በትናንት እትማችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፋና ብሮድካስር ኮርፖሬት ጋር በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳች ዙሪያ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እትማችን የቃለመጠይቁን ሁለተኛ ክፍል ይዘን ቀርበናል ።
ጥያቄ፡– ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንለፍ። ቀደም ሲል ተናግረውታል፤ በተለያየ ጊዜም ሲናገሩት ነበር። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከሞት ታድገነዋል ብለዋል። ከሞት ታደግነው ያሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን የት አደረሳችሁት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፡– አንድ ሰው ወደ ሞት ጎዳና እየሄደ እያለ ወደ ህክምና ቢሄድ፣ ህክምና ሄዶ ተመርምሮ በሽታው ከተገኘ በኋላ መድኃኒት ሲሰጠው መድሃኒት የሚሰጠው ለአስራ አምስት ቀን ሊሆን ይችላል፣ ለአንድ ወር ሊሆን ይችላል፣ ለሦስት ዓመት ሊሆን ይችላል። መድኃኒቱን እወሰደ በሄደበት ጊዜ እያገገመ፣ እያገገመ የሆነ ጊዜ ላይ የበለጠ ጥንካሬ እየያዘ ይቆማል ማለት ነው።
አንድ ያመመው ሰው ዛሬ ሆስፒታል ሄዶ አንድ መርፌ ስለተወጋ ወዲያውኑ ቆሞ ጤነኛ ሆኖ ይመለሳል ማለት አይደለም። ህዳሴን እደግመዋለሁ ከሞት ታድገነዋል። ህዳሴ ወደ ሞት እየተጓዘ ሳይሆን ወደ ህይወት እየተጓዘ ነው ። ምንም ጥርጥር የለውም ይሄ፣ ወደ ህይወት የሚደረገው ጉዞ ልክ ወደ ሞት የተደረገው ጉዞ በአንድ ጀንበር እንዳልተደረገ፣ በአንድ ጀንበር እንዳልተሞተ ሁሉ በአንድ ጀንበር ህዳሴ ተነስቶ አይቆምም።
ህዳሴ ማለት በጣም ሲበዛ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። እንኳን ልትሰራው፣ እንኳን ችግሩን ተረድተህ ልትፈታው ይቅርና ለማየትም ዓይተህ የማትጨርሰው የሚደረገውን ገለጻ ሰምተህ የማትረዳው በጣም ውስብስብ ፕሮጀክት ነው። እዚህ ሆነን እንደምናስበው በሚዲያ እንደምናየው፣ ምናልባት እናንተ የማየት ዕድል አላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ትልቅ ፕሮጀክት ነው።
ብዙ የሚያስደንቁ ሴትና ወንድ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ቀንና ማታ እየሰሩ ህዳሴ እንዳይሞት እንዲድን እና ለኢትዮጵያውያ ሕዝብ ትሩፋት እንዲሆን በጣም እጅግ አመርቂ የሚባል ስራ እየሰሩ ነው። ችግሮቹን ማየት ከፈለክ የውጩን ነው ብዙ ጊዜ የሚነገረው እንጂ ለምሳሌ ከሲሚንቶ ፋብሪካ ብንጀምር የሲሚንቶ እጥረት ህዳሴ ይነካካዋል። ህዳሴ ላይ ሲሚንቶ እጥረት እንዲቀረፍ ሲሚንቶ የሚያመርቱትን ሲሚንቶ ወደ ህዳሴ ላኩ ሲባል አሁንም በጣም በርካታ ባንዳዎች ስላሉን ጥሪ እቃውን ወደ ፋብሪካ የሚያመጣው ቤልት ይቆረጣል። ቤልት ሲቆረጥ ሁሉም ትኩረታችን ሲሚንቶ ላይ ይሆናል፤ ቶሎ መጠገን ማስተካከልና ሲሚንቶ እንዲመረት ለማድረግ። ተመረተ ችግር ተፈታ ደግሞ ሲባል መኪናዎች ከዚህ ቀደም ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ህዳሴ ግድብ ለመውሰድ ሦስት ቀን የሚፈጅባቸው ከሆነ አሁን በመንገዱ ምክንያት አስር ቀን ይፈጅባቸዋል። መንገዱን ለማስጠገን ደግሞ ኮንትራት ስናወጣና ኩባንያዎች ስንጋብዝ ሽፍቶች በዛ መንገድ ስላሉ መጠገን እንቸገራለን ይላሉ። መከላከያ ሽፍታን ተከላክሎ መንገድ እንዲጠግን አድርገን ስንፈታውና ሲሚንቶ በገፍ ሲደርስ እዚያ ደግሞ በዛ ልክ ማውረድ ፈተና ይሆናል። እዛ በዛ ልክ ማውረድ ፈተና መሆኑን ስንፈታ የመኪና ትራንስፖርት ችግር ያጋጥማል።
የትራንስፖርት ችግር ስንፈታ ገንዘብ ችግር ያጋጥማል። የገንዘብ ችግር ስንፈታ በቅርቡ ያጋጠመን አንዱ ፈተና የሰሞኑ ዝናብ እንደምታውቁት በቀን ሰላሳ፣ ሰላሳ አምስት ሴንቲ ሜትር ይጨምር ነበር ። ዝናቡ እየዘነበ የምንወስደውን ሲሚንቶ ኮንክሪት የመሙላት ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ አስተጓጉሎት ነበር። ልንሰራ አልቻልንም።
ከውጭ ያለውን ጫና ዲፕሎማሲ፣ ሚዲያ ትታችሁ በያንዳንዱ የሥራ ሂደት ውስጥ በየቀኑ ህዳሴ እየገጠመው ያለውን ፈተና እየፈቱ ማለፍ በራሱ በጣም ከፍተኛ ፈታኝ ጉዳይ ነው። እና የህይወት መስመሩ እንዲሁ ዝም ብሎ በንግግር የሚፈታ ሳይሆን በየቀኑ በመለየት፣ በመፍታት፣ በመስራት፣ ውጤት በማምጣት የሚረጋገጥ ነው። በዚህ አግባብ ነው እየሄደ ያለው።
በእኔ ዕምነት ለሱዳን ሕዝብ በረከት ፣ ለግብጽ ህዝብም ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ፣ለኢትዮጵያም ብርሀን ሊያመጣ በሚያስችለው አግባብ እየተጓዘ ነው ብዬ አስባለሁ። ማንንም ሳይጎዳ ሁላችንም ጠቅሞ የሚያስፈልገውን ውጤት ያመጣል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ።
ጥያቄ፡– በፓርላማ ባደረጉት ንግግር መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ እርስዎ አመጣሁ የሚሉት አንዱ የትርክት ለውጥ ነው። በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ እርስዎ አመጣሁ የሚሉት የትርክት ለውጥ የሚፈልጉትን ያህል ደርሷል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– እንግዲህ መጀመሪያ ትርክት ጋር ሳንደርስ ከቃል እንነሳ። ቃል በጣም ከባድ ነገር ነው። ለወንድም፣ ለእህትህ፣ ለልጆችህ የምትገባቸውን ቃሎች የማትፈጽም ከሆነ ቃል ሥጋን ሰርስሮ ገብቶ አጥንትን የመስበር አቅም አለው። በክፉም፣ በመጥፎም በጥሩም። የምንናገራቸው ቃሎች አሳዳጊ፣ አለምላሚ፣ አብቃይ መሆናቸውን፣ የሚተገበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ዝም ብሎ መናገር ብቻውን ሳይሆን አስበህ መናገር የተናገርነውን መፈጸም መቻል እጅግ አስፈላጊ ነው።
ከትርክት አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ከባህላችን፣ ከታሪካችን አብረን ከኖርንበት አጠቃላይ ልምምድ ወጣ ያሉ አዳዲስ ቋንቋዎች፣ ከፋፋይ ቋንቋዎች የሚለዩ ቋንቋዎች ላለፉት ዓመታት በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲዘሩ ኖረዋል ። እነዚህ ጉዳዮች ያኔ ስንሰማቸው ልክ እንደ ሞትና እንደ ህይወት ወዲያው ስለማይታዩ ጊዜ ወስደው፣ ስር ሰድደው፣ ፍሬ አፍርተው አሁን ዛሬ የሚያባሉን፣ የሚያጠራጥሩን፣ የሚለያዩን ሆነዋል። እኛም እንደነዚህ ዓይነት ትርክቶች ቢቀየሩ ይሻላል ስንል በማግስቱ የተሟላ ውጤት ያመጣል፣ በማግስቱ ትርክት ለውጡ ፍሬያማ ይሆናል ብለን ሳይሆን በልጆቻችን ላይ እየዘራን ከሄድን ጊዜውን ጠብቆ ፍቅር፣ ሰላም አንድነት፣ መቀራረብ ፈር እያዘ ይሄዳል የሚል እምነት ስላለን ነው።
እንግዲህ ስላነሳሃው የፓርላማ ንግግር ፣ የምመክርህ ነገር የፓርላማ ንግግር ዛሬ ተመልሰህ አድምጠው። እያንዳንዱ የፓርላማ ንግግር ያኔ የተነገረው እንደ “ሶሻል ኮንትራት” እንደ ቃል ኪዳን ተወስዶ ከሞላ ጎደል በሚያስደንቅ ሁኔታ ተፈጽሟል። እያንዳንዱን በዲሞክራሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በሁሉም ብታይ የዛኑ ዕለት እኮ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰራተኞቹ ደምወዝ ሊከፍል አይችልም ፣ 450 ሚሊዮን ዩሮ ህዳሴ ላይ ተጨማሪ ሀብት ፈሰስ “ኢንጀክት” ማድረግ ቀርቶ ደመወዝ ሊከፍል አይችልም። እንኳን የቆመ ስኳር ፋብሪካ መጨረስ ቀርቶ ቢሮ ገብቶ በማግስቱ እንዴት እናድርግ የሚለውን ጉዳይ የመመለስ ብቃት አልነበረውም።
አሁን ብዙ ብዙ ጉዳቶች ያኔ በተገባው ቃል መሰረት መስመር እየያዙ መጥተዋል። ብዙ ደግሞ ይቀረዋል። እንዳንዘናጋና እንዳንተኛ የሚያስፈልገው ነገር ለውጥ አለ ሲባል የለውጥ ጉዞ አዎንታዊ “ፖዚቲቭ” መስመር ይዘናል ማለት ነው እንጂ ሁሉ ችግር ተፈትቶ አለቀ ማለት አይደለም። ያ ትርክት ግን የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ሰዎች ከተባበሩ፣ ይቅር ከተባባሉ፣ ከተቀራረቡ፣ ከተስማሙ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ሰዎች በተፈጥሮ እጅግ የበዛ የበረከተ ብቃት አላቸው።
ጥያቄ፡– የትርክት ለውጥ ላይ ኢትዮጵያን የማግነን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን ከማጉላት ይልቅ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን ማንሳት ፣ወደ እንደዚህ ዓይነት የትርክት ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ሚያገን፣ አንድነትን ወደ ሚያጎላ ትርክት መምጣት ለምንድን ነው የተፈለገው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ይህን ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል? ኢትዮጵያን የሚከፋፍለው ሃሳብ እኮ በተነን፣ ለየን፣ አባላን፣ አፋጀን እኮ—
ጥያቄ፡– ካሁን በፊት የነበረው ትርክት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ልዩነትን የሚያጎላ፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን የሚያጠናክር፣ በእናንተ ትርክት ኢትዮጵያን የሚያገን በአንድነት ውስጥ ልዩነትን ሰብስቦ የሚይዝ እንደዚህ የሚል የትርክት ለውጥ እንደዚህ ዓይነት ልዩነት አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ማነው ያለው ይሄን? ከዚህ ቀደም የነበረው በልዩነት ውስጥ አንድነትን የሚያጠናክር ቢሆንማ ለምን እንጣላለን። ከዚህ በፊት የነበረው ልዩነትን የሚያጎላ፣ ኢትዮጵያ የምትለውን ቃል መጥራት የሚጠየፍ፣ ኢትዮጵያን በሃገራችን የተካ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለያየ መጠሪያ ሕዝቦች ብሎ የከፋፈለ—
ጥያቄ፡– የእኔም ጥያቄ ከዚያ ወደእዚህኛው ትርክት መምጣት ያስፈለገበት ምክንያት ለምንድነው የሚለው ነው ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ያ ጉዳይ በተግባር ኢትዮጵያን እየበተናት ስለሆነ፣ እያሳነሳት ስለሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት የሚጋቡ፣ የሚዋለዱ፣ አብረው የሚማሩ፣ አብረው የሚኖሩ ሰዎች በዚህ ትርክት ምክንያት አብሮ መቆም ሳይሆን አብረው በአንድ የሚያምኑ በአንድ የአምልኮ ስፍራ ማምለክ ተቸግረዋል። ክርስትና ተበትኗል፣ እስልምና ተበትኗል። እንደዚህ ዓይነት በዘር ላይ የተመሰረተ ነገር ለመፍጠር በዕምነት፣ በባህል፣ በፖለቲካ የተሰራው ሥራ አደገኛ ነው።
ያን ለመቀየርና ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ናት። በውስጧ ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፤ ብዙ ባህል ያላቸው ሰዎች አሉ፤ የተለያየ ጾታ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ። ይህ እውነት ነው፤ ይህንን እውነት መካድ “ ዲናይ” አይቻልም። እነዚህን ልዩነቶች ግን ወደ ምንጠፋፋበት ሳይሆን ተሰናስለን ጠንካራ አገር ወደ ምንፈጥርበት ማምጣት አለብን ነው የትርክቱ ዋናው ዓላማ።
ጥያቄ፡– ኢትዮጵያን ማግነን ኢትዮጵያ ያላትን ሕብረ ብሔራዊነት ሊዘነጋ ይችላል የሚል ስጋት ላላቸው ሰዎች ምንድነው ምላሽዎት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ይሄ በቁንጽል ጉዳዩን ከመገንዘብ የሚመጣ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ገንና፣ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ፣ ኢትዮጵያ በልጽጋ የሚከሳ ኦሮሞ የለም። ኢትዮጵያ ተንኮስሳና ተዳክማ ተከፋፍላ ግን ብቻውን ኦሮሞ ወይም ሌላ ዘር ሊገንን አይችልም። የኢትዮጵያ ጥንካሬ የእያንዳንዱ ብሔር ጥንካሬ ውጤት ነው። የኢትዮጵያ ጥንካሬ የእያንዳንዱ ዜጋ ጥንካሬ ውጤት ነው። ኢትዮጵያን በተለያየ ጎራ ከፋፍለን በማዳከም ጠንካራ ባልሆነች ሃገር፣ አንድ ባልሆነች ሃገር ውስጥ እየኖርን በውስጧ የሚኖሩ ሕዝቦች፣ የተለያዩ ብሔሮች ጠንካራ ይሆናሉ የሚለው ሃሳብ በጣም በጣም ስህተት ነው።
የእኛ ዓላማ እነዚህ ብሔሮች በቋንቋቸው እንዲገለገሉ፣ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ራሳቸውን እንዲያለሙ ነው ።በዚህ ምንም ብዥታ የለብንም የምንሰራውም በዚያ አቅጣጫ ነው። ነገር ግን የአንዱ ብሔር ዕድገት፣ ልማትና ከፍታ ለሌላኛው ብሔር የሚያሰጋ የሚያስፈራ እንዲሆን ሳይሆን ሁለቱ ተያይዘው በጋራ አንድ ጠንካራ አገር እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው። ያ ብቻ ነው መፍትሔው። ለዚህ እኮ ቀላል ነው መንገዱ። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሃገር ናት። እነዚህ ዜጎች አንዳቸው ላንዳቸው መከታና ጋሻ ሆነው በትብብር በፈጠራ መንገድ መስራት ከቻሉ ምንም ጥርጥር የለውም ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ በብዙ ነገር ሻል ያለች አገር ማድረግ ይቻላል።
አሁንስ? አይደለም በጣም ትናንሽ አገሮች እኮ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ይመዘናሉ። ምንም እንኳን ሚዛኑም መዛኙም አንድ አካል ቢሆንም። ይሄን ለመቀየር ጠንካራ ሃገር ያስፈልጋል። ያ ጠንካራ ሃገር የአንድን ብሔር ማንነት የሚጨፈልቅ መሆን የለበትም። ቋንቋ የሚያጠፋ መሆን የለበትም። ሰው ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር የሚያደርግ መሆን የለበትም። ለዚያ እኮ ነው በርከት ያሉ ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ ቢሆኑ ምንም ችግር የለውም ለእኛ። ያቀራርበናል እንጂ አይጎዳንም። እዚህ ወጥተን የሌሎች አገሮችን ቋንቋ ለመማር ጥረት የምናደርግ ሰዎች አንዳችን የሌላችን ቋንቋ ብንማር ይበልጥ ያግባባናል ፣ያቀራርበናል እንጂ ጉዳት የለውም። ያን ማድረግ እንችላለን ብልጽግና የሚልበት ዋናው ምክንያት አሳታፊ “ሞር ኢንክሉሲቭ” ስለሆነ ነው።
ከፌዴራል ሥርዓት አንጻር ከሆነ እያነሳህ ያለኸው ሲዳማ የሚባል ክልል እኮ የተመሰረተው በብልጽግና ነው። ጨፍላቂ ቢሆንና ብልጽግና ኢትዮጵያ አንድ ትሁንና ብሔሮች መብታቸው አይከበሩ ቢል የሲዳማ ሕዝብ በራሱ ፍላጎት የወሰነው ውሳኔ አይከበርለትም። ተጨማሪ ቋንቋዎች አይመጡም። ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አይደረግም። ሌላው ቀርቶ አሸባሪው ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ በትግራይ ውስጥ ከአርባ ዓመት በላይ የቆየ ብቸኛ ፓርቲ ነው። ብቻውን ሲያስተዳድር የነበረ ፓርቲ ነው። እሱ ሲፈርስ በቀላሉ ትግራይን የሚያስተዳድር ኃይል መፍጠር አይቻልም።
ብልጽግና ግን የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ላይ ምንም ጥርጣሬ ስላልነበረው ከራሱ ልጆች፣ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተወጣጡ ትግራይን ያስተዳድራሉ እንጂ ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከወላይታ፣ ከጉራጌ አንድም ሰው ትግራይ ክልል ሄዶ እስክናደራጅ እንኳን ለአንድ ሳምንት አስተዳድር የተባለ ግለሰብ የለም። ለምን የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ መከበር አለበት። ጥያቄ የለውም ይሄ። ቋንቋውን መናገር መቻል አለበት ጥያቄ የለውም። ያ ጉዳይ ግን ኢትዮጵያን እያፈረሰ መሆን የለበትም። ለኢትዮጵያ ጋሻ፣ መከታ እየሆነ መሆን አለበት ነው ትርክቱ። ይህ ትርክት ደግሞ ካለምንም ጥርጥር ፍሬ እያፈራ ነው፣ ፍሬው ጎምርቶና አብቦ እናየዋለን፤ በጊዜው የሚታይ ጉዳይ ይሆናልና መሰብሰብ፣ መሰናሰል፣ መደመር፣ በጋራ መቆም ይበልጥ ጠንካራ ያደርገናል እንጂ ደካማ አያደርገንም።
ጥያቄ፡– የትግራይ ክልልን በተመለከተ የማነሳው ጥያቄ የህግ ማስከበር ዘመቻው ሲከናወን የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ለምን ገቡ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ትግራይ ላይ የነበረውን ግጭት ሙሉ አውዱን ማየት ካልተቻለ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን “ኢንሲደንስ” እያነሱ መነጋገር ያስቸግራል። ትግራይ ላይ የነበረው ግጭት የኢትዮጵያ ወታደር ፊቱን ወደ ኤርትራ አዙሮ የኢትዮጵያን ድንበር የሚጠብቅ ኃይል ነበር የነበረው – የሰሜን እዝ የሚባለው። የተመታው ከጀርባው ነው። ከጀርባው ሲመታ ጀርባ መመታት ብቻ ሳይሆን ስታፍ ተበተነ ኃይል በርከት ያለ ቁጥር ያለው በጠላት ኃይል እንዲያዝ ሆኖ እግረኛው ደግሞ ወደ ኤርትራ ወጥቷል፣ ወደዚያ ሸሽቶ ገብቷል። ተደራጅቶ ተጠናክሮ ተመልሶ እንዲመጣ ነው የተደረገው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የኤርትራ መንግስት የእኛ ወታደር የእነርሱን ድንበር አቋርጦ ሲገባ አደጋ ደርሶበት ሲገባ የተቀበሉበት፣ ያበሉበት መልሶም ደግሞ እንደ ምርኮኛ ሳይቆጥሩ እናወጣዋለን ስንል የፈቀዱበት መንገድ ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ነው። የትኛውም ጎረቤት አገር ቢሆን ይህን በቀላሉ አያደርገውም። የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጋር ቆሞ የእኛ ወታደር ጥቃት ሲደርስበት አብሮ የቆመበትን ጊዜ በከፍተኛ አድናቆትና ክብር ነው የምናየው።
ይሄ መቸም ታሪክ የሚሽረው ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን ያን ውለታ ከዋሉ በኋላ ወደትግራይ ግዛት እንዴት ነው እየገቡ የመጡት ለሚለው ጥያቄ ሁለት ነው ምክንያቱ። አንደኛው፡- እነርሱ አንዲት ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ሳይገቡ አሻባሪው ቲ.ፒኤል.ኤፍ ሮኬት እየተኮሰ ጋብዟቸዋል። በተደጋጋሚ ኤርትራ ውስጥ ሮኬት እየተኮሰ ጥቃት ለማድረስ ሞክሯል። በዚህ እነርሱ ራሳችንን መከላከል አለብን የሚል አቋም እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። ያም ሆኖ በመጀመሪያው የመልሶ ማጥቃት ሂደት ውስጥ የኤርትራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልገባም።
የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ ድንበር የገባው የእኛ ኃይል ወደፊት እየገፋ በሄደ ቁጥር አብዛኛው ድንበር ላይ የነበረው ቀጠና ክፍት ሲሆን በሄድንበት አውድ ውስጥ ጠላት የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል መቋቋም እያቃተው እየተመታ እየሸሸ ስለሄደ ተሰብስቦ ወደ ኤርትራ ቢገለበጥ፣ ቢመጣ ሊያጠቃን ይችላል የሚል ስጋት ስለነበራቸው ገባ ብለው በእነርሱ የሚያዋስናቸው አካባቢዎች ላይ ድንበር ይዘዋል። ያ የሆነበት ምክንያት ድንበር አካባቢ ላይ ካስቀመጥነው ወታደር አንስተን በዚያ ወታደር ጥቃት እየፈጸምን ስለሆነ ቋሚ ኃይል ያስቀመጥነው ያለም። ክፍት ሆኖ ጥቃት እንዳይደርስብኝ የሚል መከራከሪያ አቅርቦ ነው የኤርትራ ሰራዊት ወደዚያ የገቡት እኛን ተረከቡን የሚል ነገር ተደጋጋሚ ያነሱ ነበር። በማንኛውም ሰዓት ድንበራችሁን ለመጠበቅ ዝግጁ ነኝ የሚል ቃል ተሰጥቶን ስለነበር በዛ አግባብ ነው እየተሰራ ያለው። የኤርትራ ሀይል ወደ ትግራይ የመጣበት ምክንያት አንድም የሚከላከለው የመከላከያ ኃይል ስፍራውን ለቋል። ሁለተኛ ሮኬት እየተኮሱ …
ጥያቄ፡– ስለዚህ ራሱን ለመከላከል እንጅ የኢትዮጵያን ሰራዊት ለማገዝ አይደለም የገባው እያሉኝ ነው ያሉት ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– የኤርትራ ወታደር ወደ ትግራይ የገባው የራሱን ደህንነት ለመከላከል ነው። የራሱን ደህንነት መከላከሉን እንደ ሃገር ይህንን ቦታ ሸፍናችሁ ያዝሉኝ የሚለውን ነገር በወቅቱ እኛ አልመለስንም። አሁን እየመለስን እንገኛለን። በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄ ጉዳይ መስመር እየያዘ ይሄዳል የሚል ዕምነት አለን። ስምምነት ግን ተደርሷል። ተረክበን ቦታዎችን እየለቀቁ ወደ ግዛታቸው መመለስ የሚል ስምምነት የተግባባንበት ጉዳይ ነው- መፈጸም አለበት። ይህን ተያይዞ የሚመጣው ዋናው ችግር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት የኤርትራ ወታደርም ይሁን የኢትዮጵያ ወታደር ወይም የአሻባሪው የህወሓት ወታደር በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ማንኛውም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በኤርትራ መንግስትም ተቀባይነት የለውም።
ጥያቄ፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል ዕምነት አላችሁ እናንተ? እንደዚህ ዓይነት ሪፖርቶችን ትቀበላላችሁ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን በሚመለከት ውጊያ አትፊ “ዳሜጅንግ” ስለሆነ ብዙ መዘዞችና “ኮንሴኩየንሶች” ጥፋቶች አሉት። ነገር ግን የሰብዓዊ መብት በሚመለከት በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥናት በመከላከያ ጥናት በሚንስትሮች ኮሚቴ ጥናት ግኝቶች “ፋይንዲንጎች” ስላሉ እርሱን ተንተርሰን እርምጃ የወስድንባቸው አሉ። ይሄ ውጭ ከሚደረገው አጠቃላይ ዘመቻውና ግነቱ እርሱ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ አካል ነው። እኛ ግን በነበረው ሂደት ውስጥ ተጓዳኝ የሆነ “ዳሜጅ” ጥፋት ያለባቸውን እየለየን ወታደርም ያጥፋ በህግ እጠየቅን ነው። እዛ አካባቢ ሊፈጠር የሚችል ማንኛውም ወንጀል ነክ ነገር በህግ አግባብ እያስተካከልን ነው። ይሄ ኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን። ማንም ሰው በሕዝባችን ላይ ያልተገባ ጥፋት እንዲያጠፋ አንፈልግም።
ይቀጥላል …
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013