የዛሬው የሳምንቱ በታሪክ አምዳችን አንዱ ርእሰ ጉዳይ የአምባቦ ጦርነትን ይመለከታል። በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት መካከል የተካሄደውና በአጼ ምኒሊክ አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጦርነት የተካሄደው ግንቦት 30 ቀን በ1874ዓ.ም ነበር።
“ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” የተሰኘውና ከዛሬ 50ዓመታት በፊት በጸሐፌ ትእዛዛት ገብረ ሥላሴ የታተመ መጽሐፍ በመጽሐፉ ገጾች የሰፈረው ታሪክ እንደሚያስረዳው …በዚህን ጊዜ ራስ ጎበና የከፋን ግብር ለመቀበል ሂዶ ሳለ ጎጃሞች ውላቸውን፣ መሐላቸውን አፍርሰው ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ይምጡልን ብለው ልከው ራስ ጎበናን ለመውጋት ተጓዙ። ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ተነሱ የሚል መልዕክተኛ ወደ ንጉሥ ምኒልክ ገብቶ አደረ።
ንጉሱ መልእክት እንደደረሳቸው ዳግማዊ ምኒልክ ክተት ሠራዊት፤ ምታ ነጋሪት ብለው ከእንጦጦ ከተማዋ ተጓዙ። በመጋቢት 13 ቀን ጌጃ ሰፈሩ። በነጋታው አዋሽን ተሻግረው በጊልማ አገር አቃንተው ጥቁር መሬት ደረሱ።
ደጋውን ተጉዘው አምበልታን አድርገው ትልቁን ወንዝ ደዴሳን ተሻግረው፤ የጶ ጉምቢ ሰፈሩ። ከዚህ በኋላ ጎጃሞች ሱጲ ቦሮ ላይ ሰፍረው ሳሉ፤ ሳይሰሙ በድንገት የአጼ ምኒልክ ድንኳን ሴሴ ከሚባለው ወንዝ ዳር ተተከለ። በነጋታውም ሴሴ ወንዝ ዳር ያለውን ዱር ሲያስመነጥሩ ዋሉ። ጎጃሞች ግን የንጉሡን ድንኳን፣ የመንገዱን መጠረግ ባዩ ጊዜ በሰፈራቸው ብርቱ ፍርሃትና ጭንቀት ገባበት።
ከዚህ በኋላ አጼ ምኒልክ በምዕራቡ አገር ሹም ሽር አድርገው ወደ ከተማቸው ሲመለሱ ሆሮ ጃሬ ሰፍረው በግንቦት 21 ቀን የንጉሥ ተክለሃይማኖት መልዕክተኞች መጡ። ወደ ንጉሡም በቀረቡ ጊዜ ደብዳቤውን ስጡኝ ቢሏቸው “ደብዳቤስ አልያዝንም በቃል ነው የተላክነው” አሉ። የቃሉን መልዕክት ንገሩኝ ቢሏቸው፤ መኳንንቱ ካልተሰብሰቡ አንናገርም አሉ። በዚህ ጊዜ መጋቢያ አድርገው መኳንንቱም ሊቃውንቱም ተሰበሰቡ። በዚህ ጊዜም መልዕክታቸውን በአደባባይ ተናገሩ።
የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቃል ይህ ነው፡- “ምነው እርስዎ ሁልጊዜ እኔን ያዋርዱኛል፤ ከዚህ ቀደም አገሬን ጎጃምን አጠፉት፤ እንግዲህስ አይሂዱ መጣሁ። ተጉድሩ፣ ተሆሮ፣ ተጅማ፣ ተጨለያ እወደዱት አገር የጠራ ሜዳ ይዘው ይቆዩኝ። ደብዳቤ አለመላኬ ብቻዎን አይተው ቀደው ጥለው እንዳልሰማ ሁነው ይሸሻሉ። በቃል የሆነ እንደሆነ ግን መኳንንትዎ፣ ሠራዊትዎ፣ አሽከሮችዎ፣ ሰምተው ቢሸሹ ይንቅዎታል” አሉ በማለት ተናገሩ።
ንጉሥ ምኒልክም ለመልዕክተኞቹ “ባለ ማኅተም ደብዳቤ አላመጣችሁምና ሀሰተኞች ናችሁ። ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ይህንን ቃል አልላከላችሁም። ንጉሥ ነኝ ሲል አለማኅተብ በቃል መላክ አይገባውምና አሏቸው። እነዚያም መልእክተኞች የጌታችን ቃል ነው። ሀሰት የሆነብን እንደሆነ እንቀጣ አሉ። ንጉሥም መልሰው እንደዚህስ ከሆነ ከእናንተ አንዱ ከእኔ ዘንድ ይቆይ አንዳችሁ ሄዳችሁ እውነት መሆኑን የሚያስረዳ ልኬያችኋለሁ የሚል ባለ ማኅተም ደብዳቤ ይዞ እስከ አምስት ቀን ድረስ ይምጣ። ሳይመጣ የቀረ እንደሆነ ግን እኔ ዘንድ የቆየውን እቀጠዋለሁ። ሀሰተኞችም መሆናችሁ ይታወቃል። ይህም ካልሆነ ባልታመነ ወሬ እናንተን ስጠብቅ ክረምት ይጫንብኛል። ሠራዊቱም በውሃ ሙላትና በጭቃ ይጎዳብኛል” አሏቸው። እነዚያም መልዕክተኞች እሺ ንጉሥ እንዳሉ እናደርጋለን አሉ። በዚህ ጊዜ ንጉሥ ይህንን ቃል ሰምተው ምላሹን እንዲህ ሲሉ ላኩ።
“የአንተንስ ጦርነት ሰግቼ አልሄድም። ነገር ግን ለመዋጋት ከአጼ ዮሐንስ ፈቃድ አግኝተሃልን? ተዋጋ ብለውህ እንደሆነ ባለ ማኅተም ደብዳቤህን ላክብኝ። ለጦርነቱስ አንተን መንገድ አላስመጣም። እዚያው እደጅህ እንመጣልሃለን። ደብዳቤ ግን አንተ የናቅኸውን ደብዳቤ እኛ ልንጽፍልህ አይገባንም ብለህ ንገረው” ብለው አንዱን ከነዚያ መልዕክተኞች ሰደዱ። አንዱ በዘበኛ እጅ ተቀመጠ።
ከዚህ በኋላ ይህ ነገር ሀሰትም እውነትም እንደሆነ በግሠገሳ ሄደህ አፋፍ ዘልቀህ በመነጥር አይተህ ንገረኝ ብለው ደጃች ወልዴን ላኩት። ደጃች ወልዴም ከአባይ ወዲህ ሠፈር አየሁ ብሎ መጥቶ ነገራቸው። መኳንንቱም ይህንን በሰሙ ጊዜ አፋፍ ሳይዘልቅ በር ይዘን እንዋጋው ብለው ቢመክሩ፤ እንኳን በር እይዝበት ከመጣልኝስ መንገዱን ጠርጌ በቆየሁት ነበር ብለው ንጉሡ ለመኳንንቱ ተናገሩ።
ይህ ነገር ከተፈጸመ በኋላ ተነስተው ወደ ጉድሩ ሲጓዙ ሁላ ዲላሎ ላይ በግንቦት 28 ቀን እጠራ ሜዳ ወጥተው የሰራዊታቸውን ሰልፍ አሳዩት። በነጋታው ውሎ ሆነ። በግንቦት 30 ቀን ማክሰኞ በማለዳ ተነስተው ተጉዘው ወምበር እምባቦ ሜዳ ላይ ሲደርሱ የጎጃሞች ሰልፍ ፊት ለፊት ታየ። የንጉሥና የታቦታቱ አንድ አንድ ድንኳን ሲተከል የቀረው እንዳለ ተጫነ።
ከቀኑ አምስት ሰዓት ጦርነት ገጠሙ። ንጉሥ ግን የቤት አሽከራቸውን ይዘው መሀል ለመሀል ነበሩ። በዚህን ጊዜ የንጉሥ ተክለሃይማኖት መድፍ መተኮስ ጀመረ። ሁለት ጊዜ ተተኩሶ በሦስተኛው መንኮራኩሩ ተሰባብሮ ከጥቅም ውጭ ሆነ። የጎጃም ጦርም በዚህ ተደናግጦ ተረበሸ። ተኩሱ ተጧጡፎ የባሩዱ ጭስ ፀሐይዋን ሲጋርዳት የጎጃም ጦር እንደ መናወጥ አለ።
እንደዚህም ሆነው ከበው አስጨንቀው አስጠብበው ሁለት ሰዓት ሳይሞላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ቆስለው ተያዙ። ጦርነቱ ግን እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ ቆየ የጎጃምም ሰው ለመማረክም ለመሸሽም የማይቻለው ሆነ። የሸዋ ጦር ከቦታልና። ስለዚህ ጦርነቱ እጅግ ጠነከረ። ጓዛቸውንም በሰልፍ መካከል አድርገውት ነበርና ፈረሱም፣ በቅሎውም፣ አጋሰሱም፣ አህያውም የቆመው በእርሳስ አለቀ። ብዙ ሰውም ተጎዳ። ከዚህ በኋላ በነጋታው ሰፈሩን ለውጠው ከሰፊው ቦታ ላይ ሰፈሩ። ንጉሥ ተክለሃይማኖትም በበቅሎ መሆን አልቻሉምና በአልጋ አስጓዟቸው። በዚህን ጊዜ ንጉሥ ኢትማዖ “ ለእኩይ በእኩይ ግሙራ” ያለውን አስበው እተዋጉበት ሥፍራ ሄደው የጎጃሞችን ቁስለኛ ከነነፍሱ የተገኘውን ብዙ ቁስለኛ አስነሱ።
ከዚህም ሲመለሱ ምርኮኛውን የጎጃምን ሰው “እኔ አልፈለግኋችሁም እናንተ ፈልጋችሁኝ መጣችሁ። እግዚአብሔር ግን በትዕቢታችሁ ጣላችሁ። አሁንም ከአገራችሁ ግቡ” ብለው አሰናበቱ። አጼ ምኒልክም የሞተው እንዲቀበር የተሰበረው እንዲጠገን ለቁስለኛው መድኃኒት ሊያደርጉ እረፍት አድርገው ዋሉ። በነጋታውም ራስ ጎበና በንጉሥ ትዕዛዝ ምርኮኛውን አባይ ድረስ ሸኝቶ ተመለሰ። ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ከድሉ በሁዋላ ሰኔ 19 ቀን እንጦጦ ከተማ ገቡ።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013