አያ ጅቦ አንድ ቀን ማልዶ ተነሳ። መንገድም ጀመረ።የሚሄደው ሩቅ አገር ካሉ ዘመዶቹ ዘንድ ነበር።ዘመዶቹ ደግሞ እንደሱ ጅቦች ያልሆኑ የሰው ጎረቤቶች ነበሯቸው አሉ።የዛሬን አያድርገውና ጅቦችና ሰዎች ቡና ይጣጡ፣እህል ውሀ ይገባበዙ ነበር ይባላል ። ‹‹ያው እንግዲህ ይባላል›› ነው እኔ አላየሁም።፡ ታዲያላችሁ ! አያ ጅቦ ቀኑን ሲጓዝ ውሎ ካሰበበት አገር ደረሰ። በስፍራው ሲገኝ ምድረ የጅብ ዘር ሰብሰብ ብሎ በደስታ ተቀበለው።
ምሽቱን አጎት ጅብን ሲያጫውቱና እግር ሲያሹ የቆዩ ግልገል ጅቦች በያሉበት ዕንቅልፍ ፈነገላቸው።ይሄኔ አባት ጅቦች ከእማወራዎቻቸው መከሩ። ‹‹እንግዳው ጅብ በመንገድ ደክሟል፣ ከእኛ ጋር መጣበብና መጨነቅ የለበትም›› አሉ ። ስለዚህ ምቾት ላለው መኝታ ሰዎች የሆኑ ጎረቤቶቻቸውን ማስቸገር ግድ አላቸው።
የሰው ልጆቹ ማለትም የዛኔዎቹ የጅብ ጎረቤቶች ይህን ሲያውቁ የሰው አገር ጅብ የሆነውን እንግዳ በደስታ ተቀበሉ ። እግሩን አጥበው፣ መኝታ ደልድለው፣ ሳር ቅጠል ጎዝጉዘው ጎንህን አሳርፍ አሉት። እንግዳው ጅብ ሸንከል፣ ሸንከል እያለ ከሰፊው እልፍኝ ገባ። ምቾት ካለው መኝታም አረፈ።
እምብዛም አልቆየም ። በጨለማው የሚያበሩ አይኖቹ ተንከራተቱ፣ ከግድግዳው የተሰቀሉ አጎዛና ቁርበቶች፣ ከመሬት ከመደቡ ተደራርበው የተነጠፉ ድብዳቦች በእጅጉ ማረኩት። ይህኔ በየአፍታው በአፍንጫው ውል የሚል የቆዳና ቁርበት ሽታ ማንነቱን አስታወሰው።
ጅቦ እንደምንም እየተቅለሰለሰ በመስተንግዶው የተደሰተ መሰለ ። ግና አልቻለም። ጥርሱ ይፋጭ፣ ሆዱ ይጮህ ሲጀምር ከቆዳውም፣ ከድብዳቡም፣ ከቁርበቱም ቆረጥ ቆረጥ እያደረገ መቀማመስ፣ መጎራረስ አማረው። አፉ በምራቅ ተሞላ ፣ ክፉኛ ተጎማጀ።
ጥቂት ቆይቶ ከጉዝጓዙ ያረፈው ጎኑ መቁነጥነጥ መገላበጥ ያዘ። ይሄኔ ሰዎቹ ደነገጡ።እንግዳው ጅብ ቁንጫ በልቶት እንዳይሆን ሲሉ ተጨነቁ።መብራት ይዘውም ችግሩን ሊፈቱ ቀረቡ።አያ ጅቦ ግን ፈጥኖ ከሳር ጉዝጓዝ መኝታው ተነሳና ከመሀል ወለሉ ቆመ።ዓይኖቹን በቆዳ ከተሸፈነው ግድግዳ ላይ ተክሎም ‹‹ሰዎች ሆይ! መኝታዬ ከቁርበቱ፣ከአጎዛው›› ይሁንልኝ ሲል ተማጸነ።
ነገሩ ሁሉ ‹‹ ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሳ›› መሆኑን የጠረጠሩ የሰው ልጆች ፊታቸው የቆመው ፍጥረት አያጅቦ እንደሆነ ቢገባቸው ቆመጥ ዱላቸውን ይዘው ተነሱ። ትጥቃቸውን አጥብቀውም የጎናቸውን ጠላት ሊያሳድዱና ሊወጉ ተረባረቡ ። አሩጠው አሯሩጠው አላጡትም።
ልቡ እስኪፈርስ መሮጥ የጀመረውን ወደል ጅብ ርቆ ሳይርቅ ደረሱበት። ውለታ ደግነታቸውን ፣እንግዳ ተቀባይነታቸውን ፣ መልካም መስተንግዷቸውን ፣ እያስታወሱ የቤታቸውን ጥሪት፣የላባቸውን ወዝ ሊነጥቅ ማሰፍሰፉን እንዲያስብ አድርገው ልኩን አሳዩት።
ሰዎቹ በዋዛ አልተዉትም። ወትሮም ቢሆን አውሬነቱን ያልረሳው ጅብ ‹‹በማያውቁት አገር ደርሶ ቁርበት አንጥፉልኝ›› ይሉት ንግግርን እንዳይረሳው አድርገው አቀመሱት።‹‹እሰይ! ጎሽ ! ›› እንጂ ምን ይባላል።
መላ አካሉ ቆስሎ ዱር የገባው ጅብ ታዲያ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በጎነት የዋሉለትን የሰው ልጆች በክፉ ማየት ያዘ። ሀብት ንብረቴ የሚላቸውን ጥጆቹን፣በጎቹን ከሜዳው ፣ከእረኞቹ እየነጠቀ መውሰድ ጀመረ ። ከበረታቸው ዘልቆም የአህዮቻቸውን ፣የከብቶቻቸውን ሆድ መዘርገፍ ልምዱ ሆነ ።አያ ጅቦ ጅብ ነውና ምንግዜም ማንነቱን አይረሳም።ሆዳምነቱ፣ውለታ ቢስነቱ ፣ዛሬም ድረስ አብረውት አሉ።
ወዳጆቼ! እነሆ ዛሬ የውለታ ቢሱ አያ ጅቦና የመልካሞቹ ሰዎች ታሪክ ይደገም ይዟል። የክፉ አባታቸውን እኩይ ድርጊት ማድመቅ የጀመሩት ጅቦች ያልደረቀ ቁስላቸውን እያከኩ ፣ እንደእግራቸው በተሰናከለ እሳቤ አገር ያምሱ፣ ያተራምሱ ጀምረዋል።
‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንዲሉ ሆኖ በክረምቱ ጆሯችን ጉድ ያሰማን ይዟል።በአያ ጅቦ የሚመሰለው ውለታ ቢሱ የህወሓት አማጺ እንዳይሆን ቆሳስሎና ተዳክሞ ጫካ ከገባ ወዲህ በሙት አንደበቱ ይቃትት ከጀመረ ሰንብቷል።
እንደጥንቶቹ የሰው ልጆች በእንግዳ አክባሪነቱ፣በሰላም ወዳድነቱ ዓለም የሚያውቀውን ሰራዊት በአንድ ለሊት ቀረጣጥፎ ከበላው ወዲህ አልጠግብ ባይነቱ ብሷል። ትናንት ከህዝብ ጎን ቆሞ ‹‹አለናችሁ›› ሲል የነበረ የሰሜን ዕዝ ሰራዊትም በነጋበት የህወሓት ጅብ ከተበላ አይረሴዎቹ ጊዜያት ተቆጥረዋል።
የዘመናችን አያ ጅቦ ህወሓት ግን ሰራዊቱን ጨምሮ እስካሁን የበላው፣ የሰለቀጠው ሁሉ አላጠገበውም። ያወደመው ንብረት የዘረፈው ሀብት በቃኝ አላሰኘውም። ዛሬም ከገባበት ጉድጓድ፣ ከተደበቀበት ጫካ ሆኖ በጅብኛ ድምጹ ማጉረምረም ቀጥሏል።ለነገሩ የጅብ ድምጽ ከሩቅ አፋፍ ቢሰማ አይደንቅም። አንድም ይበላው እየፈለገ፣ አንድም እየሮጠ መሆኑ ይታወቃል።
እርግጥ ነው ! ትናንት ከዝርፊያው ማዕድ የተቋደሱና ትርፍራፊው የደረሳቸው ጀሌዎች ዛሬ ከአሸባሪው ህወሓት ጎን ተወሽቀዋል። ስለቀድሞ ውለታም ፣በሙታን ልጆቹ ስም እያንጎራጎሩ ደረት ሲያዳቁት ከርመዋል ። ለነገሩ ደም እያስለቀሱ፣ ማልቀሱን፣ እየዘረፉ ቀድመው መጮሁን ተክነውታል። ከሰላ ምላስ የዘለለ የረባ ቁምነገር የሌላቸው እነ ጌታቸው ረዳ በፍርሀት ከመሸጉበት ጉድጓድ ተወሽቀው ብዙ ሲያሰሙን ሰንብተዋል።እጅ እግር በሌለው ወሬያቸውም ራሳቸውን እንደ መንግስት ሾመው የጀግንነት ባህሪን ሲተውኑ ከርመዋል። ድንቄም ተውኔት ! አሉ። ተመልካች ሁሉ እንደ ህንድ ፊልም መጨረሻውን ቀድሞ በሚያውቅበት እይታ ደርሶ ልጀግን፣ልፎክር ማለቱን ባፈሩበት ነበር።
እንሞትልሀለን ያሉትን ህዝብ በግልጽ ሲገድሉት እየታየ ዛሬም ዓይናቸውን በጨው አጥበው ፣የአዞ ዕንባቸውን ቀጥለዋል ። ወትሮም ቢሆን የጅብና የሰው ወዳጅነት ዘልቆ አያውቅም።ሁለቱ ወገኖች ስራና ግብራቸው ለየቅል መሆኑን ዓለም ያውቀዋል።
‹‹ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ›› አሉ እማማ ሻሼ። ሻሼ የሰፈራችን አንጋፋ ወይዘሮ ናቸው። እንዲህ አይነቱ ያልተገባ ጉዳይ በገጠማቸው ጊዜ ‹‹ይሉሽን በሰማሽ››ን ይደጋግማሉ።እውነታቸውን እኮ ነው። ሰሞኑን ከሰማነው አሳፋሪ ጉዳይ አኳያ የእሳቸው ተረት ቢደጋገም ምን ይገርማል።ምንም።
እስከዛሬ ጁንታው በጫረው የጦርነት እሳት የጠፋው ህይወትና የወደመው ንብረት የዋዛ አይደለም።በትግራይ ወገብ ዙሪያ እንደ እባብ ተጠምጥሞ በህዝቡ ላይ መርዙን ሲረጭ ደሙን ሲመጥ ቆይቷል፤፤ የጀመረው አመጽና ኩርፊያ እስከጫካ ባስፈረጠጠው ጊዜም ህዝቡ ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ተቀብሏል።
ለዚህ እኩይ ድርጊት የእጁን ዋጋ በእጥፍ የተቀበለው የጁንታው ቡድን ዛሬም ከመቃብር አፋፍ ቆሞ ኢትዮጵያ ትፈርስ፣ ትበተን ዘንድ ጉድጓድ መማሱን ቀጥሏል። እስከዛሬም እንደለመደው ያገኘውን እየጨፈጨፈ ፣ያልተባበሩትን እየዋጠ ቆይቷል። ትንፋሹን ለማቆየት እስትንፋሱን ለመቀጠል ያልገባበት ጉድጓድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
ወዳጆቼ! አንዳንዴ አስተዋይነት ሲኖር፣ መልካምነት ሲያመዝን የክፉዎች ሴራ ይደበዝዛል። ለነገሮች ብልሀትና ስልት ሲታከል ደግሞ አሸናፊነት በቀላሉ ከእጅ ይገባል።እንዲህ በሆነ ጊዜ የተጨነቁ ያርፋሉ፤ያዘኑ ያነቡ በተስፋ ያድራሉ።
ከሰሞኑ መንግስት የወሰነው የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትም ይህንኑ መሰራት ያደረገ ስለመሆኑ የሚያውቅ ያውቀዋል። ህዝብ አይሙት ፣ንብረት አይውደም፤ሴረኞች ከንጹሀን ጉያ ተወሽቀው ሽብር አይደውሩ፤ ሲል ከሚሻለው ውሳኔ ደርሶ ተኩስ አቁሙን ተግብሯል።
አውነታውን በይሁንታ ለመቀበል ያልታደለው የጁንታው ርዝራዥ ግን ይህ አጋጣሚ አፈሩን አራግፎ በአጽሙ እንዲቆም ያንከላውሰው ይዟል።፣ ‹‹ወግ! ነው ሲዳሩ ማልቀስ ›› አሉ ። መቼም ቢሆን በጎነትን የማያውቀው አሸባሪው ህወሓት ዛሬ እንደ አንድ ታላቅ መንግስት ራሱን ኮፍሶ ‹‹እንደራደር›› ይሉት ጨዋታን ጀምሯል ።
አይጥ ሞትን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ፣
ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ።
የሚለው የግጥም ስንኝ ትውስ አለኝ። የእነአጅሬ ጉዳይም ልክ እንደ አይጢቱና ድመቱ ጉዳይ ሆኗል። ድርጊቱም ሲባል ሰምታ በጭስ ታፍና እንደሞተችው ዶሮ ይመሰላል። ወዳጆቼ ! የእሳት ደፋር ምን ያደርጋል ነበር የሚባለው? ወደው እኮ አይስቁም ።
መቼም ! እናንተዬ ሰው ሁሉ በሳቅ ብዛት ቢሞት ኖሮ የወገኛውን ቡድን ተረታ ተረት የሰሙ ሁሉ በያሉበት ሆዳቸውን እንደያዙ ባለቁ ነበር ። ደግነቱ የጁንታው ቀልድም ሆነ ድርጊት አምሮ፣ተውቦ አያውቅም። ትናንት ወዶ እስኪጠላ አይቀጡ ቅጣት ያስቆጠረው የመከላከያ ሰራዊት ውሳኔ በተሰማ ማግስት ጅቦ ከተደበቀበት ጉድጓዱ ብቅ ብሏል። ‹‹አለኝ›› ያለውን ሰባት ግልገል ሀሳቡንም ‹‹ስሙኝ ፣አድም ጡኝ›› ማለት ጀምሯል።
ከጅቡ ግልገል ሀሳቦች ብዙዎችን ያስፈገገው ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኤርትራውን ፕሬዚዳንት በስም ጠርቶ በአለም አቀፉ ፍርድቤት ይቅረቡልኝ የማለቱ ድፍረት ነው።ጁንታው ሞፈር የሚያህል ጉድ በአፉ ሰንቅሮ ጥቂት ጉድፎችን ከሌሎች ዓይን ካላወጣሁ ማለቱ በርካቶችን ከማሳቅ አልፎ አሳፍሯል።
የአያ ጅቦ ጁንታ ልብ ዛሬም ተራራ የማሀሉ ምኞት አሁንም ያነጋግር ይዟል። ባልተሰጠው መጠን ተንጠራርቶ ለደረሰው ችግር ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ይዳኘን ማለቱ ከትዝብት ጥሎታል።ትናንት ባንኩን ሲዘርፍ ፣መብራቱን ሲያጠፋ፣ ውሀውን ሲቆርጥ እንዳልነበረ ዛሬ ቅኝቱን ቀይሮ ዘፈኑን ያሳምር፣ከበሮውን ይደልቅ ጀምሯል። እነዚህ መሰረተ ልማቶች የሚመለሱ ከሆነም ለድርድሩ እቀመጣለሁ ሲል ተመኝቷል።
አያ ጅቦ በዝርዝር ካሳለፋቸው ግልገል ሀሳቦች ሌላውና አስገራሚው ጉዳይ የ2013 ዓ.ም በጀት ይለቀቅልኝ የማለቱ እውነት ሆኗል ።፡መቼም እናንተዬ ኢትዮጵያን ታህል አገር ለሚጎመጅ ሀይል የቆመበት ዘመንና የሚመጣው ጊዜ ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም።
ጁንታው ግን ያለፈውን እና የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ የቸገረው ይመስላል።አሁን ሌላ የበጀት ዘመን ነው። ጁንታው የሚጠይቀው ደግሞ እንደሱ ታሪክ ያለቀውን የ2013 አመት በጀትን ሆኗል። ቡድኑ ምን ቢመኝና ቢያስብ እሱን እንደመንግስት ቆጥሮ ይሁንታን የሚሰጠው፣አንዳች ቁራሽ የሚያቀምሰው አይኖርም። እኛ ግን ለማስተዛዘኛ ይሆን ዘንድ የአመቱን መጠናቀቅና የአዲስ ዘመኑን መጀመር ልንነግረው እንወዳለን።
ያው እንደቅድሙ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም››ይሉትን ብሂል ልደግመው ነው። ይህን የምለው ያለምክንያት አይምሰላችሁ።የአያ ጅቦ ሌላ ግልገል ሀሳብ ቢያስገርም ቢያስደንቀኝ ነው። ጁንታው ትናንት አገር ቆርጦ ድንበር አቋርጦ የነጠቀውን መሬት ዛሬ ይገባናል ያሉ ወገኖች ገርፈው እንዳስመለሱት አሳምሮ ያውቀዋል።
አሁን ግን በሌላ ደም መፋሰስ መሬቱን ከእጁ ማስገባት፣ የቀን ቅዠት እየሆነበት ነው።እናም ቅድመ ሁኔታ በሚለው ጉዳይ ይህን ሀሳብ ሌላ ግልገል ነጥብ አድርጎ ግዛቴ ይለቀቅልኝ ሲል አካቶታል። አዎ! የሚሰማ ጆሮ ካለ መጮህ፤ የበረታ ጉልበት ካገኘም መታገል ይቻላል።
ጁንታውና መሰሎቹ ለትግራይ ሕዝብ የማይነቀል እሾህ መሆናቸውን ዓለም ሁሉ ያውቀዋል፡፤እስከዛሬ በስሙ ሲነግዱ፣በማንነቱ ማንነታቸውን ሲሸጡ ኖረዋል።ዛሬም ቢሆን የጉያው ፍም ሆነው በየምክንያቱ እያነደዱት ነው፡፤አሁን ግን እነ አያ ጅቦ ለህዝቡ የተጨነቁ ይመስል ዜማቸውን ቀይረዋል። መብት ይከበር፣ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ ማለት ጀምረዋል። እነሱ ሁሌም አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች እንጂ የእውነት ወዳጅ ሆነው አያውቁም።
ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል፡፤የትግራይ ህዝብ እሳትና ውሀውን እንዲለይ፤ወዳጅ ጠላቱን እንዲያውቅ በቂ ዕድል ተሰጥቶታል።ይህ የጥሞና ጊዜ ልቦና ላለው አስተዋይ ዘመንን ያሻግራል። በነአያ ጅቦ መረብ የገባና የተባበረ ደግሞ የእርምጃውን ርቀት ይለካል።
ጁንታው ከጉድጓድ ሳሎኑ እንዳስተላለፈው መልዕክት ምንአልባት ከአውሮፓና አሜሪካ የሚነሱ እህል ጫኝ አውሮፕላኖች ከመቀሌ እምብርት ያርፉ ይሆናል። ምናልባትም ሀይልና ስልጣኑን ሲቆጣጠር ትግራይን ይገነጥል ይሆናል፡፤ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩና በየቀኑ የሚገቡ ምርኮኞችን ባሪያ አድርጎ፣ የገደለውን ህዝብ ይሞትለት ይቀበርለት ይሆናል።ምናልባትም…….
ወዳጆቼ ! እኛ ግን እንዲህ እንላለን። ‹‹ጁንታውና መንትያው አያ ጅቦ የሰውልጆችን ውለታ መልሰው አያውቁም። ጊዜና አጋጣሚው በቀናቸው ጊዜ በእጅ ያለውን ሀብት ነጥቀው የሚበላውን ሰልቅጠው ህይወትን ይነጥቃሉ። ፡እነሆ ዛሬ አያ ጁንታው ለድርድር ያቀረባቸው ቅድመሁኔታ ተብዬዎች ይህን እውነት አሳይተዋል። አያ ጅቦ ሆይ! ከሰማህ እንንገርህ ! ከነ ሰባት ግልገሎችህ ሳታመሀኝ ብላኝ ተብለሀል።ጉድጓዱም ዋሻውም ከፊትህ ነው።ምርጫውን ለአንተ።
ከትዝብት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2013