ከ20 ዓመት በፊት ‹‹ሪሚታንስ›› ማለትም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለሀገር የሚልኩት የውጭ ሀገር ገንዘብ በግልም ይሁን በማህበር እንዲሁም በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው እንዳልነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በግለሰብ ደረጃ በሐዋላ መልክ የሚላከው ገንዘብም ምን ያህል መጠን እንዳለው አይታወቅም ነበር።
ነገር ግን ከተለያዩ ሀገራት በተለይም ወደ ታዳጊ ሀገራት የሚላከው የገንዘብ መጠን ሀገራቱ ከለጋሽ ሀገራት ከሚያገኙት ይፋዊ የልማት ዕርዳታ ገንዘብ በሶስት ዕጥፍ፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሚገኘው ደግሞ በእጥፍ የሚበልጥ ነው። ለአብነትም በ2020 የፈረንጆች ዓመት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት 540 ቢሊዮን ዶላር ከሐዋላ ማግኘት ተችሏል። ይህም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ እያደረሰ ባለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከ2019 በስምንት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።
በርካታ ዜጎች ለሥራ፣ ለኑሮና ለትምህርት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተሰደዱባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። በተለያየ አጋጣሚ በዓለም ሀገራት ተሰራጭተው የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሀገር ቤት ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ኑሮ መደጎሚያ፣ ለቤትና ለሌሎች ቋሚ ንብረቶች ግንባታ በተወሰነ ደረጃም ለኢንቨስትመንት የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ይልካሉ። ታድያ ካለው እምቅ ሀብት አንጻር በሐዋላና በኢንቨስትመንት መልክ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በተመቻቸ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው ገንዘብ እንዲልኩና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሳደግ እንዲቻል እየሰራቸው ያሉ ሥራዎች ዓለም አቀፍ የቤተሰብ የሐዋላ ቀንን ባከበረበት ወቅት ተገልጿል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላለፉት በርካታ ዓመታት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥረት ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ሐዋላ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ሊቁ፤ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው የውጭ ሀገር ገንዘብ ገቢ በአብዛኛው የሚሰበሰበው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ አስታውሰዋል። በዚህም በተያዘው 2013 በጀት ዓመት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖ ባለበት እስከ ግንቦት 30 በነበረው 11 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በባንኩ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል።
ባንኩ ሐዋላን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ምንጮችን ለማሳደግ ያለውን እምቅ ሀብት አንጠፍጥፎ ለመጠቀም በርካታ ጥረቶችን ያደርጋል። በተለይም የሐዋላ ገቢን ለማሳደግ ህጋዊ የሆነውን የባንክ አሰራር መከተል እጅግ ወሳኝ ቢሆንም በሀገሪቱ የጥቁር ገበያ መስፋፋት ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እንቅፋት ሆኗል። ለዓለም ኢኮኖሚ ተግዳሮት እየሆነ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም እንዲሁ ባለፉት ሁለት ዓመታት የረሚታንስ ወይም የሐዋላ ገቢ እንዲቀንስ የጎላ ድርሻ ነበረው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ በበኩላቸው በመላው ዓለም ተሰራጭተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህ ዜጎች በየጊዜው ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩት ሐዋላ ኤክስፖርት ከሚደረገው ገንዘብ የበለጠ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በመላው ዓለም በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዜጎች ገንዘብ ሲልኩ በሀዋላ የሚልኩበትን መንገድ በማመቻቸት ከተለያዩ የሀዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። ለዚህም በሀገሪቱ የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ምስክሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመላው ሀገሪቱ ተውጣጥተው ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተጓዙ በርካታ ዜጎች ገንዘብ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲልኩ በቅርበት ተገኝቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ባንክ ነው። በመላው ሀገሪቱ ከ1667 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእያንዳንዱ ቅርንጫፎቹ ሐዋላ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበትና እያንዳንዷ ዶላር ለሀገር ብልጽግና እና ዕድገት እንዲውል የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
በውጭ ሀገር ባሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ልማት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ ያለውን ሐዋላ በመጠቀም ገንዘብ እንዲልኩ ህብረተሰቡን ማንቃት ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የደንበኞቹን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከማርካት አንጻር የረሚታንስ ዕድሎችን ማስፋት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ባንኩ በስትራቴጂው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ዋና ጉዳይ አድርጎ በመያዝ ለተግባራዊነቱ እየተጋ ይገኛል።
በተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች ትግበራ በሐዋላ መልክ በዓለም ላይ ላሉ ደሃ ሀገራት የሚላከው ገንዘብ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከ2015 እስከ 2030 ባለው የዘላቂ ግቦች ትግበራ አንድ ቢሊዮን ሰዎች በላኪነትና በተቀባይነት የሚሳተፉ ሲሆን፤ በዚህም ስምንት ነጥብ አምስት ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ታዳጊ ሀገራት እንደሚላክ ይጠበቃል።
በስደትና በተለያየ ምክንያት ከእናት ሀገራቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ተለይተው በየሀገሩ የሚማስኑ ሰዎች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ሀገራቸውን ለመጥቀም ገንዘብ በመላክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ከሁለት መቶ ሚሊዮን የሚልቁና በተለያዩ ሀገራት ተሰራጭተው የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ለመዘከር እንዲሁም ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ማዳበር እንዲችል በማሰብ በየዓመቱ እኤአ ጁን 16 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ ሰኔ ዘጠኝ ቀን ዓለም አቀፍ የሪሚታንስ ወይም የሐዋላ ቀን ተብሎ እንዲከበር ወስኗል። ድርጅቱ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረትም እኤአ ከ2015 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር ቆይቷል። በኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ በንግድ ባንክ አማካኝነት ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተከብሮ ውሏል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013