ከአመታት በፊት በየሬዲዮ ጣቢያው በተለይ የአዲስ አበባ መስተዳድር ድምፅ በሆነው ኤፍ ኤም አዲስ 96.3 ተደጋግሞ አንድ ዜማ ተከፍቶ ስሰማ ሳቅ ያፍነኝ ነበር። እኔ የምኖርበትና አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ገፅታዎች ምን ያህል ለእይታ የማይጋብዙ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፤ የመንገዶች ዳርቻዎችና ክፍት ቦታዎች በቆሻሻ ቁልል ተሞልተው የከተማዋን ነዋሪ ምቾት ይነሱ እንደነበርም አስታውሳለሁ። በአንድ ወቅት ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ ከተማዋን ለማጽዳት ርብርብ ይደረግም ነበር። የከተማዋ የጽዳት ችግር በዚህና ከዚህም በበለጠ ሆኖ እያለ ታዲያ ባልኩት የሬዲዮ ጣቢያ “አማረች አዲስ አማረች አማረች አዲስ አማረች …” የሚል ዜማ ሲለቀቅ እጅጉን ይገርሙኝ ነበር።
የከተማችን መናገሻ የጉዳያችን መሰብሰቢያ የመዲናችን ትልልቅ ሁነቶች ማካሄጃ መስቀል አደባባይ ላይ እገኛለሁ። ከመስቀል አደባባይ እስከ ቸርችል ያለውን መንገድ ሽር እያልኩኝ መመልከት ለእናንተም ማስመልከት ፈለኩ። ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በስፋት የምንመለከተው የአዲስ አበባ አሁናዊ ገጽታን የሚያመላክቱ ምስሎች መበራከት ደግሞ ለቅኝቴ መሰረትና መነሻ ሆነኝ።
የጉዞዬን ጅማሮ ያደረኩበት መስቀል አደባባይ ሙሉ ገፅታውን ቀይሮ በፊት ከነበረው በብዙ ተለይቶ ለእይታ ማራኪ ለማረፊያ ምቹ ሆኗል። በፊት እዚህ አካባቢ ምሽት ላይ ከጓደኞቼ ጋር ቁጭ ብዬ በዋናው አውራጎዳና የሚታየውን ትዕይንት እና የመኪናዎች ምልልስ እያየን በሳቅና ጨዋታ እናመሽ ነበር። እዚያው አካባቢ ለውዝ ፣ቆሎ፣ብስኩት የመሳሰሉትን እያዞሩ የሚሸጡና ምሽታቸውን እዚያ አደባባይ ላይ የሚያሳልፉ ሽጠው የሚያድሩም ብዙዎች ነበሩ።
አሁን ይህ ቦታ የተለየ ገፅታ ተላብሷል። በአደባባዩ ከርሰ ምድር ውስጥ ጥልቅ ቁፋሮ ተካሂዶ እጅግ በዘመነ ቴክኖሎጂ የተሰናዳ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ መኪኖች በላይ የሚያቆም “ፓርኪንግ” ተገንብቶበታል፤ ለእዚያም ባለ ሁለት ወለል፤ ከላይ ባማረ ዲዛይን ዙሪያውን በሚማርክ ረድፍ የተሰሩ መቀመጫዎችና አካባቢውን ውበት የሚያላብሱና ልዩ ልዩ አይነት መብራቶች ተገጥግጠውበታል፤ በተለይ ምሽት ላይ አደባባዩ ውብ ይሆናል። በግዙፍ የመብራት ምሰሶዎች ላይ የተገጠሙት መብራቶች አካባቢውን ቀን አስመስለውታል፤ ሁሉም አይንን ይማርካሉ።
በልዩ ዲዛይን በረድፍ ለሰዎች መረማመጃና መመላለሻ የሚሆን የሳር ጉዝጓዝጋ ከተሰሩት መቀመጫዎች ጀርባ ትልልቅ ምስል ማሳያ ስክሪኖች ለአካባቢው ልዩ ውበት አላብሰውታል። አካባቢው ለሚገኝና አገልግሎት ፈልጎ ለሚመጣ የካፌና የሻይ ቡና አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንዲሁም የተለያዩ ሱቆች ተሰርተውበታል። ሆሆ ያየሁት የተለየ ነበርና ገና ከመነሻዬ ብዙ አልኩ በቅኝቴ የምዳስሰው እስከ መስተዳድሩ ነውና እግሬን ወደፊት ወረወርኩ።
ወደ ስቴዲየም ታክሲ መያዣ አቋረጥኩ፤ ጉዞ ወደ ለሀገር ሆነ ። በተባበሩት አረብ ኤምሬት ባለሀብቶች ግንባታው ከተጀመረው የወደፊቱ ዘመናዊ መንደር ደረስኩ። በግራ በኩል ወደፊት አካባቢው የሚያመላክት ገፅታ በምስል ስመለከት አንድ ልዩ ተስፋ በውስጤ አጫረብኝ ፤ነገን አስናፈቀኝ። ከምስሉ ጀርባ ደግሞ እዚህ ሸራ ላይ የተመለከተውን ዕቅድ ለመተግበር የሚሯሯጡ ሰዎችና ማሽኖች ድምፅ ይሰማል።
ወደ ቀኝ ታጥፌ ቀጥ ብዬ ፊት ለፊት ስመለከት በርቀት የከተማው መስተዳድር ይታያል። እኔም ግቤ እዚያ መድረስ ነውና ወደዚያ አመራሁ። ከአመታት በፊት እዚያ ጎዳና ላይ በእግርም በመኪናም ተመላልሼበታለሁ፤ የዛሬ ምልከታዬ ግን ከበፊቱ እጅግ የተለየ ሆኖብኛል።
በየመንገዱ ዳርና ዳር ከሚከናወኑ ግንባታዎች በተጨማሪ በዋንኛው መንገድ ግራና ቀኝ ከዚህ በፊት ያልነበረ ድምቀት አስተዋልኩ። ዳርና ዳሩ በአበባ አጊጦ ሰፋ ተደርጎ የተሰራው የእግረኞች መንገድ ለእንደኔ አይነቱ እግረኛ ብዙ መሄድ ያስመኛል። የእግረኛ መንገዶቹ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለብስክሌት ጋላቢዎች ጭምር ምቹ ተደርገው ተሰርተዋል።
ለከተማዋ ለዓመታት የመድረክ ተውኔት ቤት በመሆን ብዙ የሙያው ባለቤቶችን ያፈራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር አዲስ ህንጻ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ማነፍነፍ ፈለግሁ።፡ የአዲሱ ህንጻ ግንባታ ከተጀመረ ቆይቷል፤ አሁንም ከመሬት የወጣ ግንባታ ብዙም አይታይም። ግንባታ በሰፊ ቦታ ላይ የሚካሄድ መሆኑ ምናልባት በምጠብቀው ልክ ግንባታው አልፈጠነ ሊሆን ይችላል ስል አሰብኩ።
አዲሱ ህንፃ በቲያትር ቤቱ የወደፊት እድገትና ዘመናዊነት እንዲሁም በአካባቢው ላይ የሚያመጣው ለውጥ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ የመንግስት ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚገርም ሁኔታ እየተፋጠነባት በምትገኘው አዲስ አበባ ይህ ፕሮጀክት አለመፋጠኑ ግን አሳሰበኝ።
የቀድሞ የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ህንፃ ፊት ለፊት ቆሜ ወደ ሜክሲኮ የሚወስደውን አቅጣጫ በአይኔ አማተርኩ። እጅግ ውብ ሆነው የቆሙ ሰማይ ጠቀስ የባንኮች ህንጻዎች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ ።ይህን ስመለከት ያ ድሮ ስሰማው ሳቅ የሚያሳፍነኝ ዜማ ትውስ አለኝና እኔው መዝፈን አማረኝ። አሁን ነው “አማረች አዲስ አማረች አማረች ሸገር ደመቀች…”ብሎ መዝፈን አልኩ።
አሁን ያንን ዘፈን እዚህ ቦታ ቢያስደምጡኝ ብዬ ተመኘሁ። ወደፊት ቀጠልኩ። ዋናው የመኪና መተላለፊያ ጎዳና መኪናን እንጂ ሰዎች ታስበው የተሰሩ ሳይመስሉ የቆዩት የመከላከያ ሚኒስቴር እና ፊት ለፊት ያለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የግንብ አጥሮች ቀድሞ ማውቃቸው ቦታ ላይ የሉም፤ ለእግረኞች መንገድ ግንባታው አጥራቸውን አፍርሰው ወደ ውስጥ ገብተዋል። በተለቀቀው ቦታ ላይ ለእግረኞች ውብና ማራኪ ንጣፍ ተደርጎበታል፤ በርካታ እግረኞችም በመንገዱ ሽር ማለት ጀምረዋል። በየመንገድ ዳርና ዳር እንዲሁም አስፓልቱ መካከል ላይ የተተከሉት አበባዎች ደግሞ ለአይን ማራኪ ናቸው።
ወደፊት ስጓዝ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ጎን ያለው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ህንፃ ወደመንገዱ ተጠግቶ ተሰርቶ ነበረና ለእግረኞች መተላለፊያ ጋሬጣ እንዳይሆን በሚል የታችኛው ምድር ቤት ለእግረኞች መተላለፊያ ይሆን ዘንድ በልዩ ግንባታ ተዋቅሯል። ይህንንም የተለየ ምልከታና የሀብት ብክነትን ለመቀነስ የተደረገ ልዩ እሳቤ አድርጌ ወስጄዋለሁ። በዚህ ለመንገደኞች ታስቦ በልዩ ፕሮጀክት በተሰራ መንገድ ሽር እያልኩ መንገዴን ቀጥያለሁ።
ኢሚግሬሽን ፊት ለፊት ስደርስ ያማረው ጎዳናና የተተከሉት አበቦች ውበት አንድ የሚጠቀስ ነገር ሆኖ ሌላ ገፅታም ተመለከትኩ። የጎዳና ተዳዳሪዎች አስቸጋሪ ህይወት እየተገነባ ላለው ከተማ ትልቅ ፈተና መሆኑን። ትላንት በአካባቢው ላስቲክ ወጥረው ማደሪያቸው ያደረጉ ህፃናትና ሴቶች ዛሬም እዚያ ቦታ ላይ ገባ ብሎ የአጥሩን ጥጋጥግ ተከትለው ሸራና ላስቲክ ወጥረው ይታያል። እዚህ ላይ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ወገኖች ሊመለከትና ከከተማ ማደስና ምቹ ማድረግ ስራው ጎን ለጎን የልጆችዋንም ህይወት ለመለወጥ እያደረገ ያለውን ጥረት እዚህ ላይም መስራት እንዳለበት ታሰበኝ።
ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ዘንድ ነኝ። በመንገዴ ካስተዋልኩት ትዝብት እራሴን መለስ አድርጌ ወደመድረሻዬ ለማቅናት ወደፊት ቀጥያለሁ፤ የቸርቸልን ጎዳና ይዤ።…
……..ይቀጥላል
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም