የዘንድሮውን ሳይጨምር ኢትዮጵያ አምስት ብሄራዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች::ብዙዎች እንደሚስማሙበትም የተካሄዱት ምርጫዎች በሙሉ የምርጫ መስፈረትን የማያሟሉና የአንድን ቡድን ፍላጎት ብቻ የሚያሳኩ ነበሩ:: ለዚህ ዋነኛው ደግሞ ምርጫውን በዋነኝነት የሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተዋቀረው የገዢው ፓርቲ አባላት በሆኑ ሹማምንቶች መሆኑ የምርጫውን ውጤት ሳይታለም የተፈታ እንዲሆን አደርጎታል::አንዳንድ ጊዜ በሚያስቅና በሚያስገርም መልኩ የምርጫ ውጤቱን ሁሉ የሚገልጸው ምርጫ ቦርድ ሳይሆን ገዢው ፓርቲ ሲሆን ይታይ ነበር::
ዘንድሮ ግን ታሪክ ተቀይሯል:: ምርጫ ቦርድ ለህሊናቸው ባደሩና ምንም አይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት በሌላቸው ሰዎች በመዋቀሩ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስችሎታል::ምርጫ ቦርድ ከቅድመ መርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ባሉት ሂደቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሂደቱን መርቶ ውጤት ላይ ደርሷል:: ከመራጮችና ከተመራጮች ምዝገባ እስከ ድምጽ አሰጣጥ ሂደትና ውጤት አገላለጽ ድረስ ከተፈጠሩ ውስን እንከኖች በስተቀር ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ ኃላፊነቱን ተወጥቷል:: በቀጣይም ለሚካሄዱ ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊነት ከወዲሁ መሰረት መጣል ተችሏል::
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሚመሰገንባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ተከታታይ የሆኑ መረጃዎችን ሳይታክት ለህብረተሰቡ ማድረሱ ነው::በበርካታ ተቋማት መረጃ ለመስጠት በሚሽኮረመሙበት በዚህ ወቅት ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ተቋማዊ ስብዕና በመላበስ መረጃዎችን በተከታታ ወደ ህብረተሰቡ ሲያደርስ ቆይቷል:: አንዳንድ ጊዜ መራጩ ህብረተሰብም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያነሷቸው የሚፈልጓቸው ጥያቄዎች ጭምር በቀጥታ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዋን በቀጥታ እንዲጥቁ በማድረግ ብዥታዎችን ለማጥራት ሞክሯል:: ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለቁጥር የሚያዳግቱና አንዳንድ ጊዜም አታካች ውይይቶችን በማድረግ የምርጫ ሂደቱ የሰመረ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል::
በእነዚህና መሰል የምርጫ ቦርዱ ስኬቶች ምክንያት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ስለምርጫው አጠቃላይ ሂደትና ይዘት አስተያየት ሲሰጡ የተመለከትናቸው አንዳንድ ዜጎች እንዳውም ስድስተኛ ሳይሆን አንደኛው ምርጫ ነው መባል ያለበት ሲሉ ተደምጠዋል። ዕውነት ለመናገር ምርጫው በብዙ ነገሮች ካለፉት ምርጫዎች ለየት ማለቱን ሁሉም የሚመሰክርለት ነው።
በተለይ ከጅማሮው እስከ አሁን ባለው መረጃ የመስጠት ሂደት በእጅጉ ለየት ያለና የታደለ ነው ማለት ይቻላል። በሩቅ ስንመኘው የነበረው አይነት የምርጫ ቦርድ እውን ሆኖ ማየታችን ዕድለኞች ነንም ማለት ይቻላል::ቢያንስ ቢያንስ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችና ሰራተኞች የየትኛውም ፓርቲ አባል እና ደጋፊ አለመሆናቸው የምርጫውን ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ ትልቅ ተስፋ ፈንጠቆ ቆይቷል::
ከዚህ በላይ ደግሞ በምርጫ ቦርድ ዋና ኃላፊነት የተቀመጡት ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለእውነት የኖሩና በጨካኙ የህወሓት አገዛዝ ጭምር ፊት ለፊት ተጋፍጠው ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ የእውነትና የፍትህ ተምሳሌት መሆናቸው በርካታ ሰዎች ከጅምሩ በምርጫ ቦርድ ላይ እምነታቸውን እንዲያሳርፉ አደርጓቸዋል::ሌሎችም የወ/ሪት ብርቱካን ባልደረቦች ቢሆኑ(አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል) 24 ሰዓት በመስራት አሰልቺና አጨቃጫቂ የሚመስለውን የምርጫ ስራ በውጤታማነት ተወጥተውታል:: አስፈሪና አድልኦ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደውንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን አዲስ ስብዕና አላብሰውታል:: ሰዎች በተቋሙ ዙሪያ የነበራቸውን አስፈሪ ድባብ ቀርፈው ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረግ ችለዋል::ባለፉት ሶስት አመታት በእግራቸው ለመቆም ጉዞ ከጀመሩ ተቋማት ውስጥም ምርጫ ቦርድ በዋነኝነት ለመጠቀስም በቅቷል::
በእርግጥ! በዚህ ምርጫ ዕድሜ ዘመን በአዲስ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ለገባው ዕድሜ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በብዙ ነገር ተዋጥቶለታል! ምርጫውን ለየት ካደረጉት አንዱም ይሄው ተቋም መኖሩ ነው። መኖር ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ካለው ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኝነት አብዝቶ እራሱን አርቋል። አንዳንድ ጊዜም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት በተጻራሪ በመቆም የወሰናቸው ውሳኔዎችም ምርጫ ቦርድ የራሱን ስብዕና በመትከል ላይ ያለ ተቋም መሆኑን ያስመሰከረበት ነው::ከፓርቲ ፍላጎት ርቆም በምርጫ ሕግና ሕግ ብቻ በመመራት ሂደቱን መከወኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር በቦርዱ ላይ እምነታቸውን እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል።
ቦርዱ በዚሁ ምርጫን የመምራት ሂደቱ በቅድመ ምርጫ፣ድህረ ምርጫ ፣ የምርጫ ዕለት መረጃ ሲሰጥ የቆየበትና አሁንም ያለበት አግባብ ይበል ያሰኛል። መረጃ አሰጣጡ ደግሞ ተከታታይ መሆኑ ይደነቃል። ጥልቅና ዝርዝርነቱም በእጅጉ የሚበረታታ ነው። በቦርዱ የሚሰጡት መግለጫዎች በበቂ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱና ብዥታን የሚያጠሩ ናቸው:: እከሌ ፓርቲ ያገኘው ድምፅ ምን ያህል ይሆን፣ እከሌስ ስንት ድምፅ አግኝቶ ይሆን፣ ድምፅ በነዚህ በነዚህ ችግሮች ምን ገጥሞት ይሆን የሚሉትን ስጋቶችና ጥርጣሬዎች ሁሉ ታሳቢ ያደረገ እና በቂ መረጃም የሚሰጥ ነው ። በሚሰጣቸውም መረጃዎች ተከታታይና ጥልቀት የጥርጣሬዎቹንና ስጋቶቹንም በር ዘግቷል። በዚህ በኩል የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪዋ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስን ሳያደንቁ ማለፍ አይቻልም።
አንበሶች! እነዚህን ሁለት እንስቶች አለማድነቅ ስለምርጫ ሂደት አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ስለመረጃ መብትም ግንዛቤ ማጣት ነው። እንስቶቹ ከምርጫ በፊት ከዝግጅት እስከ ዋዜማ ያደረጉትን እንተወውና ከምርጫ ዕለት ጀምሮ ያለውን ብናወሳ እየተፈራረቁ ለዜጎች መረጃ ከማድረስ ፈፅሞ አልቦዘኑም። የዕለቱን የምርጫ ሂደት አስመልክተው ሲያደርሱት የነበረው እንቅልፍ አጥተው እስከ ማደር ያደረሳቸው ለመሆኑ አያጠራጥርም። በዚህ ዕለት በየትኛውም የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ዕድሜ ለቴክኖሎጂና በየእጃችን ባለው ስልክ ግር ላለን ሁሉ ነገር ከእንስቶቹ እጅ መፍትሄ አግኝተናል። ለአብነት በረጃጅሞቹ የመራጭ ሰልፎች ምክንያት ድምፅ ላንሰጥ እንችላለን ለሚለው ስጋታችን እዛው ሰልፍ ላይ ሳለን ሰዓቱ መራዘሙን አስመልክተው የሰጡንና መፍትሄ ያገኘንበትን መጥቀስ ይቻላል። ይሄ መረጃ አሰጣጥ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ያለው ነው። በምርጫ ህጉ መሰረት ለሕዝብ መድረስ ያለበትን ሁሉ ማድረስ ችሏል። ከዚህ ቀደም በነበሩት አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ምርጫውን ይመራ በነበረው ምርጫ ቦርድ ተደፍረው የማያውቁትን ሁሉ መረጃዎች ይፋ በማውጣት ሀቁን ለዜጎች ያጋራ ነው ማለት ይቻላል። ብራቮ ምርጫ ቦርድ!
ጌቴሴማኔ-ዘማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013