የየመን ተፋላሚ ኃይሎች ጦራቸውን ሁዴይዳ ከተሰኘችው የወደብ ከተማ ለማስወጣት መስማማታቸው ተዘግቧል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የተፋላሚዎቹን ውሳኔ ‹‹ጠቃሚ ርምጃ›› ብሎ አሞካሽቶታል፡፡ በየመን ምዕራባዊ ዳርቻ የምትገኘውና ለባብ አል-መንደብ የባህር መሽመጥ ወሳኝ መተላለፊያ የሆነችው ይህቺ የወደብ ከተማ፣ እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ በሀውቲ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ወድቃለች፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ፤ እንዲሁም በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚደገፈው የየመን ‹‹መንግሥት››እና የሀውቲ ታጣቂዎች ለሁለት ቀናት ያህል ድርድር ካደረጉ በኋላ ጦራቸውን ከከተማዋ ስለሚያስወጡበት የመጀመሪያ ዙር ተግባር እንደተስማሙ የመንግሥታቱ ድርጅት መግለጫ አመልክቷል፡፡ ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ጦራቸውን ከወደብ ከተማዋ ማስወጣት የሚጀምሩበትና ተግባሩ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ግን በግልፅ አለመታወቁንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የደረሱበት ይህ ስምምነት ባለፈው ታኅሳሥ ወር በስዊድን የተካሄደው የሰላም ድርድር ውጤት ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በስቶክሆልሙ ስምምነት መሰረት ተፋላሚዎቹ ጦራቸውን ከሁዴይዳ ማስወጣት የነበረባቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ከተወሰነበት ቀን ሁለት ሳምንታት በኋላ ቢሆንም ሊሳካ አልቻለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ18 ሚሊዮን የመናውያን ጉሮሮ የሆነችው ሁዴይዳ ከጥይት ድምፅ አረፍ ማለቷ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ምግብና መድኃኒት በአፋጣኝ እንዲያገኙ ያስችላል ብሎ ተስፋ ሰንቋል፡፡
በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰውና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል በድህነት የሚወዳደራት የለም በምትባለው የመን አስከፊ ረሀብ መከሰቱንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የርዳታ ድርጅቶች አስፈላጊውን ትብብር ካላደረጉ ጉዳቱ ባለፉት አስር ዓመታት በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ እንደሚሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላትን የሁዴይዳ ወደብ ለመያዝ የሚደረገው የተፋፋመ ውጊያ 600 ሺህ ከሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ከ120 ሺህ የሚበልጡትን ለስደት እንደዳረገ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ባለፈው መስከረም ይፋ ያደረጉት መረጃ ያሳያል፡፡
እ.አ.አ በ2015 የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ታማኞች ከሐውቲ ታጣቂዎች ጋር አብረው በፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ መንሱር አል-ሃዲ ኃይሎች ላይ የጀመሩት ጥቃት የመንን አሁን ወደምትገኝበት የእርስ በእርስ ጦርነት ከትቷታል፡፡ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ የመንሱር ሃዲን መንግሥት፤ ኢራን ደግሞ የሐውቲ ታጣቂዎችን ደግፈው የእጅ አዙር ጦርነቱን አፋፍመውታል፡፡ ከነዚህ ኃይሎች በተጨማሪም፣ ከፍተኛ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ለመቆጣጠር ለአፍታ ያህል የማይዘናጉት ምዕራባውያንም በበኩላቸው፤ በሳዑዲ ዓረቢያ ለሚመራው ጥምር ጦር የሎጂስቲክና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡
በተለይ አሜሪካ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ ያላት ፍላጎት በየመን በየዕለቱ የሚቀጠፈውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ችላ እንዲባል አድርጎታል፡፡ በየመን ለበርካታ ዓመታት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮች የሀገሪቱን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ አድርገውታል፡፡ በአገሪቱ ሰፊ ይዞታ እንዳለው የሚነገርለት ዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ፣ የየመናውያንን ሰቆቃ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ካደረገው ቆይቷል፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ሌላኛው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድንም በአካባቢው ያለውን ይዞታውን ለማስፋት እንደመሸጋገሪያና መቆያ ከሚጠቀምባቸው የአካባቢው ሀገራት መካከል የመን አንዷ ናት፡፡ የንፁሃንን አንገት መቅላት የየዕለት ተግባሩ የሆነው ይህ አረመኔ ቡድን፣ የአየር ጥቃት ለሚያሰቃያቸው የመናውያን ሌላ የሕልውና አደጋ ሆኖባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም፣ ሀገሪቱ በነዚህ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች፣ በሐውቲዎች እና በመንሱር አል-ሃዲ ታማኞች ተከፋፍላ ትገኛለች፡፡ የመናውያንም ከስቃይ የሚላቀቁበት ቀን እንደ ሰማይ ርቋቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
አንተነህ ቸሬ