የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.አ.አ በ2007 በየዓመቱ የካቲት 13 (February 20) ‹‹ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ፍትህ ቀን (World Day of Social Justice)›› ሆኖ እንዲከበር ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፣ ‹‹ሰላምና ልማት እንዲስፋፋ የምትፈልጉ ከሆነ፣ ለማኅበራዊ ፍትህ መስፈን ስሩ!›› በሚል መሪ ቃል ዛሬ ለ11ኛ ጊዜ በመላው ዓለም ታስቦ ይውላል፡፡ ቀኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የግንዛቤ ፈጠራ መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም በዕለቱ ስለማኅበራዊ ፍትህ ምንነትና ፋይዳዎች፣ በጉዳዩ ዙሪያ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራትና ስለቀጣይ እቅዶቻቸው በተለያዩ መንገዶች ያሳውቃሉ፡፡
የድህነት፣ የመገለልና የስራ አጥነት ፅንሰ ሃሳቦች በዕለቱ ጎልተው ከሚነገሩና ላቅ ያለ ትኩረት ከሚያገኙ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ማኅበራዊ ፍትህ ፍትሐዊ በሆነ የስልጣን፣ የሀብትና የኃላፊነት ክፍፍል ላይ ያተኮረ ፅንሰ ሃሳብ ሲሆን፤ አካታችነት፣ ትብብርና እኩል እድል የፅንሰ ሃሳቡ ዋነኛ መሰረቶችና ማዕከላት እንደሆኑ የስነ- ልቦናና የስነ-ሰብዕ ጥናት ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ በዓለም አገራት መካከል ያለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ማገርሸቱን ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ቡድኖች ልዩነቶችን ለማለዘብ ማኅበራዊ ፍትሕ በሚባለው ፅንሰ ሃሳብ ላይ የሙጥኝ ብለዋል፡፡ ማኅበራዊ ፍትህን የማስፈን እንቅስቃሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልማትን ለማስፋፋትና ሰብዓዊ ክብርን ለመጠበቅ በሚያደርገው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ድርጅቱ ይገልፃል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት የማኅበራዊ ፍትህና የፍትሃዊ ሉዓላዊነት ድንጋጌ (Declaration on Social Justice for a Fair Globalization)ን ማፅደቁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለማኅበራዊ ፍትህ መስፈን እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች መካከል አንዱና ለትግበራውም ያለውን ቁርጠኛነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ድንጋጌው በስራ እድል (ቅጥር)፣ በማኅበራዊ ዋስትና እንዲሁም በመሰረታዊ የስራ መርሆዎችና መብቶች ፍትሃዊ ክፍፍልና ጥበቃ ላይ ያተኮረ ማዕቀፍ ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትህ ለአገራት ሰላማዊ ግንኑኙትና ብልፅግና ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት ያምናል፡፡ ድርጅቱ እንደሚለው፣ ፆታን፣ እድሜን፣ ዘርን፣ ባሕልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን መሰረት ያደረጉ የኢ-ፍትሐዊነት ተግባራትን የማስወገድ እርምጃ ማኅበራዊ ፍትሕን የማስፈን የመጀመሪያ ደረጃ ተግባር ነው፡፡ የማኅበራዊ ፍትህ መስፈን ድህነትን ከመዋጋትና ፍትሃዊ የሆነ የምጣኔ ሀብት ክፍፍልን እውን ከማድረግ ተግባራት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው በመሆኑ፤ ለአገራት ትብብርና ብልፅግና እንዲሁም ለዜጎች ሕይወት መሻሻል ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ማኅበራዊ ፍትሕ የድህነት ቅነሳና የፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል ዋነኛ መሳሪያ እንደሆነ ተደጋግሞ ቢገለፅም በዓለም ዙሪያ ድህነት ቅነሳውን ለማፋጠንም ሆነ የሀብት ክፍፍሉን ፍትሐዊ ለማድረግ በተግባር እየታየ ያለው እውነታ ግን ችግሩ ስር የሰደደና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚስፈልግ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
የዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአሁኑ ወቅት ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ አስጊ የፀጥታ ሁኔታ ባላቸው አካባቢዎች የሚኖር ነው፡፡ ከዚህ መካከል ደግሞ 400 ሚሊዮን ያህሉ ከ15 እስከ 49 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ በማኅበራዊ መደብና በፆታ ልዩነቶች ምክንያት የሚስተዋሉ ልዩነቶች ማኅበራዊ ፍትህን በሚፈለገው ደረጃ ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እየጎተቱት ይገኛሉ፡፡ የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የፆታ እኩልነት አስተማማኝ መሰረት ካልያዘ በስተቀር፣ ማኅበራዊ ፍትሕን የማስፈን ጥረት ምኞት ብቻ ሆኖ እንደሚቀር ደጋግመው ሲገልፁ የሚስተዋሉትም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
አንተነህ ቸሬ