
ይናገር ቢሆን እሱ ራሱ ብዙ በተናገረ ጥሩ ነበር፤ አደባባዩ።ስላለፈው ማለቴ ነው ፤ የአሁኑንማ ራሱም አሳምሮ ይናገራል። እንዲናገር ተደርጎ ነው የተገነባው። ለማናቸውም እኔ ትንሽ ልበልለት ። መንግሥታት ህዝባቸውን ሰብስበው ክተት ጠርተውበታል፤ ድላቸውን ከህዝቡ ጋር ሆነው ተቋድሰውበታል፤ ድጋፍ ሰብስበውበታል። በአንጻሩ ህዝቡም ለመንግሥታቱ ድጋፍ አርጓል፤ ጫንቃውን ቢያጎብጡበት ደግሞ ወዲያ ብሎ ተቃውሞ ወጥቶበታል።በዚሁ አደባባይ። መስቀል አደባባይ።
በዓላት በአይነት በአይነት ተስተናግደውበታል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል ደመራን በዓል በየዓመቱ በድምቀት አክብራበታለች። በደመራ በዓል ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ዜማዎችንና ትርኢቶችን በማሳየት በልብሰ ተክህኖአቸው አሸብርቀው በተንጣለለው አደባባይ ሞልተው ብዙ ትውስታዎችን ጥለውበታል። ምእመናን ጧፍ እያበሩ ፣ ርችት እየተተኮሰ ፣ ደመራ እየተቀጣጠለ ያልታየ ተአምር የለም። ቱሪስቶችም አፋቸውን ከፍተው በአድናቆት ተመልክተውበታል፤በየካሜራቸው ትውስታዎችን ይዘውበታል።
ኢትዮጵያውያን ነቅለው በመውጣት የኦሎምፒክ ጀግኖቻችን በመቀበል ፈንድቀውበታል። ብሄር ብሄረሰቦች በባህላዊ አልባሶቻቸው ፣ በዜማና ውዝዋዜያቸው ታይተውበታል። ወታደራዊ ትርኢቶች ተስተናግደውበታል።
እንደ ታላቁ ሩጫና የመሳሰሉት ስፖርታዊ ውድድሮች ፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ወዘተ ተደርገውበታል። በግልም ይሁን በቡድን የአካል አንቅስቃሴ ተደርጎበታል። ይህቺን ዓለም የተሰናበቱ ጀግኖች መንግሥታዊ ስንብት የተደረገበትም ነው፤ መስቀል አደባባይ።
ደርግ የአደባባዩን ስያሜ አብዮት አደባባይ በሚል ቀይሮ ለ17 ዓመታት ድጋፉን ተቃውሞውን፣ ድሉን አሰምቶበታል፤ ኮሎኔል
መንግስቱ የቀይሽብር ይፋፋምን አስፈላጊነት በዚህ አደባባይ ህዝብ በተሰበሰበት በጠርሙስ ደም ይሁን ቀይ ቀለም በማድረግ ከክቡር ትሪቪውኑ ቁልቁል በመወርወር የገለጹበት እዚሁ አደባባይ ላይ ነበር። መለስ ዜናዊ በ1997 ምርጫ ኢህአዴግን በመደገፍ ወጥቷል ብለው የተመለከቱትን አደባባዩን የሞላውን ህዝብ ማእበል ሲሉ የገለጹትም ነበር። ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ድጋፍ የወጣውና ሱናሚ በሚል የተጠራው ሰልፍም የተስናገደው በዚሁ አደባባይ ነው። አንድ ነገር ላስታውስ ። በዚህ የምርጫ ወቅት ኢህአዴግ በዚህ ሰልፍ ወቅት መብራት በማጥፋት መሪዎቹና ደጋፊዎቹ እንዳይገናኙ ማድረጉን አስታውሳለሁ።
በሰላማዊ ሰልፍ ወቅት በተቀሰቀሱ ሁከቶች ዜጎች የሞቱበት እና የተጎዱበትም ስፍራ ነው። በ1966ቱ አብዮት አንድ ወቅት ላይ የሰራተኛ ቀንን ለማክበር በተወጣ ሰልፍ በተነሳ አለመግባባት በርካታ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ለጉዳት ተዳርገውበታል። የምርጫ 97 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ቁጣ የደመራ በዓልን ሊያከብሩ የወጡ ነዋሪዎች በድንጋይ የተደበደቡበትና ፖሊስም ሁከቱን ለመቆጣጠር ሲል ሰልፈኞችን ያጎሳቀለበት አደባባይም ነው።
በ2010ዓ.ም ለመጣው ሀገራዊ ለውጥና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ህዝቡ ያለውን ድጋፍ ወጥቶ የገለጸውም በዚሁ አደባባይ ነበር። በዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በተደረገ የግድያ ሙከራ የሰው ህይወት የጠፋው ፤ የአካል ጉዳት የደረሰውም በዚሁ አዳባባይ ነበር። አደባባዩ ትእይንተ ብዙ ነው ፤ ተዘርዝሮ አያልቅም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዚህን ታላቅ አደባባይ ፋይዳ በሚገባ ተገንዝቧል፤ በቀጣይም ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ እንዲሁ። አደባባዩን እንደገና በመገንባት አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ ይበልጥ ሊጠቅም በሚችል መልኩ ውብ አድርጎ መልሶ ገንብቶታል፤ ታላቅ ተግባር ሊባል ይገባል።
ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ አድርጎም ነው አዳዲስ አገልግሎቶችን ጭምር እንዲሰጥ አድርጎ የገነባው። ይህ አደባባይ ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በተገኙበት ነው የተመረቀው።
ይህ በ55 ሺ ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ የሚገኝ አደባባይ እድሳት አይደለም ግንባታ ነው የተደረገለት። ካሬ ሜትሩ ያው ቢሆንም አደባባዩ እንዲሰፋ ተደርጓል። ጥልቀት እንዲኖረው ተደርጓል። በሆድ እቃው ባለሁለት ወለል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ተገንብቶለታል። ከአንድ ሺ አራት መቶ በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚያስችል ነው። ሁሉንም ዋጥ አድርጎ አላየሁም እንዲል ተደርጎ ነው የተገነባው። ከዚህ በኋላ መስቀል አደባባይ የምትሄዱ ባለመኪናዎች መኪና የት አቆማለሁ ብላችሁ አታስቡ።
ግንባታው በሚያስገርም ፍጥነት ነው የተካሄደው። በዘጠኝ ወራት ይህን ያህል ፕሮጀክት ማጠናቀቅ ትርጉሙ ብዙ ነው። የፕሮጀክት መጓተት ትልቅ ፈተና በሆነባት ሀገራችን ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት በዚህ አጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ትምህርት ይሆናል። 24 ሰዓት ግንባታው ይካሄድ ነበር።
አደባባዩ መንገዶቹን ጨምሮ ከ500 ሺ በላይ ህዝብ አይዝም ነበር አሉ። አሁን ግን አንድ ሚሊዮን ህዝብ እንዲይዝ ተደርጎ ከውብ መቀመጫዎችና አረንጓዴ ስፍራ ጋር ተገንብቶለታል። ለህዝባዊ ስብሰባም ለግል ጉዳይም ዘና ብለው ተቀምጠው ያሰቡትን ማድረግ የሚያስችል ስፍራ ተደርጓል።
ስድስት ግዙፍ ስክሪኖች የቆሙለት ሲሆን፣ በዚህም ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎች እንዲሁም ዘና የሚያደርጉ ፕሮግራሞች ሊተላለፉበት ስለሚችሉ የአደባባዩ ተገልጋዮች መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትና የሚዝናኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ቀድሞ በነበረው አንድ ግዙፍ ስክሪን የውጭ ኳስ ለመመልከት ምን ያህል ሰው ይሰብሰብ እንደነበር ይታወሳል።
አደባባዩ በምሽት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ተገንብቷል። ግዙፍ መብራቶች ተገጥመውለታል። ጤፍ የሚያስለቅሙ የሚባሉ አይነቶች። በየመቀመጫዎቹና ደረጃዎቹ ስርም ልዩ ልዩ ባለቀለም መብራቶች ተገጥመውለታል። አደባባዩን ለማዘመንና ሰፊ አገልግሎት እንዲሰጥ በሚል ብዙ ብዙ ተሰርቷል፤ እኔ ጥቂቱን ነው የጠቀስኩት፡፤ እኔ ባጎደልኩ … ይሙላ እንደሚሉት .. ይሁን ።
በአደባባዩ አካባቢ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንድ ሶስተኛው በቀን የሚተላለፍበት መሆኑ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ተገልጿል።ምን ያህል ወሳኝ አደባባይ እንደሆነ ያዙልኝ። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከመስቀል አደባባይ የሚቀር የለም ማለት ነው። አዲስ አበቤ በተሽከርካሪ ሲያልፍ፣ በእግሩ ሲያቋርጥ፣ ለተለያዩ ጉዳዮች ሲል ከመስቀል አደባባይ አይቀርም።
በዚህ ላይ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በአላት፣ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ አቀባበሎችና ሀገራቸውን ያገለገሉ የጀግኖች ሽኝቶች .ወዘተ ሲታከሉበት አዲስ አበቤዎች ከመስቀል አደባባይ እንደማይቀሩ ማሰብ ይቻላል።
አሁን ደግሞ ከዚህም በላይ አዲስ አበቤዎችንና ሌሎች እንግዶችንም እንዲስብ ተደርጎ ተገንብቷል። የእስከ አሁኖቹ አገልግሎቶች መቀጠላቸው እንዳለ ሆኖ ፣እነዚህን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ምቹ በሆነ መልኩ ማካሄድ የሚያስችል ግንባታ የተካሄደ መሆኑ መስቀል አደባባይን የሚረግጡት ቁጥር ብዛት በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ይጠበቃል።
የመኪና ማቆሚያው በርካታ ሰዎች አካባቢውን እንዲረግጡ ያደርጋል። ከአንድ ሺ አራት መቶ በላይ መኪና ሲያቆም እያንዳንዱ መኪና ሶስት ሰው እንኳ ቢይዝ ከ4ሺ ሁለት መቶ በላይ ሰዎች በአካባቢው እንዲገኙ ያደርጋል። በዚህ ላይ የመኪና ማቆሚያውን የሚያስተዳድሩ በርካታ ሰዎችም አሉ።
የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ጭምር ተደርጎ የተገነባ እንደመሆኑ ሱቆቹ በርካታ ሰዎች ሊስተናገዱባቸው የሚችሉ ናቸው። መጸዳጃ ቤቶችና መታጠቢያ ቤቶች ጭምር ተሟልተውለት ወደ ሥራ ከገባው ከዚህ ግዙፍ አደባባይ በላይ በቀጣይ ለመገናኘት የሚመች ስፍራ የለም። አንድ ሶስተኛው አዲስ አበቤ የሚተላለፍበት እኮ ነው። እናም መስቀል አደባባይ እንገናኝ!
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013