ዘመን የተለያዩ ልማድና ድርጊቶችን በራሱ ሂደት አመላክቶ ለሌላ አዲስ ሁነትና ትዕይንት ቦታውን ይለቃል። በአንድ የዘመን ሂደት ውስጥ የሚለመድ ያ ዘመን ሲያልፍ ደግሞ የሚረሳ ብሎም ሙሉ በሙሉ የሚተው አልያም አብቦና በተሻለ መልክ እንደ አዲስ ሆኖ የሚለመድና የሚያድግ ነው ፋሽን። ኢትዮጵያዊያን ጠቢባን ናቸው ፤ለዓለም በተለያየ መልክ የራሳቸውን ልዩ ጥበብ ያወረሱ፤ ልዩ ገፅታቸውም በብዙ ያሳዩ ድንቅ ባለሙያም ጭምር።
ድሮ እናት አባቶች ይጠቀሙበትና አምረውና ደምቀው የሚታዩበት የፀጉር አሰራር የዛሬ ላይ ባህር ማዶ ተሻግሮ አምሮና በተለየ መልክ ስናየው መነሻው የኛ ሣይሆን የእነሱ የሚመስለን ብዙዎች ነን። በተለይ ጥንት ላይ አርበኞች ይጠቀሙበት የነበረው የፀጉር አሰራር፣ ወጣቶች ይለዩበት የነበረው የፀጉር ቁርጥ፣እናቶች ማንነታችን ያሳዩበት የነበረው የፀጉር አሰራር ለዚህ ማስረጃ ነው።
ፋሽን ዘርፈ ብዙ እይታ፣ አይነተ ብዙ ጥብብ መሆኑ ግልፅ ነው። ፋሸና ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ይዘልቃል። ፋሽን ሆኖ የሚቆይ ተለምዶም የሚዘወተር ፈጠራ ደግሞ ባለሙያዎች ይፈጥሩታል። የዛሬ ፋሽን አምዳችን በአገራችን ዛሬ ላይ የሚዘወተሩ የሴቶች ፀጉር ስራ አይነቶችን እና አሰራራቸውን ለመመልከት ብዕራችንን አንስተናል።
ጥንት አያቶቻችን ይሰሩት የነበረው የፀጉር ፋሽን በተለያዩ ታሪካዊ ፎቶና የጥንት ምስሎች ላይ እንዴት ያስውባቸው እንደነበር ማስታወሱ በቂ ነው። ደምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ ከአያቶችዋ የወረሰችውን የፀጉር ስራ ጥበብ ተጠቅማ አንድ የዘፈን ክሊፕዋ ላይ የታየችበት የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ዶቃዎች ያለበት ቁጥርጥር የጸጉር ስራ በሁሉም የተወደደና የተተገበረ ተወዳጅ ፋሽን መሆኑ ይታወሳል።
ቁንጮ፣ ሳዱላ፣ ቁንዳላና ጋሚ የእኛ የሆኑ የፀጉር ስራ መዋቢያዎቻችን ለዘመናት የቆዩ ከሁሉም በፊት በራስ ልማድ የተካንባቸው ናቸው። ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው የሆነ ባህል የተላበሱ የራሳቸው አሻራ ባረፈበት የአለባበስ ስርዓትና ልምድ አምረውና ደምቀው የሚታዩ የባህል አማባሳደሮች ናቸው። በእናቶች ተፈትሎ በሸማኔዎች ተሸምኖና በሰፊዎች በተለያየ ዲዛይን ተሰርቶ ከሚለበሰው የአገር ባህል ልብስ ጋር የሚሄድ የፀጉር ስራ በተለያየ ዘመንና ሁኔታ የተለያየ አይነት አሰራር አለው።
በተለይም በብዙ የአገራችን ክፍል ላይ በስፋት የተለመደው ሹሩባ አሰራሩ የተለያየና በፀጉር ተሰሪዋ እንስት ፍላጎትና ምርጫ የሚከወን ነው።
ወይዘሪት ሄራን በቀለ ቄራ ሄለን የውበት ስራ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የውበት ስራ ሙያ ተምራ አሁን ላይ የራስዋን የሴቶች የውበት ሳሎን በመክፈት በመስራት ላይ ትገኛለች። የፀጉር ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና በብዙዎች ዘንድ በልዩ ትኩረት እየተሰጠበት ያለ መሆኑን የምትናገረው ሄራን፣ በተለይም በአገራችን ከጥንት ጀምሮ የነበረው ሹርባ ስራ ዛሬ ድረስ ተወዳዳሪ የሌለውና የብዙ ደንበኞች ምርጫ መሆኑን ትናገራለች። የሹሩባ ስራ አይነተ ብዙ መሆኑን የምትናገረው ሄለን፤እንደ ደንበኞችዋ የፊት ቅርፅና የመሰራት ፍላጎት ወቅቱን በሚመጥን መልኩ የተለያዩ የፀጉር ስራዎችን ትሰራለች።
ድሮ እናቶች ሲሰሩዋቸው የነበሩት የሹሩባ ስራዎች ዛሬም ድረስ የሚዘወተሩ በብዙዎችም የሚመረጡ መሆናቸውንም ታስረዳለች። የፀጉር ስራ አይነቶቹም የተለያየ ስያሜ ያላቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጉንጉን፣ አምፖሎ፣ ሰፌድ(አከንባሎ)፣ ድርብ፣ ገብስ ስራ፣ ማጭድ ቅድ፣ ጨረቃና ብዙ ስያሜዎች እንደየአካባቢው ይሰጠቸዋል።
ጉንጉን ከሁሉ የሹርባ ስራ አይነቶች ቀለል ያለና ሴቶች ሌላ ሰሪ ካላገኙ በራሳቸውም ሊሰሩት የሚችሉት ነው። ሌሎቹ የሹሩባ ስሪቶች ፀጉር በተለያየ መጠን ተሰንጥቆ ወይም ተከፍሎ ወደ ላይ ሲሰራ ጉንጉን ግን በተለየ መልኩ ወደ ውስጥ እየተቀበረ ይሰራል። ድርብ ፤ሌላኛው የሹሩባ አይነት ሲሆን ከስር አንድ ቀጭን ሹሩባ ይሰራና ከላይ ደግሞ ሌላ የሚደረብበት የፀጉር ስራ አይነት መሆኑ ነው ባለሙያዋ የምትገልፀው። የዚህ አይነት የሹሩባ አሰራሮች ብዙውን ጊዜ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተለይም በአማራና በትግራይ አካባቢ ይዘወተራል።
አምፖሎ ደግሞ ሌላኛው የሹሩባ ስራ አይነት ነው። ስያሜውን ያገኘው የፀጉር ስራው ሲጠናቀቅና ሲታይ አምፖል የሚመስል ቅርፅ ስለሚያላብስ መሆኑንም የፀጉር ስራ ባለሙያዋ ሄራን ታስረዳለች። የዚህ ፀጉር አሰራር አሁን ላይ በብዙዎች የሚተገበር መሆኑንና ስራውም ከፀጉር መነሻ ግንባር ጀምሮ እስከ መሃል አናት ከኋላና ጉንና ጎን ተጀምሮ ወደ መሀል ይመጣና ሁሉም መሀል አናት ላይ ይገናኛል፤ ከዚያም የቀረው ፀጉር በአንድ ላይ እንደ ገመድ ይሰራል።
ሌላኛው የሹሩባ ስራ አይነት በብዙዎች ሰፌድ ወይም አከንባሎ እየተባለ ይጠራል። ይህም ስያሜ የወጣው የፀጉር ስራው ሲጠናቀቅ ከሚታየው ቅርፁ የተነሳ ነው። የፀጉር ስራው ክብ እየሆነ ሄዶ መጨረሻ ላይ ወደ መሀል ይሄዳል። ከዚያም የተቀረው ፀጉር ቅድም አምፖሎ እንደተሰራው እንደ ገመድ ይገመዳል ማለት ነው። ከአምፖሎ ጋር ያላቸው ልዩነት ፀጉሩ ሲሰራ በራስ ቅል ላይ ክብ ተደርጎ እየተሰራ መግጠሙና አንደኛው አምፖሎ ደግሞ ቀጥ ተደርጎ መሰራቱ ነው።
ሹሩባ ሲሰራ እንደ ሚሰሩት ደንበኞች ወይም ሴቶች ፍላጎትና የፀጉር መጠን የራሳቸውን ፀጉር አልያም ደግሞ ዊግ ተጨምሮበት እንደሚሰራና እንደ ድርብ ያሉት የሹሩባ ስራዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ በዊግ ስፌት ታግዞ ይሰራል። ገብስ ስራ የሚባለው የሹሩባ አይነትም በተለያየ ቀለም በተለይም ገብስማ በሆነ ዊግ ፀጉር ተውቦ በስፌት የሚሰራ የሹሩባ አይነት ነው።
ከሹሩባ በተለየ የሚሰሩ አይነተ ብዙ የፀጉር አሰራሮች መኖራቸውና የምትገልፀው ደግሞ የፀጉርና የውበት ባለሙያ የሆነችው ቤዛዊት በላይነህ ናት። በተለይም አሁን ላይ ከጣሊያን ከብራዚልና ከህንድ የሚመጡና የሚሸጡ የሰው ፀጉሮች (ሂዩማን ሄሮች) ሴቶች ከራሳቸው ፀጉር ጋር በማድረግ በተለያየ መልኩ እንደሚያሰሩ ትገልፃለች። አሁን አሁን የተለመደና በተለያዩ ሴቶች የሚመረጥና ሲታይም የሚያምር መሆኑን የምታስረዳው ቤዛዊት ሂዩማን ሄሮቹ እንደ ሴትዋ ፊት ቅርፅ ፍላጎት ዌቪ፣ፍሪዝ፣እና ተተኩሶ ቀጥታ ወደታች የሚለቀቅ የፀጉር ፋሽን በብዙዎች ተመራጭ ነው።
እነዚህ ከውጪ የሚገቡና ሴቶች ለፀጉራቸው ማማርና የተለያየ ውበት ማጎናጠፊያነት የሚጠቀሙባቸው ፀጉሮች እንደየፀጉሩ ተመራጭነትና ርዝመት ከ8 ሺ እስከ 15 ሺ ድረስ ገበያ ላይ የሚሸጡ መሆናቸውን ባለሙያዋ ታስረዳለች።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013