በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በ1950ዎቹ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ካስነበባቸው የውጪ ዜናዎች መካከል ተነባቢ ናቸው ብለን ያሰብናቸውን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
የዘር ልዩነት እንዳይጠቀስ ተጠየቀ
ለንደን፡- የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር አሌክስ ዳግላስ ሂዩም ፓርቲያቸውን በመደገፍ በዘር ልዩነት ላይ የሚያደርጉትን ንግግር እንዲያስወግዱ የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ መሪ የሆኑት ሚስተር ሔሮልድ ዊልሰን አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትር ዊልሰንም ባቀረቡት ማሳሰቢያ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባል የሆነው አንድ ሰው መራጮች የጥቁሩን ጉርብትና ከፈለጉ የሌበር ፓርቲን መደገፋቸው ነው” ሲል ተናግሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተባለም በማለት ነገሩን አስተባበሉት ብለዋል፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር አሌክስ ዳግላስ ሂዩም ለዚህ ወቀሳ መልስ ሲሰጡ “በፓርቲዬ ስም ሆኜ ስናገር የዘር ልዩነትን ለማውገዝ የቆረጥን መሆናችንን አረጋግጣለሁ” በማለት አስረድተዋል፡፡
ምንም እንኳ የብሪታኒያ መንግስት የዘር ልዩነት በማንኛውም ስፍራ እንዳይደረግ የሚደግፍ ቢሆንም የሌበር ፓርቲው መሪ ሚስተር ሄሮልድ ዊልሰን ሀሙስ ዕለት ባቀረበው ማሳሰቢያ የሰው ቀለም የንግግር ምሳሌ ሆኖ እንዳይጠቀስ አመልክተዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ የዘር፣ የቀለም እና የሀይማኖት ልዩነቶች ገነው የሚታዩባት ደቡብ አፍሪካ ብትሆንም፣ እንደዚህ ያለው ተግባር
በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እና በተለይም በአሜሪካ ውስጥ መፈጸሙ ስውር አይደለም፡፡
(ሮይተርስ)
መጋቢት 19 ቀን 1956
በጋዜጣው ሪፓርተር
ጀርመናዊቷ በጫማ ስፌት የዓለም
ሻምፒዮና ሆነች
ከሙኒክ፡-በጫማ መስፋት የዓለም አሸናፊ የሆነችው በሙኒክ ከተማ የምትኖረው የ፳፭ ዓመት ዕድሜ ያላት የምዕራብ ጀርመኗ ሚሊስ በርጊት እስቴል መር የተባለችው ሴት ናት፡፡
ሚሊስ በርጊት እስቴልመር በብሪታንያ የብላክ ፑል ከተማ ውስጥ በቅርቡ ተደርጎ በነበረው የጫማ መስፋት ውድድር ላይ አብላጫ ውጤት በማግኘት የዓለም የጫማ ስፌት አሸናፊ ሆናለች፡፡
በኤሮፓውያን አገሮች ውስጥ በየዓመቱ በሚደረገው በዚህ የጫማ ስፌት ውድድር ታሪክ ውስጥ አንድ ሴት ከፍተኛውን ሽልማት ስታገኝ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ሚኒስ እስቴልመር ለውድድሩ ወደ ኢንግላንድ ከመሔዷ በፊት ለጋብቻ ተገዝቶላት የነበረውን ጫማ ካስቀመጠችው ስፍራ አንስታ በዳንስ የተጎዳውን ሶል፣ ሊያልቅ የደረሰውን ተረከዝና የተበላሸውን ቦታ ሁሉ እንደገና በማደስ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአዲስነቱ የነበረውን መልክ ልትሰጠው ችላለች፡፡
ጀርመናዊቱ ሚሊስ እስቴልመርም በውድድሩ ላይ አሸናፊ ከሆነች በኋላ አንድ የብር ዋንጫና “በዓለም ከፍተኛ ችሎታ ያላት ጫማ ሰፊ” መሆኗን የሚገልጥ አንድ የምስክር ወረቀት አግኝታለች፡፡ የሚሲስ እስቴልመር ባለቤት ነጋዴ ነው፡፡ ጫማ መስፋት ያስተማራት የለም፤ ነገር ግን በጥረቷ ከዚህ ለመድረስ ችላለች፡፡
መጋቢት 17 ቀን 1956
የውርርድ ጣጣ 7ሺህ አስወጣ
ከኬፕታውን፡-አንድ የሆላንድ ጋዜጠኛ ምንም ገንዘብ በእጁ ላይ ሳይዝ “ሐመርፌስት” ከተባለች የኖርዌይ ሰሜናዊ ወደብ ተነስቶ “ኬፕታውን”ከተባለችው የደቡብ አፍሪካ ወደብ እደርሳለሁ ብሎ በመወራረድ ፰ ቀኖች ያህል ከተጓዘ በኋላ ባለፈው አርብ ከተባለው ወደብ ለመድረስ ስለቻለ የተወራረደበትን ፩ ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ወይም ፯ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ለማግኘት በቅቷል፡፡
ይህን ውርርድ ከአንድ ሲዊዲን ተወላጅ ጋር እ. አ. አ ባለፈው ዓመት ኤሮፕ ውስጥ ያደረገው የሆላንዱ ጋዜጠኛ በአንድ ካናዳ የወሬ ወኪል ተቀጥሮ የሚሰራ ማርክ ቮን ቬህ የተባለ የ፳፪ ዓመት ወጣት ነው፡፡
ተወራራጁ ስዊዲናዊ በገዛ ቅብጠቱ የ፯ሺህ ብር ኪሰራ ገብቷል፡፡ የውርርዱ ስምምነት ማርክ ቮን ቬህ ምንም ገንዘብ በእጁ ሳይዝ ከሐመርፌስት ወደብ ተነሰቶ እየለመነ ቢሆንም ልክ መጋቢት ፲፰ ቀን ፶፮ ዓ.ም ከቀኑ በ፬ ሰዓት ኬፕታውን በመድረስ ወደ ሐመርፌስት ቴሌግራም እንዲያስተላልፍ ነበር፡፡
በውርርዱም መሰረት ማርክ ቮን ቬህ ፰ ቀኖች ያህል በመጓዝ ፳፪ አገሮችን አቋርጦ መጋቢት ፲፰ ቀን ፶፮ ዓ.ም ባለፈው ዓርብ ከተወሰነ ሰዓት ቀደም ብሎ ከቀኑ ልክ በ4፡00 ሰዓት ኬፕታውን እንደደረሰ ወደ ሐመርፌስት ቴሌግራም ለማስተላለፍ በቅቷል፡፡
መጋቢት 23 ቀን 1956
በአስዋን ግድብ ስራ 227 ሰዎች ሞተዋል
ከካይሮ፡-የአስዋን ግድብ መስራት ከጀመረበት ቀን አንስቶ እስከአሁን ድረስ በጠቅላላው 227 የሚሆኑ መሐንዲሶች ቴክኒሺያኖች እና ሰራተኞች የሞቱ መሆናቸውን “አክባር” የተባለው የግብጽ ጋዜጣ ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል፡፡
ይህም የታወቀው የተባባረው ዓረብ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጋማል አብድል ናስር የሶቪየት ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክታ ክሩስቺቨ የግድቡ ፕላን የመጀመሪያ ደረጃ ስራ ግንቦት ፯ ቀን ዓ.ም ፶፮ በሚመጣው ሳምንት ሲያልቅ የዓባይ ወንዝ በጥቅም ላይ ለመዋል የተቻለ መሆኑን በማረጋገጥ ንግግር የሚያደርጉ መሆናቸውን ካመለከተው መግለጫ ነው ሲል ጋዜጣው አስረድቷል፡፡
በዚህ ታላቅ ግድብ ስራ ላይ ህይወታቸው ካለፈው ሰራተኞች ውስጥ ሰባቱ የሶቬየት ተወላጆች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ብዙዎቹ አደጋዎች ሊደርሱ የቻሉት ከድንጋዮች መናድ ከኤሌክትሪክ ሽቦ መያዝ እና ከጭነት መኪናዎች መገልበጥ መሆኑን “አክባር” የተባለው ይህ የግብጽ ጋዜጣ አመልክቷል፡፡ በግድቡ ስራ ላይ 30 ሺህ ሰራተኞች መሰማራታቸው ተረጋግጧል፡፡
(ኤ ኤፍ ፒ)
ሚያዚያ 30 ቀን 1956
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013