በአስተሳሰብና ማህበራዊ ለውጥ ላይ በስፋት የሚሰሩ ናቸው። አሁን ደግሞ ሰዎች በራሳቸው፣ በቤተሰባቸው፣ በተቋማቸው ይሁን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለምን ብለው እንዲጠይቁ እና መልካም ለውጥ እንዲያመጡ ለማበረታታት የሚያስችል “ለምን ኢትዮጵያ” የሚል እንቅስቃሴን መስርተው እየሰሩ ይገኛሉ።
“ለምን ባይነት” ዳር ቆሞ ሌላውን መጠየቅ ሳይሆን ለመፍትሄው አስተዋጽኦ ማድረግን ያስቀድማልና ሰዎች ይህንን እንዲያደርጉ በማሰብም ራሳቸውን በማካተት እንዲሰሩ ለማድረግም እየተጉ ናቸው። ከዚህ አኳያ የእንቅስቃሴው መስራች አቶ አዱኛ ሂርጳን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እና የ”ለምን ኢትዮጵያ” እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ሲል አዲስ ዘመን ጠይቆ እንደሚከተለው አጠናቅረናል። መልካም ንባብ ተመኘን።
አዲስ ዘመን፡– ለምን ኢትዮጵያ ለምን ተመሰረተ?
አቶ አዱኛ፡– “ለምን ኢትዮጵያ” ሰዎች ለምን ብለው ጠይቀው በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቁ እንዲሁም ደግሞ ለተግባራዊነቱ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ለማነቃቃትና ለማነሳሳት ነው የተቋቋመው። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለምን ማለት ብዙም አይደገፍም። ለምን የሚሉ ጥቂቶች ቢኖሩም ዳር ቆሞ ለመተቸት እንጂ ለመፍትሄው መስራት ብዙም አይታይም ። ነገር ግን አገራችን ብዙ ለምን ተብሎ ሊጠየቁ የሚገቡ ነገሮች ያሉባት፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅና በተግባር የሚለውጣት ዜጋ ያስፈልጋታል።
ስለዚህ “ለምን ኢትዮጵያ” ትክክለኛውን መንገድ በተከተለ መልኩ ጠያቂ ትውልድ መፍጠር እና ማስነሳትን ዓላማው አድርጎ ይሰራል። ለዚህ ደግሞ ብዙ አይነት የአድቮኬሲ ወይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ያከናውናል። ከእነዚህ መካከል በማህበራዊ ሚዲያ እና በድርጅቱ ድረ ገፅ ላይ ሰዎች ለምን ብለው እንዲጠይቁ የሚበረታቱ ኪነጥበባዊ ይዘት ያላቸውን የተለያዩ የካርቶን ስዕሎች፣ ጦማሮችን በመለጠፍ ይሰራል።
ከዚህ በተጨማሪም የአስተሳሰብ መዋቅራችን እንዲለወጥ እና የመፍትሄ አካል እንድንሆን የሚሞግት የ “ለምን” አሻራ የተባለውን የልብወለድ መጽሐፍ ለአንባብያን አቅርበናል። ለሀገር እድገት እና አንድነት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ማፍለቂያ፣ የሃሳብ መገበያያና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረጊያ የውይይት፣ የክርክር እና የግንዛቤ ማስጨባጫ “የለምን ወግ” መድረኮችንም በማዘጋጀት ይሰራል።
“ለምን ኢትዮጵያ” የግንዛቤ ማስጨበቻ ስራዎች ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ አካል ስለመሆን ምሳሌ ለመሆንም ይሰራል። ለዚህ ምሳሌ ለመጥቀስ ህዝብን የሚያንቀሳቅሱ ጥሩ ነገሮች ተጀምረው መቋጫቸው ወይም ውጤታቸው ሳይታይ ለምን ይቆማሉ የሚለው ጥያቄ ነው። ለዚህ ያገኘነው መልስ በህዝቡ ዘንድ እንደ መልካም ልማድ ወይም ባህል እንዲሆኑ ስለማይሰራ ነው።
የባህል አብዮት እንዲመጣ ደግሞ ከልጆች መጀመሩ አማራጭ የለውም። ስለዚህ በሃገር አቀፍ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ‘በልጆች ልብ ውስጥ የዛፍ ችግኝ እንትከል’ በሚል መሪ ሃሳብ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 13 ዓመት የሆኑ 200 ሕፃናትን ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል። ሕጻናቱ በማህበራዊ ሚዲያዎችና በኢንተርኔት ምዝገባ ያካሄዱና ከአዲስ አበባ አራቱም አቅጣጫዎች የተውጣጡ ናቸው ። በዚህ ዓመትም ከዚህ ጋር በተያያዘ ችግኝን የመትከል እንቅስቃሴ በአገር አቀፍ ደረጃ ልንሰራበት አቅደናል። ይህ ደግሞ መሪም ሆነ ትውልድ ቢያልፍ በልጆች ላይ የተሰራ የአዕምሮ ለውጥ ስለሚሆን የተግባሩን ዘላቂነት ያረጋግጣል።
ለምን ብሎ የማይጠይቅ ትውልድ፣ ቤተሰብም ሆነ አገር ካለበት ልማድ መውጣት አይችልም። ያለፈውንም ሆነ የወደፊቱን ለማየት እድሉ የተዘጋበት ነው። ለማደግም ቢሆን ምንም መንገድ አይኖረውም። ስለዚህም ለምን ባይነት ባለንበት ሁኔታ እንዳንረካና የበለጠ እንድንሰራ ያበረታታል። ለመፍትሄው ቅርብ መሆንም ነው። ለምን ባይነት የመፍትሄ ማህፀን ነው እንደሚባለው።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ለምን ባይነት እንዴት ይታያል?
አቶ አዱኛ፡– ህጻናት በቤት ውስጥም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ለምን ብለው መጠየቃቸውን እናያለን። የሚጠይቋቸው ነገሮችም አስገራሚ ናቸው። የአንድ የአራት ዓመት ህጻን በ24 ሰዓት ውስጥ በአማካኝ 385 ጊዜ ለምን ብሎ እንደሚጠይቅ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚህም እናቶች ላይ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው። ሆኖም መላሽ ግን የላቸውም። የእኛ ሀገር ማህበረሰብ አባታዊ እይታ ያለው ነው። ቤተሰብ ውስጥ ይህንን አትጠይቅ፤ እኔ ያልኩህን ተቀበል፤ ማድረግም ያለብህ እኔ ያልኩህን ብቻ ነው ይባላል። ይህ ደግሞ ስናድግ ሳይታወቀን የመጠየቅ ባህላችንን አዳክሞታል። ጠይቀን የምናገኘውን የመፍትሄ ሃሳብም አሳጥቶናል። በተለይም አዳዲስ ፈጠራዎች እንዳይበራከቱ በር ዘግቷል።
በትምህርት ቤት ያለውን ሁኔታም ያየን እንደሆነ ለምን ተብሎ የሚጠየቅበት ዋና ቦታ መሆን ቢገባውም ይህንን ግን በበቂ ደረጃ አንመለከትም። እኔ የነገርኩህን ተቀበል አይነት አሰራር ነው ያለው። እንዲያውም ለምን ባይ ተማሪዎች በአስተማሪዎቻቸው ዘንድ በጥሩ አይታዩም። አንድ አስተማሪ ልጆችን የሚመግብበት ሥርዓትን ነው የሚከተለው። መሆን የነበረበት ግን ልጆች ራሳቸው እንዲመራመሩ ማድረግ ነው። ውስጣቸው ያለውን ነገር እንዲያወጡና አዲስ ነገር ፈልገው እንዲያገኙ ማበረታታት ነው የነበረባቸው። ስለዚህ ማህበረሰባች መጠየቅን የሚያበረታታ አይደለም ማለት እንችላለን። ይህ ነገር መቀየር አለበት። እኛ እንግዲህ የጎደለውን ለመሙላት የራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን ብለን እየተንቀሳቀስን ነው። ምክንያቱም የነበረውን አመለካከት ብቻ ማስቀጠል የትም አያደርስም።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ሃሳብ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል?
አቶ አዱኛ፡– ከሁሉም በላይ ወጣቱ በሚገባ እየወደደው መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ማሳያው እየተሳተፈ ያለው ወጣት ብዛት ነው። ቤተሰቦችም ቢሆኑ ለልጆቻቸው ነጻነት ሰጥተው ለምንን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ላይ መስራት እንዳለባቸው ወደማመኑ እየገቡ ናቸው። አሁንም ቢሆን ሃሳቡን ብዙ ሰው ይደግፈው እንጂ ወደ መሬት ለማውረድ ብዙ ሥራን ይጠይቃል። ምክንያቱም ትውልድን የተሻገረን አስተሳሰብ በአዲስ አስተሳሰብ መተካት ቀላል አይደለም። ስለሆነም የተቀበለውን እያበረቱ በአዲሱ ትውልድ ላይ አዲስ አስተሳሰብ እየተከሉ መሄድ ያስፈልጋል።
ወጣቱ አዲስ ነገርን ለመሞከር ፈጣን በመሆኑ ይህንን አስተሳሰብ ይፈልገዋልና በሥራው የሚጠመድበትን ዘዴ መቀየስ ይገባል። ለምን ባይነት ለመፍትሄ እንጂ ዳር ቆሞ ለመተቸት መሆን ስለሌበት መፍትሄ ሰጪነቱን ማስፋት ላይ መስራት ለነገ የሚባል መሆን የለበትም።
ለምን ብሎ በመጠየቅ ሁሉም ነገሮች መፍትሄ አያገኙም። ነገር ግን ምክንያታቸው ታውቆ ዳግም ችግር እንዳይሆኑ ማድረግ ይቻላል። ሂደቶች ናቸው ወደመፍትሄው የሚመሩት። ቶማስ ኤዲሰን ከብዙ ሙከራው በኋላ ነው መብራት ማብራት የቻለው። ለምን በዚህ አይሆንም ብሎ 999 ጊዜ ሞክሯል። ስለዚህ ለምን ብሎ መጠየቅ ቢዘገይም ወደ መፍትሄ ይመራል ብሎ “ለምን ኢትዮጵያ” ያምናል። ለየትኛውም ነገር ምክንያታዊ ሆኖ ለምን ማለትን ገንዘብ ማድረግና አዕምሮን ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ዛሬ የቆፈርኩት መሬት ለምንም ካልጠቀመ መከፋት የለብንም።
እርሱም ጥቅም ላይ የሚውልበት ነገር ስላለው አልሆነንም ብሎ ማሰብ ይገባል። ለሌላ ዓላማ የሚውለውም ለምን አልሆነም ሲባልለት ብቻ ነው። ስለዚህም ለምን ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ለማሰብ፣ ለመመራመር ተጨማሪ ጡንቻ እንደሚያገኙ ማመን አለባቸው። ጠያቂነት በራሱ ብርታት መሆኑን ማመንም ይኖርባቸዋል። በተለመደው የትምህርት መመዘኛ ተማሪ የሚመዘነው በሚመልሰው ጥያቄ ብዛት ነው። እሱም በወረቀት ላይ እንጂ በተጨባጭ የህይወት ችግር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡ – ለምን ኢትዮጵያ የትኛውን ጉዳይ በስፋት መርጦ ይሰራል?
አቶ አዱኛ፡– ለውጥን የምናየው ያለ ክፍፍል ነው። ምክንያቱም ፖለቲካውና ማህበራዊው እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቹ የተሳሰሩ ናቸው። አንዱን ከአንዱ መነጠልም መስራትም አይቻልም። ስለዚህም ለውጥን ያለ ልዩነት ማስተናገድ ዓላማ ተደርጎ ይሰራል። ሁል ጊዜ ሥራ ሲሰራ መገናኘት ያለበት አካል ሊገናኙት ግድ ነው። ሆኖም ፖለቲካዊ መስመር ብቻ ተከትሎ የሚከናወን ነገር የለም። እንደ ሲቪክ ሶሳይቲ በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ አካላትን እናበረታታለን። የእኛም ዓላማ የሰዎችን አስተሳሰብ ማንቃትና ወደ ስራ ማስገባት ነው። በተለይም ውይይትን ከምንም በላይ እንዲወዱ ማድረግ ዋነኛ ግባችን ነው። ምክንያቱም የአገሪቱ ችግር በዋናነት የሚፈታው በውይይትና በመነጋገር እንደሆነ እናምናለን።
የእኛ አገር ችግር የሃሳብ ችግር የለበትም። ዋናው ችግር ሳይወያዩ መጓዝ ነው። በግሌ ሮጬ አገር እለውጣለሁ ብሎ ማመንም ነው። ነገር ግን ይህ ማንንም አገር ቢሆን አይበጅም። በዚህ የተለወጠም አገር የለም። በህብረት ሃሳቡን ወስዶ በጋራ መስራት ሲቻል ብቻ ነው ለውጡ ውጤቱን የሚያሳየው። ስለሆነም መፍትሄው ሌሎች ጋር የመጣው እኛ ዘንድ ያልታየው ተቀራርቦ መወያየት ባለመቻላችንና ብትን ሃሳብ ፤ በግለሰብ ብቻ ውስጥ ያለ ሃሳብ መበራከቱ ነው። ነገር ግን በውይይት የዳበረ ቢሆንና ሁሉም የድርሻውን ወስዶ በጋራ ለአንድ ነገር መቆም ቢችል ሃሳቦች ውጤት እንጂ ሃሳብ ሆነው አይቀሩም ነበር። የተለየ ችግር እኛ አገር የለምና መፍትሄው ላይ የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ ማመን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በአገር ደረጃ የጅምላ ፍረጃ በስፋት ይታያል። ይህንን እርሶ እንዴት ያዩታል?
አቶ አዱኛ፡– የሃሳብ ለውጡም የሚያስፈልገው ይህ ነገር በመኖሩ ነው። አንድ ሰው አይቶ ያንን ሰው ምን እንደሚሰራ ሳይረዳ በሆነ ነገሩ ይፈርጀዋል። ከዚያም በኋላ ከዚያ ሰው ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ አይሆንም። ይህ ደግሞ የውይይት ባህልን በብዙ ነገር ያዳክመዋል። ተገዶ እንኳን ቢወያይ ፍረጃው በውስጡ ስላለ ወደ ውጤት ለመቀየር ይቸገራል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ስለ እባብ ያለን አመለካከት ነው። ሁሉንም እባብ መርዛማ አድርገን እንፈርጃለን። ነገር ግን ጥናቶች የሚያሳዩት መርዛማ እባቦች ከ 25 በመቶ አይበልጡም። ይሁንና 75 በመቶ የሚሆነው እባብ በመርዛማነት እንዲፈረጅ አድርጎታል። የሰውም ልጅ እንዲሁ ሁሉንም ሰው በብሔሩ አለያም በእምነቱ በጅምላ መፈረጅ ተለምዷል።
ይህ ፍረጃ በአገር ደረጃ ብዙ ነገሮችን እያሳጣን እንደሆነ እገነዘባለሁ። ምክንያቱም ሰዎች በጾታ ጭምር ፍረጃ ይደረግባቸዋል። ስንት አገር የለወጡ ሰራተኛ ሴቶች እያሉ ሴቶች ሃላፊ መሆን አይችሉም ይባላል። በቅጽበታዊ ንግግር ጭምር የእንትና ወገን ነው መባል ብዙዎችን እያራቀም ይገኛል። ስለሆነም ለመነጋገር በር የሚከፈተው ሰውን መጀመሪያ ልወቀው ማለት ሲጀመር ብቻ ይመስለኛል። አስተሳሰቡን በትክክል መረዳት ሳይቻል ለፍረጃ መፍጠን የምናገኘውን ጥቅም ጭምር ይቀንስብናል።
ሰዎችን በማሸማቀቅም እንዲሁ ለአገር የሚያበረክቱትን እንዲተው እናደርጋለን። ዛሬ ብዙዎች ውጪ ናፋቂ ሆነው ሌሎችን እንዲያገለግሉ የሆኑበት ምክንያትም ይህ እሳቤ ያመጣው እንደሆነ ይሰማኛል። ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ጥላቻ ባለበት ቦታ መደማመጥ አይቻልም። ዜሮ ወይም መቶ መስጠት ባለበት ቦታ የሃሳብ ልዕልና መቼም አይኖርም። ሌላው ‹‹ከእኛ ጋር ካልሆንክ የእኛ ጠላት ነህ›› የሚለው የኮሚኒዝም ጊዜ አስተሳሰብ ጋር መክረማችን የራሱ አሉታዊ አስተዋፅኦ አለው።
አገራችንን ከወደድናትና እንድታድግልን የምንፈልግ ከሆነ እንደአገር ሃሳብ እንዲበልጥ መስራት ያስፈልጋል። በብሔርና በሃይማኖት እንዲሁም በሌሎች ነገሮች መፈራረጁ ዛሬ መቆም አለበት። ሰዎችን ስናግባባም ችግር መንቀስ ሳይሆን ችግሩን ማሳየትና መልካሙን እያጎሉ ማበርታት ይገባልም።
ሙሉ መደገፍ ወይም ሙሉ መቃወም ለሰራተኛው ሙሉ ችግር መሆን ነው። ምክንያቱም ውጤታማ ቢሆን ያለበትን ችግር ማሳየት አይቻልበትም። በብዙ የሚደክምም ከሆነ እንዲሁ ድካሙን እንጂ ስኬቱን እንዳያይ ያደርገዋል። አንዱ ጋር የሌለውን ሌላው ጋር ለማግኘት እንዳይቻልም በር ይዘጋል። የተሻለ ሃሳብንም ለማግኘት ብዙ ያለፋል። ከመደነጋገር መነጋገር ይሻላል የሚለው እሳቤ እንዳናራመድም ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ጉዳይ በለምን እንዴት ያዩታል?
አቶ አዱኛ፡– የምርጥ ነገር ጠላት ጥሩ ነገር እንጂ መጥፎ ነገር አይደለም እንደሚባለው አገር ወደተሻለው ነገር እንዳትደርስ ያደረገን ዛሬን ለመኖር እንደዋስትና የምናያቸው ነገሮች ናቸው። እነዚያ ነገሮች ከእጃችን ሲወጡ በቁጭት እንድንነሳ ያደርጋል። እርዳታ የማይጠቅመው አገር አይኖርም። ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ያግዛል። ሆኖም በእርዳታ ሰበብ ራሳችን አዕምሯችንን ተጠቅመን እንዳንሰራ እና ልባችን እንዲመነኩስ ካደረገው እንዲሁም ሌሎች በእኛ ላይ እንዲሰለጥኑ ካደረገ ከስረናል።
ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለባት አገር ነች፤ ድንግል መሬት እና ብዙ የተፈጥሮ ሀብት አለን። ይህ ደግሞ በሰው ሃይልም ሆነ በተፈጥሮ ፀጋ አለመጠቀም መቻላችን እጅግ ሊያሸማቅቀን የሚችል ጉዳይ ነበር። ነገር ግን እስከዛሬ ከወሬ አልፈን እንዳንሻገር ሆነናል። መስራትና ማየት ስንጀምር ደግሞ ከእኛ ልትወጡ ነው ብለው ጉሮሯችን ላይ የሚቆሙ እንዲበዙና ጫናው እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ለምን የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ከዚህ አንጻር ይመስለኛል።
የአገር ደህንነት ዋስትና መከላከያ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናም ጭምር ነው። በኢኮኖሚ ደካማ የሆነ አገር የማንም መጫወቻ እንደሚሆን እሙን ነው። አሁንም ያንን አስበው ነው ጫናውን ለማሳረፍ እየሞከሩ የሚገኙት። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ሀብታችንን እንድንጠቀም፣ በቁጭት ተነስተን በህብረት ለአገራችን እንድንሰራ እድል አድርገን ከተጠቀምንበት እናተርፋለን። ተአምር መስራት የሚችሉ ሰዎች ሃሳባቸው እንዳይወጣ ስለአፈናቸው እንጂ ተአምረኛ መሆናችንን ለዛሬ ጫና አሳራፊዎች በብቃት ያሳዩ ነበር። እናም ይህ ጫና መምጣቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገሬ አለሁላት እንዲሉ ያነሳሳል ብዬ አስባለሁ።
አሁን ባለው ለውጥ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንለካው ይህንን ተግባራችንን ለምን ቀደም ብለን አልጀመርነውም እንድንለው ያደርገናል። ለዚህም በአብነት የምናነሳው ስንዴ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ነው። ከውጭ የምናስመጣውን አቅም በብዙ መጠን ቀንሰናል። ስለዚህም የውጭ ጫናውን በመከራ ውስጥ የመጣ በረከት አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል። ሰርቶ ማሳፈር እንደሚቻልም ልናሳይበት ያስፈልጋል። እኛን በፍቅር እንጂ በገንዘብ አሊያም በጉልበት እንደማይገዙን ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ጠንከር ብለን እየሰራን ውስጣችን ያለውን ልዩነት በመነጋገር እየፈታን የለውጥ ጉዟችንንም በዚያው ልክ እንዲያዩት ማድረግ ላይ በስፋት መትጋት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡– በለምን ኢትዮጵያ የባህል አብዮት እንደሚያስፈልግ ይገለጻል። ምን ማለት ነው?
አቶ አዱኛ፡– ኢትዮጵያ በባህል ደረጃ ሀብታም ነች። ይሁን እንጂ ጥሩና ሊሻሻል የሚገባቸው እንዲሁም እርሷ የሌላት ባህሎች ሊኖሩ ይችላሉ። በመሆኑም አብዮት ይህንን ሁሉ አቀናጅቶ የተሻለ ባህል ባለቤት ያደርጋልና አብዮቱ ያስፈልጋል የተባለበት ምክንያት ይህ ነው። ለምሳሌ ችግኝ ተከላውን ብናነሳ አካባቢውን የሚወድ ፣ ለአካባቢው ባለአደራ የሆነ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር ይህንን ባህል በልጆች ላይ መስራት ያስፈልጋል። ባህላችን ካልነበረ ባህል ማድረግ ላይ መስራት ከሆነ ደግሞ ማሳደግ ይገባልና የባህል አብዮት ግድ ነው።
በባህላችን ብዙ የሚለፉና ሰራተኛ የሆኑ ህዝቦች የተለያየ ስም ይሰጣቸዋል። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የእደጥበብ ባለሙያ አንዱ ነው። እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ይናቃሉ፤ ከዚያም አልፎ ከማህበረሰቡ ጭምር እንዲገለሉና በስራቸው እንዲሸማቀቁ ይደረጋሉ። የባህል አብዮት ያስፈልጋል የምንልበትም ምክንያትም ሰዎች ዋጋ ከፍለው ገንዘብ እንዲያገኙና የሚሰሩ ሰዎች እንዲደነቁ ማድረግን ዓላማ አድርጎ ነው።
በብዙ የዘር ሃረግ ውስጥ ሰው በአንድ ሀገር ያለ ቀርቶ ከድንበር ተሻግሮ ከሌላው ሀገር ሰው ጋር መቀላቀሉ አይቀርም። በዛ ላይ በኛ ባህል ጋብቻ የሚደረገው ሰባት ቤት ወደ ኋላ ተቆጥሮ፣ አለመገናኘቱ ተረጋግጦ መሆኑ ከአጥራችን እንድንሻገር አባቶቻችን ምን ያህል ይፈልጉ እንደነበር ማሳያ ነው። ዝምድና ሌላውን በማኖር እንደሆነ የሚያሳይ ነውና ይህ ባህላችን ደግሞ በደንብ ሊፈተሽና ሊያድግ የሚገባው ነው። መቼ እንዳጣናቸው የማናውቃቸውና በሌላ የተተኩብንንም ፈልፍሎ ማውጣት ያስፈልገናል። ባህሎቻችን በሁሉም መስክ አንኳር መፍትሄ ሰጪ ናቸው። ስለዚህም ለፖለቲካው፣ ለኢኮኖሚው እንዲሁም ለማህበራዊው መድህን እንዲሆኑም ማድረግ የመጀመሪያ ሥራችን ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ባህላችን አለን ከሚባለው እኩል ሲሄድ አይታይም። ይህ ለምን ሆነ ይላሉ?
አቶ አዱኛ፡– ለዚህ ምሳሌ አንድ ጉዳይ ላንሳ። የእስራኤል እረኞችንና የበጎቻቸውን ሁኔታ። እረኞቹ እንደ እኛ በልምጭ ከኋላ ሆነው እየመቱ የሚፈልጉት ቦታ ላይ አይወስዷቸውም። በጎቹን እርሱ በሚመራቸው መንገድ እንዲሄዱ ከማላመዱ በላይ በጎቹ በእርሱ ላይ እምነት እንዲጥሉ ማድረግ ይችላል። እነርሱ የተሻለውን እያዩ ይሄዳሉ በጎቹ ከኋላቸው ይከተሏቸዋል። የእረኞቹ ድርሻ የለመለመ መስክ የት እንዳለ ማየት ብቻ ነው። ውሃም ካስፈለጋቸው የቱ ዘንድ ቢሄዱ የተሻለ መጠጣት ይችላሉ የሚለውን ያስባል። ከዚያ እርሱ መንቀሳቀስ ብቻ ነው የሚጠበቅበት። በጎቹም አምነውት ይከተሉታል። በእርግጥ ይህ ዝም ብሎ አይመጣም። ይህ ዜጎቿ ሃላፊነታቸውን አውቀው እና ነፃነታቸው ተጠብቆ የሚኖርባት እንዲሁም ተአማኒነታቸውን አይቶ ህዝብን ከራዕያቸው ጎን ማሰለፍ የቻሉ መሪዎች በየደረጃው ያሉባትን አገር ለመፍጠር መስራትን ይጠይቃል።
በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ግን ተመለስ ብቻ ነው መርሁ። መሪው የፈለገውን እንጂ በጎቹ የሚያምኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ አልተለመደም። ከኋላ እየዠለጡ መምራት ደግሞ መንዳት ነው። የአስተሳሰብ ለውጡም በግዴታ እንጂ በመተማመን ላይ የተመሰረተ አይደለም። በግዴታ የማድረግና የማስደረግ ዝንባሌን በባህላችን ለምደነው ኖረነዋል። በተለይ በቤት ውስጥ ይጀመርና በተቋማት ላይ ሲተገበር ትክክል የሆነ ያህል ይሰማናል። አለቆች እኔ ብያለሁ፣ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው ወዘተ በማለት ሳያምኑበት፣ ሳያሳምኑ ያሰራሉ። ዛሬ ድረስ ያልተቀየሩ ባህሎቻችንም እነዚህ ናቸው።
አብዛኛው መሪም ቢሆን እንዲሁ ህዝቡን ለመምራት እንጂ ለማሳመን ሲጥር አይታይም። ሁሉንም ማሰብና መስራት ያለባቸው እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ። ይህ ደግሞ መስራት የሚችሉትን እንዳይሰሩ አድርጎ አቅማቸውን ያዳክመዋል፤ ጉልበታቸውና እውቀታቸው በማይሆን ነገር ላይ እንዲፈስም ያስገድዳቸዋል። ነገር ግን አሳምኖና በመግባባት ህዝቡ ራሱን እንዲመራ መንግስትን ጭምር እንዲያርም ቢደረግ ኖሮ ሁሉ ነገር ይስተካከል ነበር።
የእኛ ባህል አስተሳሰብ መሪዎችን በሚወዷቸው ብቻ ማስከበብ ነው። ወዳጆችም ቢሆኑ ከተገዢነት ሳይላቀቁ ያላቸውን ቦታ ላለመተው እውነቱን የሚናገሩበት መንገድ ዝግ ነው። ስለሆነም ለመሪው ተቃራኒ ሃሳብን ለማየት አይችልም። ተቃራኒ ሃሳብ ከሌለ ደግሞ የተሻለ መደላደል ላይ ነኝ ተብሎ ስለሚታሰብ መሪዎች ለእድገት አይሰሩም። ከመቆጣጠር በፊት ማሳመን፤ ከግዴታ በፊት ውዴታን ማስቀደም ቦታ አያገኙም። በተቃራኒው ወገን ደግሞ ጭፍን መቃወሞች ስለሚበዙ ጎራ ለይቶ መቀመጥ ይንሰራፋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ አገርን ማሳደግ አይታሰብም። ስለዚህም ልምዳችን ባህላችን ማስቀደም ያለበትን ባለማስቀደሙ ያለንን ያህል እንዳንጠቀምበት ሆነናል የሚል እምነት አለኝ።
ከላይ ካልኩት በተጨማሪ መልካሙን ባህል ያወቁ እና የሚኖሩት ደግና አቃፊ፤ እኔን ሳይሆን እኛን የሚያስቀድሙ የማህበረሰብ ክፍሎች ዝም ማለታቸው ክፉዎች እንዲገኑ አድርገዋቸዋል። ጥቂት ቢሆኑም መድረኩን የያዙት ክፉዎች በመሆናቸውም የእነርሱ ሃሳብ ብቻ ተሰሚነት አገኘ። ይህ ደግሞ ጥቂት ሆነው እንዲረብሹን፣ እንዲያስቸግሩን እድል ሰጣቸው። በተመሳሳይ በጎዎቹ እንዲወጡና እንዲያስተምሩ አልተበረታቱም። እያንዳንዱ ግለሰብ ከዝምታ ወጥቶ የእኔ ድምጽ ዋጋ አላት ማለት መጀመርም ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡– የብሔር አስተሳሰብ በ” ለምን” እንዴት ይታያል?
አቶ አዱኛ፡– በቀለምም ይሁን በደም ወይም በሌላ በሰው ልጆች መካከል መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለና የሰው ዘር በሙሉ አንድ ብቻ እንደሆነ እንረዳለን። ነገር ግን በደም ላይ ባይመሠረት በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በሥነልቦና፣ በመኖሪያ አካባቢና በመሳሰለው ላይ ተመስርተው ሰዎች የጋራ መሠረት (ማንነት) አለን ብለው ሊያምኑ ይችላሉ። ይህን ከአንድ መሰረት የመሆን እሳቤ ግን ልናከብርላቸው ይገባል። ይህን ዘረኝነት ነው የምንል ካለን ተሳስተናል ።
የራስን ማንነት መውደድና ማክበር ዘረኝነት አይደለም። የራስን ባህል ለሌሎች ማስተዋወቅና እንዲያድግ መሻት ዘረኝነት ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው ። በራስ ማንነት ባህልና እሴት መኩራት ዘረኝነት ሆኖ አያውቅም፤ ሊሆንም አይችልም። ዘረኝነት ማለት የራስን ባህልና ቋንቋ እየወደዱ የሌሎችን መጥላትና ማናናቅ ነው። ዘረኝነት ማለት የራስን ባህል እያሳዩ የሌሎች እንዲታይ አለመፈለግ ነው። ዘረኝነት ማለት በራስ ማንነት እየኮሩ ሌሎች በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ ማድረግ ነው። ዘረኝነት ማለት የራስን ቋንቋ ብቻ ማክበር ሌላው አሳንሶ ማየት ነው። ዘረኝነት ማለት በአጠቃላይ የሌሎችን ባህል፣ሃይማኖት፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ አለማክበር ነው።
ችግሩ ማንነቱ ላይ ተመስርቶ እንደራስ ያልሆነን መጨቆን፤ ማግለል፤ ማንኳሰስ እንጂ እራሱ ማንነቱ አይደለም። ችግሩ በማንነት ላይ ተመስርቶ በመድልዎ፤ በዝምድናና በቡድን መሥራትና ለሙስና ማመቻቸት እንጂ እራሱ ማንነቱ አይደለም። ለእሱ መፍትሄው ደግሞ መተማመን እና ተጠያቂነት የሚፈጥር ተቋም እንጂ ማንነትን አጥፍቶ አንድ አይነትነትን ማበረታታት አይደለም። ለዚህ ደግሞ የሚያበቃው በትክክል አለመተርጎማችን ነው።
የቡድንም ሆነ የግለሰብ መብት የሚከበረው ከተዘረጋው ግልጽ እና ፍትሃዊ ተቋማት የተነሳ እንደሆነም ቀዳሚ ምስክሮች ናቸው። “DC language access act” ከተሰኘው ፍትሃዊ ህግ የተነሳ በዋሽንግተን ዲሲ በአገልግሎት ተቋማት ጥቅም ከሚውሉ ስድስት ቋንቋዎች ውስጥ አማርኛ አንዱ ሆኗል። ይህ የሆነው ኢትዮጵያውያን ተደራጅታችሁ ማንነታችሁን መሰረት ላደረገ መብት ድምፃችሁን ስላሰማችሁ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የሰዎች ሁሉ መብት ሳያዳላ የሚያስተናግድ ተቋም ስለተመሰረተ ሁሉም ለወገኑ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ለሆነው ሁሉ መጮህ አለበት። የማህበረሰቡ አስተሳሰብም ቢሆን ሰው ወደ እኛ የሚመጣው ሊያሳድገን፤ ሀብታችንን ሊጨምርልን ነው ብሎ እንዲያምን መሰራት ይኖርበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ዱባይ ያነሱት ጉዳይ ለዚህ አብነት ይሆናል። ሌሎችን ያለሙት ከሌሎች ዓለማት የመጡ እንጂ የአገሬው ሰው አይደለም። እናም ውጣልኝ ትተን ናልኝን ልናጎለብት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት እድሉን እንስጥዎ?
አቶ አዱኛ፡– አገር የምታድገው በመነጋገርና በመጠየቅ መሆኑን አምነን በዚያ ላይ መስራት ያስፈልጋል። በማህበራዊውም፣ በኢኮኖሚውም እንዲሁ በፖለቲካው ዘርፍ አገራችን ያለችበት ሁኔታ አይገባንም ልንል ይገባናል። ለምን እንዲህ ሆንን ብለን ብንነጋገር ለዚህ አገር የተሻለ እድል እናመጣለን። ይህንን ለማድረግና መፍትሄ የሚሰጡ ሰዎች ደግሞ ስፍር ቁጥር የላቸውም። እናም እነርሱን ለመጠቀም እድል እንስጣቸው። ታላቁ ሩጫ ላይ ማንም ሰው ሄዶ ተወዳድሮ ማሸነፍ እንደሚችል ሁሉ መልካም ሃሳብ ያለው ሰው የሚያሸንፍባት አገርን ለመፍጠርም እንትጋ። በተለይ ተቋማት ላይ የሚሰሩ አመራሮችና ሰራተኞች በተሰጣቸው የአገር ሃላፊነት ጉዳዮች ላይ ችግሮችን እያዩ ዝም ከማለት ይልቅ ለምን ብለው መጠየቅን ገንዘብ ያድርጉ። ለምን የሚሉ ሰዎች እድል ይሰጣቸው። ምክንያቱም “ለምን” ን እውቅና ስንሰጠው “እንዴት” የሚለው ጥያቄ ይከተላል።
ለምን ለስራና ለፈጠራ ያነሳሳል። ለምን ወደ ጥናትና ምርምር ይመራል። ለምን ለጋራ ዓላማ ያሰባስባል። ሀገራችን ‹ለምን እንዲህ ይሆናል፤ ለምን እንዲያ አይሆንም› የሚሉ ጠያቂ ትውልዶች ትፈልጋለች። ያለንበት የኢኮኖሚ ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ በቅን ልቦና በመነጋገር፤ በመተባበር የማይፈቱ አይደሉም። ችግሩ ለምን ባይ ጠፍቶ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ በእጃችን ይዘን መምሸቱ እና መንጋቱ ነው። ካሁን በኋላ ግን አያለሁ ይህ ሲቀየር ፣ አያለሁ ለምን ባይ ሰራዊት ሲነሳ፤ አያለሁ በእኔ ዘመን ይቺ ምድር ይለፍላት የሚሉ እራሳቸውን የካዱ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሀገር ጥቅም የሚያስቀድሙ ትውልዶች ለሀገር እድገት ሲንቀሳቀሱ፤ አያለሁ፤ ስኬት ለብቻ መበልጸግ እንዳልሆነ የገባቸው ወጣቶች የወደቀውን ሲያነሱ ፣ የተራበውን ሲያበሉ ፣የታረዘውን ሲያለብሱ፤ አገራችን በተስፋ ጎዳና ሲያስኬዷት አያለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ አዱኛ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013