‹‹እምቢኝ›› አሉ። ውዝግቡ በውስጥና በውጭ በር ቀጠለ። ለውጥ አልመጣም። ወጣቱ ጥበቃ ደሙ ይፈሳል፤ ደጋግሞ ያቃስታል። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ መኮንን በሩን ከፈቱ። ፖሊሶች እሳቸውን ይዘው ደም ወደተነከረው ጥበቃ አመሩ። ሰውነቱ ቀዝቅዟል። ትንፋሹ ቆሟል።
የፖሊስ ምርመራ …
ረዳት ኢንስፔክተር አዳሙ ወዳጆ የተፈፀመውን ወንጀል መርምሮ የተጠርጣሪን ቃል ተቀብሏል። አቶ መኮንን ድርጊቱን ስለመፈፀማቸው አምነዋል። በታላቅ ፀፀትና ለቅሶ መጠንቀቅ እንደነበረባቸው ተናግረዋል። መርማሪው ቃላቸውን በፖሊስ የወንጀል መዝገብ 1247/1/ ላይ በአግባቡ መዝግቧል።
ውሣኔ…
የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻ ውሣኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው በመረጋገጡም ጥፋተኝ መሆናቸውን አረጋግጧል። በዕለቱ ባሳለፈው ውሣኔም ግለሰቡ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዘጠኝ ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጡ ሲል በይኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013