መንግስት ለመንገድ መሰረተ ልማት አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የመንገድ ግንባታዎችን አካሂዷል፤ እያካሄደም ይገኛል። በዚህ ግንባታም ክልልን ከክልል፣ ዞንን ከዞን ፣ወረዳን ከወረዳ፣ ከተማን ከከተማ፣ ቀበሌን ከቀበሌ ማስተሳሰር ተችሏል፤ ለማስተሳሰርም እየተሰራ ነው።
በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታው በከተሞች ሰፋፊና ዘመናዊ መንገዶች መገንባት ተችሏል። በእዚህ በኩል አዲስ አበባን ለአብነት መጠቀስ ይቻላል። በከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢዎች ሰፋፊ መንገዶች ተገንብተዋል፤ የቆየ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለባቸው መንደሮችም ቤቶችን በማፍረስ ጭምር መንገዶች እንዲሰፉና እንዲዘምኑ ማድረግ ተችሏል ። የትራፊክ ፍሰትን ማሳለጥ የሚያስችሉ ማሳለጫዎች ግንባታዎችም ተካሂደዋል ።
ይህ አገሪቱ በመሰረተ ልማት ላይ ያደረገችው ጥረት እድገቷን በተለያዩ መስፈርቶች በሚመዝኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር አድናቆት ሲቸረው ይሰማል ። እነዚህ ተቋማት አገሪቱን የሚያስተሳስሩ የአውራ ጎዳና ግንባታዎች የተሻለ አፈፃፀም እንዳላቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲጠቁሙ ሰምተናል። ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የመንገድ ሥራ አፈፃፀም ባለፉት 20ና 30 ዓመታት አዎንታዊ እመርታ ማሳየታቸውንም እንዲሁ ሲገልፁ ተደምጠዋል።
የዚያኑ ያህልም በዚሁ ዘርፍ ላይ አያሌ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ። የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ በፍትሐዊነትና ተደራሽነት እንዲሁም በጥራት፣ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ዘርፉ እጅግ ብዙ ትችቶች ይቀርብበታል ። አገሪቱ በግንባታ ፕሮጀክት መጓተት ስሟ የጎደፈ ለመሆን ተዳርጋለች። ለእዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር መሆኑ ታምኖበታል ። ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና የአቅም ውስንነት ፣ የቴክኖሎጂ ውስንነት እና የመሳሰሉት የግንባታው ዘርፍ ተግዳሮቶች በሚል ይጠቀሳሉ።
ዛሬ በፕሮጀክት መጓተት ወደ ተፈተነ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት ይዣችሁ እሄዳለሁ ። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መውጫ በር ላይ ይገኛል። ከአዲስ አበባ ግን አንወጣም። ይህ በር ከከተማችን መግቢያ አምስት በሮች አንዱ ነው። የላም በረት፣ ኮተቤ ካራ መንገድ ።
ኮተቤ ካራ የሚባለው አካባቢ በአዲስ አበባ ውስጥ አንጋፋና እድሜ ጠገብ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ነው። አካባቢው የበርካታ የግልና የመንግስት ተቋማት መገኛም ነው፤ የቀድሞው “መምህራን ኮሌጅ” የአሁኑ የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ ፣ አንጋፋው ደጅ አዝማች ወንድይራድ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፣ መብራት ኃይልን ጨምሮ ማህበራዊ ትስስራቸው ጥብቅ የሆነ በርካታ ነዋሪዎች እንዲሁም የንግድ ተቋማትም የሚገኙበት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በሥጋ አቅርቦቱ በስፋት የሚታወቀው “ካራ” የተሰኘው የቄራ አገልግሎት እና የላም በረት የአውቶብስ መናኸሪያ በዚሁ አካባቢ ይገኛሉ።
ይህ ቁልፍ ስፍራ ግን ከመንገድ መሰረተ ልማት አንፃር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ። መሰረተ ልማቱ አንጋፋ አካባቢነቱን ያላማከለ ነው። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች መንገዶች የትራፊክ እንቅስቃሴን በሚገባ ማሳለጥ በሚያስችላቸውና በዘመናዊ መልኩ የተገነቡ ቢሆንም፣ ይህ አካባቢ ግን የትራፊክ እንቅስቃሴውን ሊመጥን የሚችል መንገድ ከተጠማ ዓመታትን አሳልፏል።
መንገዱ መጠነኛ ማሻሻያና አስፋልት እየተደረገበት ቆይቶ ይሆናል እንጂ ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅትየተቀየሰ መንገድ ነው ማለት ይቻላል፤ መሠረታዊ ለውጥ ያልተደረገበት የሚባል ነው።
እርግጥ ነው ሁለት መንገዶች ተገንብተውለታል። ከ10 ዓመት በፊት የተገነባው በላምበረት፣ ወሰን ካራ የሚደርሰው መንገድ እና በእንግሊዝ ኤምባሲ በአበቤ ሱቅ ይዞ በጀርባ በኩል እስከ ኪዳነምህረት የሚደርሱ ሁለት መንገዶች ተገንብተዋል። እነዚህ መንገዶች ቢገነቡም የበሩን የትራፊክ እንቅስቃሴና የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተራክቦ የሚሸከሙ አይደሉም።
ከብዙ ምጥ በኋላ የዋናው የላም በረት ኮተቤ ካራ መንገድ (የአስመራ መንገድ ተብሎ ይጠራል በተለምዶ) ፋይዳ ታምኖበት ግንባታውን ማካሄድ የግድ ሆኖም ወደ ግንባታው ከተገነባ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁንና ግንባታው ከዛሬ ነገ ይጀመራል ሲባል በግምትና ወሰን ማስከበር ስራ ሳቢያ ዓመታትን ወስዶ ነበር የተጀመረው።
ግንባታው በአገር ውስጥ ተቋራጭ ቢጀመርም፣ አሁንም ድረስ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሊሆን አልቻለም። የግንባታው መጓተት የፈተናቸው ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ለመንግሥትና ለመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም በስፍራው ተመላልሶ ለመቃኘት እንደቻለው በግንባታው በኩል አሁን አሁን መሻሻሎች መታየት ቢጀምሩም እየተገባደደ ነው ማለት የሚያስችል ሁኔታ ቢኖርም፣ ገና ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ታዝቧል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የካራ ኮተቤ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታው የተጀመረው በ2009 ዓ.ም በተክለ ብርሃን አምባየ ኮንስትራክሽን ኩባንያ አማካኝነት ነበር፤ ተቋራጩ ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ውሉን በመሰረዝ ግንባታውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በራሱ የግንባታ ኃይል ለማከናወን ውልገብቶ ስራውን የጀመረው ከአራት ወራት በፊት ነው።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ፕሮጀክቱን ሲረከብ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጥቶ በነበረው መረጃ ግንባታውን የተከበው 52 በመቶ እያለ ነበር ። የክረምት ወራት ከመግባቱ በፊት ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ይፋ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ግንባታው ሳይጠናቀቅ የክረምት ወር ገብቷል።
ለዘመናት በመንገድ እጦት እየተቸገረ የሚገኘው የላም በረት ፣ኮተቤ ካራ አካባቢ ሕዝብ ግንባታው ሊጠናቀቅለት ቢቃረብም፣ የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ግን በመንገዱ ላይ የተጋረጠ ሌላ አደጋ አስተውሏል። መንገዱ የጥራቱ ጉዳይ አስተማማኝ አይደለም የሚል ምልከታና ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በከተማ ውስጥ ከሚያሰራቸው ሰፋፊ መንገዶች የተለየ ቅርፅና ለአደጋ የሚያጋልጥ ደሴት በአስፋልት መንገዱ መካከል ላይ በአርማታ መልክ ተጋግሮ በየቦታው ተቀምጧል። መንገዱን ለማስፋት የቦታ ችግር ባይታይም የዲዛይን ችግር ይስተዋልበታል። መንገዶቹ አላስፈላጊ በሆኑ እጅግ አደገኛ የአርማታ ደሴቶች ተከፋፍሎ ይታያል።
ይህም አንድ መኪና እንደልቡ እንዳይሄድ አለፍ ሲልም ስለአካባቢው ግንዛቤ የሌለው አሽከርካሪ በጭለማ በቀላሉ ለአደጋ እንዲጋለጥ የማድረገ እድሉ የሰፋ መሆኑንም አስተውለናል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል የዚህን አካባቢ የቆየ የመንገድ እጦትና አሁን የተፈጠረውን የመንገድ ጥራት ጉድለት ልብ ሊለውና ግምገማ ሊያደርግበት ይገባል የሚል አስተያየት አስቀምጠን ሃሳባችንን በዚሁ ለመቋጨት ወድደናል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013