ያየነው መልካም ነገር ይበልጥ ጠንክሮ እንዲቀጥል፣ የታዘብነው ስህተት እንዲታረም በቅኝታችን ስናመላክት በመንገዳችን የገጠመንን ስናስመለክት ቆይተናል። ዛሬ በጋዜጠኛው ቅኝት አምዳችን አይናችን ያስተዋለው ሰሞንኛ ጉዳይ ስንጓዝ እንደ ዘበት ከማለፍ ይህ ጉዳይ ቢነሳ ለመከላከሉ አንድ ጥቆማ ይሰጣል አልንና በዚህ መልኩ ቃኘነው። ክረምቱ በሚያስከትለው ጎርፍ የሚዘጉ መንገዶች ለብልሽት የሚዳረጉ ጎዳናዎች የቅኝታችን ትኩረት ሆነዋል።
የአገሪቱ መዲና የአገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ አሁን ላይ አሮጌ ገፅታዋ በአዲስ እየተቀየረ በተለየ መልክ እየተዋበች ለነዋሪዎችዋም በድጋሚ እየተሰራች መሆኗ ግልፅ ነው። ታዲያ እነዚህ ከተማዋን የማስዋብና በተለይ የእግረኛ መንገዶቿን የማስፋት ስራ ሲከወን እጅግ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነውና ይህን ማንሳት ፈለግን። የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ማሳለጥ እንዲያስችል በትልልቅ በጀት የሚሰሩ መንገዶች ለረጅም ጊዜ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች መካከል ዋንኛዎቹ ከመንገዱ ጋር ተያይዘው የሚሰሩ የክረምት ፍሳሽ መውረጃ ቦዮች ናቸው።
ክረምት በገባ ቁጥር ለመንገድ ጥገናና ለውሃ መውረጃ ቦዮች መልሶ እድሳት ተብሎ እቅድ ሲያዝና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ይታያል። ይህ እቅድ መንገዶቹ ሲሰሩ የውሃና የጎርፍ መውረጃ ቦዮች አስፈላጊነት ታምኖ በትክክል አለመሰራቱ አልያም ደግሞ ቢሰራም መንገዱንና አካባቢው በሚመጥን መልኩ አለመሰራቱን ያመላክታል። በእርግጥ በአሮጌ መንገዶችና በአዳዲስ ሰፈሮች ጥገናና ግንባታ ቢደረግ አያስገርምም፤ ነገር ግን በአዲስ መልክ የተሰሩና ብዙ በጀት ተይዞ የተገነቡ መንገዶች ትንሽ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር መንገዶቹ የውቅያኖስ ያህል ውሃ ቋጥረው ለእግረኛና ለመንገደኛ አስቸጋሪ ሆነው ይታያል።
ነገር ግን በአብዛኛው የከተማዋ ክፍሎች የሚታዩ ሰፋፊ የመኪና እና የእግረኛ መንገዶች በዝናብ ውሃ ሞልተው ሲታዩ መንገዶቹ የአካባቢውን ሁኔታ መሰረት አድረገው ላለመገንባታቸው ትልቅ ማሳያ ነው። የአስፓልት መንገዶቹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው ቢሰሩም ክረምቱን ተከትሎ በሚመጣው ጎርፍና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስብት ይታያል። በየአስፓልት መንገዱ መሀል ላይ ተቦርቡሮና ተሸርሽሮ ለትራፊክ አደጋ መከሰትና ለተሽከርካሪዎች ጉዳት መንስዔ ሲሆን ይታያል።
መንገዶች ሲሰሩ ክረምትን እንዲሻገሩ የታለመላቸው አገልግሎት በትክክል መወጣት እንዲችሉ ከዲዛይኑ ጀምሮ ሊታሰብበት ይገባል። መንገዶቹ የሚበላሹት በሁለት መንገዶች ነው ፤አንደኛውና ዋንኛው የመንገዱን ግንባታ የሚያካሂደው ድርጅት አካባቢውን መሰረት ያደረገ ጥራቱን የጠበቀና ለውኃ መውረጃ ቦዮች ትኩረት ያደረገ ግንባታ አለማድረጉ ሲሆን፣ ሁለተኛው የከተማው ነዋሪ በየመንገዱ ላይ ያላግባብ በህገወጥ መንገድ የሚጥለው ቆሻሻ ለውሃ መውረጃ ቦዮች መዘጋት ዋና ምክንያት በመሆናቸው ነው።
ሁሌም የምመላለስበት አንድ መንገድ አለ። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ፅህፈት ቤት ፊት ለፊት ያለው ዋንኛው ጠባብ አስፓልት መንገድ። ይህ መንገድ ሁሌም ቢያንስ በ3 ወር ልዩነት አስፓልቱ ላይ ከውሃ መውረጃ ቱቦ ያፈተለከ ውሃ ይተኛበታል። በዚህም መንገዱ ቢያንስ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ጥገና ይደረግለታል። የዚህ መንገድ ችግር አካባቢው ላይ ያለው የውሃ መውረጃ ቱቦ በትክክልና አስፈላጊ በሆነ መልኩ እስከመጨረሻው ጥገና ተደርጎለት በትክክል አለመሰራቱ ነው፤ የሚያሳዝነው ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከተው ዋንኛ ባለቤት እዚያው በሩ ላይ መሆኑና ለዚህ መፍትሄ አስቀምጦ አለመስራቱ ነው፤ በየጊዜው ለጥገና የሚወጣው የመንግስት እና የህዝብ ሀብት ለብክነት ሲዳረግ ለመከላክል አለመሞከሩ በእጅጉ ያሳስባል።
ለማሳያነት ይህንን አነሳን እንጂ በየመንደሩ ክረምት ሲገባ የውሃ መውረጃ ቱቦ በትክክል ባለመሰራቱና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ብዙ ወጪ የተደረገባቸው የአስፓልት መንገዶች ብልሽት ሲገጥማቸው ይታያል። በእርግጥ በመንግስት ተሰርተው አገልግሎት እንዲሰጡ ክፍት የሚሆኑ መንገዶችና በትክክል የውሃ መውረጃ ቦይ ተሰርቶላቸው ለአገልግሎት የሚበቁ መንገዶችም በህዝብም በሚገባ ባለመጠበቃቸው የተነሳ ጉዳት ሲደርስባቸው ይስተዋላል።
ዛሬ ላይ በየመንደሩ ለፅዳት ስራ የተቀጠሩና ከተማዋን የሚያስውቡ ሰራተኞች “ቆሻሻ አውጡ” እያሉ ጠዋትና ማታ በየመንደራችን ሲጠይቁ፣ ጆሮ ሳንሰጣቸው አጠራቅመን ጨለምለም ሲል በየቱቦውና የጎርፍ ውሃ መውረጃው በፌስታል፣ በዶንያ፣ በካርቶን፣ወዘተ፣ ጠቅልለን የምንወረውረው ቆሻሻ የክረምት ውሃ እንዳይተላለፍ እያረገ ነው። እኛ የጣልነው ቆሻሻ የውሃ መውረጃውን ዘግቶ ውሃው መውረጃ ሲያጣ ወደ ዋናው አስፓልት መመለሱ አይቀርም፤ በዚህም ተሽከርካሪውና እግረኛው እጅጉን እየተቸገረ ይገኛል።
በብዙ እርዳታና ከሌሎች ልማቶች ተቀንሶ የሚሰሩት ብዙ ወጪን የሚጠይቁት መንገዶችም የታሰበውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጡ ወዲያው ይጎዳሉ፤ ይበላሻሉም። ሌላ መንገድ ለማስራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ሊውል የሚገባው በጀት በድጋሚ ለዚሁ መንገድ ጥገና ይውልና አገሪቱን ለብክነት ይዳርጋል።
ለዚህ እንደ ህዝብ ሀላፊነትን በትክክል መወጣት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። መንገዶች በትክክል የታለመላቸውን አገልግሎት ለረጅም ጊዜ እንዲሰጡ ከብልሽት መጠበቅ ይኖርብናል። በመንገድ ግንባታ ወቅትም በየመንደሩ የሚታዩት የውኃ መውረጃ ቦዮች በትክክል የታለመላቸውን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ታስበው መሰራት ይገባቸዋል። ይህም የመንገድ ስራ አሰሪው ተቋምና በዚህ ስራ ላይ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ተቋማት አገራዊ ጠቀሜታ በሚያስጠብቅ መልኩ መሰራቱን መከታተልና የሚሰሩት መንገዶች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ለአገልግሎትም በሁሉም ወቅት አመቺ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።
ሌላኛው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳውና በመንገዶች ብልሽት ላይ ትልቅ እንቅፋት የሚፈጥረው የተቀናጀ መሰረተ ልማት በትክክል አለመተግበሩ ነው። የመንገድ አስፈላጊነት ሲታሰብ በዚያ አካባቢ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልምቶች /የስልክ፣ የመብራት፣ የውሃ / አገልግሎት ዝርጋታዎች ካልታሰበ ሌሎችም ከመንገድ ልማቱ ጋር አብረው ተቀናጅተው ካልተሰሩ አንዱ ያነፀው በሌላው መፍረሱና መልሶ ጉድጓድ መሆኑ፣ ሌላው ያደሰው ባንዱ ማርጀቱ አይቀሬ ነው።
አሁን ላይ በየመንገዶቹ ጥጋጥግ የሚታዩት የውኃ መውረጃ ቦዮች መዘጋት ነገ ክረምቱ ጠንከርከር ሲልና ዝናቡ ሲበረታ የዋንኞቹ መንገዶች ፀር መሆናቸው አይቀርምና በየአካባቢው የሚመለከተው አካል ነገ ትልቅ ወጪ ሊያስከትል የሚችል የዛሬ ቸልታውን አቁሞ መንገዶቹን ለፍሳሽ ውሃም ለተገልጋይም ምቹ መውረጃና መተላለፊያ ይሆኑ ዘንድ ማሰናዳት ይጠበቅበታል። እንደ ማህበረሰብም በየአካባቢያችን ያሉ የጋራ መንገዶችን ከብልሽት መጠበቅ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው። አበቃሁ ፤ቸር ይግጠመን!
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013