ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንዶ ገነትን ሲጎበኟት ‹‹ወንዶ›› ትባል እንደነበረና ለምለምነቷን አይተው ‹‹ምን ወንዶ ብቻ ገነትም ነው እንጅ›› ማለታቸውን ተከትሎ ወንዶ ገነት መጠሪያዋ መሆኑና ስሟም በዚሁ ፀንቶ እስካሁን እየተጠራችበት ትገኛለች። አያሌ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መዳረሻ የሆነው ዋቢሸበሌ መዝናኛ ሆቴል፣ የተፈጥሮ ፍል ውሃ እና ማራኪ የመልከዓ ምድር አቀማመጧ በብዙዎች እንድትጎበኝና እንድትመረጥ አድርጓታል።
ከወንዶ ገነት ከተማ መስተዳድር ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት በተገኘው መረጃ መሠረት፤ ወንዶ ገነት 12 ብሄርሰቦች ይኖሩባታል። በ1970ዎቹ የተካሄደውን የወንዶገነት የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ አካባቢውን ለም አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሃብት በራሱ ምድሪቱን ገነት ለሰዎች ደግሞ ለመኖር የሥበት ማዕከል ሆና እንድታገለግል አድርጓታል። በወንዶ ገነት ከዓመታት በፊት በተደረገ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 50ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች እንዷላት ቢነገርም ከንግድ እንቅስቃሴዋ፣ የዙሪያዋ ገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ መካለልና ከገጠር ወደ ከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ፍልሰት በመኖሩ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ በእጥፍ ሳይጨምር አይቀርም የሚሉ ግምቶች አሉ። የዛሬው ፅሁፋችን የሚያተኩረው በወንዶ ገነት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ አይደለም። እንደመነሻ ይሆነን ዘንድ በጨረፍታ ወንዶ ገነትን ነካካን እንጂ የዛሬ ትኩረታችን በአካበቢው ያላቸው ፍልስፍና ካላቸውና ጠንካራ አርሶ አደር ከሚባሉ ወንዶ ገነት አጠገብ ከምትገኘው ወንዶ ገነት ባሻ ቀበሌ ተገኝተን ከአርሶ አደር ባጂኦ ኦላቶ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ልናካፍላችሁ ነው ።
የአርሶ አደሩ ፍልስፍና
አርሶ አደሩ ለትምህርት ከሚሰጡት ዋጋ አንጻር ‹‹እንኳንስ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ይቅርና በትምህርት ቤት ደጃፍ ያለፈም ክብር አለው›› የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ስለትምህርት ጥቅም ሲያወሩ ዓለምን የቀየረው ትምህርት ነው ከሚል ተነስተው ነው ። ትምህርት ሀገርን ያሳድጋል፤ ኢትዮጵያም የምታድገው በተማሩ ሰዎች ነው ሲሉ ይናገራሉ። ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ደግሞ የተለየ ነው። መከበር በሀገር ነው ሌላ ሀገር የለንም። ኢትዮጵያ ማለት ህይወት ናት፤ ማን በሕይወቱ ይቀልዳል ሲሉ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹት በአደባባይ ጭምር ነው። ‹‹የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ህልውና የሚወስኑ ናቸው። በመገናኛ ብዙኃን በኩል እና በሌሎች ሀላፊዎች በሚደርሰን መረጃ አሁን ህዳሴ ግድቡ ሊጠናቀቅ ደርሷል። ለዚህ እስከ ፍፀሜው ከመንግስት ጎን እንቆማለን ፤እኛ ባንኖር ልጆቻችን አሉ ›› ይላሉ።
አርሶ አደር ባጂኦ ኦላቶ በመመካከር ያምናሉ፤ ይመክራሉ፤ ምክር ይቀበላሉ። ባህላዊ የችግር መፍቻ መንገዶች ውጤታማ ናቸው የሚል ጽኑ አቋም አላቸው። ከቤት ውስጥ ጀምሮ መመካከር መነጋገርና መደማመጥ መኖር አለባት ሲሉ ይናገራሉ፤ እሳቸውም ይሄንኑ ሀሳብ በተለይም ደግሞ ከትዳር አጋራቸው ጋር ስለቤታቸው፤ ልጆቻቸውና ንብረታቸው በሰከነ መንፈስ እንደሚወያዩ ይናገራሉ። የሚያደርጉትንና ለማድረግ ያሰቡትንም በጋራ ሃሳብ አዋጥተው በጋራ የመወሰን ልምድ እንዳላቸው ነው የገለጹት።
በገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ያላቸውን ልምድ ሲገልጹም‹‹ በአሁኑ ወቅት በኦሞ ፋይናንስ የብድርና ቁጠባ ተቋም አባል ነኝ። በሌሎች የንግድ ባንኮችም ከዕለት ጉርስ የተረፈ ተቀማጭ ገንዘብ አለኝ። ለረጅም ዓመታት ገንዘብ በጨርቅ ቋጥረን ከቤታችን እናስቀምጥ ነበር፤ ዛሬ ግን ባንክ በወረዳችን ቁጠባ ተቋም ከአጠገባችን ስለተከፈተ አንድም ብር ብትሆን አነሰ በዛ ሳንል በባንክና በቁጠባ ተቋም ለማስቀመጥ በቅተናል ›› ይላሉ። መመካከር መልካም ነገር ነው የሚሉት እኚህ አባት፤ ቤት ንብረታቸው ሕይወት ትዳራቸው እየተቃና የመጣው በጋራ በመወሰናቸውና በመስራታቸው ብሎም በሰከነ መንፈስ በመነጋገራቸው መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህ የመመካከር ባህላቸው ቤታቸውና ንብረታቸውን በወጉ ለማስተዳደር ጠቅሟቸዋል። ከትንሿ ሳንቲም እስከ ትልቅ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ፣ የኑሯቸውን ፊትና ኋላ ለመወሰን በጋራ መመካከሩ በጣም ጠቅሟቸዋል። ከቅርብ ዘመድ፣ ከሩቅ ባዕድ ጋርም እንደምን መኖር እንዳለባቸው ጥሩ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።እንዲያው መመካከር የሕይወታቸውና የትዳራቸው ሁሉ መሰረት ሆኖ ሌሎችም ነገሮችን በመመካከር እንዲመሩት ይመክራሉ።
አርሶ አደሩ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት ወረድ ብሎ ህብረተሰቡን ምን ላግዛችሁ እያለ ይጠይቃል። ጥንት የነበረው መንግስታት በመልክተኞቻቸው እና በተወካዮቻቸው ብቻ ያገኙን ነበር። ግን አሁን እየሆነ ያለው ለዘመናት ስንመኘው የነበረው ነውና ፈጣሪ ምስጋና ይግባው ይላሉ።
አሁን በሰፈራችን በርካታ መሰረት ልማቶች እየተሟሉ ነው። ከወንዝ ውሃ ተላቀን ቧንቧ ውሃ በሰፈራችን ደርሷል። ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች በየመንደሩ እየተበራከቱ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ጥሪጊያ መንገዶች በመሰራታቸው አምቡላንሶች አርሶ አደር መኖሪያ ድረስ ወርደው ወላዶችን ወደ ጤና ጣቢያ እታመጡ በሰላም እየተገላገሉና ጤናማ ልጅ እየታቀፉ ነው። አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብም መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮለታል። ትምህርት ቤቶችም በቅርበት በመከፈታቸው ልጆችን በወቅቱ ወደ ትምህርት ገበታ መላክ ችለናል ይላሉ። አሁን ምን ጎደላችሁ ብሎወደ እኛ የሚመጣ ችግራችን የሚገነዘብ ጠያቂ መንግስት አግኝተናል ሲሉ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ።
አኗኗሬን ወደድኩት
አርሶ አደሩ አኗኗራቸው በየጊዜው ለውጥ እንዳለው ይናገራሉ። ቀደም ሲል በጓዳቸውና በማሳቸው የሚያበቅሉትን ቡና ጥሩ ገበያ ስለማያገኙለት እንደ ነገሩ ጣል ያደርጉት ነበር። በተለይ ደግሞ በችግራቸው ጊዜ ተገቢውን ገበያ አያገኙም በፈለጉት ወቅም በጥሩ ገበያ አይሸጡትም። ቢሸጡም አስደሳች ገቢና ገበያ አልነበረም። አሁን ግን ከላይ እስከ ታች ብዙዎች የሚሳተፉበት የገበያ ሠንሰለት በመፈጠሩ ቡናቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መልካም የአኗኗር ዘይቤን እየተከተሉ ስለመሆኑም ይናገራሉ። ከቡና በተጨማሪም በሰፊው እንሰት እንደሚተክሉና ዓመቱን ሙሉ በቂ ቀለብ እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ከእነዚህም ሌላ ለቤታቸው የሚሆኑ አዝዕርቶችን ይዘራሉ፤ ይህንንም ዓመቱን ሙሉ ይመገባሉ የተረፋቸውን በቅርበት ለሚገኝ ገበያ ያቀርባሉ።
በአሁኑ ወቅት የሚመለከቱት ገበያ እና የገበያ ሥርዓት ዘመናትን ሲናፍቁት ነበር። ምርት አምርተው ተቀባይ ያጣሉ። አሊያም ደግሞ በሚፈልጉት ሰዓት ምርታቸውን የሚቀበላቸው ነጋዴ አያገኙም። ረጅም ርቀት ተጉዘው ለመገበያየትም ይገደዱ ነበር። በአሁን ዘመን ያለኝን አኗኗሬን ወደድኩት የሚሉት እኚህ አባት፤ ለዘመናት ጎስቋላ የነበረው ቤታቸው እየተቃና ደስታቸውም እየጨመረ ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ እኔ ነኝ ብለው ራሳቸውን በምሳሌት ያነሳሉ። ለዚህም ውጤት ደግሞ የራሳቸውን ጥረት መሆኑን በመጠቆም።
የጎደለን ነገር ማስተካከል
ብዙ ነገሮች በየዓመቱ መሻሻሎችን እያመጡ ነው ይላሉ የለምለሚቷ መንደር አርሶ አደር። ግን ደግሞ በዚያው ልክ መስተካከል ያለባቸው አያሌ ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። በማሳቸው ላይ በስፋት እንሰት ተክለው ዓመታትን ተከታትለውና ተንከባክበው ወደ ፍሬው ሲቃረቡ የእፅዋት ተባይ እያስቸገራቸው ነው። በተመሳሳይ መንገድ ቡና ላይ መሰል ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ችግር የአንድ ወቅት ብቻ ተከስቶ የሚያልፍ ሳይሆን በየዓመቱ እየተመላለሰ ስጋት ውስጥ እያስገባቸው ነው። ለዚህ መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድና ፍጥነት እንደ አርሶ አደሩ ፍላጎት እንዳልሆነና መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ይጠይቃሉ። በየጊዜው ለሚከሰቱ አዳዲስ በሽታዎችም በቂ ምርምር በማድረግ ምርታቸው ሳይጎዳ መፍትሄ እንዲበጅ ይሻሉ።
ከዚህ በተረፈ ደግሞ በቂ ምርት አምርተው አልፎ አልፎ የገበያው ጤናማ አለመሆን ለጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። በተለይም የቡና ፍሬ አፍርቶ ምርት በብዛት በሚመረትበት ወቅት ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው። በጥቂት ወራት ልዩነት ደግሞ ገበያው በሁለት እና ሦስት እጥፍ እያሻቀበ አርሶ አደሩን የበይ ተመልካች እያደረገው መሆኑን ይናገራሉ። ምንም እንኳን እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ዩኒዮኖች፣ ማህበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች ቢፈጠሩም የአርሶ አደሩን ችግር በተፈለገው መጠን ማቃለል አለመቻላቸውን ይጠቁማሉ። ይህን ችግር መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡትና አርሶአደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ እንዲመቻች ፍላጎታቸው ነው።
ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪም ቡና ለቀማ የሚካሄደው በተለምደው በእጅ በመሆኑ ብዙ ምርት እንደሚባክን ይናገራሉ። ለዚህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ሥራ የሚያቀሉ መንገዶች ቢኖር ምኞታቸው ነው። እነዚህ ጉዳዮች መስመር ከያዙ ትልቅ ተስፋ፣ ብዙ ምርታማነት ብዙ ተጠቃሚነት አለ ብለው ያምናሉ።
አቶ ባጂኦ ኦላቶ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በወሰዱት የምርጫ ካርዳቸው ይበጀኛል ያሉት ፓርቲ መርጠዋል። ፓርቲ እንዲያሸንፍ ምኞታቸው ነው ካልሆነም ለኢትዮጵያ የሚበጀው ህዝብ ይወሰናል ይላሉ። ነገር ግን ምንም ይሁን ምንም ምርጫ ያሸነፈው አካል ሠላምን እንዲያሰፍን ቀዳሚ ፀሎታቸው ነው።፡ ከምንም በላይ ደግሞ አርሶ አደሩ በሚፈልገው ጊዜ አቤት የሚል መንግስት ይፈልጋሉ። በወቅቱ ግብዓት የሚያቀርብላቸው አካል አብዝተው ይሻሉ። ምርታቸውን የሚረከባቸው ደንበኛ ነጋዴ፣ ጥሩ ገበያ የሚመቻችላቸው መንግስታዊ አካል ለቤተሰባቸው ሕይወት ለኑሯቸው መሰረት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
በመጨረሻም አንድ መልዕክት ማስተላለፍ ይልጋሉ። አሁን ባለንበት ወቅት የምርጫ ወቅት ነው። ሰላማዊ እንዲሆን አበክርን መሥራት አለብን። ምርጫ ዛሬም ነገም ያለ እና በቀጣይም የሚመጣ ሰው ሰራሽ ሂደት ነው። ነገሮች አመጣጣቸውንና አካሄዳቸውን ሠላማዊ ለማድረግም ወሳኞች ህዝብ ነው። በመሆኑም የተሻሉ መልካም ነገሮችን ለማድረግ ሰላም ይቀድማልና ስለሰላም አብዝተው አንደሚጸልዩ ይጠቅሳሉ። ሌሎችም ስለሰላም እንዲሰሩ ይማፀናሉ።
አርሶ አደሩ ሳይማሩ የተማሩ የሚባሉ አይነት ብልህ፣ በስራ ጎበዝ ደግሞም የአካበቢያቸው የተጣላ አስታራቂ ሽማግሌ ናቸው። ሀገር የሚያምረው በሰው ነው ሰው መዋደድ መከባበር አለበት ብለው ያስባሉ። መከባበር መደማመጥ ሲኖር የሚያለያዩ ነገሮችን በማራቅ የሚያቀራርቡ ነገሮች ላይ በማተኮር ሁሉም ሊሰራ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። ከመንግስት ጋር መተባበር አካበቢን ሰላም መጠበቅ ልማትን ማሳደግ የእያንዳንዱን ዜጋ የሚቀይር በመሆኑ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013