የነሐሴ ዝናብ ብሶበታል። ቀኑን ሙሉ ‹‹እኝኝ›› እንዳለ ውሏል። ዕለቱን ለአንዴም ብልጭ ያላለችው ጸሀይ በዳመናው ተሸፍና በወጀቡ ተሸንፋ ተሸፍና ውላለች። ዝናቡ የቀኑ ብቻ የበቃው አይመስልም። ሀይሉን አጠንክሮ ምሽቱንም መቀጠል ፈልጓል።
ብርድና ጭቃውን መቋቋም ያሰቡ አንዳንዶች አለባበሳቸው ተለይቷል። ዣንጥላ የያዙ፣ ካፖርት የደረቡ፣ በወፋፍራም ልብሶች የተጀቦኑ መንገደኞች በርክተዋል። በየጎዳናው የበቆሎ እሸት የሚጠብሱ፣ ድንች የሚቀቅሉ፣ ሻይ፣ቡና የሚያፈሉ ከእጃቸው እሳት ሙቀትን ይጋራሉ።
እንዲህ አይነቱ ዕድል የሌላቸው ውርጭና ዝናቡን ለመሸሽ በየቦታው፣ በየጥጉ መሽገዋል። አሁንም ዝናቡ እንደጨከነ ነው። በውሽንፍር ታጅቦ፣ ቅዝቃዜን ደርቦ ያወርደዋል። ‹‹አበቃ›› ሲሉት እየቀጠለ፣‹‹አባርቷል›› ሲባል እየጨመረ መግቢያ መውጫ አሳጥቷል።
ነሐሴ 25 ቀን 2012
ጉለሌ ልዩ ቦታው ቀለበት ፓርኪንግ ከተባለው ስፍራ ባልንጀሮቹ ተገናኝተዋል፡፤
ብርድና ዝናቡ ያስጨነቃቸው አይመስልም። አንድ ሀሳብ አንስተው በብርቱ ያወጋሉ። ያነሱት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ስሜታቸው ያሳብቃል። ዕቅዶች፣ ዘዴዎች፣ ደጋግመው ይቀርባሉ። በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል። ልምዶች፣ የቀደሙ ታሪኮች ይመዘዛሉ። ‹‹ይሆናሉ›› የተባሉ ነጥቦች ይሁንታ ሲቸሩ በአንድ ድምጽ ይጸድቃሉ ። ቅዝቃዜው አይሏል፣ ዝናቡ ቀጥሏል።
አሁን ባልንጀሮቹ ሀሳባቸው ተቋጭቷል። የሚፈጽሙትን ተነጋግረው ጨርሰዋል። ሰዓትና ቦታውን፣ ዘዴና ብልሀቱን ነድፈዋል። በተባለው ሰዓት በቪትዝ መኪናቸው ወደ ቦታው ተጣደፉ። ከስፍራው ሲደርሱ አሻግረው መቃኘት ያዙ። የፈለጉት ጉዳይ በቦታው እንዳለ ነው።
በአካባቢው የሰዎች መኖር አላስጨነቃቸውም። የሚሹትን ከሩቁ አይተው አረጋግጠዋል። የመኪናቸውን ሞተር አጥፍተው አጠገቡ ሲቆሙ፤ አስፈሪነቱ አላስደነቃቸውም። ግዙፍነቱ አልገረማቸውም። ዙሪያውን ከበው መላ አካሉን ነካኩት፣ ደባበሱት። ሲጠጉት ስሜታቸው ተለየ። ወዲያው የስድስቱም ሀሳብ ተናበበ። የነገውን መልካም ውጤት ሲያስቡ አዲስ ተስፋ፣ ብሩህ መንገድ ታያቸው። እሱን እያለሙ ምራቃቸውን ደጋግመው ዋጡ።
ድንገቴው ባለጉዳይ…
ከፖሊስ ጣቢያው በድንገት የደረሱት ግለሰብ በፊታቸው ድንጋጤ ይነበባል። መረጋጋት አልቻሉም። የሆነውን ለመናገር ትዕግስት አጥተዋል። ሁኔታቸውን ያስተዋለው የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ እንደታገሳቸው ቆየ። ይህ አይነቱ ስሜት በዚህ ቦታ የተለመደ ነው። ተበዳዮች በስፍራው ሲደርሱ ይይዙት ይጨብጡት ያጣሉ። የቻሉ፣ የሆነባቸውን በአግባቡ ለመናገር ይሞክራሉ። ይህን የማይሞክሩት የውስጣቸውን በዕንባና በጩኸት ይገልጻሉ።
ሰውዬው ፖሊሱ ከጠቆማቸው ወንበር አረፍ እንዳሉ እንደምንም ተረጋጉ። ጥቂት ትንፋሽ ስበውም የሆነውን በዝግታ ማስረዳት ጀመሩ። ፖሊሱ ብዕሩን ከማስታወሻው አገናኝቶ ያዳምጣቸው ያዘ። ተበዳዩ ባለጉዳይ መናገር ጀመሩ። አሁንም በድንጋጤ የወዛው ፊታቸው በወጉ አልተረጋጋም።
አቶ መኮንን የቤተሰብ አባወራ ናቸው። የእሳቸውና የመላው ቤተሰቡ መተዳደሪያ ሆኖ ዓመታትን ያዘለቃቸውን ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ከአንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሺህ ብር በላይ አውጥተውበታል። ይህ መኪና ለግንባታ የሚሆን አቅርቦትን ያመላልሳል። መኪናው ሲለው አሸዋ፣ አልያም ብረትና ብሎኬት ለመጫን ‹‹በቃኝ›› አይልም።
ድምጽና ግዝፈቱን እያዩ ከሩቁ የሚሸሹት ብዙ ናቸው። ፍጥነትና ሀይሉን ሲጨምር፣ ደንብ ሲተላለፍ ደግሞ የአደጋው ነገር ‹‹አያድርስ›› ያሰኛል›። ህይወት ቀጥፎ፣ አካል አጉድሎ ንብረት ያወድማል።
ሲኖን መሰል ተሽከርካሪዎች በሚተራመሱበት ስፍራ በርካቶች እንጀራ ያገኛሉ። ከሚጫን ከሚወርደው፣ ከሚገባ፣ ከሚደለለው ሁሉ ተሳታፊዎች ናቸው። የአባወራውን ቀይ ሲኖትራክ እንደ ዓመሉ አባብሎ የሚይዝ ቤተኛ ሾፌር አለ። ሾፌሩ መኪናው ብልሽት ሲገጥመውና ጥገና ሲያሻው የጎደለውን ያሟላል። ውስጡ ባኮረፈ በታመመ ጊዜም ድምጽና ፍጥነቱን አጤኖ መፍትሄ ይፈልጋል።
አንዳንዴ በሲኖዎች መንደር የስራ ውሎ እንደታሰበው አይሆንም። መኪናው የሚጭነው ከሌለ ከሩጫው ሊገታ ይችላል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ሾፌሩ መኪናውን ለጠባቂዎች በዕምነት ትቶ በጊዜው የቆየበትንና የሚገባቸውን ይከፍላል። ግዙፉ መኪና ለቀናት ከቆመ ባትሪው ይደክማል፤ ባትሪው ሲሞትና ሲቀዛቀዝ እንደሻው አይሆንም። በዋዛ መግፋትና ማንቀሳቀስ ፈታኝ የሆነው ግዙፍ መኪና እንዲህ በገጠመው ጊዜ ሙያዊ እገዛን ይሻል።
ሾፌሩ ታደለ መኮንን በእንዲህ አይነቶቹ ግዙፍ መኪኖች ላይ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን የሚዘውረውን የአቶ መኮንን አበበን ሲኖ ከሚፈለገው እያደረሰ ሲመልሰም ከተሰጠው ስራና ሀላፊነት ጋር ነው። ታደለ ሲኖትራኩን አዘወትሮ በሚያቆምበት የቀለበት ሰፈር አካባቢ ብዙዎች ያውቁታል።
የእሱን ሲኖ ጨምሮ ሌሎች መኪኖችን የሚጠብቁት ወጣቶች በማህበር የተደራጁ ናቸው። እነሱ ወጪና ገቢ ደንበኞችን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከደንበኞቻቸው አንዳንዶቹ ውሎ አዳሪዎች ሌሎቹ ደግሞ ቆይተው ከራሚዎች ናቸው። ሁሉም መኪኖች እንደ መጠንና አይነታቸው ዋጋቸው ይለያል።
በቆይታቸው ልክ አስልተው ሂሳብ የሚቀበሉት ሸሪኮች የልፋታቸውን እኩል ይካፈላሉ። ሸሪኮቹ ጓደኛሞች የሚጠብቋቸውን መኪኖችና ሰዎቻቸውን ይለያሉ። የእጅ ዓመል ያለበት ጎማ እንዳይፈታባቸው፣ መስታወት እንዳይሰብርባቸው፣ ፍሬቻ እንዳይፈታባቸው ደጋግመው ይቃኛሉ።
መኪኖቹን በሀላፊነት ከተረከቡ በኋላ እንደ አዲስ እረኛ ማለት ናቸው። ዕንቅልፍ ይሉት የላቸውም። ከሚጠብቋቸው መካከል የአንድ መኪና ዕቃ ቢጎድል ዕዳ ከፋዮች እንደሚሆኑ አያጡትም። ይህን የሚያውቁት ጓደኛሞች ሁሌም ጥበቃቸው በንቃት ነው።
በአገልግሎታቸው የሚረኩ ብዙዎች ታማኝነት፣ ትጋታቸውን አይተው ክፍያን ከጥሩ ጉርሻና ምስጋና ጋር ይቸሯቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የተጠቀሙበትን ለመስጠት ደጅ እያስጠኑ ያሳዝኗቸዋል። ከሸሪኮቹ መካከል ሚስት አግብተው፣ ልጆች ወልደው የሚኖሩ አሉ። ሌሎችም በሚያገኙት ገቢ ቤተሰብ ያሳድራሉ፣ ራሳቸውን ያስተምራሉ።
ሾፌሩ ታደለ ሰሞኑን እንደለመደው ሲኖትራኩን ይዞ ከቀለበት ፓርኪንጉ ደርሷል። መኪናውን ያዩ ወጣቶች ለግዙፉ ሲኖ ቦታ ሊሰጡት እያመቻቹ ነው። ታደለ ከቦታው እንደቆመ ሞተሩን አጥፍቶ ወረደ። የመኪናው በርና መስኮት መዘጋቱን አረጋግጦም ስፍራውን በእግሩ አቋረጠ። የሚያውቁት በአንገታቸው ሰላም አሉት። አጸፋወን እየመለሰ ወደመንገዱ ወጣ።
ታደለን የመሰሉ ሾፌሮች ቦታውን በቋሚነት ሲጠቀሙ የወር ክፍያ አስልተው ይሰጣሉ። ወጣቶቹ ሸሪኮች ከእነሱና ከሌሎች ተመላላሽ መኪኖች ቋሚ ገቢ ለማግኘት ጠዋት ማታ ይተጋሉ። የያዙትን ቆጥበው ነገ እስኪነጋ፣ ሌላ ሲሳይ እስኪያመጣ ይጠብቃሉ። መኪኖች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ።
‹‹ወንድማማቾች የመኪና ጥበቃ›› የሚል ስያሜ ያለው ማህበር ከተመሰረተ ዓመታት ተቆጥረዋል። በማህበሩ አባል ሆነው የሚሳተፉ አንዳንዶች ከሾፌር ታደለ የማይነጠለውን ግለሰብ አዘውትረው ያዩታል። በቅጽል ስሙ ‹‹ቻይና›› የሚባለው ሰው አንዳንዴ ወደ መኪናው ማቆሚያ ብቅ እያለ ሲኖትራኩን ያሞቃል፣ ያንቀሳቅሳል።
ከሾፌሩ እጅ ቁልፍ ሲቀበል የሚያዩት ሸሪኮች ሰውዬው የመኪናው ባለቤት የቅርብ ዘመድ ስለመሆኑ ሰምተዋል። ባገኛቸው ቁጥር ጥሩ ሰላምታ አለው። ብሩህ ፈገግታውን የሚያዩ አቀባበሉ ይማርካቸዋል። ቻይና እንደለመደው መኪናውን በቁልፍ አስነስቶ ሞተር ያሞቃል። ጥቂት ቆይቶም ወደመጣበት ይመለሳል።
ምሽቱ እየገፋ ነው። ዝናቡ አሁንም ቀጥሏል። ቻይናና አብሮት ያለው ግለሰብ ከአራቱ ሰዎች ጋር ከመኪናው ማቆሚያ ደርሰዋል። ሁሉም አንድ ጉዳይ እንዳስጨነቃቸው ያስታውቃል። በፊታቸው የሚነበበውን ስሜት ዋጥ ያዳረጉ ደግሞ ለመረጋጋት ሞክረው ተሳክቶላቸዋል።
በፓርኪንጉ ያሉት ጠባቂዎች ከመጡት ሰዎች መሀል ቻይናን አውቀውታል። አመጣጡ እንደለመደው ሞተሩን ለማስነሳት መሆኑን እየገመቱ ነው። ሾፌሩ ታደለ ከአንድ ቀን በፊት መጥቶ ከቆመ ሀያ ቀናት ያስቆጠረውን መኪና ለማንቀሳቀስ ሞክሯል። ባትሪው መሞቱን አረጋግጦም መኪናውን በነበረበት አቁሞት ተመልሷል።
ተረኛ ሸሪኮቹ የቻይናን አመጣጥ ከሾፌሩ የትናንትና ሙከራ ጋር አዛምደዋል። ቻይና ወደግቢው የመጣው ባትሪ ያደከመውን መኪና መላ ለማለት እንደሆነ እያሰቡ ነው። ጠጋ ብለው ሁኔታውን ለመረዳት ሞከሩ። ከቻይና ጋር የመጣው እንግዳ የሲኖትራኩ ባለቤት መሆኑ ተገራቸው። በተለየ አክብሮት እጅ ነስተው በአካባቢው ቆም አሉ።
ሁለቱ ሰዎች የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 59393 ኢት የሆነውን ሲኖትራክ እያዩ ነው። በዙሪያቸው የቆሙ ሌሎች የእነሱን እይታ ያጤናሉ። ሁሉም ትኩረታቸው አንድ ሆኗል። ዙሪያ ገባውን እየቃኙ የሚሆነውን ይጠብቃሉ። ቻይና እንደለመደው ቁልፉን እያሽከረከረ ወደመኪናው ቀረበ። አብሮት ያለው ሰው በአጭር ርቀት ከኋላ ተከተለው።
የግቢው ሸሪኮች የሚሆነውን ያያሉ። ቻይና ከመሪው ፊት ተቀምጦ ሞተር ለማስነሳት እየሞከረ ነው። በመስኮቱ አሻግሮ እየቃኘ ቁልፉን ሰክቶ ጠመዘዘ። መኪናው ከወትሮው በተለየ ቱፍ… ቱፍ… የሚል ድምጽ አሰማ። አሁንም ቻይና ቁልፉን ሳይነቅል ደግሞ ሞከረ። መኪናው እንደወትሮ ምንጥቅ ብሎ አልተነሳም። እየተንተፋተፈ መንቀጥቀጡን ቀጠለ። በሌሎቹ አማካሪነት መኪናውን በቻርጀር ለማስነሳት ተሞከረ። አልተሳካም።
ቻይናን ተከትሎ ጋቢና የተቀመጠው ደበበ ጠጋ ብሎ አንድ ጉዳይ ሹክ አለው። ውጭ ያሉት የሁለቱን ምክር አልሰሙም። ወዲያው ሁለቱ ከነበሩበት ወርደው ሌሎቹን ተቀላቀሉ። ጥቂት ቆይቶ በጋራ ውይይት ከአንድ ጉዳይ ደረሱና በእኩል ተስማሙ።
ከደቂቃዎች በኋላ አንድ ላዳ ግቢውን አቋርጦ ሲገባ ታየ። እነቻይና ዘንድ ተጠግቶም ትዕዛዙን ተቀበለ። ከሲኖትራኩ የወጣውን ባትሪ ቻርጅ እንዲያደርግ ተሰጠው። ባትሪውን ከመኪናው አስገብቶ ከግቢው ፈጥኖ ወጣ። ጥቂት ቆይቶ ሲመለስ ቻርጅ ያደረገውን የመኪና ባትሪ ይዞ ነበር።
ሰዎቹ ለባለታክሲው የሰጡትን መልሰው ተቀበሉት። ቻይና ወዲያው ባትሪውን ከመኪናው አስማምቶ ለማሰነሳት ሞከረ። ሲኖው እንደቀድሞው አልሆነም። ድምጹ ተስተካክሎ ለመነሳት ተዘጋጀ። የሁሉም ፊት በፈገግታ ደመቀ።
የሲኖው ሞተር መሞቅ እንደጀመረ ቻይና መሪውን ለእንግዳው አስረክቦ ከመኪናው ወረደ። የሲኖውን ነፍስ መዝራት ያስተዋሉት የግቢው ሸሪኮች ሰብሰብ ብለው ወደቻይና ቀረቡ። ቻይና ምን እንደሚፈልጉ አውቋል። መኪናው የቆመበትን ቀን በቀን ሂሳቡ አስልተው እንዲነግሩት ጠየቀ።
ሸሪኮቹ ሲኖው የቆመበትን ቀናት በሰላሳ ብር የቀን ሂሳብ አስበው ነገሩት። ጊዜ አልፈጀም። የተጠየቀውን የሃያ ሶስት ቀናት የጥበቃ ገንዘብ ስድስት መቶ ሰላሳ ብር ቆጥሮ ከፈለ። ሸሪኮቹ ቻይና ተመልሶ ከጋቢናው ሲገባ መኪናውን እያንቀሳቀሰ ያለው የሲኖ ባለቤት ነው የተባለው እንግዳ ስለመሆኑ አስተዋሉ። ሲኖትራኩ በአፍ በአፍንጫው የከረመ ጭሱን እየተፋ፣ ከእሱ ባነሱት ላይ እያናፋ ጉዞ ጀመረ። ግቢውን ለቆ ሲወጣ ከደጅ ያሉ እግረኞች ሁሉ እየተደናገጡ ከመንገዱ ገለል አሉ።
በማግስቱ ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል ሲሆን ሾፌር ታደለ ወደ መኪና ማቆሚያ ፓርኪንጉ ደረሰ። የእሱን መምጣት ያዩት ወጣቶች ሰላምታቸውን ቸሩት። አጸፋውን እየሰጠ አልፏቸው ተራመደ። እግሮቹ መንገዱን አቋርጠው ከለመደው ስፍራ አደረሱት። ሸሪኮቹ እርስ በርስ እየተያዩ አሻግረው አዩት። ታደለ ካሰበው ሲደርስ ዓይኖቹን አላመነም።
ትናንት መጥቶ የጎበኘው ሲኖትራክ ዛሬ ከቦታው የለም። ልቡ እየመታ፣ አፉ እየደረቀ ወደ ሸሪኮቹ አፈጠጠ። መኪናው ወዴት እንደሄደም ጠየቃቸው። ሁሉም በአንድ ድምጽ የእሱ ዘመድ ቻይና ትናንት ከመኪናው ባለቤት ጋር መጥቶ ሰውዬው እየነዳ እንደወሰደው አሳወቁት። በድንጋጤ ክው እንዳለ እጁን በአፉ ጭኖ ቆየ። ከአፍታ በኋላ ወደመኪናው እውነተኛ ባለቤት ደውሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው።
ከፖሊስ ጣቢያው
ከፖሊስ ጣቢያው ደርሰው ቃል መስጠት የጀመሩት ሰው መናገራቸውን ቀጥለዋል። የጠፋው ሲኖትራካቸው አየር ጤና አደባባዩ አካባቢ ስለመቆሙ ሰምተዋል። አሁን ከቀድሞው ስሜታቸው የተረጋጉ ይመስላሉ። መርማሪው ቃላቸውን ወስዶ እንደጨረሰ ቀጣዩን እርምጃ ለመውሰድ ራሱን ከሌሎች ቡድኖች ጋር አደራጀ።
የፖሊስ ምርመራ
ሲኖው የቆመበት ቦታ እንደታወቀ የተደራጀው ቡድን ከስፍራው ደርሶ ምርመራውን አጠናቀቀ። ሾፌሩን ጨምሮ በፓርኪንጉ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ይዞና አስሮ የሆነውን ሁሉ ጠየቀ። ሰባቱ ሸሪኮች ያዩትን፣ ያስተዋሉት አንድ በአንድ ተናገሩ።
መርማሪው ድርጊቱን የፈጸሙት ተጠርጣሪዎች በተመሳሳይ ቁልፍ መኪናውን ስለመክፈታቸው አረጋገጠ። በቅጽል ስሙ ቻይና የተባለውን ግለሰብና የመኪናው ባለቤት የተባለውን አጋሩን ይዞም ቃላቸውን በተዘጋጀው መዝገብ ላይ መዘገበ። ከሶስት እስከ ሰባት ያሉ የፓርኪንጉ ሰራተኞች ከተጠየቁበት ወንጀል ነጻ ሆነው የዓቃቤ ህግ ምስክር በመሆን ቀረቡ።
ውሳኔ
ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በችሎቱ ተሰይሟል። በስርቆት ወንጀል ተከሰው የቀረቡት ሁለቱ ሰዎች የፍርድ ውሳኔቸውን ለማግኘት ቀርበዋል። ችሎቱ የቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከህጉ አጣምሮ ባጤነው መሰረት ተከሳሾቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋጧል። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ሁለቱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡልኝ››ሲል ወስኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013