ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ ከተማ ትምህርቷንም ተከታትላለች:: ዛሬ የወጣትነት ዕድሜ ክልልን ተሻግራ ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት ብትሆንም ለሥራ ያላት ሞራል እና ንቁ ስሜት ቅልጥፍጥፍ ካለው የሰውነት አቋሟ ጋር ተባብሮ ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለች አስመስሏታል:: ከዛሬ አስራ ስድስት ዓመት በፊት ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅላ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርታለች :: ከሥራ ፈጠራ ጋር በተያያዘም ሥሟ በብዙ ይነሳል ::
ተቀጥሮ ከመስራት ባለፈ የራስ ሥራን ፈጥሮ መስራት አዋጭና የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገና በለጋነቷ የተረዳችው ሥራ ፈጣሪዋ በቀዳሚነት ባቋቋመችው የሶል ሬብልስ ካምፓኒ ትልቅ ዝናን አትርፋለች:: በተለይም የውጭ ሀገር ገበያን ሰብራ መግባት በመቻሏ ለብዙዎች አርአያ ሆናለች:: በስፋት ከታወቀችበት የሶል ሬብልስ ምርቶች በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎችም ብቅ ያለችው ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም ጥላሁን የዛሬ የስኬት እንግዳችን ናት:: ቤተልሔም ዛሬ ላይ ለደረሰችበት ስኬት ቤተሰቦቿ ከፍ ያለ እገዛ የነበራቸው መሆኑን በነበረን ቆይታ አጫውታናለች::
በስፋት የምትታወቅበትን ሶል ሬብልስን ለ12 ዓመታት ጠንክራ በመስራት ውጤታማ እንዲሆንና ከሀገር ውስጥ አልፎም በውጭው ዓለም ተደራሽ እንዲሆን አድርጋለች:: የውጭው ዓለም ምን እንደሚፈልግ ጠንቅቃ ያወቀችው ሥራ ፈጣሪ ባለ ብሩህ አእምሮዋ ቤተልሔም በሶል ሬብልስ ጫማ ፋብሪካ ያገኘችውን እውቅና እንዲሁም ልምድ ቀምራ ወደ ቡናው ዘርፍም ጎራ ብላለች :: በቡናው ዘርፍ ጋርደን ኦፍ ኮፊ የሚባል ኮፊ ሀውስ ገንብታ እየሰራች ትገኛለች። በዚህ ያላበቃችው ቤተልሄም የጤፍ ምርትን በመጠቀም የጤፍ ችብሶችን በስፋት ለመስራት መንገዱን ጀምራለች :: የሀገራችንን ምርት በጥሬው ወደውጪ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ በመላክ ገቢውን ከፍ ማድረግ ይቻላል። በሀገር ውስጥም የስራ ዕድል ይፈጥራል ። እናም ሁሉን አቀፍ ጥቅም እና ገቢ ላይ አተኩራ ትሰራለች።
‹‹ማንም ሰው ሥራ የሚጀምረው የሚጎድለውን ነገር ለመሙላት ነው›› የሚል ዕምነት ያላት ወይዘሮ ቤተልሔም ሥራ ከመጀመሯ አስቀድሞ ሥራ ያልነበራትና ሥራ እንዲኖራት በብርቱ የምትሻ ጠንካራ ሴት ነበረች :: ይህን መሻቷን ለመሙላትም ሥራ መሥራት እንዳለባት በማመን ተቀጥራ ሰርታለች :: ተቀጥሮ ከመስራት ባለፈ የራሷ የሆነን ሥራ በመሥራት ለዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደምትችል በማመን ሶል ሬብልስ የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ማቋቋም ችላለች ::
ያደገችበት ማህበረሰብ፣ የተማረችው ትምህርትና ከአካባቢዋ ያገኘችው ዕውቀት በስፋት የምትታወቅበትን ሶል ሬብልስ የጫማ ማምረቻን እንድታቋቁም ያስቻላት እንደሆነ ታነሳለች :: ባቋቋመችው ፋብሪካም የጎደላትን ነገር ማሟላትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈም የዳበረ ልምድ አግኝቼበታለሁ የምትለው ቤተልሔም ሥራው ሌሎችንም ማገዝ እንድትችል ያገዛት መሆኑን ትናገራለች::
ሌሎችን ማገዝ ሲባልም የሥራ ዕድል መፍጠርን የሚያካትት ሲሆን፤ ማንም ሰው ሥራ ሲጀምር እንደ ዘርፉ አይነት ሰፊ እና ጥቂት የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል የምትለው ቤተልሔም፤ እርሷም ሶል ሬብልስ የጫማ ፋብሪካን ስታቋቁም ለአምስት፣ ለአስር፣ ለአስራ አምስት እያለች በቋሚነትና በኮንትራት 300 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች::
መነሻዋን በሶል ሬብልስ ያደረገችው ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም በአሁን ወቅት ዓለም አቀፍ ገበያን ሰብራ መግባት ችላለች :: ሴት ሆኖ ስኬታማነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ገበያን ሰብሮ መግባትን ስታነሳ ደግሞ ሴት መሆን በራሱ የሚፈጥረው ጫና ቢኖርም በመጀመሪያ ጠንካራ፣ አዋጭና ጥሩ ሀሳብ ወይም ፈጠራ ይዞ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ታምናለች :: ሲቀጥልም የምርት ጥራት፣ አይነት፣ ዋጋና ተከታታይነት ሊኖር የግድ መሆኑን ትናገራለች ። ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ መግባት ያስቻላትም ይኸው መሆኑን እና ትልቅ ትምህርት ያገኘችበት፤ ጥሩ ዕውቀት የቀሰመችበት እንደሆነም አንስታለች ::
ማንኛውም ሰው የሚያመርተውን ትክክለኛ ምርት፣ በትክክለኛው ዋጋ፣ ቦታና ጊዜ ማቅረብ ከቻለ ውጤታማ መሆን ይችላል :: በተለይም አጋዥ ሲኖር ደግሞ የበለጠ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የምታምነው ቤተልሔም አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የባለቤቷ እገዛ ትልቅ ቦታ ያለውና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ እንደሆነም ተገልጻለች::
በተለይም ሶል ሬብልስ ጫማ ዓለም አቀፍ ገበያውን መቀላቀል የቻለው ዓለም አቀፍ ገበያው ከሶል ሬብልስ ማግኘት የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ማቅረብ ስለቻለ ነው:: ስለዚህ ማንም ሰው ትክክለኛ ምርት በትክክለኛው ጥራት፣ ዋጋ፣ ጊዜና ቦታ ማቅረብ ከቻለ ዓለም አቀፍ ገበያውን መቀላቀል እንደሚችል ታምናለች::
ቤተልሔም በስፋት ከምትታወቅበት ሶል ሬብልስ ጫማ በተጨማሪ የተቆላና የተፈጨ ቡና ለውጭ ሀገር ገበያ ታቀርባለች :: በዚህም የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ መጫወት የሚችል ነው :: በዚህ ብቻ በቃኝ ያላለችው ሥራ ፈጣሪዋ ፤ የኢትዮጵያውያን ብቸኛ ተወዳጅ ምግብ የሆነውን ጤፍ እሴት በመጨመር የጤፍ ችብስና የተለያዩ ምርቶችን በማዘጋጀት ለዓለም ገበያ እያስተዋወቀች ትገኛለች ::
ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች ሀገር ከመሆኗም በላይ በርካታ ሥራዎችን መስራት የሚችል ወጣት ያለባት ሀገር እንደመሆኗ ሰፊ ዕድሎች አሉ :: በተለይም ወጣት ከመብዛቱ ጋር ተያይዞ ፍላጎትም አብሮ ይጨምራል :: ስለዚህ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ሊፈጠሩ የግድ ነው ። በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ወጣቶች የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሁሉም ዘርፍ ሰፊ ሥራ መስራት ተገቢ ነው ትላለች ::
ሰዎች ዓላማ እና ለሚሰሩት ሥራ ራዕይ ካላቸው ራሳቸውን አካባቢያቸው መቀየር ይችላሉ ። ለአገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ :: ገበያ፣ የሰው ፍላጎትና የአኗኗር ዘዴ በየጊዜው የሚቀያየሩ ነገሮች ናቸው :: ስለዚህ በተቻለው ፍጥነት ሁሉ ከገበያው ከአኗኗር ዘዴና ከአመራረት ስልት ጋር ራሳችንን በፍጥነት ማስተካከል እንዳለብን እና ይህን ማድረግ ሲቻል ደግሞ ኢንዱስትሪውን ማሻሻል ይቻላል ::
ኢትዮጵያ ያላት ጥሩ አጋጣሚ ሌሎች ሀገራት እንዴት ውጤታማ እንደሆኑ ልምዳቸውን በማምጣት መሞከርና መስራት ይቻላል :: ስለዚህ የቆዳ ኢንዱስትሪውን ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለመለወጥ ብዙ መስራት ያስፈልጋል :: በተለይም ከገበያው መቀያየር ጋር እራስን በማዘጋጀት ዘመናዊነትን የተከተለ አሰራር በመዘርጋት ገበያው የሚፈልገው ምን እንደሆነ ለይቶ ማቅረብና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያላትን ዕምነት ታጋራለች::
ምርቶችን ከወቅቱ ጋር ማሻሻል ያስፈልጋል የምትለው ቤተልሔም፤ ገበያ ሁሉንም ነገር መወሰን ይችላል:: ገበያው የሚፈልገውን ነገር ተከታትሎና ጥናት አድርጎ ማቅረብ አስፈላጊ ነው:: በመሆኑም ሶል ሬብልስ ፋብሪካ በአብዛኛው የሚጠቀመው ጨርቆችን ሲሆን ነገር ግን ከቆዳ ንክኪ ውጭ የሆነና ዓለም አቀፍ ገበያው የሚያቀርባቸውን አዳዲስ ምርቶች በመከተል በፍጥነት ምርቱን በማምረት ገበያውን እየተቀላቀለ የሚገኝ ካምፓኒ ነው::
ይሁንና ዓለም አቀፍ የጤና፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በአሁን ወቅት በመላው ዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አጋጥሟል :: ሶል ሬብልስም እንደማንኛውም ዓለም አቀፍ ካምፓኒ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አጋጥሞት ሰነባብቷል :: በዚህ ምክንያትም የሰራተኞች ቁጥር ቀንሶ ቆይቷል :: ነገር ግን በአሁን ወቅት ካምፓኒ በአዲስ መልክ ወደ ገበያው ለመግባትና ለዜጎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በእንቅስቃሴ ላይ ነው ::
ገና በአፍላ ዕድሜዋ ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀለችውና የግል ሥራ ፈጥራ ከሀገር ቤት አልፋ የውጭ አገር ገበያ ውስጥ መግባት የቻለችው ቤተልሔም፤ በስፋት የታወቀችበትን ሶል ሬብልስን ጨምሮ በቡና እንዲሁም ከጤፍ የሚዘጋጁ የተለያዩ ምግቦችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ገበያ እያስተዋወቀች ትገኛለች:: አሁን ደግሞ ምርቶችን አምርቶ ወደ ገበያ ከማቅረብ ወጣ ብላ የባንክ መስራች ሆኗ ወደ ፋይናንሱ ዘርፉ ተቀላቅላለች::
በምስረታ ላይ ያለው ሰላም ባንክን ከመሰረቱት መካከል ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም አንዷ ናት። ባንኩ ዓላማ አድርጎ የተነሳውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ማቃለል ላይ ያተኮረ ነው። በአገሪቱ ሰፊ ክፍተት የሚታይበትን እና ፍላጎትና አቅርቦቱ አልጣጣም ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በሥራ ፈጠራው ዘርፍ ትልቅ አቅምና ልምድ ያላት ቤተልሔም ማንኛውም ቢዝነስ ከችግር የሚነሳ በመሆኑ በአገሪቱ ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት ወደ ዘርፉ ለመግባቷ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች::
በመሆኑም ሰላም ባንክ ምንም እንኳን ያለውን ችግር ሙሉ ለሙሉ መፍታት ባይችልም በተወሰነ እርቀት ተጉዞ በተቻለ አቅም በስፋት የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ አቅዶ እየሰራ ነው :: ሥራው የሚሰራው በሰላም ባንክ መስራቾች ብቻ ሳይሆን መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሚሆኑበት ነው :: ይህን ማድረግ ሲቻልም በብዙ መጠን የቤት ፍላጎቱን ለማቃለል ይቻላል::
ሰላም ባንክ በዋናነት ፋይናንሱን በመሸፈን በተለይም ወጣቶችና ሴቶች መኖሪያ ቤት በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል :: ወደ ዘርፉ መግባት ያስገደዳቸው በአገሪቱ ያለው ከፍተኛ ፍላጎት እንደሆነ ያነሳችው ቤተልሔም፤ በአሁን ወቅት የጀመረችው ሰፊ ሥራ ከመሆኑም በላይ ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነና ይህንንም ከግብ ለማድረስ እየሰራች ነው::
ዓለም አቀፍ ገበያውን ሰብሮ በመግባት ልምድ ያላት ቤተልሔም ሥራ ፈጠራን በተመለከተ አሁን በጀመረችው የባንክ ምስረታ ላይ እያንዳንዱ ሥራ ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ በማንሳት በተለይም ሰፊ ክፍተት ያለበትን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ያስችላል:: ለበርካታ ዓመታት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞቹ ቤት የመግዛት አቅም የሌላቸው መሆኑን ቀጥራ በምታሰራቸው ሰራተኞቿ ታውቀዋለች :: ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ወደ ኢንደስትሪያላይዜሽን ስትገባም የሰራተኛ ፍልሰት አለ :: ስለዚህ ሰራተኞች በቀላሉ ቤት መግዛት የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር ጊዜው አሁን በመሆኑ ባንኩ ይህንኑ ግዙፍ ሀሳብ ዕውን ሊያደርግ ወደ ስራ ገብቷል ::
በምስረታ ላይ ያለው ሰላም ባንክ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች የቤት ባለቤት መሆን እንዲችሉ አቋም ይዞ የተነሳ የመኖሪያ ቤት ባንክ መሆኑን ያጫወተችን ቤተልሔም፤ በሥራ ፈጠራው ዘርፍ ያገኘችውን ዕውቀት እንዲሁም ውጤታማነትን ከተማረችበት የውጭ ገበያ ያገኘችውን ተሞክሮ በመቀመር በቀጣይ ከአጋሮቿ ጋር የጀመረችውን የመኖሪያ ቤት ባንክ ምስረታ ዕውን ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች :: እኛም ባንኩ ይዞ የመጣው ዓላማ ተሳክቶ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ተመኘን ::
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013