ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጣሊያንና ፈረንሳይ በወረት ሳይሆን በእውነተኛ ፍቅር የታሰረ አንድነት መስርተው ያለፉትን ስምንት አስርት ዓመታት ዘልቀዋል። የአውሮፓ ህብረት መስራች፤ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ እንዲሁም የቡድን ሰባት አባል አገር በመሆንም በጋራ ተሳስረው፤ ለጋራ ጥቅምና ደህንነት አብረው ሰርተዋል።
ካለፉት ዓመታት ወዲህ ግን በቀድሞዎቹ ወዳጆች መካከል የፍቅር ሰንሰለቱ ተዳክሟል። በተለይ ፖለቲካዊ ግንኙነታቸው ነፋስ ገብቶበት ወደ መቃቃር ተሸጋግረዋል። ይህ መቃቃር እውን መሆን የጀመረውም የአውሮፓ ህብረት መስራችና ሶስተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ጣሊያን ባለፈው ዓመት አዲስ የጥምር መንግስት ከተመሰረተና «የፋይቭ ስታር» ንቅናቄ ወደ ስልጣን ከመጣ አንስቶ ነው።
በአሁን ወቅት ሁለቱ አገራት የማይስማሙባቸው ብዙ ልዩነቶች አላቸው። በተለይ የጣሊያን ፖለቲከኞች በፈረንሳይ ላይ የሚያቀርቧቸው ትችቶች በርካታ ናቸው። ከሁሉ በላይ አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ፣ የሁለቱ ድንበር ተጋሪ አገራት የፍልሚያ መነሾ ስትሆን፤ የወቅቱ የጣሊያን ፖለቲከኞች ከስምንት ዓመታት በፊት በሊቢያ ምድር የሆነው ሁሉ የፈረንሳይ ጥንስስ መሆኑን ይስማሙበታል።
ፈረንሳይ በአፍሪካ የምታራምደውን ፖሊሲ የአንድ ወገን ተጠቃሚነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፤ በሊቢያ ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ ሰላም ከሆነች የነዳጅ ዘይት ፍላጎቷን ማሟላት አትችልም ሲልም ይወቅሳል።
ከሁሉ በላይ የሁለቱ አገራት ፍጥጫ መነሾ ለመሆን የበቃው ግን በሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞችን በማዳን ተግባር የተሰማራቸው አኳሪየስ መርከብ የጫነቻቸውን ስደተኞች በጣሊያን ወደብ ለማውረድና መልህቋን ለመጣል በሮም በኩል ፈቃድ መከልከሏንም ተከትሎ ነው።
በስደተኞች ጉዳይ ከህብረቱ አባል አገራት የተለየ አቋም የያዙት የወቅቱ የጣሊያን ፖለቲከኞች ይህን ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎም፤ ስደተኞችን ያሳፈረችው መርከብ ማረፊያ ፍለጋ ቆይታ የኋላ ኋላ ወደ ፈረንሳይ ማርሴይ ወደብ ብታቀናም በፓሪስም ቢሆን ፈቃድ አላገኘችም።
ይህ የፈረንሳይ ተግባር ውሎ ሳያድር የወቅቱ ዋነኛ አነጋጋሪ የፖለቲካ ጉዳይ ለመሆን መብቃቱን ተከትሎም ኢማኑኤል ማክሮን ምንም እንኳን በይፋ የሮም ፖለቲከኞችን ባይወርፉም በመላ አውሮፓ ብሄርተኞችንና አቀንቃኞች ማቆጥቆጣቸውን ለመናገር ደፍረዋል።
ይህን የሰሙት የጣልያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ ታዲያ ለዚህ መልስ ለመስጠት ጊዜ አላባከኑም። ‹‹ማክሮን መልካም ሰው ቢሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞቹን በመቀበል ምግባሩን ያሳይ ነበር» በማለት ለፓሪስ ትችት መልስ ሰጥተዋል።
በአገራት መካከል በወቀሳና በመወራረፍ የተጀመረው ግብግብ አዲሱ የጣልያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ፋይቭ ስታር ሙቭመንት መሪ ሉዊጂ ዲማዮ «አፍሪካውያን አገራቸውን ለቀው ለስደት የሚዳረጉት በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ምክንያት ነው፤ ፈረንሳይ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም አፍሪካን ቅኝ መግዛቷን አላቋረጠችም» ሲሉ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ይበልጡኑ ግሏል።
ከዚህ በተጓዳኝ፤ ሳልቪኒም በመጪው የአውሮፓውያን ምርጫ የፈረንሳይ መራጮች ከመጥፎው ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ነፃ ማውጣት እንዳለባቸውና ይህም እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ሲናገሩ መደመጣቸው ዲማዮ በፈረንሳይ የሚካሄደውን ጸረ-መንግስት ተቃውሞ እንደሚደግፉና የማክሮን ተቃዋሚዎች ጋር መወያየታቸው በአገራቱ መካከል በተለኮሰው እሳት ላይ መጠኑ የበዛ ነዳጅ አርከፍክፎበታል።
ይህ የሮም ፖለቲከኞች ተደጋጋሚ ትችትና ወቀሳ እያደር ሰላም የነሳት ፈረንሳይ ታዲያ መሰል ተግባር በጎረቤት አገራት መካከል ተቀባይነት እንደሌለውና የአውሮፓ ህብረት መርህም የሚፃረር መሆኑን በማስረገጥ «ጣሊያን በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው፤ ይህን ደግሞ ፈፅሞ ልታገሰው አልችልም ስትል» ተደምጣለች። ከዚህ ተሻግራም ሮም የሚገኙትን አምባሰደሯን በመጥራት ያልተጠበቀ እርምጃ የወሰደች ሲሆን፤ ይህም ተግባርም እኤአ 1940 ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሎለታል።
የፈረንሳይ መንግስት ቃል አቀባይ ቤንጃሚን ግሪቮክስ፣ አገራቸው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ጣሊያን ለወራት ስደተኞችና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በተመለከተ መሠረተ ቢስ ውንጀላ በማካሄዷ ነው፡፡ የጣሊያን ሰሞንኛ ተግባር የአውሮፓውያንን ህብረት መዋጥን ያለመ የሰነፍ ዲፐሎማሲ ውጤት ነው፡፡ እናም የህብረቱ አባል አገራት ለዚህ የወረደ ተግባር ተገቢውን አፀፋ ሊመልሱ ይገባል ሲልም አስታውቋል።
ይህን የሰሙት ሳልቪኒም፣ ‹‹ምንም እንኳን ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አያበላሹትም፡፡›› በማለት ነገሩን ማለዘብን መርጠዋል። ከፓሪስ አለቃ ጋር ለመመካከር በእግራቸው ሳይቀር ለመሄድ ዝግጁ ስለመሆናቸው አሳውቀዋል።
ከሁሉ በላይ ለሁለቱ የአውሮፓ ህብረት መስራች አገራትና ፖለቲከኞች ሽኩቻ ዋነኛ ምክንያትም ቀጣዩ የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫም መሆኑም ይነሳል። በእርግጥም ሁለቱ አገራት ህብረቱን አስመልከቶ የሚያራምዱት ሃሳብና አቋም የየቅል ነው። ማክሮን በተለይ በአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ለውጥ ዘዋሪ መሃንዲስ በመሆን ከፊት የተሰለፉ ሰው ናቸው። ብራስልስም ቢሆን የሰውየውን የለውጥ እንቅስቃሴ በአድናቆትና በበጎ ጎኖ በመመልከት አስፈላጊው ድጋፍ ለመስጠት አልቦዘነም።
ፋይቭ ስታር ሙቭመንት በሌላ በኩል፤ ጣሊያንን ከህብረቱ እንድትፋታ በተለይም አገሪቱ የቀድሞ መገበያያ ገንዘብ ሊራን ዳግም እንድትጠቀም፤ የአውሮፓ ህብረት የበጀት ህገ ደንቦችን እንዲለወጡ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተዳደርና መዋቅር እንዲሻሻል ፍላጎት አለው።
ማክሮን በህብረቱ አገራት መካከል ጠንካራ የውጭ ደህንነት፣ የወታደር፣ የኢኮኖሚ ትብብር እንዲኖር ፍላጎት አላቸው። የፋይቭ ስታር አቀንቃኞች በሌላ ጎን ከአውስትራሊያ፣ ከፖላንድና ከሃንጋሪ አጃቢዎቻቸው ጋር ለህብረቱ ጀርባ ስለመስጠት የሚዳዱ ናቸው።
ይህ በሆነበት ታዲያ ወቅታዊው ሁለቱ ወገኖች ሽኩቻ ለአውሮፓው ፓርላማ ምርጫ ድምፅ የተቃርኖ ሃሳባቸውና አጀንዳቸው ተቀባይ ለማድረግና በተለይ የጣሊያን ፖለቲከኞች በማክሮን የአውሮፓ ህልም ላይ ጫና ለማሳደር የወጠኑት ዘዴ ነው የሚሉም ተበራክተዋል።
የአገራቱ ልዩነትና የሽኩቻቸው ተልዕኮ ምንም ይሁን ምን በመካከላቸው ያለው ልዩነትና መቃቃር እያየለ የመምጣቱ ግን በርካቶች መጪውን እንዲሰጉ ያስገድዳቸው ጀምሯል። በዚህ ረገድ ሰፊ ሃተታ የሰራው የሲ.ኤን.ቢ.ሲው ዴቪድ ሬይድ፤ ‹‹በአሁን ወቅት የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ተቀይሯል። ይህም መጪውን አሳሳቢ ያደርገዋል» ብሏል።
የ ዘ ኢንዲፔንደንቱ ጃ ኪም ሴንጉብታ «የብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት የመፋታት ፖለቲካዊ ውጥረት በላይ የወቅቱ ዋነኛ የአውሮፓውያኑ ራስ ምታት ሁለቱ ድንበር ተጋሪ አገራት ትኩሳትና በመካከል ያለው እሰጣ ገባ ነው›› ሲል አስነብቧል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው እሰጣ ገባም መቋጫውን ከማግኘት ይልቅ እያደር እየጋለ መምጣቱን ያመላከተው ዘገባው፤ ይሁንና ይህ ጡዘት እያደር በጋለ ቁጥር ቀጣዩን የአውሮፓ ፖለቲካዊ ካርታ የማሳየት አቅሙ ግዙፍ እንደሚሆንም ግምቱን አስቀምጧል።
የጋርዲያኗ ናታሊ ኑጋያርዴ በበኩሏ፤ ‹‹በሳልቪኒና ዲማዮ ጥምረት ማክሮን ላይ የሚቃጡ ትችቶችና ከፓሪሱ የሚመለሱ አፀፋዎቹ በሙሉ ቲያትር ናቸው፤ ፍጥጫው ያለመጠን መጋነን የለበትም፡፡ ይሁንና ውጥረቱ እያደር ከናረ ለአውሮፓውያን ህልውና አደገኛ ነው» ብላለች።
የፎርብሷ አናሊሳ ጊራርዲ በበኩሏ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ፍልሚያ መቋጫውን እስካላገኘ በተለይ በኢኮኖሚ ረገድ የሚኖረው ጫና እጅጉን ከሚታሰበው በላይ የላቀ ስለመሆኑ አትታለች። እንደ ዘገባው ከሆነም፤ ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ ግንኙነት ረብጣ ቢሊየኖችን የሚዘወር ነው። በ2017 ብቻ 76 ነጥብ 6 ቢሊዮን ፓውንድ የንግድ ልውውጥ ተካሂዷል። በተለይ ፈረንሳይ በጣሊያን ምድር በመገኘት ብልጫ ያላት ሲሆን፤ ከ1 ሺ 900 በላይ የንግድ ተቋማትና ከ250 ሺ በላይ ሰራተኞችን ትዘውራለች።
ወቅታዊው የአገራቱ ፍጥጫ ታዲያ ይህን የኢኮኖሚ አጋርነት በእጅጉ እንደሚያዳክመውና በተለይም ከጣሊያን ቱሪን እስከ ፈረንሳይ ሊዮን የሚዘረጋው የፈጣን ባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክትን ጨምሮ የሌሎች ፐሮጀክቶች እጣ ፈንታም አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ያመላከተው ዘገባው፤ አገራቱ ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ሳይሆን የነገ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራቸውን ለማስቀረት ግንኙነታቸውን ማደስ ግድ ይላቸዋል ብሏል።
የሁለቱ አገራት መጪውን ታሳቢ በማድረግ ከሽኩቻቸው መታቀብ ከሁለንተናዊ ግንኙነታቸው መቀጠል ባሻገር በተለይ ለአውሮፓውያኑ አንድነት መቀጠል ወሳኝ መሆኑ የተሰመረበት ሲሆን፤ ልዩነቶችን ለማጥበብም በጣሊያንም ሆነ ፈረንሳይ መሪዎች በኩል የአቋም ለውጥ ሊመጣ ግድ እንደሚል ተመላክቷል።
ከቀናት በፊት የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮንና የጣሊያኑ አቻቸው ሴርጊዮ ማታሬላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለሁለቱም ጠቃሚ ስለመሆኑና ልዩነቶችን ማጥበብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ. በስልክ መክረዋል መባሉ፤ አገራቱ የጥል ግድግዳን አፍርሰው የጥላቻና የመቃቃር መጋረጃን እንደሚቀዱ ተስፋን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
ታምራት ተስፋዬ