ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ውብ ሀገር ስለመሆኗ በብዙ የታደለችና እልፍ ምስክሮችም ያሏት ናት፡፡ የአየር ንብረቷን ጨምሮ ተፈጥሮ በእጅጉ ያደላት ኢትዮጵያ በተለይም ሀገረሰብ በሆኑ በርካታ የባህል እሴቶቿና ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ሀገር በቀል የዕውቀት ዘርፎቿ ትታወቃለች፡፡ ከባህላዊ መድሃኒቶቿ መካከልም ባህላዊ የዕፅዋት መድሃኒት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ባህላዊ መድሃኒት ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ በህክምናው መስክ ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሀገረሰባዊ የዕውቀት ዘርፍ ነው።
የተለያዩ የተፈጥሮ እጽዋትን በመጠቀም ከሚገኘው ባህላዊ ህክምና በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬን በመጠቀም ንጽህናና ውበትን መጠበቅ እንደሚቻልም እየታየ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ የሆነ ምግብ ሲመገቡት ለጤና ተስማሚ እንደሆነ ሁሉ ተፈጥሯዊና ከኬሚካል ውጭ የሆኑ መዋቢያ ቁሳቁሶች መዋብም ሆነ ንጽህናን መጠበቅ ከተስማሚነቱም በላይ አዋጭ በመሆኑ በአሁን ወቅት ብዙዎች ወደ ተፈጥሮ በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡
የዛሬው የስኬት እንግዳችንም ተፈጥሯዊና ሀገር በቀል ከሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎች ተፈጥሯዊ የሆኑ የመዋቢያ ቁሳቁሶችና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በማምረት ‹‹አፍሪ ኸርባል›› የመዋቢያ ቁሳቁስ አምራቾችን ይዘን ቀርበናል፡፡የአፍሪ ኸርባል የመዋቢያ ቁሳቁስ መስራችና ባለቤት ከደቡብ ክልል የተገኙት አቶ ሀብቴ ዘውዴ ናቸው፡፡ ወደ ዘርፉ ለመግባት መነሻቸው በአካባቢያቸው በብዛት የሚገኙ አትክልትና ፍራፍሬዎች ሲሆኑ በተለይም አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ የመሳሰሉትን በቤት ውስጥ ሴቶች ለፊታቸው እንዲሁም ለጸጉራቸው መዋቢያ በስፋት ሲጠቀሙበት እየተመለከቱ ማደጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ወደ ተፈጥሮ እንመለስ በሚል መርሆ በተፈጥሮ የሚገኙ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በዋናነት በመጠቀም የተለያዩ የጸጉር ቅባቶችን፣ መታጠቢያ ሳሙናዎችን፣ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነሮችን ለአዋቂና ለህጻናት ጭምር እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት ተፈጥሯዊ የሆነ ነገር ሁሉ ከፍተኛ አቅም ያለው፣ አዋጭና ተስማሚ መሆኑን በማመን ነው፡፡ ይህንንም ከልጅነት ጀምሮ ቤተሰባቸውን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን በሚባል ደረጃ በቤት ውስጥ በተግባር ሲጠቀሙት የነበረ በመሆኑ ጥቅሙን በሚገባ መረዳት ችለዋል፡፡
ታድያ ማህበረሰቡ የሚያውቀውንና ሀብቱ የሆነውን ነገር ጥቂት ሳይንሳዊ ሂደቶችን በመጨመር ተስማሚና ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ መንገድ ብናቀርብለት የተሻለ ይሆናል በማለት ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥራው ገብተዋል፡፡ ወደ ሥራው ሲገቡ ማህበረሰቡን ለማሳወቅ ማገዶ ቢጨርሱም አሁን ያላቸው ተቀባይነት ግን የሦስት ዓመት ዕድሜ ያለው አይመስልም፡፡በመሆኑም በአሁን ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛው የክልል ከተሞች ጭምር የአፍሪ ህርባል ምርቶች ተወዳጅና ተፈላጊ ሆነዋል፡፡
‹‹ተጠቃሚው አስቀድሞ የሚያውቀው ነገር በመሆኑ ባቀረብንለት ምርት አቀባበሉ ጥሩ ነው›› የሚሉት አቶ ሀብቴ፤ የህዝቡ አቀባበልም ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸው ዛሬ በስፋት ገበያ ውስጥ መግባት መቻላቸውን አጫውተውናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ የሆኑት የአፍሪ ህርባል መዋቢያና የንጽህና መጠበቂያ በዋናነት ለጸጉር ጠቃሚ የሆነ ፕሮቲንን በውስጡ የያዘውና ከፍተኛ የሆነ ቅባት ያለው የጉሎ ፍሬን ጨምሮ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ሮዝመሪ ወይንም የጥብስ ቅጠል፣ ጥቁር አዝሙድና አቮካዶ ከመሳሰሉት ምርቶች ነው፡፡
አጠቃላይ አስር የሚደርሱ ፈሳሽ ቅባቶችን ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ከሆኑ ምርቶች ተጨምቆ ከሚገኝ ዘይት የሚመረት ሲሆን፤ በተጨማሪም የሞሪንጋ፣ የነጭ ሽንኩርትና የእርድ ሳሙናን ጨምሮ ስድስት አይነት ደረቅ ሳሙናዎችንም ያመርታል፡፡ሻምፖና ኮንዲሽነርም እንዲሁ በደረቅ ሳሙና መልክ የሚመረት ሲሆን ፈሳሽ ያልሆነበት ምክንያትም ፈሳሹ ከፍተኛ የሆነ ኬሚካል የሚፈልግ በመሆኑና የኬሚካሉን መጠን በመቀነስ ተፈጥሯዊ የሆነውን ግብዓት ለማጉላት እንደሆነም አቶ ሀብቴ አስረድተውናል፡፡
አፍሪ ኸርባል የመዋቢያና የንጽህና ምርቶች መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ተፈጥሯዊ በሆኑ ምርቶች የሚመረት ነው፡፡ነገር ግን እጅግ በጣም ጥቂት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኬሚካሉን ቀንሶ ሳሙናን ከፈሳሽ ወደ ጠጣር የመቀየር ሥራ ይሰራል፡፡በመሆኑም አብዛኛው ማህበረሰብ ምርቱን በሚገባ አውቆት፣ ተረድቶትና በተጨባጭ ውጤት አግኝቶበት ጥቅሙን ፈልጎ እየተጠቀመ በመሆኑ በአሁን ወቅት በሁሉም የሀገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡
ገበያውን ሰብሮ ለመግባት በሰፊው የሰሩበት በመሆኑ የምርቶቹ ጥራትና ተፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል፡፡በዚህም መሰረት ምርቶቹ በማንኛውም ሱፐር ማርኬቶች፣ ሱቆች መድሃኒት ቤቶች እንዲሁም በከነማ መድሃኒት ቤቶች በሙሉ ይገኛል፡፡ድርጅቱ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በፈጠረው የገበያ ትስስር ምርቶቹን በየጊዜው ያቀርባል፡፡
በአሁን ወቅትም ከፍተኛ ፍላጎት እየመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ አሁን ላይ እያመረተ ካለበት ቦታ የተሻለና ሰፋ ያለ የማምረቻ ቦታ የሚያስፈልገው መሆኑን አቶ ሀብቴ አንስተዋል፡፡አሁን እያመረቱ ካለው መጠን በእጥፍ ማምረት የሚጠይቅ ፍላጎት እየመጣላቸው በመሆኑ በስፋት አምርተው ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገር ገበያም ተደራሽ ለመሆን የቦታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
አፍሪ ኸርባል የመዋቢያና የንጽህና መጠበቂያ ማምረቻ ድርጅት ምንም እንኳን በጀማሪ ስሜት ያለ ቢሆንም ዘርፉ ገና ያልተነካና ብዙ ሊሰራበት የሚችል መሆኑን የውጭ ሀገር ገበያን ለመቀላቀል ግን ሰፊ ዕድል ያለው በመሆኑ ጠንክረው እየሰሩ እንደሆነ አቶ ሀብቴ ይናገራሉ፡፡እንደሳቸው መረዳት ዘርፉ በተለይም ለውጭ ንግድ እጅግ ምቹና ሰፊ ዕድል ያለው ዘርፍ ነው፡፡ በውጭው ዓለም ቀድሞም ለተፈጥሮ ምርት ያላቸው ዕውቀት የዳበረ በመሆኑ ተፈጥሯዊ ምርቶችን የመጠቀም ከፍተኛ ልምድ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና እየተጀመረ ያለው ተፈጥሯዊ የውበትና የንጽህና መጠበቂያ ዘርፍ ውስጥ ብዙዎች ቢሰማሩም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያምናሉ፡፡
በተለይም ወደ ውጭ ሀገር መላክ ሲቻል ሀገሪቷ በሁለት መንገድ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡ በቀዳሚነት በከፍተኛ መጠን በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን ምርቶች ማስቀረት ይቻላል፡፡ ቀጥሎም በሀገር ውስጥ የሚመረተውን ምርት በጥራትና በብዛት በማምረት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ኢኮኖሚውን ያግዛል፡፡ ለዚህም በአሁን ወቅት የአፍሪ ኸርባል ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አቶ ሀብቴ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅቶችን ጀምረዋል፡፡
ጅማሬውን ፍጻሜ ለማድረስ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ጨምሮ በዋናነት መንግሥት ካገዛቸው በቅርቡ የውጭ ሀገር ገበያውን ለመቀላቀል ደፋ ቀና እያሉ ስለመሆናቸውም አቶ ሀብቴ
አጫውተውናል፡፡ ዘርፉ በተለይም ከአርሶ አደሮች ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ምርቶቹን በጥራት ማግኘት እንዲቻል ከገበሬው ጋር በቀጥታ በፈጠሩት ትስስር ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የተሻለና ጥራት ያለውን ምርት ማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ከሚያገኘው ጥቅም ጎን ለጎን ትስስር የፈጠሩ አርሶ አደሮችም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡
አፍሪ ኸርባል ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት እያደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለው በዋናነት ሰፋፊ የእርሻ መሬት መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ተፈጥሯዊ የሆኑትን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ሲቻል ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች በፋብሪካ ደረጃ በማምረት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከውጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረትም የውጭ ምንዛሪን ማዳን ይቻላል፡፡ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ይህም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
አፍሪ ኸርባል ከስሙ ጀምሮ ‹‹አፍሪ›› ማለት በአጭሩ አፍሪካን የሚወክል ሲሆን፤ ለአፍሪካውያን የሚስማሙ ምርቶችን በጥራትና በስፋት በማምረት በመላው አፍሪካ ተደራሽ ለመሆን አልሞ የተነሳ ድርጅት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በአሁን ወቅት በሀገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ አፍሪካውያን ደንበኞች ያሉትና እነዚህ ደንበኞችም ወደ ሀገራቸው ሲሄዱ የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራሉ፡፡ይህም ወደ ውጭ ገበያው ለመግባት መንገድ እየጠረገ መሆኑ ይታመናል፡፡
የሥራ ዕድልን በተመለከተም 150 የሚደርሱ ዜጎች በሽያጭ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሲሆን፤ በማምረት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሰራተኞችም አሉ፡፡ በተለይም የመጭመቂያ ማሽኖችን ተጠቅመው ጥቁር አዝሙድን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመጭመቅ የሚገኘውን ዘይት ለመዋቢያና ለንጽህና መጠበቂያ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ያመርታሉ፡፡ ከዘርፉ የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን ወይም ፋጉሎ ለከብቶች ማደለብያ የሚውል በመሆኑ ለገበያ በማቅረብ በዚህም ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡
ማንኛውም ባለሃብት እና ሥራ ፈጣሪ ዘርፉን ማየትና መረዳት ቢችል የተሻለ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል የሚሉት አቶ ሀብቴ፤ ዘርፉ ገና ያልተነካ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ያለውን ትልቅ የተፈጥሮ አቅም በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡ተፈጥሯዊ ምርቶቹንም በሙሉ አቅም መጠቀም ከተቻለ በእርግጠኝነት የመዋቢያና የንጽህና መስጫ ቁሳቁሶችን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡
ድርጅቱ ከሚያመርታቸው አሥር አይነት ቅባቶችና ስምንት አይነት ሳሙናዎች በተጨማሪ ሎሽን፣ ስክራብ ወይም ተፈጥሯዊ በሆኑ ማር፣ ሩዝ፣ እርድና መሰል ግብዓቶችን በመጠቀም የሚዘጋጁ የፊት ጥራትን መጠበቅ የሚያስችሉ ምርቶችንም በቅርቡ ወደ ገበያ ይዞ ይገባል፡፡
አፍሪ ኸርባል በሚያመርታቸው ምርቶች አብዛኛው ተጠቃሚ ጥሩ የሆነ ምላሽ እየሰጠ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም አልፎ አልፎ ቅባቶቹ በተለይም የቀይ ሽንኩርት ቅባት ከፍተኛ ሽታ ያለው በመሆኑ ሽታውን ለመቀነስ በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሰረት ሽታውን እየቀነሱ ነው፡፡ ይሁንና ወደ ገበያው የገቡበት ራዕይ ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደያዘ ምንም አይነት ኬሚካል ያልተቀላቀለበትንና ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የማያመጣ ምርትን ለማቅረብ በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ጠረኑን ብቻ ለመቀነስ የተለያዩ ፍሌበሮችን በመጠቀም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ወደ ተፈጥሮ እንመለስ በሚል መርሆዋቸው ተፈጥሯዊና ሀገር በቀል የሆኑ ምርቶች ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተጠቅመው ውጤታማ መሆን የቻሉት አቶ ሀብቴ የመዋቢያና የንጽህና መስጫ ቁሳቁሶቹን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ ተደራሽ በመሆን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው፡፡ዘርፉ ገና ያልተነካና በሰፊው ሊሰራበት የሚችል በመሆኑም ሌሎችም ቢሰማሩበት ሀገሪቷ የተሻለ ተጠቃሚ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ወደ ተፈጥሮ በመመለስ ተፈጥሯዊ በሆኑ ምርቶች እና ሀገር በቀል በሆኑ ዕውቀቶች ተጠቅመን ሀገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ እንሁን በሚል መልዕክታቸው አበቃን፡፡
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013